Thursday, June 20, 2024

የመቀሌው ጉዞና አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመንግሥት ከፍተኛ ባሥልጣናትን ያካተተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ የልዑካን ቡድን፣ ሰኞ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. መቀሌ መግባቱ ትልቅ ዜና ነበር፡፡ ይህንን አጋጣሚ እንደ ታላቅ የሰላም ድል የቆጠሩት እጅግ በርካታ ቢሆኑም፣ ጉዳዩ ሕግንም ሆነ መርህን ያልተከተለ ስሜታዊ ዕርምጃ ያሉም አሉ፡፡

የሰኞው የልዑካን ቡድን ጉዞ ሲጀመር ያልተጠበቀና ድንገተኛ ነበር፡፡ የሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ እንዲሁም አፈ ጉባዔ ታገሰ በሰጡት መግለጫ ክስተቱን ‹‹በጎ ድንገታዊ አጋጣሚ›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ወደ መቀሌ በሄደው የልዑካን ቡድን ውስጥ ደግሞ የኢንዱስትሪ፣ የሥራና ክህሎት፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የፍትሕ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የመንግሥት አገልግሎት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መካተታቸው፣ ለጉዳዩ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው ያደረገ ነበር፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርና የሌሎችም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በመቀሌው ጉዞ ተካተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪና በመንግሥት ወገን የሰላም ስምምነቱ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ እንዲሁም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳም የዚህ ጉዞ አካል ነበሩ፡፡

የፌዴራል መንግሥት የልዑካን ቡድን ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተጨማሪም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ያካተተም ነበር፡፡ የልዑካን ቡድኑ ስብጥርም ሆነ ድንገታዊ ጉዞው የበለጠ ትኩረት እንዲስብ ያደረጉት ደግሞ፣ ጉዞውን በተመለከተ እየወጡ ያሉ መግለጫዎችና አስተያየቶች ነበሩ፡፡

የልዑካን ቡድኑን ጉዞ በሰበር ዜና ያሠራጨው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ የጉዞው ዓላማ የሰላም ስምምነቱን ‹‹ዋና ዋና ዓላማዎች በታቀደው መሠረት እንዲፈጸሙ ለማድረግ›› መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በትግራይ ሚዲያዎች እንደተገለጸው ከሆነ ደግሞ፣ የልዑካን ቡድኑ ከሕወሓት ባለሥልጣናት ጋር ብቻ ሳይሆን ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋርም ተወያይቷል፡፡

አቶ ታገሰና ደብረ ጽዮን  (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፣ እንዲሁም ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳና አቶ ጌታቸው ረዳ ከሚዲያዎች ጋር ካደረጉት አጭር ቆይታ ይህ የልዑካን ቡድን ጉዞ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ በጎ የሚባል ስሜት የፈጠረ አጋጣሚ እንደሆነ መታዘብ ተችሏል፡፡

አፈ ጉባዔ ታገሰ እንደተናገሩት፣ በመንግሥት በኩል የሰላም ሒደቱን ለማፋጠን ዝርዝር ውይይት ተደርጓል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም ለሰላም ስምምነቱ ምን ያድርግ? በሚለው ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባሉበት ዝርዝር ውይይት በመንግሥት በኩል አድርገናል፤›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶችን ሥራ እንደገና ማስጀመርን ጨምሮ፣ የሰላም ስምምነቱ በታቀደው ልክ በተግባር እንዲተረጎም ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ እንደሆነም ነው አፈ ጉባዔው ያስረዱት፡፡

የትግራይ ክልልን ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ የሰጡት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሕዝቡም ሆነ ሕወሓት የሰላም ስምምነቱን መተግበር በእጅጉ  እንደሚፈልጉት ተናግረዋል፡፡ ከረድኤት አቅርቦት እስከ መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ሥራ መጀመር በሰፊው የዘረዘሩትና የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥትን ያመሠገኑት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ሒደቱ ከዚህ በላይ ይፋጠን›› ብለዋል፡፡

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በዚህ መግለጫቸው ለሰላም ሒደቱ እጅግ ፈተና ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ወሳኝ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ‹የአየር በረራና ንግድ እንዴት ይከለከላል?› ሲሉም አክለዋል፡፡

