Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘምዘም ባንክ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት በመጀመር በፈር ቀዳጅነት የሚጠቀሰው ዘምዘም ባንክ፣ በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ 146 ሚሊዮን ብር ኪሣራ ሲያጽፍ፣ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡

ባንኩ የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጸጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው ኪሣራ ተጠባቂ መሆኑን አመልክቷል፡፡ እንደ ባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት፣ ከወለድ ነፃ ባንክ ከባህሪው አንፃር ፋይናንስ ያደረገው (ያበደረው) ገንዘብ ትርፍ በአንድ ጊዜ የሚገኝበት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የተመዘገበ ኪሣራ እንጂ፣ ፋይናንስ እያደረገ ካለው ኢንቨስትመንቱ ትርፍ እያጻፈ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በሥራ መጀመርያው ዓመት ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱም ኪሣራ ለማጻፉ አንድ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፋይናንስ የተደረገው የገንዘብ መጠን ከ680 ሚሊዮን ብር ላይ የደሰ ሲሆን፣ ለፋይናንስ የሚያውለው ተጨማሪ አቅም እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡

ሰሞኑን የባንኩን ወቅታዊ አቋምና በዓለም አቀፍ ተቋማት ያገኛቸውን ሽልማቶች በማስመልከት በተሰጠ መግለጫ ላይ፣ ባንኩ የደንበኞቹን ቁጥር እያሳደገ ከመሆኑም በላይ እያቀረበ ያለው ብድርም እስካሁን ወደ ባንክ መጥተው ፋይናንስ ለማግኘት ያልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡

በባንኩ ፋይናንስ አሰጣጥ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ በድሪ፣ ባንኩ የሚያሰባስበውን ተቀማጭ ገንዘብ በሙሉ ፋይናንስ እያደረገው ነው፡፡

‹‹እስካሁን ብድር ፈልጎ ያላገኘ ወይም ይህንን ዘርፍ አናስተናግድም ብለን የመለስነው የለም›› ያሉት ወ/ሮ መሊካ፣ አሁንም ፋይናንስ (ብድር) የሚፈልግ ሁሉ በራቸው ክፍት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአንፃሩ ግን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለአገሪቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር፣ የብድር አሰጣጡ እንዴት እንደሚስተናገድ በቂ መረጃ የሌለ መሆኑ እንደ አንድ ተግዳሮት የሚወሰድ በመሆኑ፣ ይህንን በተገቢው ደረጃ ማስረጽ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ባንኩ እየሰጠ ያለው አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሊካ እንዳስታወቁት፣ አንደኛው ሽልማት የተሰጠው የግሎባል ብራንድ በተባለ ሸላሚ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት የዘንድሮውን ምርጥ አዲስ የፋይናንስ አካታች ብራንድ ሽልማት (Best New Financial Inclusion Brand) ለዘምዘም ባንክ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግሎባል ብራንድ በዘንድሮው የአሥረኛ ዙር የምርጥ ብራንድ ሽልማትን ከ130 አገሮች የተውጣጡ 18 ሺሕ ድርጅቶችን ያወዳደረ ሲሆን፣ ዘምዘም ባንክ ባስቀመጠው ልዩ ራዕይ፣ እሴቶችና ባለልዩ ብራንድ በመሆን እንደተመረጠ የሽልማቱ አዘጋጅ ግሎባል ብራንድ በማስታወቁ፣ ሽልማቱን ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዘምዘም ባንክ ይህንን ሽልማት እንዲያገኝ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ ከተቋቋመበት አንዱና ዋና ዓላማው የሆነውን የሸሪአ መርሆዎችን መሠረት አድርጎ የሚሄድ መሆኑን ከማሳየት አንፃር፣ የባንኩ ብራንድ ገላጭ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ ስትራቴጂውን በአግባቡ ቀርጾ፣ በተለይም ከእምነቱና ከባህሉ ጋር ተስማሚ የሆነ አገለግሎት ባለመኖሩ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ሳያገኙ ለቆዩ የማኅበረሰብ አካላት እንዲሁም፣ የባንኩን ቢዝነስ ሞዴል ፈልገው ለሚመጡ ለማንኛውም ማኅበረሰብ አማራጭ የባንክ አገልግሎት ይዞ በመቅረቡ ለሽልማት መብቃቱን ወ/ሮ መሊካ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ካምብሪጅ ኢስላማዊ ፋይናንስ አድቫይዘሪ የተባለውና መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዓለም አቀፍ ተቋም፣ ዘምዘም ባንክን ‹‹ጠንካራ ስላሚክ ባንክ በኢትዮጵያ›› በሚል እንደሸለመው ተገልጿል፡፡ በኢንዶኔዥያ ጃካርታ በተካሄደው የስምንተኛ ዙር የሽልማት ሥነ ሥርዓት፣ ዘምዘም ባንክ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ ሞዴልን ተደራሽ ለማድረግ ባደረገው ብርቱ ጥረት ሽልማት እንደሰጠው ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሽልማት ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ኢስላማዊ ፋይናንስ ሽልማት (GiFA)፣ በኢትዮጵያ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እንዲጀመር፣ የፋይናንስ አካታችነት እንዲስፋፋና የባንክ ኢንዱስትሪው እንዲጎለብት በማድረጋቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሽልማት መስጠቱን ፕሬዚዳንቷ አስታውሰዋል፡፡ ድርጅቱ በፋይናንስ አልግሎት ልህቀት ላይ የሚሠራ ተቋም እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ለባንኩ ከተሰጠው ዕውቅና በተጨማሪ የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ የ(Islamic Retail Banking Awards/IRBA) የዓመቱ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚና እንዲሁም ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ ሴቶችን ዕውቅና በተሰጠበት ሌላው መርሐ ግብር፣ በዘርፉ ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ‘WOMANi CEO 2022’ ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ባንኩ አስታውቋል፡፡

ዘምዘም ባንክ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲጀመር ከ15 ዓመታት በፊት ሲንቀሳቀስ የነበረ ባንክ ሲሆን፣ በወቅቱ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ መቋቋም እንደማይችል መንግሥት በማስታወቁ ራሱን አክስሞe ነበር፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ራሱን በቻለ ባንክ መስጠት እንደሚችል መመርያ በመውጣቱ፣ ዘምዘም ባንክ እንደገና በመደራጀት በኢትዮጵያ የመጀመርያው ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ በመሆን ወደ ሥራ ሊገባ ችሏል፡፡ ዘምዘም ባንክን ተከትሎም ሒጅራ ባንክ ወደ ገበያ የገባ ሲሆን ሦስተኛው ከወለድ ነፃ ባንክ ሆኖ በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ራሚስ ባንክ ነው፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ የሚፈቅደው ሕግ ከወጣ ወዲህ አሥራ አንድ ባንኮች አገልግሎቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡

አሥራ አንዱ ባንኮችና ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙት ባንኮች በድምሩ ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ የሰባሰቡ ሲሆን፣ ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከወለድ ነፃ አስቀማጭ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች