Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሰላማችን ሰላምታ ብቻ ሳይሆን ሰላምም ስጡኝ ይላል

ሰላማችን ሰላምታ ብቻ ሳይሆን ሰላምም ስጡኝ ይላል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አገራችንን ላለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠማትና በሦስት ዙር እየተመላለሰ የተዋጋቸው ጦርነት የጦርነትን መርገምት፣ ፍዳና ጣጣ ብቻ በውጤትነት ያስከተለ አደጋና ጥፋት ብቻ አልነበረም፡፡ ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር፣ የዴሞክራሲን መደላድል የማሰናዳት የመጀመርያና የሥር አጀንዳችንን አናግቷል፡፡ የአገራችንንም ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአደጋ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ በሰላም ጥበቃና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ስም ሕገወጥ ለሆነ ማዕቀብና ጣልቃ ገብነት አደጋ አጋልጦን ቆይቷል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ግንባር (ሕወሓት) መካከል ግጭትን በቋሚነት በመግታት አማካይነት፣ ለዘላቂ ሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስደው መንገድ እውነትም መያዙና መጀመሩ በጣም ጥሩና እርግጥም ነበር፡፡ እውነትና ጥሩ ነበር ማለት ግን መንገዱ ዝም ብሎ የውኃ መንገድ ነው፣ ነበር፣ ወደፊትም እንደዚያው ይሆናል ማለት አይደለም፡፡

ለምሳሌ የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም አንድ ብሎ እንደ ተጀመረ የተዋዋይ ወገኖች የመጀመርያው ግዴታ ግጭትን ማቆም ነው፡፡ ይህ የመጀመርያው ግጭት/ተኩስ የማቆም ዕርምጃ ራሱ በየቦታውም ሆነ በተለያየ ቦታ ቀላልና እንደሚገመተው እንዳልነበረ ቀስ ብሎ እየተገለጸልን የመጣው ‹‹ዜና›› አስረጂ ነው፣ ወይም ጠቋሚ ነው፡፡ እዚሁ ተኩስ ማቆም የመጀመርያውና ‹‹ቀላሉ›› ሊባል የሚችለው የስምምነቱ ግዴታ ላይ ትንሽ ቆየት ብለን፣ ለምሳሌ የሕወሓትን ወገን የዚህ ጉዳይ/ግዴታ አፈጻጸም ከደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የመቀሌ መግለጫ እንመልከት፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በዚያኑ ዕለት ትግራይ፣ መቀሌ ‹ድንገት› ለጉብኝት ለተገኘው በአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ለተመራው የፌዴራል መንግሥት የልዑካን ቡድን በሰጡት ማብራሪያ ቀላል ነው ያሉት የተኩስ አቁሙ እንኳን፣ ‹‹የተኩስ ማቆም ነው እንጂ ሌላው ውይይት ያስፈልገዋል፡፡ … ሠራዊቱም እንዲሁ፡፡ አቁም ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን? ምን ተፈጠረ? ሊል ነው፡፡ ብዙ ጥያቄዎችም ፖለቲካዊ ጭምር ያለበት ነውና ዝም ብሎ በትዕዛዝ ሊሆን አይችልም፡፡ [ስለዚህ] ወደ ውይይት፣ ሠራዊቱን ከላይ እስከ ታች በአጭር ጊዜ ውይይት እንዲካሄድበት፣ መንግሥትም በመዋቅሩ…›› ተወያይቶበታል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንን ማብራሪያና ምክንያት ራሱን ይዘን የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊትን ተኩስ እንዲያቆም ለማድረግ ትዕዛዝ ብቻ በቂ አይደለም ማለት ይቻላል ወይ ብለን እንጠይቅ፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87 የመከላከያ መርሆዎች ድንጋጌ፣ ከእነ ውሱን የአፈጻጸም ዕውን ይሁን የይስሙላ ታሪኩ ጥያቄዎችን ይመልሳል፡፡ የወታደሩ የሲቪል አመራር ጽንሰ ሐሳብ የሚገኘውም እዚሁ ድንጋጌ ውስጥ ነው፡፡ የወታደሩ ታዛዥነት ለሲቪሉ አመራር ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ለግዳጅ የሚሠማራው ተኩስ አቁም ተብሎ የሚያቆመው በገዛ ራሱ ውስጥ መክሮና ዘክሮ ሳይሆን፣ ሪፐብሊኩ ሲያዘው ነው፡፡ በዚህ ሥሌትና ፍጥርጥር የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት (ስለዴሞክራሲ ከተወራ) ዴሞክራሲን ይጠብቃል እንጂ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ›› ውሳኔ ውስጥ አይገባም፡፡ ይህንን ጥበብና ቲዮሪ፣ ዛሬ የሌላኛው ተዋዋይ ወገን አባል ሆነው በተከታተልናቸው የፕሪቶሪያ/ናይሮቢ ስብሰባ የምናያቸው ጄኔራል ፃድቃን ያኔ በደህናው ጊዜ ደጋግመው ሲያስተምሩን ሰምቻለሁ፡፡ የመጀመርያው በመከላከያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በበላይ አመራርነት ለመቀጠል ከፓርቲ አመራርነት ብቻ አይደለም ከፓርቲ አባልነት ሲሰናበቱ በፎርም፣ በቄንጥና በ‹‹ክብር›› ጭምር ዓይተናል፣ ተነግሮናልም፡፡ ቆይቶም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ይሰጡ በነበሩ ወቅታዊ መግለጫዎች ውስጥ ጄኔራል ፃድቃን አንዳንድ ጉዳዮችን ሲያብራሩና ጥያቄዎችን ሲመልሱ፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሲቪሉን ፖለቲከኛ ሥራ ከወታደራዊ ሚና ጋር አላደባልቅም ሲሉ፣ ይህ እኔን አይመለከተኝም፣ የእኔ ሥልጣንና ድርሻ ፖለቲከኞች ያዘዙኝን መሥራት ነው ሲሉ እናውቃለን፡፡

ጄኔራል ፃድቃን ደጋግመው የሰጡን ትምህርት ለምን በ‹‹ትግራይ ሠራዊት›› ውጥስ ቦታ አጣ? ለምን ‹‹ተኩስ አቁም››ም ሆነ ‹‹ተኩስ›› ብሎ ትዕዛዝ ብቻውን በቂ አልሆነም? ብሎ መጠየቅ አጉል መሞላቀቅ ወይም መዘባነን መሆኑን ለውጡ የተጀመረበት ምክንያት ራሱ፣ በለውጡ ላይ የተተኮሰበት ምክንያት ራሱ በቂ ማስረጃና ማብራሪያ ነው፡፡ ሰላማችንን ከነሳን፣ ካሳጣን ምክንያት አንዱም ይኼው ነው፡፡ እንዲህ ካለ ጅምር የምንነሳ መሆኑን የሚያውቁ ጭምር ሳይቀር እዚያው ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የታኅሳስ 17 ቀን ንግግር ውስጥ መንግሥት፣ አፈ ጉባዔ፣ ምክር ቤት፣ ፓርቲ፣ ሕዝብ በሚሉት ቃላት ሲበሳጭ፣ ሲብከነከንና ሲደብን የአገሪቱን አንፃራዊ ሰላም በዚህ ምክንያትና የኢትዮጵያ ልዑክ ደግሞ ለዚህ ምላሽ አልሰጠም ብሎ በ‹‹ንጭንጭ›› እና በጭቅጭቅ እገዘግዛለሁ፣ እጎዳለሁ ሲል እየመሰከርን ነው፡፡

የአገራችን የፖለቲካ ሰላም ከተኩስ ማቆም በላይ በርካታ የሰላም መሠረተ ልማቶችን መገንባት ይሻል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አየር እየጠራ ወደ የሠለጠነና የሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊና ሕጋዊ ‹‹ግብግብ›› እንዲለወጥ የግድ ይሻል፡፡ እዚህ የተባለው ዓይነት ውድድርና ግድድር ውስጥ የሚገቡ ኃይሎችም ሁሉም የተወሰነ የዴሞክራሲያዊ አመለካትና ዴሞክራሲያዊ የድርጅት አኗኗር መለኪያን ያለፉ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሕግ ያዛል፡፡ ለወጡ ሲመጣ በማዕከላዊ/በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል ደረጃ ሥልጣን ላይ የነበሩ እንዲሁም ከውጭ፣ ከስደትም፣ ከጫካም የገቡ ፓርቲዎች፣ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት አልተለወጡም፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር አልያዙም፡፡ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለምሳሌ ከሌሎች መካከል መግቢያው ላይ፣ ‹‹ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ›› ነው ሲል፣ እንዲሁም በአንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ 3 የስምምነቱን ግብ ሲደነግግ፣ ‹‹ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ነውጠኝነትን የትግል መሣሪያ ማድረግን›› ዕንቢ ማለት ሲል ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ተፎካካሪ ኃይሎች ለዚህ ይገዛሉ፣ ይህንን ሕግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያከብራሉ ማለቱ ነው፡፡

በሰላም ስምምነቱ አማካይነት መልክ የያዘው የተኩስ ማቆምና ሌሎችም ተከታይ ዕርጃዎች ሰላምታ አቅርቡልኝ፣ ሰላምታ ስጡኝ ብቻ ሳይሆን፣ ከእነ ሰላም ስምምነቱ ‹‹ሰላም ስጡኝ›› የሚሉት ይህን ሁሉ ከቁጥር በማስገባት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁሉም ነገር መነሻ ሕገ መንግሥቱን በማድረግ ነው፡፡ ይህንን ራሱን የሚቃወሙ፣ ሕገ መንግሥቱ ለምን የስምምነቱ መነሻ ሆነ የሚሉ፣ አንