Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶችን የሚያውኩ ተግዳሮቶች

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶችን የሚያውኩ ተግዳሮቶች

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ቀደም ባሉት ጊዜያት (ምናልባት ከስምንት ዓመታት በፊት) የማውቀውና በኬንያ የቻይና ዴይሊ ጋዜጣ የአፍሪካ ክፍል አዘጋጅ የነበረ ባለሙያ አንድ ፕሮግራም ላይ ሰሞኑን አግኝቼ ነበር፡፡ ይህ ሰው ስለአገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምናልባት እኛ ከምናውቀውም በላይ ግምገማዊ መረጃ አለው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ትልልቅ የቻይና ኩባንያዎች ጋር ባለው ግንኙነትም፣ የቻይና ባለሀብቶችን ፍላጎት ቢያንስ በራሳቸው መነጽር ለማየትም አይቸገርም፡፡

በውይይታችን መሀል ታዲያ እንዴት ነው ቻይናዊያን ባለሀብቶች ወደ አፍሪካ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ጨመረ ቀነሰ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ያላቸው የኢንቨስትምንት ሁኔታ ምን ይመስላል? ቀደም ባሉት ዓመታት ከተጀመሩ የጋራ ጥረቶችና ተስፋዎች አኳያስ ግንኙነቱ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ‹‹የአንድ መንገድ አንድ ቀበቶ›› (One Way One Belt)፣ ዓለም አቀፍ የልማት ኢንሼቲቭ ከወራት በፊት በተደረገው ተጨማሪ ስምምነት መሠረት እየተተገበረ ነውን የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት ሞክሬ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቻይናዊን ቁጥብና ንግግራቸውም በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ እንደ መሆኑ፣ እ.ኤ.አ. ግንቦት 2022 ድኅረ ኮቪድ-19 የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን) እና የቻይና ምክትል የንግድ ሚኒስትር ቺያን ኮሚንግ በአፍሪካ ቻይና የትብብር ጉባዔ ስምምነት ላይ ተመሥርተው  ያደረጉት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም ሒደት በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ከመጥቀስ ተቆጥቦ፣ ቻይናዊያን ባለሀብቶች እየገጠማቸው ያለው ተግዳሮትና ሥጋት ላይ ነበር ያተኮረው በንግግሩ፡፡ ተጨማሪ የጽሑፍ መረጃም በኢሜይል በመላክ ጭምር አጠናክሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀዳሚነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት በርከት ያሉ ነባርና ትኩረታቸውን ወደ አገራችን ያደረጉ የቻይና ባለሀብቶችን የማያበረታታና ትኩረት የገደበ መሆኑን አልሸሸገም፡፡ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ በስፋት ለመሰማራት ያለሙ ባለሀብቶች ከስድስትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ እየሆነ ያለውን ሁሉ ከመታዘብ አልፈው፣ መጨረሻውን በመጠበቅ ላይ ነው ያሉት ባይ ነው፡፡

በትልልቅ መሠረተ ልማቶችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የተሰማሩትም ቢሆኑ፣ በአንድ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት ሥራቸውን በታቀደው ጊዜና ሀብት መሠረት ለማከናወን ገድቧቸው ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ ውስጥም እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ መንግሥት ዋነኛ ትኩረቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መሆኑ፣ በተፈጠረው ጫና የበጀት በወቅቱ አለመለቀቅና ፕሮጀክቶችን ቀልጥፎ ማጠናቀቅ አለመቻሉም የማያበረታታ ወቅታዊው “ሴናሪዮ” ሆኖባቸዋል፡፡

በእርግጥ የእኛን አገር ጨምሮ ወደ አፍሪካ የመጡና የሚመጡ ኢንቨስተሮች ያጋጥሟቸዋል የሚባሉ ሌሎች ተግዳሮቶችም አሉ፡፡ የአፍሪካ አገሮች ሁሉም አንድ ዓይነት ባለመሆናቸው በውስጣቸው ሰፊ የባህል፣ የቋንቋ፣ የንግድ ሥራ አካሄድ፣ የሕግ ሥርዓትና የፖለቲካ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ስለዚህ የቻይና ባለሀብቶችም ሲመጡ ከእነዚህ ተግዳሮቶች ጋር ፊት ለፊት መግጠም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተግዳሮት በቀጥታ ፊት ለፊት መግጠም የሚፈልገው የውጭ የቢዝነስ ኃይል ቁጥሩ የሚቀንሰውም ለዚህ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ቻይናዊያን ወጥ በሆነ ሥነ ልቦናና ፖለቲካዊ መስተጋብር የተገነቡ፣ ሠርቶ በመቀየርና በትጋት ሥራ የሚያስቀድሙ፣ ከሞላ ጎደል በአንድ ዓይነት የመግባቢያ ቋንቋና ማዕከላዊነት ውስጥ የቆዩ እንደ መሆናቸው በአንድ አገር ውስጥ ወጣ ገባና የማይናበብን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መስታጋብር አይሹትም፡፡ በተለይ በሕዝቦች መካከል የሚታይን መፈላቀቅ፣ እንደ ሥራ ጠልነት፣ ሌብነትና ለአገር አለመቆርቆር አምርረው ይፀየፉታል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያዊያን ለቻይናም ሆነ ለሌሎች አገሮች ባለሀብቶች መስህብ ሊሆኑ የሚችሉት ሲስማሙ፣ ሲደማመጡና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ሰላማቸውን ጠብቀው ያላቸውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብት ወደ ጥቅም መቀየር ሲችሉ ነው የሚለው ባለሙያው ታሪካዊዋ፣ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላትና ለአፍሪካም እንደ መሪ የምትቆጠረው ኢትዮጵያ ፈጥና ወደ ተቃና መንገድ መምጣቱ እደሚጠቅማት ነው የሚመክረው፡፡

ይህ መሆን ሲችል በሌሎች አፍሪካ አገሮች እየገጠሙ ያሉትን የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የሙስናና የቅልጥፋና ዕጦትን የመሰሉ ችግሮች ለማስወገድና ለማስተካከል የሚከብድ አይሆንም፡፡ አለመግባባትና አለመረጋጋት ካለ ግን (እንደ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ፣ ወዘተ. ሁሉ) ችግሮቹ ስለሚባባሱና መደበቂያ ስለሚገኙ፣ ከእነ ጭራሹ ልማትና ዕድገትን ማደናቀፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሮቹን በአንድ ጊዜ ማስወገድ ባይቻል እንኳን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ለአብነት ሲጠቅስም ‹‹የቻይና አፍሪካ ምርጥ ተሞክሮ ማዕከል›› (SACE) የሚባል ተቋም፣ የቻይና ኩባንያዎች ከኬንያ ጋር ሲሠሩ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ዓይነትና ባህሪያት እያጠና ሪፖርት የሚያወጣ ፋውንዴሽንን ይጠቅሳል፡፡ ወደፊትም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተግዳሮቶችና ባህሪያትን እያጠና እንዲያቀርብ ተስፋ የተጣለበት ነው ይህ ድርጅት፡፡ መቀመጫውን ኬንያ ባደረገው በዚህ ድርጅት አማካይነት በተሠራው ጥናት ላይ የተመሠረተ (Business Perception Index Survey-Kenya) የተባለ መግለጫም አለ፡፡

ጥናቱ ሰዎች ኬንያ ስለሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ባህሪያት እንዲያውቁ፣ የቻይና ኩባንያዎች ስለሚያጋጥሟቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ችግሮች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና እነዚህ ሁኔታዎች (ተግዳሮቶች) በኬንያ ያሉ የቻይና ኩባንያዎችን ምርታማነትና ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት እንደሚያሳድሩ የሚመለከታቸው ዜጎች አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ታስቦ የተሠራ ነው፡፡

