Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየመብት አባቱ ማነው?

የመብት አባቱ ማነው?

ቀን:

በአብርሃም ጴጥሮስ

ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ስለምናገኛቸው አገልግሎቶችና ስለሚደርሱብን የመብት ጥሰቶችና እንግልቶች ስናወራ ብዙ ብንቆይም መግባባት አልቻልንም፡፡ እኔ የምለውና እሱ የሚለው ለየቅል ሲሆንብኝ ለመሆኑ የመብት አባቱ ማነው ብዬ ጠየቅኩት፡፡ እሱም በተራው እኔ የነፍስ አባት እንጂ የመብት አባት አላውቅም አለኝ፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን የነፍስ አባት እንደሚያስፈልገን ሁሉ በምድራዊ ሕይወታችን የሚደርሱብን በደሎችን ለመከላከል የመብት አባት እንዳለን፣ ነገር ግን እንደማናውቀውና እንደማንጠቀምበት ቀለል ባሉ በየዕለቱ ከሚገጥሙን የመብት ጥሰቶች በምሳሌነት በማጣቀስ ሳስረዳው፣ የነፍስ አባት ብቻ ሳይሆን የመብት አባትም እንዳለ ተግባባን፡፡ ጓደኛዬን የመብት አባት ስለመኖሩና ማን እንደሆነ አስረድቼ፣ ያሳመንኩበትን ወግ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚመለከት መስሎ ስለተሰማኝ ላጋራችሁ ወደድኩኝ፡፡

ጉዳዩ ሩቅ አይደለም፡፡ የእኛው የኢትዮጵያውያን የልቦናና የአስተሳሰብ ውቅር የተሠራበት ሁኔታ የግልና የወል መብቶቻችንን የሚያስከብርልን የመብት አባት እንዳለ በየዕለት ኑሯችን በሚገጥሙን ችግሮች ስናስተጋባ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ የነፍስ አባታችንን ለይተን የምናውቀውን ያህል የመብት አባታችንን ሳናውቅ አንድ ወገን ለመብቶቻችን መጣስና መከበር ተጠያቂ ነው ብለን ማሰባችን ነው፣ ከጓደኛዬ ጋር እንድወያይና ለእናንተም ማጋራት ያስገደደኝ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መንግሥት ሕግ የማርቀቅ፣ የማውጣትና የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት፡፡ የወጡት ሕጎች፡ አገሪቱ ያፀደቃቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ደንቦችና መመርያዎች ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ እንዲጠቀምባቸው ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥም ከመንግሥት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ኃላፊነቱ በአግባቡ ከተወጣ አገልግሎት ሰጪውና ተቀባዩ በተቀመጠው ሕግና ሕግ መሠረት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥና እንዲቀበል ማድረግ፣ የአገልግሎት ሰጪውና ተቀባዩ ኃላፊነት ነው፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ሲስተም መዘርጋትና የግብይት ሥርዓቱ ምንም ዓይነት እሴት ከማይጨምረው ደላላ መዘውር ማላቀቁ የመንግሥት ሚና መሆኑን ግን መዘንጋት ሳይኖርበት፣ የእኛ ሚና ላይ ትኩረት ማድረጉን መርጫለሁ፡፡ በእኛ አገር የሚስተዋለው ግን ከዚህ በተለየ ነው፡፡ እውነታውን በጭብጥ ለማስደገፍ አንዳንድ ጉዳዮችን በወፍ በረር መዳሰስ ተገቢ ነው፡፡

መንግሥት በከተሞች ያለውን ድህነት ለመቀነስ በተለይም ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩትን ዜጎች ለመደጎም በሚል ለዘይት፣ ለነዳጅ፣ ለስኳር፣ ለዱቄት፣ ወዘተ. በዓመት በርካታ ቢሊዮን ብሮች ድጎማ ያደርጋል፡፡ ሆኖም ይህ ድጎማ ለታሰበለት ማኅበራዊ መሠረት ተጠቃሚነት ሲውል አይታይም፡፡ ቢሊየነሩም ከድህነት ወለል በታች ያለውም ዜጋ የዚህ ድጎማ ተጠቃሚ እየሆነ በመምጣቱ፣ መንግሥት የድሆችን አኗኗር ለመደጎም የነበረው ዕሳቤ ውጤት አምጥቷል ማለት አይቻልም፡፡

መንግሥት ለመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ከሚያወጣቸው በርካታ ቢሊዮን ብሮች በተጨማሪ፣ የአገልግሎቶችና የዕቃዎች መሸጫና መጠቀሚያ በየጊዜው የሚከለስ ታሪፍ አውጥቷል፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ በየወሩ ሲከለስ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆኑ የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች፣ የከተማ ታክሲዎች፣ ወዘተ. ተመጣጣኝ የሆነ ታሪፍ አውጥቶ በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ያስተዋውቃል፡፡ ሆኖም የወጣው ታሪፍ ሥራ ላይ ሲውል አይታይም፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች በወጣው ተመን መሠረት አገልግሎት መስጠትን እንደ ሬት ይመራቸዋል፡፡

ለምሳሌ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ታክሲዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታስቦ፣ እሰከ ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር 3.50 ብር፣ ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ 6.50 ብር፣ ወዘተ. እንዲያስከፍሉ በአዲስ አበባ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ታሪፍ ወጥቶላቸዋል፡፡ ይህ ታሪፍ በኤሌክትሮኒክስና በኅትመት ሚዲያዎች ለሕዝብ ከመገለጹ ባሻገር፣ ተሳፋሪው ሊያየው በሚችለው ግልጽ ቦታ (ከሾፌሩ ጀርባ) እንዲለጥፉ ይገደዳሉ፡፡ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ሲያገኟቸው እንዳይቀጡ የታሪፉ ዝርዝር በተባለው ቦታ ተለጥፎ ይታያል፡፡ ሆኖም የሚጠይቁት ክፍያ እጥፍና ሁለት እጥፍ ነው፡፡ በሁሉም መስመሮች ተሳፍሬ ጥናት ስላላደረግኩ፣ ይህ ድርጊት ሁሉም ባለታክሲዎች ይፈጽሙታል ብሎ መደምደም በአግባቡ የሚሠሩትን ያለ በደላቸው መኮነን ስለሚሆን አብዛኞቹ ማለቱ ተገቢ ነው፡፡

ለዚህ በቂ ምሳሌ እንዲሆን ከኮልፌ ሉካንዳ እስከ ጦር ኃይሎች ጫፍ ድረስ ያለውን እንመልከት፡፡ ይህ ርቀት 2.5 ኪሎ ሜትር ሲሆን በታሪፉ መሠረት ሊከፈል የሚገባው 3.50 ብር ሆኖ እያለ፣ የሚከፈለው ግን ከጧት እስከ ማታ አሥር ብር ነው፡፡ በዚሁ መስመር የትራንስፖርት ተጠቃሚ ከሆኑና ከታሪፍ ውጪ ለምን እንደሚያስከፍሉ ቢጠይቁ፣ የሚገጥምዎት ተቃውሞ ቀላል አይደለም፡፡ በጣም የሚገርመው ጥያቄውን የሚቃወመው ሾፌሩና ረዳቱ ብቻ ሳይሆኑ ተሳፋሪዎች ጭምር መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ያህል እጥፍ ማስከፈላቸው ሳያንስ ተሳፋሪዎች እንደ ሰርዲን ታጭቀው ነው የሚጓዙት፡፡ አሥራ ሁለት ሰዎች መጫን የሚገባው ሚኒ ባስ አሥራ ስምንትና ከዚያ በላይ ይጭናል፡፡ ጠጋ ጠጋ በሉ ሲል ረዳቱ ዝም ካሉ ወይም ለምን እጠጋለሁ ካሉ የሚወርድብዎ የስድብ ውርጅብኝና ግልምጫ አያድርስ ነው፡፡ አንዳንዴ ጎትቶ ሊያወርድዎትም ይዳዳዋል፡፡ ይህንንም ሲደረግ አምስት ደቂቃ ለማትቆይበት ምን አለ ብትተባበር እያለ፣ ለሒሳቡም እኛ እንሞላለን ብሎ መብቱን አሳልፎ የሰጠውና ሌላውም ስለመብቱ እንዳይናገር የሚያደርገው ተሳፋሪ ጉዳይ ሁሌ የሚገርመኝ ትዕይንት ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ የተማረረው አንዳንድ ተጠቃሚ ደግሞ ተጨቃጭቆ የእርስዎ ዓይነት ምላሽ ሲገጥመው ምን ዓይነት ዘመን ላይ ነው ያለነው፣ መንግሥት ምን እየሠራ ነው ሲል ይደመጣል፡፡ የመብት አባቱ ማነው ብዬ የጀመርኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ መንግሥት እኮ የነዳጅ ድጎማ አድርጎ፣ ታሪፍ አውጥቶ፣ ለሕዝብ ከማሳወቅ አልፎ በየታክሲው በሚታይ ቦታ እንዲለጠፍ አድርጓል፡፡ የመብታችን አባት እኛው ሆነን እያለን መንግሥትን የመብት አባት አድርጎ መንግሥትን ሲኮንኑ መኖር፣ የልቦናና የአስተሳሰብ ውቅራችን የተዛባ መሆኑ በቂ ምልክት አይሆንም ትላላችሁ?

አንድ ሰሞን ከ250 እስከ 300 ብር ይሸጥ የነበረው ዘይት በአንድ ጊዜ በደላላዎችና በሕዝብ ሥቃይ ሀብታቸውን በሚያደልቡ ጥቂት ስግብግብ የኢኮኖሚ አሻጥረኛ ነጋዴዎች አማካይነት ከ1‚000 ብር እንዲዘል ከማድረግ አልፎ፣ የዘይት ጀሪካን በዓይን ማየት ብርቅ እስኪሆንብን ድረስ የመሰወር ሥራ ተሠርቷል፡፡ የተደበቁት ዘይቶች ከየጢሻው ሲያዙ ዓይናችን የተራበችውን የዘይት መያዣ ማየት ስትጀምር እሰይ ዘይት ተገኘ ከማለት ውጪ ለምን እንዲህ ሆነ አንልም፡፡ የመግዣው ዋጋ ያው አሁንም እንደተሰቀለ ነው፡፡

ይህንን ችግር ይፈታሉ ተብለው የተቋቋሙ አንዳንድ የሸማቾች ማኅበራትም ችግሩን የሚፈቱ ሳይሆኑ፣ አባሪ ተባባሪ ሆነው ለእነዚያ ሰው በላ ነጋዴዎች ያሸጋግሩታል፡፡ ከሸማቾች ከ21 ብር ጀምሮ ይገዛ የነበረው አንድ ኪሎ ስኳር አሁን በፌስታል ተቋጥሮ በየመንገዱ በ120 ብር ይቸበቸባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከየት አመጡት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ፣ መንግሥት ምን እየሠራ ነው ማለት ይቀለናል፡፡ ምክንያቱም የመብት አባታችን መንግሥት ነው የሚል አሳሳች መንፈስ ሸብቦን የሚጫንብንን የኢኮኖሚ አሻጥር ተቀብለን በ1‚000 ፐርሰንት ቢጨምርም፣ እያጉረመረሙ ገዝቶ ከመጠቀም ባለፈ ለአንድ ሳምንት እንኳን ምርቶቹን ከመግዛት ተቆጥበን ደንበኞቻችንን ለመቅጣት የሚጠቅም  የጋራ አስተሳሰብ መገንባት አልቻልንም፡፡

የከተሜውን ሸማችና አምራቹን በቀጥታ ለማገናኘት በሚሠሩ ሥራዎች፣ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ ዋስትና ዕጦት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተቻለ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ መንግሥትም ይህንን በአገራችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የመንግሥት ጥረት ግን ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል ኅብረተሰቡ የመብት አባት መንግሥት ነው ብሎ ከማሰብ አባዜ ወጥቶ ለምን ብሎ በመጠየቅ፣ ያላግባብ ሲጨመር ባለመግዛት፣ ከታሪፍ ውጪ የሚያስከፍሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን በጋራ በመታገልና ለሕግ አካል አሳልፎ በመስጠት የመንግሥትን ጥረት አግዞ የኢኮኖሚ አሻጥረኞችን ሴራ የማክሸፍ ልምድ ልናዳብር ይገባል፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ያለ እጅ መንሻ ለመፈጸም የማይፈልጉ የመንገግሥት አመራሮችና ባለሙያዎችን ማስቆም ያለብን እኛው ባለጉዳዮች እንጂ፣ በመንፈስ የሳልነው የመብት አባት እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የራሳችንን ድርሻ እየተወጣን መንግሥት ጥረቱ በሲስተም እንዲታገዝ ካደረገልን የራሳችን መብት አባት ራሳችን እንሆናለን እያልኩ ከምን አገባኝነት አስተሳሰብ ወጥተን፣ ሁላችንም ለጋራ ጥቅማችን የቻልነውን ጠጠር እንወርውር እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...