በሌላም በኩል ‹‹የፖለቲካው ውይይት ገና አልተጀመረም፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ አጠንክሮ የሰላም ስምምነቱ መተግበርን ይፈልጋል፡፡ ስምምነቱ ገና በክልል ምክር ቤቱ ባይፀድቅም፣ ሁሉም ወገን ተቀብሎት በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲተረጎም እየደገፈ ይገኛል፤›› ሲሉም አሻሚ የሚመስል ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹የወራሪዎች መውጣት ለሰላም ሒደቱ ወሳኝ ነው›› ሲሉ የተደመጡት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎችና የኤርትራ ጦር በማለት በስም በመጥራት ከትግራይ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ከአገልግሎቱ መቀጠል በፊት ወራሪዎች ይውጡልን›› የሚል ጠንካራ አቋም ነበር ያንፀባረቁት፡፡

ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹ከኬንያና ከናይጄሪያ ሽምግልና መለመናችን ለእኛ ትልቅ ውርደትና አሳፋሪ ነው፤›› ብለው ሲናገሩም ተደምጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከጦርነቱ በፊት በአገር ሽማግሌዎች ችግሮችን ለመፍታት የተሞከሩ ጥረቶችን ሲጀመር የገፋው ማን ነበር? የሚል ጥያቄን ዳግም እንዲነሳ ያደረገ ነበር፡፡

የልዑካን ቡድኑ የመቀሌ ጉብኝት፣ በተለይ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሕወሓት አመራሮች ጋር ሲያደርጉት የታየው ግንኙነት ሌሎች ጥያቄዎችና  ትችቶችንም ማስነሳቱ አልቀረም፡፡

የሁለቱ ወገን ባለሥልጣናትን መተቃቀፍና የሞቀ የወዳጅነት ስሜት የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን በመለጠፍ ‹‹የሞተ ተጎዳ›› ሲሉ ፀፀት የተሞላው መልዕክትን ያጋሩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተዋንያን ብዙ ነበሩ፡፡ በመንግሥትና በሕወሓት ጦርነት ያለቀው ወጣት ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ ስለመቅረቱ ተቺ ጽሑፎችና መልዕክቶችን የለጠፉም ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ‹‹’ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፣ ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም’ አለ ጥልሽ›› ብሎ የለጠፋት በጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ግጥም የተለወሰች የሽሙጥ መልዕክት እጅግ ብዙ ግብረ መልሶችን የፈጠረች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆናለች፡፡ የጋዜጠኛውን ፖስት ተከትሎ ‹‹ወይ ዘንድሮ አለ ኤፍሬም››፣ ‹‹ፍታኝ አለች ሐመልማል››፣ ‹‹ፀጉሬንም ቆጥረሃል አለች ሚካያ››፣ ‹‹ሳያት ታሳዝነኛለች አለ ታምራት››፣ ‹‹ወሬኛም ያውራ ሀሜት ይደስኩር፣ እኛስ ሆነናል ፍቅር በፍቅር አለ ነዋይ ደበበ››፣ ወዘተ በሚሉ በዘፈን ግጥሞች ሽሙጥ ማስተጋባት የሰሞኑ የማኅበራዊ ገጾች ፋሽን ሆኗል፡፡

ከቀልዱና ከሽሙጡ ባለፈ ግን ስለሰሞነኛው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዞ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ ክርስቲያን ታደለ፣ ‹መንግሥታዊነት ሆይ የት አለሽ?› ሲሉ በጠየቁበት ጽሑፋቸው፣ ከልዑካን ቡድኑ ጉዞ ሊቀድም ይገባዋል ስላሉት ጉዳይ አንስተዋል፡፡

ሕወሓት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀ ቡድን መሆኑን ያስታወሱት አቶ ክርስቲያን፣ ጉዞውን ከዚህ ጋር በማነፃፀር፣ ‹‹አስፈጻሚው አካል በማናለብኝነት የሚሠራው ሕጎችን የመጣስ ልምምድ›› በማለት ነበር የጠሩት፡፡