በጥናቱ መሠረት የቻይና ኩባንያዎች በኬንያ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ምንድናቸው ሲባል፣ ጥናቱ ከዳሰሳቸው 75 የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ 53 በመቶ ያህሉ ኬንያ ውስጥ ቢዝነስ ለመሥራት ዋናውና ቁልፍ ተግዳሮት ሙስና ነው፡፡ ሙስና ግንባር ቀደሙ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ እነዚህ 53 በመቶ ኩባንያዎች ‹‹ሙስና በጣም ትልቁ ችግር›› መሆኑን ሲያረጋግጡ፣ ሌሎች 15 በመቶ ደግሞ ‹‹ትልቁ›› የሚለውን ቃል ትተው ‹‹ሙስና ችግር ነው›› ብለዋል፡፡ ይህ ማለት በአጠቃላይ 68 በመቶው ሙስና ችግር መሆኑን መስክረዋል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ከሙስና ቀጥሎ ያለውን ችግር ለማወቅ በተደረገ ጥናት 60 በመቶ ያህል ኩባንያዎች፣ ‹‹ሌብነት፣ ዝርፊያ፣ ማበላሸትና በማውደም በማቃጠል የሚደርሱ ኪሳራዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ 71 በመቶ ያህሉ ኩባንያዎች ጥበቃ የቀጠሩ ቢሆንም ችግር መኖሩን ይናገራሉ፡፡ አጥኚዎቹ እንደሚሉት 184 የቻይና የግልና የመንግሥት ኢንተርፕራይዞችን በስልክና በኢሜይል ተገናኝተዋቸዋል፡፡ 75 በመቶ ያህሉ ከጥናቱ ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 38 ኩባንያዎች በማኑፋክቸሪንግና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆኑ፣ የተቀሩት በአገልግሎት ዘርፍ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህን ወደ ሁሉም አገሮች አስፍቶ በመመልከት ችግሮችን በጋራ የማረም ፍላጎት ያለ ይመስለኛል ነበር ያለው፡፡

ለነገሩ ‹ኧረነስት ኤንድ ያንግ› በተባለ ድርጅት አማካይነት የወጣ ሪፖርትም እንደገለጸው፣ የኬንያ የግል ዘርፍ በዓለም ዋንኛ ተብለው ከተጠቀሱ በሙስና የተዘፈቁ ዘርፎች አንዱ ነው ማለቱን ቢዝነስ ዴይሊ የተባለ የኬንያ ጋዜጣም አሥፍሮታል፡፡ ጥናት ከተደረገባቸው የኬንያ ኩባንያዎች ሲሶ (አንድ ሦስተኛ) ማለትም ከሦስት ኩባንያዎች አንድ ጨረታ ለማሸነፍ ጉቦ የሰጠ ነው፡፡ ያለ ጉቦ የሚሆን ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ 27 በመቶ የሚሆኑ የኬንያ የተለያዩ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ሥራ አስኪያጆች፣ የፋይናንስ ተቆጣጣሪዎችና የውስጥ ኦዲተሮች ለተደረገላቸው መጠይቅ በሰጡት መልስ በየኩባንያቸው ከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር (Fraud) መኖሩን አምነዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኬንያ ከአፍሪካ አራተኛ መሆኗ ነው፡፡ ግብፅ 44 በመቶ፣ ናይጄሪያ 30 በመቶ፣ ናሚቢያ 28 በመቶ ከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ስሟ የለም ወይም ተረስታለች ለማለት በቂ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡

እውነት ለመናገር በእኛም አገር ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና እንኳን የውጭውን ባለሀብት፣ ዜጋውንም እያማረረው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የመንግሥት ቅድሚያ ትኩረቱ አገር ማረጋጋትና ሰላም ሆኖ እንጂ፣ ሙስናው ብርቱ ትግል እንደሚጠይቅ ታምኖበት ጥረት መጀማመሩ ይታወቃል፡፡ ጠንካራ የአሠራር ማሻሻያዎችን የለውጥ ዕርምጃዎችም መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

ዛሬ እኮ ጉቦ ዓለም አቀፍ ገጽታ ነው ያለው፡፡ ‹‹አንድ ሰው ጉቦ ሲፈልግ አፉን አውጥቶ አይናገርም፡፡ ነገር ግን ተገልጋይ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ያጓትትበታል፣ ቶሎ አይጨርስም፣ ጉዳይን አይፈጽምም (በጉዳይ ገዳይ እንዲፈጸም ሊገፋም ይችላል)፡፡ ይኼኔ እጁን በገንዘብ ቅባት ማለስለስ እንዳለብን ይታወቀናል፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዳይ ይፋጠንልናል፡፡

የትም ቢሆን ‹‹ጉቦ አምጡ›› ብሎ ቃል በቃል አፍ አውጥቶ የሚጠየቅ ላይኖር ይችላል፡፡ ጥገኛው ‹‹ጉቦ ስጡኝ›› ባይልም ሥራ ሲያጓትትና ሲያመላልስ፣ ጉቦ ፍለጋ መሆኑ ይገመትና በእጅ መሄድ ይጀመራል፡፡ በነገሩ ውስጥ ደላላና ጉዳይ አቀባባይ ከገባ ደግሞ የመንግሥት አሠራርና ሕግ ዋጋ ያጣል፡፡ ይኼም ነው አንዱ የባለሀብት ማማረሪያ፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዴ በራሳቸው በባለሀብቶቹ ውስጥም አጭበርባሪዎች ባይጠፉም፡፡

በመረጃ ሰጪዬ ዕይታ መሠረት ከሌሎች ኩባንያዎች በይበልጥ የቻይና ኩባንያዎች ሙስናና ሌላ የቢዝነስ ተግዳሮት የሚገጥማቸው ሕጉን ስለማያውቁም ጭምር ነው፡፡ ቻይናዎች ለኢንቨስትመንት በሚገቡባቸው አገሮች ያሉትን ሕግጋት ከሥራቸው ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ የታቀደና የተቀናጀ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ለማሠራጨት ደግሞ ኢመደበኛ በሆኑ ዘዴዎች መጠቀም ይሻላል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ይህን በጥሩ ጅምር እየሄዱበት ነው፡፡

የዓለም ባንክ በ2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ያለውን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት 69 የቻይና ኩባንያዎች 95 ጥያቄዎችን እንዲመልሱ መጠይቅ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ቻይናዎቹ ራሳቸው ያጋጠማቸውን ችግር እንዲገልጹ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡

ለመጠይቆቹ በተሰጡት መልሶች መሠረት የቻይና ኢንቨስተሮች ‹‹በኢትዮጵያ አሉብን›› ያሏቸው ዋንኛ ችግሮች (እንቅፋቶች) ‹‹የንግድ ሕጎችና የጉምሩክ ማስተላለፍ ቅልጥፍናና ብቃት ማነስ›› የሚሉት ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮች ኬንያ ውስጥ በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጡ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ አሁን (ከለውጡ ወዲህ) እነዚህ ነገሮች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉም መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

የቻይና ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ‹‹በኢትዮጵያ አሉብን›› ከሚሏቸው ችግሮች ውስጥ ከንግድ ደንቦችና ከጉምሩክ ማስተላለፍ ቅልጥፍናና ብቃት ማነስ ቀጥሎ፣ በሁለተኛ ደረጃ ችግር ናቸው ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥጋት ነበር፡፡ አሁንም ይህ ሥጋት ተባብሶ እንጂ ተቃሎ የሚታይ እንዳልሆነ ያስረዳል ባለሙያው፡፡ ከለውጡ በፊት በአካል ላይ የሚደርሱ የጥቃት ወይም የግል ደኅንነት ሥጋት በኢትዮጵያ የለም ወይም አልተጠቀሰም ነበር ያለው መረጃ ሰጪዬ፡፡ አሁን ግን አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች የውጭ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸው ዕገታና የኢንቨስትመንት ዝርፊያ መታየቱ በውጭ ባለሀብቶች ሥጋት ማሳደሩ አይቀሬ ነው ይላል፡፡ እናም ከሁሉ በቀደመ ለመንግሥት የአገር መረጋጋትና የሕዝብ ደኅንነት ላይ መሥራት አስፈላጊ ሆኗል፡፡

በእኛም አገር ሆነ በሌሎች ታዳጊ አገሮች የሠራተኞችን የትምህርት ደረጃ የማሻሻል ሥራ በቀጣሪዎቹ (ቻይናዎች) እና በሌሎች የተለያዩ ተቋማት ትብብር ጭምር የሚሳካ ነው፡፡ የአንድ ወገን ኃላፊነት አይደለም፡፡ ቀጣሪዎች የቀጠሩትን ሠራተኛ ከሥራው ጋር ማስተዋወቅና መለስተኛ ሥልጠና መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያም የቻይና ኩባንያዎችን ከትምህርት ቤቶች ጋር በማገናኘት የዕውቀት ሽግግር ማድረግ ይቻል እንደሆነ፣ መላ እየተበጀና ዘዴ እየተዘረጋ እንደሚገኝ የመንግሥታቱ ስምምነት ያሳያል፡፡

የተሻለውና ተመራጩ ግን ተማሪዎች በአገሪቱ ባሉት ትምህርት ቤቶች የሚሰጡትን የሙያና የቴክኒክ ሥልጠናዎች ወስደው ከተመረቁ በኋላ ወደ ሥራ ቢገቡ ነው፡፡ የሕግ ተግዳሮቶች የሚባሉት በአብዛኛው ከሠራተኛ ማኅበራት መደራጀት፣ ከመነሻ ደመወዝ አወሳሰን የወሊድና የተለያዩ የፈቃድ የማግኘት መብቶች ከሠራተኛ መብት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ቢሆኑም፣ በዚህ ረገድ የከፋ ክፍተት እንደማይታይ የታወቀ ነው፡፡ ግን ቀሪ ነገሮች ካሉ መፈተሽ ይጠቅማል፡፡

ቻይናውያን ወደ አፍሪካ ሲመጡ ዕውቀታቸውን፣ ቴክኖሎጂያቸውንና ካፒታላቸውን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን የሄዱበትን አገር ባህል፣ ፖሊሲ፣ ሕጎችና ደንቦች ያለማወቅ ችግር አለባቸው፡፡ ይህን ራሳቸውም የሚናገሩት ነው፡፡ እንዲህ ይላል ‹‹የቻይና ዴይሊ›› ው ጋዜጠኛ፡፡ ‹‹When chinese companies go to africa, we take talent, technology and capital, but we lack an understanding of local laws, policies and culture.›› ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ቢሆን ግን ከራሳቸው ጥረት ባሻገር የእኛ የኢንቨስትመንት፣ የውጭ ጉዳይና የባህልና ቱሪዝም… መሥሪያ ቤቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ዋናው ቁም ነገር ቻይናዎች ያሉባቸውን እነዚህን ክፍተቶች እንደ ሕዝብም ልንሞላላቸው ወይም እንዲሟሉላቸው ልንተባበራቸው ኃላፊነት ያለብን መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ ጥቅማችን የጋራ ነውና መርዳትና ማገዝ አለብን፡፡ ሊያውቁት የሚገባ ባህላችንን፣ የእርስ በርስ ግንኙነቶቻችንም፣ በዓላቶቻችንን፣ የቀጣሪዎች አያያዛችንን፣ የምንታገላቸውንና የምንታገሳቸውን ማኅበራዊ ልምዶችና አመለካከቶቻችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማሳወቅ ይጠበቅብናል፡፡

በአስተያየት ሰጪዬ ዕይታም ሆነ ከሚዛናዊ ዕሳቤ አንፃር ሲታይ ራስን ከማዳከምና የወል ጥቅምን በውዝግብ ከማወክ ወጥተን እንደ ሙስና፣ ወንጀል፣ ሥርቆት ማስፈራራት፣ ንብረት መዝረፍ ወይም ማውደም የሥራ መሣሪያዎችን መሰወር ወይም ማበላሸት፣ በአገራችን ባህልም ሆነ እምነቶች ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን፣ በተግባራችንም ጭምር ልናረጋግጥላቸው ይገባል፡፡ አሁን እነዚህ ነገሮች መጓደላቸው ባለሀብቶች እንዳይሳቡ አድርጓል፡፡

ቻይናዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የውጭ ባለሀብቶችም በአገራቸው የሚያመርቱትን ሸቀጣ ሸቀጥ ወደ እኛ አገር የሚያመጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ እዚሁ አገራችን ውስጥ አምርተው ለእኛም የሥራ ዕድል ፈጥረው ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ አቅርበው እነሱም አትርፈው እኛም የምንጠቀምበትን ሥራ እንዲሠሩ የተመቻቸንና ተመራጭ መሆን አለብን፡፡ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ይበልጥ የተጠናከረ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ከእነሱ የሚፈለገውንም በግልጽ ማሳወቅ ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ ብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች ከቻይና ጋር በሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ግን በራሳቸው በቻይና አንዳንድ ባለሙያዎችና ኩባንያዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የኢኮኖሚ አሻጥሮች እንደሚፈጠሩ ማወቅና ነቅቶ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ የቻይና ኢንቨስተሮች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችን በማስወገድ ልንተባበራቸው ይገባል ሲባል፣ ግዴታቸውን (በተለይ ከግብርና ከቀረጥ አኳያ)  አይውጡ ማለትም አይደለም፡፡

ስለቻይና ምርቶችና ሥራዎች ያለንን የተሳሳተ ግምት ማስተካከል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ አገር ምርቶች በጥራት ደረጃዎች ልኬት ማለፋቸውን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ ቻይና ትልቅ ሕዝብ፣ ትልቅ ታሪክ፣ ትልቅ ሥልጣኔና ቴክኖሎጂ፣ ትልቅ ተስፋና ትልቅ ራዕይ ያላት ታላቅ አገር ናትና ከቻይና ባለሀብቶችና ባለሙያዎች ጋር በትኩረት መሥራት ይበጀናል እንጂ አይጎዳንም፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...