Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መዘረፉን ዋና ኦዲተር አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግዥ መመርያ ሳይከተል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለአበል በሚል ያላግባብ ከፍሏል የተባለው፣ የቀድሞው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የአሁኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአገር ሀብትን ለዝርፊያ መዳረጉን የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ባለፈው ሳምንት በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት ሒሳብ ሕጋዊነት ኦዲት ቀርቦ ገምግሟል፡፡

በኢንስቲትዩቱ ላይ ተገኘ የተባለው የኦዲት ግኝት ስፋት፣ ቋሚ ኮሚቴውን ጨምሮ  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ኃላፊዎች የሰላ ትችት እንዲሰነዝሩ አድርጓቸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ኢንስቲትዩቱ በግልጽ ጨረታ ማከናወን ሲገባው ከመመርያ ውጪ ሲገዛ እንደነበር መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ኦዲተሯ በውስን ጨረታ መግዛት የሚቻለው የዕቃዎች አቅራቢ ውስን ሲሆን ገልጸው፣ ኢንስቲትዩቱ ግን በግልጽ ጨረታ ሊገዛ የሚችለውን ተግባራዊ ባለማድረጉ መንግሥትን ከውድድር የሚያገኘውን ገቢ አሳጥቶታል ብለዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ከአበል አከፋፈል ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ 2.9 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ወጪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ የአበል አከፋፈሉ ደግሞ አዳማ ከተማ ለምርምርና ለጥናት የሄዱ በሐዋሳ ስም እንደተከፈላቸው፣ ከቢሯቸው ሳይወጡ አዳማ እንዲሄዱ ተደርጎ አበል መከፈሉን፣ ለስምንት ቀናት ተብሎ ደግሞ የ30 ቀናት እንደተከፈለ ለቋሚ ኮሚቴው ዋና ኦዲተር ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

‹‹ይህ ገንዘብ ተዘርፏል ነው የምለው ቃል በቃል፣ መመለስ አለበት፤›› ሲሉ የገለጹት ዋና ኦዲተሯ፣ ተቋሙ ማስረጃ የሌለው 401,210 ብር ከሆቴሎች ጋር በመነጋገር ከሁነቱና ከኦዲት ግኝቱ ጋር ተመሳሳይነት የሌለው ሰነድ ማስረጃ መቅረቡን ጠቅሰው ገንዘቡ አንዲመለስ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ በተገኙ ጉድለቶች የተሳተፉ ሰዎች በአግባቡ ሊጠየቁ ይገባል ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ በተጨማሪም መሥሪያ ቤት በግኝቱ ላይ እንደታየው በቢሮ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች በመስክ እንደሚሠሩና ይህንንም  መለስ ብሎ ማየት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአሁኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል፣ ሰፋ ያለ የሥነ ምግባር ብልሽትና የአሠራር ክፍተት እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ባነሷቸው ጥያቄዎችና ባቀረቡት ሐሳብ አስረድተዋል፡፡

 

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳረጋገጠው፣ኢንስቲትዩቱ በአብዛኛው የኦዲት ግኝቱ ከግዥና ከግዥ መመርያ ጋር የተያያዘ  ቢሆንም የግዥ መመርያ አለመከተል፣ ግዥ በማዕቀፍ መግዛት ሲገባ በታትኖ መግዛት፣ የግዥ ስፔሲፊኬሽን ሳይገናዘብ መግዛት፣ ከውሎ አበልና ከሥልጠና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ዋነኞቹ ክፍተቶች ናቸው፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት የኦዲት ግኝቶቹን በሚመለከት ምላሽ ከሰጡት የማዕከሉ አመራሮች አብዛኞቹ፣ በሒሳብና በንብረት አያያዝና አስተዳደር ረገድ በታዩት የኦዲት ግኝቶች ላይ የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ ለተነሱት ጉድለቶች ‹‹ዕርምት ወስጃለሁ›› ቢልም፣ ቀጣይ ለሚኖረው እንቅስቃሴ እንጂ ጉድለቱ ለታየበት ወቅት እንዳልሆነና ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ሰዎች ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባው የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተቋሙ በበጀት አጠቃቀም፣ በንብረት አያያዝና አስተዳደር፣ እንዲሁም በሥነ ምግባር ረገድ በርካታ ግድፈቶች ያሉበት በመሆኑ ማዕከሉና ተጠሪ የሆነለት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሮቹን በአስቸኳይ ማስተካከል እንዳለበት አስታውቀው፣ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መርሐ ግብርና ሪፖርት ማቅረብ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች