Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የእንስሳት ዕርባታን በባለሙያ የመደገፍ ጉዞ

በእንስሳት ዕርባታ ዘርፍ ከሚሠሩ የግል ድርጅቶች አንዱ ትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ በእንስሳት ዕርባታ፣ በከተማ ግብርናና በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ዜጎችን የማማከር፣ የማስገንዘብና የተለያዩ ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የከተማ ግብርናን ለማዘመን ወጣቶችን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ የዶሮ ዕርባታ በዕውቀት የሚመራበትና የሚሠራበትን መንገድ ለወጣቶችና ለሌሎችም የማማከር አገልግሎትን እየሰጠ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአነስተኛ መካከለኛ ደረጃ የእንስሳት ዕርባታ ውስጥ መሰማራት ለሚፈልጉ ሰዎች የባለሙያ ሥልጠና ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ስለ ማኅበሩ እንቅስቃሴ ምክትል ሥራ አስኪያጁን ተክሌ ሽፈራውን (ዶ/ር) ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ትረስት አግሮ ማን ነው?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- በእንስሳት ሕክምና በተካኑ ባለሙያዎች በ2013 ዓ.ም. የተመሠረተው ትረስት አግሮ የማማከር ማኅበር ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በከተማ ግብርና በእንስሳት በዶሮ ዕርባታ፣ በከብት ማደለብ ላይ ለተሰማሩ ሥልጠና የሚሰጥ ነው፡፡ ሥልጠናው በዘልማድ የሚሠሩትን በዕውቀት ላይ ተመሥርተው እንዲሠሩ ስለሚያደርግ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በዘልማድ ሲሠሩ ተጠቃሚ ቢሆኑም እንኳን የዕለት ጉርሳቸውን ወይም ዓመት ቀለባቸውን ብቻ የሚሠፍሩ ናቸው፡፡ እንደ እኛ ያሉ ድርጅቶች ሲያማክራቸውና ሥልጠና እንዲያገኙ ሲያደርጓቸው ውጤታማ መሆን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጤናማ ዝርያ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ሌሎችም ሙያዊ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ ከቀለብ አልፈው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዋና ዓላማችን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ውጤታማ እንዲሆኑና ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ምርት እንዲያቀርቡ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ያሉባቸውን የዕውቀት ክፍተት በሥልጠናና በማማከር መሙላት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከማማከር በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎቻችሁ ምንድናቸው?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የእንስሳት ዕርባታ ውስጥ መሰማራት ለሚፈልጉ ዜጎች የባለሙያ ሥልጠና ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ከተጨማሪ ለዚህ የሚሆን ምርት እናቀርባለን፡፡ ማኅበራችን ለየትኛውም ተቋም፣ ወጣቶችና የማኅበረሰብ ክፍሎች በሥራ ላይ የሚገኙና ወደ ሥራው ለሚገቡ ዜጎች ከሥልጠና ባሻገር ምርቶችን እናቀርባለን፡፡ በዋናነት ሥራችን ሙያዊ የማማከር ሥራ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ግን ጤናማ የሆኑ የዶሮ ጫጩቶችን፣ ለሥጋና ለወተት ምርት የሚሆኑ ላምና ከብቶችን ማኅበራችን ያቀርባል፡፡ ከምንሠራባቸው ፕሮጀክቶች መካከል በመንግሥት ደረጃ እየተተገበረው ያለው ‹‹የሌማት ትሩፋት›› ላይ በማማከርና በሌሎች ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ፕሮጀክቱ፣ በዋናነት በየክፍላተ ከተሞች የሚተገበር ሲሆን፣ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዶሮ ጫጩት፣ እንቁላል፣ የወተት ላም፣ የሥጋ ከብት ከማቅረብ በተጨማሪ ፍየልና በጎችንም ለሽያጭ እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡– ማኅበራችሁ የባለሙያዎች ስብስብ ስለሆነ በዘርፉ ያለውን ሀብትና ውስንነት እንዴት ያዩታል?