Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በዘመናችን በጣም የሚያስገርሙ፣ የሚያናድዱ፣ እንደ ወፈፌ ለብቻ የሚያስቁ በርካታ ገጠመኞች አሉን፡፡ እኔ ግን የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› የሚለውን መጽሐፍ ሳስታውስ ያለንበት ሁኔታ ድንቅ ይለኛል፡፡ ፕሮፌሰሩ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያኑረውና ካነሱዋቸው በርካታ ነጥቦች ጋር እጅግ በጣም እስማማለሁ፡፡ ያው ተፈጥሯዊ ስለሆነ በምንስማማው እየተደጋገፍን፣ በማንስማማው እየተለያየን በሰላማዊ መንገድ መነጋገር የዴሞክራሲ መገለጫ ስለሆነ እኔም በዚያው ስሜት ውስጥ ሆኜ የገጠመኝን እነግራችኋለሁ፡፡

ለገጠመኜ መነሻ የሆነኝ ግን የፕሮፌሰሩ መጽሐፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ታሪካችን ከሽፏል ወይስ እኛ ነን የከሸፍነው?›› እየተባባልን ዙሪያ ገባውን ውይይት ማጧጧፍ ሲገባን፣ ከመክሸፍም በላይ ሌላ መዘዝ የሚያመጣ አጋጣሚ ስለገጠመኝ እንዲህ ላወጋችሁ ወደድኩ፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይ አገራዊ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት፣ ለትውልድ መዳን ሲባል አጀንዳ ቢሆን ብዬም እመኛለሁ፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ቀን ከጓደኞቼ ጋር አመሻሽ ላይ ቢራ ለመቀማመስ የምናዘወትረው ‹‹ባር›› ጎራ እንላለን፡፡ ሥፍራው ደግሞ ስድስት ኪሎ ነው፡፡ መጠጥ ቤቶቹ ከበዙበት አካባቢ፡፡ ቢራችንን አዘን ስለበርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እየተወያየን ሳለ፣ ሁለት ወጣት ወንዶችና ሁለት ወጣት ሴቶች ግር ብለው ገብተው አጠገባችን ያለውን ጠረጴዛ ከበው ተቀመጡ፡፡ ወዲያው አንደኛው ለግላጋ መሳይ ወጣት አንድ ጠርሙስ ጂንና ሱፐር ሚንት ከስድስት ጃንቦ ድራፍቶች ጋር ሲያዝ ሰማን፡፡ በትዕዛዙ ገደብ የለሽነት እየተያየን የሚከተለውን መጠባበቅ ጀመርን፡፡

- Advertisement -

ቀልጣፋው አስተናጋጅ ስድስት ጃምቦ ድራፍቶችን ካቀረበ በኋላ ጠርሙስ ጂንና ሱፐር ሚንት ይዞ መጣ፡፡ ስድስቱም ወጣቶች ጃምቦ ድራፍታቸውን በአንድ ትንፋሽ ካጋመሱ በኋላ፣ በወጣቱ አጋፋሪነት ጂንና ሱፐር ሚንት በግራና በቀኝ ሆነው ብርጭቆአቸው ውስጥ ተንቆረቆሩ፡፡ ጃምቦ ብርጭቆዎቹ መሙላታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ሁሉም ወደላይ አንስተው ‹‹ቺርስ›› ተባባሉ፡፡ አኳኋናቸው ሁሉ በእንዲህ ዓይነቱ የአጠጣጥ ዘይቤ የተካኑ መሆናቸውን ያሳብቃል፡፡

አስተናጋጁን በዓይን ጥቅሻ ጠርቼ፣ ‹‹የየት ሠፈር ልጆች ናቸው?›› አልኩት፣ ከዚህ በፊት እዚህ አካባቢ ዓይቼአቸው አላውቅም፡፡ እሱም ወደ እኔ በጣም ተጠግቶ፣ ‹‹የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ እኛ ሁለት ሁለት ቢራችንን ሳንጨርስ ወጣቶቹ ሦስተኛ ጃንቦ ድራፍት አዘው ጂኒኑና ሚንቱን እያንጠፈጠፉ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ጃምቦው በጎደለ ቁጥር አልኮሉ በፍጥነት ነበር የሚሞላው፡፡ እኔ ስለነሱ ታከተኝ፡፡ የወጣትነቴን ዘመን በስፖርት ያሳለፍኩ በመሆኑ እነዚህ ለግላጋዎች አልኮል ሲጋቱ አንገፈገፈኝ፡፡ 

ከጓደኞቼ ጋር በሐዘን እየተያየን ይህንን ጉድ በምሬት ስናስተውል ሌላ ሁለት ወጣት ወንዶችና ሴቶች ያሉበት ቡድን ደረሰ፡፡ በፊት ከመጡት ጋር ሰላምታ ተለዋውጠው ሌላ ጠረጴዛ ከበቡ፡፡ ለእነዚህም ጃንቦ ድራፍት፣ ጂንና ሚንት መቀዳት ጀመረ፡፡ ምን ይሆን ጉዱ? በኋላ ስናጣራ ወጣቶቹ የመጡት በአካባቢው ከሚገኝ ጫት ቤት መሆኑን ተገነዘብን፡፡

ከጫት በኋላ ‹‹ጨብሲ›› የሚባለው ነገር የተለመደ ነው፡፡ አለበለዚያ ምርቃና እንዲህ በቀላሉ አይሰበርም፡፡ የመጠጥ ፍላጎት በጣም ከመጨመሩ የተነሳ ምንም ስለማያስመርጥ፣ ቅዥት ውስጥ ከሚከተው ምርቃና በስካር መገላገል መፍትሔ ሆኖ ስለሚታይ፣ ታዳጊዎቻችን ከማይቋቋሙት ባላጋራ ጋር ትግል ውስጥ ገብተዋል፡፡ የሚጠጣው አልኮል ብዛትና የሚጨሰው ሲጋራ ስላስመረረን ጥለናቸው ውልቅ አልን፡፡

በነጋታው ጠዋት መደዳ ካሉ ካፌዎች በአንደኛው በስልኬ የዓለም ዜና እያየሁ ማኪያቶ ስቀማምስ ማታ በአልኮል ሲቃጠሉ የነበሩት ወጣቶች ዓይናቸው ቀልቶ፣ ፊታቸው አመድ መስሎ፣ በንፋስ እንደሚወዛወዝ ሸንበቆ ወዲያና ወዲህ እያሉ መጡ፡፡ ሳያቸው በጣም አዘንኩ፡፡ በተለይ ሴቶቹ ፀጉራቸው ተንጨባሮና ለዛቸው ጠፍቶ የአመድ ማፈሻ መስለው ሳያቸው ውስጤ ተንዘፈዘፈ፡፡ ኬክ በለስላሳ እየጎረሱ ማላመጥና መዋጥ ሲያቅታቸው ማየት አሳዛኝ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ማናገሩ ምንም ውጤት ስለሌለው ሒሳቤን ከፍዬ ትቼያቸው ሄድኩ፡፡

ትናንት አልኮል ይጋቱበት የነበረውን ‹‹ባር›› ባለቤት ስለማውቀው ባገኘው ብዬ ወደ እዚያ አመራሁ፡፡ እንዳሰብኩትም አገኘሁት፡፡ የምሽቱን ትዕይንት አንስቼለት የጠዋቱን የወጣቶቹን ሁኔታ ሳነሳለት፣ በብስጭት ስሜት እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ፣ ቤተሰብ ዩኒቨርሲቲ ተማሩ ብሎ ይልካቸዋል፡፡ እነሱ ግን እንኳን የተማሪ ወግ ሊኖራቸው ያሳፍራሉ…›› አለኝ፡፡ አነጋገሩ ምሬት የተሞላው በመሆኑ የሚናገረውን ለማዳመጥ ራሴን ዝግጁ አደረግኩ፡፡

ከጫቱና ከመጠጡ በላይ ምን አጋጥሞት ይሆን? ‹‹እነዚህ ልጆች እኮ እንስሳ ሆነዋል ማለት ይቀላል፡፡ እኔ በበኩሌ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምን እንደሚማሩ ግራ እየገባኝ ነው፡፡ ተግባራቸው ሁሉ ከማይም አይሻልም፡፡ ይብላኝ ለወላጆች፣ ይብላኝ ለአገሪቱ፡፡ በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ ነገሮችን ነው የምናየው፡፡ አንደኛ ወሲብ ሲፈጽሙ ኮንዶም አይጠቀሙም፡፡ ሁለተኛ ማን የማን ጓደኛ እንደሆነች ግራ እስከሚያጋባ ድረስ እየተፈራረቁ ይዳራሉ…›› እያለ ሲንገፈገፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የከሸፈው ታሪክ ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ ጭምር መሰለኝ፡፡ የነገውን አገር ተረካቢ ትውልድ እንዴት እንታደገው? ሌላው ቢቀር ለአገራችን ስንል መስዋዕትነት እንክፈል፡፡ ‹‹አባት የሞተ እንደሆን በአገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ ዕለት ወዴት ይደረሳል?›› የሚባለው በዚህ ጊዜ አይመስላችሁም?

(አብርሃም ወልደ ገብርኤል፣ ከስድስት ኪሎ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...