Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ

ቀን:

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የማኅበረሰብ ደኅንነት ዋስትና በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉና በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

ይህ የተገለጸው ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ከኤስኦኤስ የሕፃናት መንደር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‹‹የዜጎች ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭነትና የባለ ድርሻ አካላት ምላሽ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ፣ ማንኛውም ድርጅት በተለይም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው ሥራዎች በተለይም የሴቶችን፣ የሕፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን የአረጋውያንንና ሌሎች ለጉዳትና ችግር ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅምን ማካተታቸውን ማረጋጋጥ እንዳለባቸው በአዋጅ በአስገዳጅ ሁኔታ መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስና የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ ደኅንነት ዋስትና በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ በመሳተፍ፣ በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አቶ ጂማ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዜጎች ደኅንነትና የመኖር ዋስትና ከማስጠበቅ አኳያ ከመንግሥት ጎን ለጎን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አይተኬ ሚና እንዳላቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ2011 ዓ.ም. የወጣው አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጅ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አጽንኦት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

በማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ የተጠቀሱትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድልና የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ የማኅበራዊ መድን አገልግሎትና ልማታዊ ሴፍቲኔትን ማስፋፋት፣ የመሠረታዊ አገልግሎትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ ለጥቃትና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዲያገኙ ማድረግ በሚሉት ጉዳዮች ላይ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባቸው በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዜጎች ከሥራ አጥነት፣ ከቤተሰብ መበተን፣ ከአቻ ግፊትና ከሌሎች ገፊና ሳቢ ምክንያቶች እንዲሁም ግጭትና ጦርነት በሚያስከትሉት ማኅበራዊ ችግር በርካቶች ወደ ጎዳና መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅንጅት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ የገጠመውን ማኅበራዊ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ችግሩን ከምንጩ ለይቶ በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት ዜጎች በሚገባ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ መቋቋሚያ አዋጅ ቀርፆ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ እንዲፀድቅ ግፊት ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በተበታተነ መንገድ የሚደረገውን የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች ተጋላጭነት ድጋፍ በማዕከል አቀናጅቶ መምራት እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ተገልጿል፡፡

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ ለዜጎች የጎዳና ሕይወት ተጋላጭነት የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ከምክክር ባለፈ ተግባርና የድርጊት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን የማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ይረዳል የተባለለት ብሔራዊ የማኅበራዊ ጥበቃ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ለረዥም ዓመታት መዘግየት፣ አግባብ እንዳልሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባሳለፍነው ሳምንት ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ረቂቁ ከተዘጋጀ በኋላ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባት ሲገባው ይህን ያህል ጊዜ መቆየቱ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ፣ አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...