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት 40 በመቶውን የሚሸፍነው የግብርና ዘርፍ ነው፡፡ በቀንድ ከብቶች ብዛት ወይም ሀብት ከአፍሪካ የመጀመሪያዎቹ መሆናችን ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ዜጋ በቀን፣ በሳምንት፣ በወር ምንያህል የሥጋና የወተት ተዋፅኦ ይጠቀማል የሚለው ሲታይ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም ዋና ችግሩ በባለሙያ ያልታገዙ ሥራዎች ስለሚሠሩ ነው፡፡ ልማዳዊ የሥጋ ከብት ማድለብ፣ የወተት ላም ዕርባታ ላይ የሚሠሩ ዜጎች በርካታ ቢሆኑም በባለሙያ የታገዙ ባለመሆናቸው ውጤታማ አልሆኑም፡፡ ለዚህም እንደ ማኅበር የማማከርና የማሠልጠን ሥራ እየሠራ እንገኛለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የባለሙያ እገዛ እንደ ቅንጦት የሚቆጥሩም አሉ፡፡ በሥራችን ከሚገጥሙን ችግሮች አንዱ የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ለምሳሌ የዶሮ ዕርባታ ሥራ ቀላልና ከባለሙያ ምክር ውጪ የሚሠራ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ይህም ወደ ሥራ ሲገቡ በዘልማዳዊ አሠራሮችን ስለሚከተሉ ውጤታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ ተመልክተናል፡፡ ለዚያ ነው ማኅበራችን በእነዚህ ሥራዎች ላይ የባለሙያ ምክርና እገዛ የሚፈልግ ነው ብለን የተነሳነው፡፡ ሕንፃ ሲሠራ ብዙ አማካሪ ድርጅቶች ይሳተፉበታል፡፡ መንገድም ሲሠራ እንዲሁ ነው፡፡ ጤናችን ለመጠበቅም እንዲሁም የአማካሪና የባለሙያ እገዛን እናገኛለን፡፡ የእርሻና የእንስሳት ዕርባታ ዘርፉም ቢሆን የሠለጠኑ ባለሙያዎች ምክር ካላገኙ ውጤታማ አይሆኑም፡፡ በከተማ ግብርና ለመሥራት የተደራጁ፣ ትልልቅ የእርሻ ባለሀብቶች የግድ የባለሙያ ምክርና እገዛ የሚሹ ናቸው፡፡ እንደዚያ ከሆነ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ማምረትና በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ማኅበራችን  በተለይ በእንስሳት ዕርባታ ዘርፍ የማማከር ሥራን ተደራሽ ማድረግ ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ባለሙያዎች አሏችሁ? ተደራሽነታችሁ እስከምን ድረስ ነው?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- በእንስሳት ሕክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ አሥራ አንድ ባለሙያዎች አሉን፡፡ በአጠቃላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን ጨምሮ ለ20 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፡፡ ማኅበራችን ወደ እንስሳት ዕርባታ የሚገቡ ሰዎችን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም ውስጥ የዶሮ ዕርባታ፣ የከብት ማድለብ፣ የወተት ላምና ሌሎችም ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ሥራችን በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራንም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ በስፋት እየሠራን እንገኛለን፡፡ እስከ ወረዳ መዋቅር ድረስ ወርደን የሥልጠናና የማማከር ሥራ እንሠራለን፡፡ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችም የእኛን የማማከር ሥራ ፈልገው አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሠልጣኞቻችሁ ከሥልጠናው በኋላ ወደ ሥራ ሲገቡ ምን ዓይነት ተግዳሮት ይገጥማቸዋል?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- ወደ ሥራ ሲገቡ የሚቸገሩበት ዋነኛው ጉዳይ የፋይናንስ እጥረት ነው፡፡ እኛም በሥራችን ላይ ሥልጠና የምንሰጣቸው ሰዎች የገጠመን ችግር ብለው የሚነግሩን የገንዘብ ወይም የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የአቅም ውስንነት፣ የመኖ ችግርና ሌሎችም ያልዘረዘርናቸው ችግሮች ይገጥማቸዋል፡፡ በዋነኛነት ግን የፋይናንስ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በማማከር፣ በሥልጠናና በእንስሳት ዕርባታ ተጠቃሚነታችሁ ምን ያህል ነው? ቀጣይ ግባችሁ ምንድነው?

ተክሌ (ዶ/ር)፡- በማማከርና በክህሎት ሥልጠና የምናገኘው አብዛኛው ሥራ ፕሮጀክት በመሆኑ በስምምነቱ መሠረት ክፍያ እናገኛለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ የሥጋ ከብትና የወተት ላም በማድለብና የዶሮ ዕርባታ ላይ የሚሠማሩ ደግሞ የተሻለ ዝርያ ከእኛ በመግዛት ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ አንዳንዴም መልሰን እንገዛቸዋለን፡፡ የማኅበራችን ቀጣይ ግባችን ልክ እንደ ሌሎች ዘርፎች በእንስሳት ዕርባታና በከተማ ግብርና የማማከር ሥራችን ማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሰዎች ሙያው ማማከር ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ዘርፍ ላይ የራሳችን አበርክቶ ማድረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...