Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ብድር ሲሰጡ ከተማን ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም ያማከለ ማድረግ አለባቸው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ እያሳረፉ ያሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የብድር አቅርቦታቸውን ግን በከተማ አካባቢ የተወሰነ በመሆኑ፣ ወደ ገጠር ማስፋት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

ገዥው ይህንን የገለጹት ገዳ ባንክ በይፋ ወደ ሥራ መግባቱን በማስመልከት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ባንኮች ለአገር ኢኮኖሚ እያበረከቱ ያሉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ የሚባል መሆኑን የጠቆሙት ይናገር (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ነባርም ሆኑ አዳዲስ ባንኮች ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ በሁሉም መለኪያና ደረጃ አዳዲሶቹም ሆኑ ነባሮቹ ባንኮች ጤናማና ትራፋማ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢኮኖሚውን በብድር በመደገፍ በተለይ ለግሉ ዘርፍ እየሰጡ ያሉት ድጋፍ ኢኮኖሚውን እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

‹‹ኢኮኖሚው በአብዛኛው በብድር የሚንቀሳቀስና ባንኮችም በየዓመቱ እየሰጡ ያሉት ብድር እየጨመረ የመጣበት ወቅት በመሆኑ፣ የአገራችን ባንኮች ኢኮኖሚውን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፤›› በማለት እንቅስቃሴያቸውን እንደሚገፉበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባንኮች አሁን እየሰጡ ያሉት ብድር ለከተማ አካባቢ ብቻ መሆኑን እንደ ክፍተት ያመለከቱት ገዥው፣ በዕለቱ ወደ ሥራ የገባው ገዳ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ገጠሩን ማዕከል ያደረገ፣ በተለይ ለግብርና ብድር ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ለግብርና ቅድሚያ ይሰጥ ማለት ሌሎች እንደ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ብድር አያስፈልጋቸውም ማለት እንዳልሆነ የጠቆሙት ገዥው፣ ‹‹በአብዛኛው የአገራችን ባንኮች የብድር አሰጣጥ ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ግን፣ ከተማ ላይ ብቻ ያዘነበለ በመሆኑ፣ ይህንን ወደ ገጠር ማስፋት ስለሚያስፈልግ፣ ባንኮች ዓይናቸውን ከከተማ ውጪ ገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ እንዲጥሉም ጠይቀዋል፡፡ የባንክ ተደራሽነትን በገጠር ለማስፋትና የብድር ተጠቃሚ ለማድረግ የተለመዱ የባንክ አገልግሎቶችን መከተሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ስለሚጠበቅ፣ በዚያ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች የብድር ሥርጭትን በተመለከተ ባንኮች እየሰጡ ያሉት ብድር ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል መሆኑን ገልጸው፣ ከባንኮች እየተበደሩ ያሉ ዜጎችም ወደ 300 ሺሕ አካባቢ የሚጠጉ ብቻ በመሆናቸው፣ ይህንን አሠራር መቀየር እንደሚኖርባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡

የተበዳሪዎችን ቁጥር ለማብዛትም ሆነ የባንክ ተደራሽነትን ለማስፋት ቴክኖሎጂን መሠረት ማድረግ የግድ መሆኑንና ገዳ ባንክም በዚሁ መንገድ መሄድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ብድር ለመስጠት የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የግድ በመሆኑ፣ እዚህ ላይ መረባረብ ጠቃሚ እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ከባንኮች የሚሰጥ ብድር ምንጩ ቁጠባ መሆኑን ያስታወሱት ገዥው፣ ‹‹ባንኮች ቁጠባን መሠረታዊ ሥራቸው አድርገው መውሰድ ይኖርባቸዋል፤›› በማለት፣ ገዳ ባንክም ወደ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ በቁጠባ ላይ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ገዳ ባንክ በገጠር በአርሶ አደሮችና በአርብቶ አደሮች አካባቢ ባንክን ተደራሽ በማድረግ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ያለን ማኅበረሰብ ማገልገል ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡ ቁጠባን በማሰባሰብም ሆነ በሌሎች የባንክ አገልግሎቶች በተለይ በገጠር አካባቢ ገና ብዙ የሚቀረው በመሆኑ፣ ይህ ባንክ በገጠር አካባቢ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ያሳሰቡት ገዥው፣ አንዱና ትልቁ የትኩረት አቅጣጫውም ማድረግ ያለበት ይህንኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በገጠር በተለይ የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ ከአነስተኛ ብድር ጀምሮ እስከ መካከለኛና ከፍተኛ ብድር በማቅረቡ ረገድ ይህ ባንክ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም የውጭ ባንኮች ይገባሉ ተብሎ ስለሚታሰብና ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋርም ሆነ ከውጭ ባንኮች ጋር የሚኖር ውድድርን ተወጥቶ ወደ ትልልቆቹ ባንኮች መድረስ እንዲቻል ከፍተኛ ጥረት ልታደርጉ ይገባችኋል በማለት ለባንኩ አመራሮች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ስለዚህ ገዳ ባንክ የኢትዮጵያ ባንክ ነው፡፡ በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች አገልግሎቱን እየሰጠ፣ ይህንን ትልቅ  ስም ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ ገዳ ባንክ ሲመሠረት ዘግየት ብሎ የተመሠረተ ባንክ ቢሆንም፣ ቴክኖሎጂን ከተጠቀመ፣ ቁጠባ ላይ ከተረባረበ የአገልግሎት አሰጣጡ የተሻለ ደረጃ ላይ ከደረሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ወዳሉ ባንኮች መሸጋገር የሚችልበት ዕድል እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የራሳቸውን ሕንፃ ገንብተውና ገዝተው ወደ ሥራ ከገቡ ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ገዳ ባንክ፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርፆ ኢንዱስትሪውን እንደተቀላቀለ የገለጹት፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወልዴ ቡልቱ እንዳሉት፣ በዚህ ስትራቴጂው መሠረት ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመ ነው፡፡ ‹‹ባንኩ የአዲሱ ትውልድ ባንክ እንደመሆኑ መጠን በዘመናዊ አገልግሎት የባንክ ተደራሽነትን ለማስፋት የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

በገዳ ባንክ የሥራ ማስጀመርያ ፕሮግራም ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ባንኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን አስተዋጽኦ የሰፋ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ጥሩ ተወዳዳሪ ሆኖ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ገዳ ባንክ በ25 አደራጅ ኮሚቴ አስተባባሪነት ከ28 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተቋቋመ ባንክ ነው፡፡ 552 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 1.57 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ይዞ ወደ ገበያው የተቀላቀለ መሆኑም ታውቋል፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ፣ ከባንኩ ባለአክሲዮኖች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች