Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው

ቀን:

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ብሔራዊ ምክር ቤት ሊቋቋም ነው፡፡

በግንቦት 2014 ዓ.ም. የፀደቀው የጤና መድን አዋጅ ተፈጻሚነቱን በበላይነት የሚመራውና የሚገመግመው ብሔራዊ ምክር ቤት ከትናንት ቅዳሜ ታኅሳስ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራውን እንደሚጀምር፣ የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት አስታውቋል፡፡ የጤና መድን አገልግሎቱ ይህን ያለው ታኅሳስ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ረቂቅ አዋጅ በአንቀጽ 11 የብሔራዊ ምክር ቤት ኃላፊነት፣ የአባላት መዋጮ መጠን ትመና፣ የጥቅም ማዕቀፍ ዝርዝር የማውጣት፣ የቀጥታ ክፍያ መጠን፣ የመጠባበቂያ ፈንድ በመቶኛ የፌዴራልና የክልል ቋቶች ክፍፍልና ሌሎችም የተሰጡት ተግባራት ኃላፊነቶች መሆኑ ተነግሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ብሔራዊ ምክር ቤቱ ለአሥር ዓመታት በተሞክሮ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በበላይነት ሲቆጣጠር፣ የአባላት መዋጮና የአገልግሎት ጥራትን ጭምር ይቆጣጠራል፤›› ሲሉ የጤና መድን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ምክር ቤቱ በአሥራ አንዱ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ርዕሰ መስተዳደሮችና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 ለዓመታት ተግባራዊ የተደረገው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ የመንግሥት ሠራተኞች ጡረተኞችንና የግል ቀጣሪ ድርጅቶችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ማኅበራዊ ጤና መድንም በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዛቸውን ሦስት በመቶ፣ ጡረተኞች ደግሞ አንድ በመቶ ለጤና መድን አገልግሎት ተቆራጭ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ታኅሳስ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ሥራውን የጀመረው የጤና መድን ብሔራዊ ምክር ቤት የክልል ፕሬዚዳንቶች አባል ሲሆኑበት፣ የአሥር ዓመቱን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አፈጻጸም ይገመገማሉ ተብሏል፡፡

በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ የወጣው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሁሉም ዜጎች አባል የመሆን ግዴታን ተፈጻሚነት የሚያረጋግጠው ምክር ቤቱ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ፍሬሕይወት ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በአሥር ዓመታት ውስጥ 80 በመቶ አርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑንና 45 ሚሊዮን ዜጎች አባል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በ894 ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎት መዳረሱን፣ 150 የአርብቶ አደሮች ወረዳዎች ግን እስካሁን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ 150 የአርብቶ አደሮች ወረዳዎች በበጀት ዓመቱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ቁጥር 217 የፀደቀው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች አንቀጽ 22 እና 25፣ የዜጎችን የጤና መድን ተጠቃሚነት ይተነትናል፡፡ ድንጋጌው በጤና አገልግሎት ዜጎች ያሉበት ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ከግምት ሳይገባ የመጠቀም መብት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

በተጨማሪም በሥራ ማጣት፣ በሕመም፣ በአካል ጉዳት፣ በእርጅናና በሌሎች ራስን ለመደገፍ ከባድ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ዋስትና ማግኘት ከመሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች መካከል መሆኑ ተደንግጓል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. ኅዳር 27 ቀን 2012 በነበረው 67 መደበኛ ጉባዔ ተወያይቶ ባፀደቀው ዓለም አቀፍ የጤናና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ትኩረት ከሰጣቸው ርዕሶች ዋነኛው ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ነው፡፡

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከኪሳቸው ለጤና በሚያወጡት ገንዘብ ምክንያት ወደ ድህነት እየገቡ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ይህንን ከፍተኛ ወጪ በመፍራትም የጤና አገልግሎት ከማግኘት እያስቀራቸው መሆኑን ጉባዔው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

በጉባዔው ላይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ከተሰጣቸው የቤት ሥራ አንዱ፣ በጤና አገልግሎት ሥፍራዎች የሚደረግ የቀጥታ ክፍያ ማስቀረት የሚያስችል የቅድመ ክፍያ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...