Wednesday, February 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ወጣቶች ከስህተታቸው የማይማሩ ፖለቲከኞች መቀለጃ አትሁኑ!

የኢትዮጵያ ታዳጊዎችና ወጣቶች ቁጥራቸው ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ70 በመቶ በላይ ቢሆንም፣ ከስህተታቸው መማር በማይፈልጉ ፖለቲከኞች ምክንያት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች የከፋ የድህነት ሕይወት ይገፋሉ፡፡ የረባ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ትምህርት፣ የጤና ክብካቤና የመሳሰሉትን ተነፍገው በችጋር ይጠበሳሉ፡፡ ወጣቶች የተመጣጠነ ምግብና ደረጃውን የጠበቀ የኑሮ ዘይቤ ከማጣታቸውም በላይ፣ ጥራት ያለው ትምህርት ስለማያገኙ የአድሮ ቃሪያ ፖለቲከኞች መፈክር ተሸካሚ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በአገራቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሪ ተዋንያን መሆን የሚገባቸው በርካታ የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ሥራ አጥ ሆነው የምስኪን ወላጆቻቸው ተጧሪ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት የከፋ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ወጣቶች ከብሩህ ተስፋ ይልቅ የጨፈገገ ነገ ነው የሚታያቸው፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞችም ለወጣቶች የወደፊት የተሻለ ዓለም መፈጠር መሥራት አይፈልጉም፡፡ እንፈልጋለን ብለው ቢደሰኩሩም አቅሙም ሆነ ችሎታው የላቸውም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ፍላጎት መሳካት ስለሚማስኑ፣ ወጣቶችን የሚፈልጓቸው ዘመን ያለፈበት አውዳሚ መፈክር ለማሸከም ብቻ ነው፡፡  

የብዙዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ካለፈ ስህተት ለመማር አለመፈለግ ያተረፈው ውድቀት ነው፡፡ በሠለጠኑ አገሮች ፖለቲካን የሙሉ ጊዜ ሥራ ያደረጉ ፖለቲከኞች ከትርፍ ጊዜ ፖለቲከኞች የሚለዩት፣ የወጣቶችን መሠረታዊ ፍላጎት ለማወቅ የሚያስችል የጠራ ዕውቀት በመጨበጣቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅትም ይሁን ስብስብ የራሴ የሚለው ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት ይኖረዋል፡፡ ከአባላቱም አብዛኞቹ ፖለቲካን በሚገባ የተረዱ ወጣቶች ሲሆኑ፣ የፓርቲያቸውን ዓላማ ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ አገርና ሕዝብን ያስቀድማሉ፡፡ የራሳቸውን ፓርቲ ዓላማ ከሌሎች ጋር የሚያነፃፅሩበት ዕውቀት በመጨበጥ፣ ፓርቲያቸው ሁሌም የሐሳብ የበላይነት አግኝቶ ተወዳዳሪና ተመራጭ አጀንዳ እንዲኖረው ይታገላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ከሚርመሰመሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያህሉ ለወጣቶች ዕድል ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠየቅ፣ ከአንድና ከሁለት ፓርቲዎች በስተቀር ሁሉም ‹‹ቢከፍቱት ተልባ›› ናቸው፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶችን ያገለሉ፣ ከተራ ደጋፊነት በላይ አጀንዳ ቀራጭ እንዳይሆኑ የሚያርቁ፣  በወጣቶች ወይም በሴቶች ለመመራት ፈቃደኛ ያልሆኑ፣ በምርጫ ወቅትም ሆነ በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻቸው ለወጣቶች ፍላጎት ቅድሚያ የማይሰጡና ከስህተታቸው የማይማሩ ናቸው፡፡

ልዩነት ተፈጥሯዊ በመሆኑ የግድ በሁሉም ነገር ላይ አንድ ዓይነት አቋም ማራመድ አይጠበቅም፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ልዩነት መኖሩም አይገርምም፡፡ ነገር ግን የተለየ ሐሳብን በነፃነት እያራመዱ መወያየት፣ መከራከርና መደራደር ያልተቻለው ወጣቶች ስለሚገለሉ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መተማመን ጭልጥ ብሎ ጠፍቷል፡፡ መተማመን ባለመኖሩም ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት መከባበር ብርቅ ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የቂመኞችና የበቀለኞች መራኮቻ የሆነው አዲሱ ትውልድ በመገፋቱ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነቁና በበቁ ወጣቶች ሲደገፉ፣ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ተቀምጠው ለመነጋገር አያዳግታቸውም፡፡ የነጠረ ርዕዮተ ዓለምና ዓላማ አለን ብለው ስለሚያምኑ፣ ከጉልበት ይልቅ ለሐሳብ ልዕልና ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ የፖለቲካውን ስስ ብልት ስለሚያውቁት ከተፎካካሪዎቻቸው በተሻለ የመራጮችን ቀልብ መሳብ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወጣቶችን የሚያማልል አማራጭ ይዘው መቅረብ ስለሚችሉ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆኑት ግን አሁንም የብሔርና የእምነት ካርድ እየመዘዙ፣ በለመዱት የጥፋት ጎዳና ላይ ሆነው ስህተታቸውን ይደጋግሙታል፡፡

ዘወትር እንደምንለው ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት በችጋርና በመከራ እንድትኖር የተፈረደባት፣ የትም ቢፈለግ ሊገኝ የማይችል አርቆ አሳቢና አስተዋይ ሕዝብን በቅጡ ለመምራት ባቃታቸው ፖለቲከኞች ምክንያት ነው ቢባል ማስተባበል አይቻልም፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የሚወጡትም ሆኑ ሥልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ተገዳዳሪዎች ትልቁ ችግራቸው፣ ከታሪክ አለመማራቸውና ለሕዝብና ለአገር ክብር አለመስጠታቸው ነው፡፡ ሕዝብና አገርን ከፓርቲ ወይም ከቡድን ፍላጎት በታች በማድረግ የሚገባበት ቁማር፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለቻቸውን ሀብትና ፀጋዎች አውጥታ እንዳትጠቀም በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ ፖለቲከኞቹ አንዳቸው ከሌላው ውድቀት ከመማር ይልቅ፣ እርስ በርስ በሚፈጥሩት ሽኩቻ የባሰ ውድቀት በመፍጠር ወጣቶችን ተስፋ ቢስ ማድረግ ነው የተካኑበት፡፡ የረባ ርዕዮተ ዓለም ሳይኖራቸው የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ወጣቶችን ገለል ያደርጋሉ፡፡ ለወጣቶች ሕይወት መቀየር የሚበጅ አጀንዳ ሳያፈልቁ ሕይወታቸውን የሚያመሰቃቅሉ ቅራኔዎችን መፈልፈል ልማዳቸው ነው፡፡ እነሱንና የቅርብ ሰዎቻቸውን የማይነካ የፖለቲካ እሳት እያቀጣጠሉ ንፁኃን ወጣቶችን ከማገዱና አገር ካስወደሙ በኋላ፣ በሰላም ስም ታርቀው ለመተቃቀፍ ማንም አይቀድማቸውም፡፡

የነገ ባለተስፋ ወጣቶች ከአገሪቱ ፖለቲከኞች ባህሪ በመነሳት ሕይወታችሁን መለወጥ ይጠበቅባችኋል፡፡ ማንም እየተነሳ ለሚረጨው ከንቱ ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ ላለመጋለጥ ራስን በዕውቀት ማደርጀትና ሞጋች መሆን ያስፈልጋል፡፡ ‹‹መጪው ጊዜ የወጣቶች ነው›› የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወጣቶች ጥራት ያለው ትምህርት ሲያገኙ በማንም ከንቱ ሽንገላ አይታለሉም፡፡ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ በላይ ወረዳ፣ ከወረዳ በላይ ዞን፣ ከዞን በላይ ክልል፣ ከክልል በላይ አገር፣ ከአገር በላይ ደግሞ እጅግ በጣም ሰፊ ዓለም አለች፡፡ ዘመኑ እጅግ በተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች አጋዥነት የሰው ልጅን ሕይወትና የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ደግሞ ብሔር፣ እምነት ወይም ዜግነት፣ እንዲሁም ዘርና ፆታ ሳይለይ ለሁሉም ተደራሽ እየሆነ ነው፡፡ የዘመኑ ወጣት ጥርሱን ነክሶ ተምሮ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ራሱን ከድህነት ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት አማራ ይሁን ኦሮሞ፣ ትግሬ ይሁን ጉራጌ፣ አፋር ይሁን ሶማሌ፣ ወዘተ ራሱን በሥልጣኔ ከተራቀቁ አገሮች ወጣቶች ተርታ ማሠለፍ ይችላል፡፡ ዋናው ቁምነገር ዘመኑን የሚመጥን ዕውቀት መጨበጥ ነው፡፡

ወጣቱ መርህ አልባ ከሆኑ ፖለቲከኞች በማፈንገጥ እነሱኑ መልሶ መሞገት የሚችለው፣ ለዘመኑ የሚመጥን ዕውቀት ሲጎናፀፍ ብቻ ነው፡፡ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መፈክር አልሸከምም ማለት የሚችለው፣ በደመነፍስ እንዳይነዳ የሚያደርገው የተሟላ ዕውቀት ሲኖረው ነው፡፡ አገርን እየዘረፉ ለማደህየት በብሔር፣ በእምነትና በጥቅም ጉድኝት ከሚደራጁ ወሮበሎች ጎራ መለየት የሚችለው፣ ኢሞራላዊና የጭካኔ ድርጊቶችን ማጋለጥ የሚያስችሉ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችን ሲላበስ ነው፡፡ ከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከቂመኝነት፣ ከሌብነት፣ ከሴረኝነትና ከክፋት ድርጊቶች በመላቀቅ ለአገርን ለሕዝብ የማሰብ ኃላፊነት የወጣቱ መሆን አለበት፡፡ ወጣቱ ትውልድ ለዚህ ዘመን የሚመጥን የፖለቲካ ቁመና ይዞ ሲገኝ፣ ለዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትከሻ ላይ ሲያናጥሩ የኖሩት ከንቱዎች ገለል ይላሉ፡፡ ለዘመኑ በማይመጥን የከሰረ ሐሳብ አገርን ግራ ማጋባት ማብቃት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለዓመታት በዕብሪትና በድንቁርና ከስህተታቸው ከማይማሩ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ያርቁ፡፡ ወጣትነት ለአገር ትልቅ አስተዋፅኦ የምታበረክቱበት ስለሆነ፣ ወጣቶች ሆይ ከስህተታቸው የማይማሩ ፖለቲከኞች መቀለጃ አትሁኑ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

በሰነድ መዘግየት ምክንያት ኢትዮጵያ ቻይና ላላደጉ አገሮች በሰጠችው ከታሪፍ ነፃ ዕድል ሳትካተት ቀረች

‹‹የሒደት ጉዳይ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ተገልላ አይደለም›› ንግድና ቀጣናዊ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

በጀማል ሙሀመድ ኃይሌ (ዶ/ር) "ሆድ ባዶ ይጠላል..." "ከሆድ የገባ ያገለግላል…” ከጥቂት ዓመታት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር፣ አገርን ሌላ አስከፊ ቀውስ ውስጥ የሚከት የሃይማኖት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ...

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...