Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረገው ሴፍቲኔት ፕሮግራም

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረገው ሴፍቲኔት ፕሮግራም

ቀን:

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ ቦታዎች ፈልሰው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እየጨመረ ለመምጣቱ የመዲናዪቱ ጎዳናዎች ምስክር ናቸው፡፡ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ዘልቆ የነበረው ጦርነት በርካታ ዜጎች ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በየጢሻውና ጉራንጉሩ ሥር ውሎና አዳራቸውን ያደረጉ ዜጎች ተበራክተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል፡፡

ከፕሮጀክቶቹም መካከል በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት በ450 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያው ዙር የተተገበረው አንዱ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ለአምስት ዓመታት ቆይታ በነበረው ፕሮጀክት የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ታኅሣሥ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መኮንን ያዬ ፕሮጀክቱን አስመልክተው ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ በኩል ተቀርፆ ተግባራዊ ተደረገው ፕሮጀክት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት ዓይነት መርሐ ግብሮች ላይ ያጠነጠነ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ ተግባራዊ ለማድረግም 450 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ እንቅስቃሴ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን ከዓለም ባንክ በኩል 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር መገኘቱን፣ ቀሪው 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት መሞላቱን አክለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ አምስት ዓመታት ጊዜ የፈጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከድህነት ወለል በታች ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ጎዳና ላይ የወጡ ዜጎች እንዲሁም አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ መኮንን ጠቁመዋል፡፡

በ11 ከተሞች በተተገበረ አንደኛ ዙር የልማት ሴፍቲኔት ፕሮጀክትም ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ 20,991 ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ያስታወሱት አስተባባሪው፣ ከ70 በመቶ በላይ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተደራሽ እንደሆኑም አክለው ገልጸዋል፡፡

ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው 93,122 ዜጎችን በየወሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስታውሰዋል፡፡

ዜጎች በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ዘላቂ በሆነ መንገድ እንደሆነና አዲስ የተጀመረው ፕሮጀክትም እነዚህ ዜጎች በቋሚነት መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች መልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ መመቻቸቱን፣ በዚህም 800,000 ዜጎችን ተደራሽ እንደሆኑ አክለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱም ከቀረበው 450 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 424 ሚሊዮን ዶላር ሥራ ላይ መዋሉን፣ በፕሮጀክቱም 600,400 ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ፣ 1.4 ሚሊዮን ዜጎችን መድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በአሁኑ ወቅት 550 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ዓለም ባንክ 400 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፣ ዜጎች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ በማኅበረሰብ አቀፍ ጥምረት የሚደገፍበት አሠራር ከመዘርጋት ባለፈ፣ ከወጡ በኋላ በተገቢውን የተሃድሶ፣ የምክክር የሥልጠናና ሌሎች አገልግሎቶችን አግኝተው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ዙሪያ ባሉ የአፈጻጸም ክፍተቶች በሚኒስቴሩና በዓለም ባንክ በኩል ግምገማ እንደሚካሄድና በነበሩ ክፍተቶች ላይ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት ወ/ሮ አየለች አስረድተዋል፡፡፡

ከመረጃ ሥርዓት አኳ ያ ያሉትን ክፍተቶች በመለየት የመረጃ ሥርዓቱ እንዲጠናከር መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ አሠራሩ በተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ሕፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ሚኒስቴሩ የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እየሠራ ነው ያሉት ወ/ሮ አየለች፣ ይህንንም ለማጠናከር ከታች ጀምሮ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው? የሚለውን ለመለየት ሚኒስቴሩ ጥናት እያካሄደ ሲሆን፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግና ከመሠረቱ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም አካላት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ብለዋል፡፡

በፓርላማ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ በመከለስና የማኅበራዊ ጥበቃ አዋጅ በመቅረፅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አስታውሰዋል፡፡

ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከው አዋጅ ሲፀድቅም በድህነት ወለል ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለው ገልጸዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በ11 ከተሞች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በፕሮጀክቱ ተካታ የነበረችው መቀለ ከተማ በጦርነቱ ምክንያት በከተማ ለሚገኙ ዜጎች ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ለዓለም ባንክ ተመላሽ እንደተደረገ አስረድተዋል፡፡

በፕሮጀክቱ በተለያዩ ምክንያቶች ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ሕፃናትና አዋቂዎችን የያዙ እናቶችና አረጋውያን ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለመደገፍና ለማቋቋም እንዲያስችል የተቀረፀው የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ ፀድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ሚኒስቴሩ ያላሳለሰ ጥረት የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...