Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፊስቱላ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች አሳሳቢ ደረጃ ላይ  መድረሱ ተገለጸ

ፊስቱላ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች አሳሳቢ ደረጃ ላይ  መድረሱ ተገለጸ

ቀን:

በኢዮብ ትኩዬ

የፊስቱላ በሽታ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ የጤና ሚኒስቴርና ሐምሊን ፊስቱላ አስታወቁ፡፡

ፊስቱላ በሽታ በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ትኩረት እንደሚሻ፣ የጤና ሚኒስቴርን ወክለው በሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት አቶ ፍቃዱ ያደታ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ጉዳዩን በማስመልከት ሐሙስ ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት አቶ ፍቃዱ፣ ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን በማፈላለግ የሚያደርገውን ጥረት እንዲቀጥል፣ የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ ዕገዛዎችን እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩላቸው፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ ጋር በመተባበር የፊስቱላና የማህፀን መውጣት ችግሮች ያለባቸውን እናቶች አፈላልጎ በማግኘትና በማከም፣ ላለፉት አራት ዓመታት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ለበርካታ ዓመታት በፊስቱላ በሽታ ችግር ውስጥ እየኖሩ ያሉና ወደ ሕክምና ተቋም ያልመጡ በርካታ እናቶች  አፈላልጎ ማግኘት መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ እናቶችና እህቶችን ማግኘት አስቸጋሪ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ያሉበት አካባቢ ገጠር በመሆኑ፣ ፊስቱላ ሊታከምና ሊድን እንደሚችል መረጃ የማግኘት ክፍተት በመኖሩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

መረጃውና ዕውቀቱ የሌላቸው እናቶች በየማጀታቸው እንደተቀመጡም መረዳት ስለመቻሉም ተጠቅሷል፡፡ ‹‹በሕክምና ተቋማት ፊስቱላን ለማከም ቀላል ነው›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ከዓመታት በፊት በፊስቱላ በሽታ የተጠቁ ሰዎችን አፈላልጎ ማግኘት ግን ለተቋማቸው ትልቅ ፈተና መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በፊስቱላ የተጠቁ ሰዎችን ለማግኘት ባደረገው የማፈላለግ ሥራ፣ 30 እና 40 ዓመታት ከችግሩ ጋር የኖሩ እናቶች ማግኘት ስለመቻሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ አደረግኩት ባለው ዳሰሳ 1,042 እናቶችን አፈላልጎ ማግኘትና ማከም መቻሉን ገልጿል፡፡ እነዚህ እናቶችን አፈላልጎ ማከም የቻለው ተቋሙ በቀረፀው የአራት ዓመታት ፕሮጀክት ብቻ እንጂ፣ በተለመደው መንገድ ግን በ2014 በጀት ዓመት ከ2,500 በላይ እናቶች የፊስቱላ ሕክምና እንደተደረገላቸው አስታውቋል፡፡

በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ከ3,000 በላይ እናቶችን ለማግኘትና ሕክምና ለመስጠት እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡

ተቋሙ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት ግን በርካታ እናቶች የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ሳይችሉ፣ በየቤታቸው ተቀምጠው የበሽታው ሰለባ ሆነው እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት ከሆነ፣ አሁንም ቢሆን አዲስ አበባን ጨምሮ የፊስቱላ በሽታ ተጠቂዎች እየተገኙ ነው፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት፣ በተለይም በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኘው የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ሥራ ለማቆም ተገዶ እንደነበርና በዚህም በርካታ እናቶች በበሽታው ሊጠቁ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

ምን ያህል እናቶች እንደተጎዱ የሰላሙ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ሲረጋገጥ የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ጥናት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ እንዲሁም በበሽታው የተጎዱ ሰዎች አፈላልጎ ለማከም ሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ፊስቱላን ከየወረዳው ለማጥፋት ‹‹ከወረዳ እስከ ወረዳ›› የሚል ፕሮግራም መቀረፁን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ800 በላይ ወረዳዎችን ለማሰስ እንደታቀደና በቅርቡ እንደሚጀመር ከተቋሙ በተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ የማህፀንና ፅንስ ሐምኪ ዶ/ር የሺነህ ደምረው በበኩላቸው፣ የሕክምና ተቋሙ ለማከም ባለው ሙሉ አቅም መሠረት በፊስቱላ በሽታ የተጠቁ እናቶች እየመጡ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ከተቋሙ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና ሌሎች ክልሎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን አፈላልጎ ለማከም ታቅዶ ከትግራይ ክልል ውጭ ሕክምናውን መስጠት ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል፡፡

የፊስቱላ በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታል ያሉት ዶ/ር የሺነህ፣ በኢትዮጵያ  ብዙ ጊዜ እየተከሰተ ያለው ከቀዶ ሕክምናና ከካንሰር ጋር በተያያዘ መሆኑንና ከ90 በመቶ በላይ ግን በተራዘመ ምጥ እንደሚከሰት አብራርተዋል፡፡

ከሦስት ቀናት በላይ ምጥ የቆየባቸው እናቶች ብዙውን ጊዜ ሲወልዱ ፅንሱ እንደሚሞትና እናቶችም ለፊስቱላ በሽታ እየተጋለጡ ስለመሆኑም ተብራርቷል፡፡ ሽንት፣ እንዲሁም ሽንትና ዓይነ ምድር 24 ሰዓት መቆጣጠር የማይቻል ከሆነ እናቶች የፊስቱላ በሽታ ተጠቂ እንደሆኑ የሚያሳይ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...