እንደ አቶ ክርስቲያን ሁሉ የልዑካን ቡድኑን ጉብኝት መርህንም ሆነ ሕግን  ያልተከተለ ብለው የተቹት ቢኖሩም፣ ይሁን እንጂ ከጦርነትና ግጭት ምንም እንደማይተርፍ በመጥቀስ በርካቶች ጉብኝቱን ታላቅ የሰላም ዕርምጃ ሲሉ የጠሩት በርካታ ናቸው፡፡ ጉዞውን የኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት ተምሳሌት አድርገው ያቀረቡትም ብዙዎች ናቸው፡፡

በተለይ የትግራይ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ መድኅን ገብረ ሥላሴ ያሠፈረችውን የማኅበራዊ ገጽ መልዕክትና በተለያዩ ሚዲያዎች የትግራይ ነዋሪዎች ያንፀባረቁትን ስሜት በማጣቀስ፣ የሰሞኑ ጉዞ ትልቅና በጎ አንድምታ ያለው ስለመሆኑ እየገለጹ የሚገኙ በርካታ ናቸው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድን አውሮፕላን መቀሌ ሰማይ ላይ ሲመለከት ሕዝቡ በደስታ ወደ አደባባይ ወጥቶ ዕልል አለ፤›› መባሉ ብዙ ሐሳብ እንዲንሸራሸር የሚጋብዝ ነበር፡፡ ይህን በሚመለከት ሐሳብ የሰጡ በርካቶች ሰላምና ወንድማማችነትን የመሰለ ነገር እንደሌለ ሲገልጹ ነበሩ፡፡

ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ያጋሩትና የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት በፈረሰው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር የመቀሌ ከንቲባ የነበሩት አቶ አታክልቲ ኃይለ ሥላሴም፣ ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ነበር ያጋሩት፡፡

‹‹የትግራይ ሕዝብ ስሜት እጅግ ከፍተኛ ተስፋን የሰነቀ ነው፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፈው መከራ በሰላም ስምምነቱ መተግበር እንደሚያበቃ ሕዝቡ ተስፋ አድርጓል፤›› ሲሉ አቶ አታክልቲ ጉዞው የፈጠረውን ስሜት ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ቀናት ትግራይ ክልል ካሉ ሰዎች ጋር መደዋወላቸውን የጠቀሱት አቶ አታክልቲ፣ ‹‹እንግዶቹ እንደሚመጡ ከታወቀ ጀምሮ የደኅንነት ጥበቃው በመቀሌ ሲጠናከር፣ መቀሌ ሰማይ ላይ የሚበረው አውሮፕላን የኢትዮጵያ መሆኑ ሲታወቅ ሕዝቡ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ውስጥ ገብቶ ነበር፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

ሕዝቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የከፈለው ዋጋ ምን ያህል እንደጎዳውና ከዚያ ጉዳት ለመላቀቅ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት መታዘባቸውን የተናገሩት አቶ አታክልቲ፣ ያልተቀረፉ አሳሳቢ ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡

‹‹ሕወሓት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች አሁንም ቢሆን ዕርዳታ እየተከፋፈለ አይደለም፡፡ ዕርዳታ ወደ ትግራይ በሰፊው እየገባ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ግን በአግባቡ እየደረሰው አይደለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ለዕርዳታ ተብሎ የመጣ ዘይት ሲሸጥ ነበር፡፡ የሰላም ተስፋው በእጅጉ የሚደነቅ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሕወሓት አሁንም በወንጀል ላይ ሌላ ወንጀል በሕዝቡ ላይ እየፈጸመ መሆኑ ይታሰብበት፤›› በማለት ነበር አሳሳቢ ያሉትን ጉዳይ ያስረዱት፡፡

የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው፣ እንዲሁም አፈ ጉባዔ ታገሰ እንደተናገሩት፣ የልዑካን ቡድኑ አባላት ያለ ጠባቂና ያለ አጃቢ መቀሌ ተገኝተው ስለሰላም መምከራቸው እጅግ ትልቅ ቦታ የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ብዙዎች ሲስማሙበት ታይቷል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ሬድዋን (አምባሳደር) ከባድ መሣሪያዎችን ማስረከብን ጨምሮ ትጥቅ የማስፈታት ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ይህ ሁሉ ለሰላም ሒደቱ በተግባር መተርጎም ትልቅ ዕርምጃ ቢባልም፣ ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ብዙ ጉዳዮች እንደሚቀሩ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -