Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበተገባደደው 2022 የተስተናገዱ ክስተቶች

በተገባደደው 2022 የተስተናገዱ ክስተቶች

ቀን:

የምዕራባውያኑ 2022 ጦርነት፣ ተቃውሞ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖና ሌሎችንም አስተናግዶ ሊጠናቀቅ ሦስት ቀናት ቀርተውታል፡፡ የፓኪስታንና የናይጄሪያ ጎርፍ፣ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት፣ እንግሊዝ የህንድ ዝርያ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መሾምና የንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ሞት፣ በ2022 የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ለሦስተኛ ጊዜ ዋንጫ ማንሳቷና ባጠቃላይም ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኩነቶች የተከሰቱበትም ነው፡፡

‹‹ያሳለፍነው ዓመት ዓለም ዳግም በፍቅር ሊያስታውሰው የሚችለው ዓይነት አልነበረም፤›› ሲልም ዘ ፌዴራል በድረ ገጹ አስቀምጦታል፡፡

ዓለም በተገባደደው 2022 ካስተናገደቻቸው ኩነቶች የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ ሞት አንዱ ነው፡፡ ንግሥት ኤልሳቤጥ በእንግሊዝ ታሪክ ረዥም ዕድሜ በንግሥና የኖሩ ሲሆን፣ ለ70 ዓመታትም በንግሥነት አገልግለዋል፡፡ ይህ ከንግሥት ቪክቶሪያ ጋር ሲነፃፀር የሰባት ዓመታት ብልጫ አለው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተገባደደው 2022 የተስተናገዱ ክስተቶች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አውሮፓን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካና ሌሎች አገሮች በድርቅ ተመትተዋል (ሮይተርስ)

ባለቤታቸው የቀድሞው የኤደንበርግ መስፍን ልዑል ፊሊፕ 100ኛ ዓመታቸውን ሊያከብሩ ሁለት ወራት ሲቀራቸው በጥር 2021 የሞቱ ሲሆን፣ ንግሥት ኤልሳቤጥ ደግሞ ይህን ዓለም የተሰናበቱት በመስከረም 2022 በ96 ዓመታቸው ነው፡፡

ዓመቱ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊዮንን የተሻገረበትም ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መረጃ እንደሚያሳየው፣ ህንድ 177 ሚሊዮን ሕዝብ በመጨመር በዓመቱ የተመዘገበው የሕዝብ ቁጥር ስምንት ቢሊዮን ለመድረሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ አገሮች የመጀመርያዋ ሆናለች፡፡

የዓለም ሕዝብ ቁጥር በአንድ ቢሊዮን ለመጨመር 11 ዓመታት ያህል የፈጀበት ሲሆን፣ ዘጠኝ ቢሊዮን ለመድረስም 15 ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ተመድ ተንብይዋል፡፡

አሥር ቢሊዮን ለመድረስ እስከ 2080 ሊደርስ እንደሚችል የገመተው ድርጅቱ፣ እስከ 2050 ባሉ ዓመታት የዓለም ሕዝብ ቁጥር ይደርስበታል ተብሎ ከተተነበየው ግማሽ ያህሉ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚመዘገበው በኮንጎ፣ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ፣ በህንድ፣ በናይጄሪያ፣ በፓኪስታን፣ በፊሊፒንስና በታንዛንያ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

ዘንድሮ በግብፅ ሻርም አል ሻክ የተካሄደው የኮፕ 27 ጉባዔ፣ በኢኮኖሚ የበለፀጉ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ አገሮች ካሳ ለመክፈል የተስማሙበት ነው፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት፣ በከፍተኛ ሙቀት፣ በጎርፍ፣ በድርቅና በረሃብ፣ በአውሎ ነፋስም እየተጎዱ ያሉ አገሮች ካሳ ለማግኘት ዓመታት ያህል የጠበቁ ቢሆንም፣ ተስፋ የተጣለበት ውሳኔ የተላለፈው በጥቅምት 2022 በተከናወነው የኮፕ 27 ጉባዔ ላይ ነው፡፡

እንግሊዝ የመጀመርያውን የህንድ ዝርያ ያላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር የሾመችውም በተገባደደው ዓመት ነው፡፡ ቦሪስ ጆንሰን ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በወግ አጥባቂው ውስጥ በተደረገ ምርጫ ሊዝ ትረስና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ተወዳድረው የነበረ ቢሆንም፣ ትረስ ነበሩ በምርጫው ያሸነፉት፡፡ ሆኖም ትረስ ግብር ለመቀነስና የንግድ አሠራሩን ለማሻሻል የጀመሩት ሥራ የእንግሊዝን ኢኮኖሚ ይበልጡኑ በማዳከሙ፣ ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ሱናክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡

በዓመቱ ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን የሾመችው እንግሊዝ እ.ኤ.አ. ከ1812 ወዲህ ከሾመቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሮች ውስጥ የ42 ዓመቱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በዕድሜ ትንሹ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡ እሳቸው ለእንግሊዝ በዕድሜ ትንሹ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ሳይሆኑ በቀለምም ከቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተለዩ ናቸው፡፡

የኢኮኖሚ ቀውሱን መቋቋም ያቃታቸው የሲሪላንካ ዜጎች የፕሬዚዳንታቸውን ጎታባያ ራጃፓክሳ መኖሪያ በተቃውሞ ያጥለቀለቁትም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ የነዳጅና የምግብ ማብሰያ ጋዝ መወደድ፣ መሠረታዊ ምግቦች ከገበያ መጥፋት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለረዥም ሰዓታት መቆራረጥ እንዲሁም መድኃኒቶች ከፋርማሲዎች መጥፋትና ሌሎችም ከቤታቸው ፈንቅሎ ያስወጣቸው ሲሪላንካውያን ፕሬዚዳንታቸውን ድንገት ከአገር እንዲኮበልሉ አድርገዋል፡፡

የ73 ዓመቱ የሲሪላንካ ፕሬዚዳንት ጎታባያ ራጃፓክሳ የአገሪቱን 22 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ለኢኮኖሚ ቀውስ ዳርገዋል ያሉት ተቃዋሚዎች፣ የፕሬዚዳንቱን ቤት ገርስሰው የገቡበት ሁኔታ ለፀጥታ ኃይሎችም ፈታኝ ነበር፡፡

ዓለምን ያነጋገረው የሲሪላንካ ክስተት በሕዝብ ማዕበል የታጀበ ተቃውሞ ብቻ አይደለም፡፡ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች በፕሬዚዳንቱ ቤት ሲዋኙ፣ ሲመገቡ፣ ሲተኙ፣ በጂም ውስጥ ስፖርት ሲሠሩና ሲዝናኑ በመታየታቸውም ነው፡፡

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ዓለምን ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል የዳረገ የ2022 ከባድ ክስተት እንደሆነ ዘ ፌዴራል ያስቀምጣል፡፡

በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምክንያቱ የሚመዘዘው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ከፈራረሰች ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

በ1922 የአሁኖቹን ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ ቤላሩስ፣ አዘርባጃንን ጨምሮ 15 አገሮችን ይዞ የተመሠረተው ሶቪየት ኅብረት፣ በ1991 ከፈራረሰ በኋላ ዩክሬን በአቶሚክ ጦር መሣሪያ ብዛት በዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ለሩሲያና ለአሜሪካ ሥጋት ነበር፡፡

በወቅቱም የዩክሬንን የኑክሌር መሣሪያ ለማስፈታት አሜሪካና ሩሲያ ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም ዩክሬን በመቶዎች የሚቆጠሩ የኑክሌር አረር ለሩሲያ ስታስረክብ፣ ሩሲያ ደግሞ በምላሹ ለዩክሬን ሥጋት ላትሆን የደኅንነት ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡ ነገር ግን ይህ እ.ኤ.አ. በ2014 መልኩን ቀይሯል፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት ሩሲያና ዩክሬን ወደ ጦርነት የገቡበትና ክራይሚያም ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሩሲያ ደጋፊ የሆኑትን የምሥራቅ ዶንባስ ክልሎች ሩሲያን መደገፍ የጀመሩበት ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የተሻለ ግንኙነት የሻረከ ሲሆን፣ በ2022 ደግሞ በፊት ከነበረው ጦርነት በባሰና ምዕራባውያንም ወታደሮቻቸውን ከመላክ በመለስ ባሳተፈ ጦርነቱ በዩክሬን ምድር እየተካሄደ ነው፡፡

ጦርነቱ ወደ ኑክሌር ይቀየራል የሚል እምነት እንደሌላቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቢያስታውቁም፣ የምዕራባውያኑ የሩሲያን ኢኮኖሚ ለማንኮታኮት ማዕቀብ እየጣሉ መገኘት፣ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መርዳትና በሚዲያዎቻቸው ተጠቅመው ሩሲያን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማግለል አካሄዳቸው ወደ አውዳሚ የኑክሌር ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ሥጋት ደቅኗል፡፡

በአውሮፓ የነገሠው ውጥረት እንዲቆምና በዩክሬንና ሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ፣  ኔቶ ዩክሬንን ከአባልነት ጥያቄ እንዲያግድ ብቻ ሳይሆን፣ በምሥራቅ አውሮፓ ካሉ አገሮች ከ1997 በኋላ ኔቶን ከተቀላቀሉ አገሮች ውስጥ የወታደሮችና የመሣሪያዎች ልክ ላይ ገደብ እንዲጥልም ሩሲያ አሳስባለች፡፡

ኔቶ ከ1997 ወዲህ አብዛኛውን ምሥራቅ አውሮፓ፣ ፖላንድ እንዲሁም የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል አገሮች ኢስቶኒያ፣ ሊቱኒያ፣ ላትቢያና የባልካን አገሮችን አባል ያደረገው ኔቶ፣ ሩሲያን በኔቶ ወታደሮችና መሣሪያዎች እንድትከበብ ማድረጉን ሩሲያ ‹‹የደኅንነት ሥጋቴ ነው›› ትለዋለች፡፡ ምዕራባውያንን ለሩሲያ ደኅንነት ‹‹ሕጋዊ ዋስትና›› መስጠት አለባቸው ስትልም አሳስባ ነበር፡፡

ወደ አፍሪካ ሲመጣ ደግሞ ለ15 ወራት ሳይደረግ የቆየው የሶማሊያ የፓርላማ ምርጫ ተካሂዶ አገሪቱ ፕሬዚዳንቷን ሐሰን ሼኪ መሐመድ የመረጠችበት ወቅት ነው፡፡ ኬንያ አጠቃላይ ምርጫ አካሂዳ ዊልያም ሩቶን እንዲሁም አንጎላ ጆአ ላውሬንሶን ፕሬዚዳንት ያደረጉበት ዓመትም ነው፡፡

ቡርኪና ፋሶ ሁለት መፈንቅለ መንግሥቶችን በዓመቱ ስታስተናግድ፣ ማሊና ፈረንሣይ ውጥረት የገቡበትም ነው፡፡

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በሩዋንዳ መካከል ውጥረት የነገሠውም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ የሩዋንዳው ፖል ካጋሜ የኤም 23 አማፅያንን ይረዳሉ በማለት የኮንጎ ባለሥልጣናት ያሳወቁበት ወቅትም ነው፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማቆም ከስምምነት የተደረሰውም በ2022 ነው፡፡ አሜሪካ ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ ከፍተኛ ባለሥልጣኗን ወደ ታይዋን መላኳ በቻይናና በታይዋን መካከል ቀድሞ የነበረውን ውጥረት ያባባሰው ሲሆን፣ ቻይናም ይህንን ‹‹የአንድ ቻይና ፖሊሲ››ን መጣስ አድርጋ እንደምትቆጥረው ያስታወቀችበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...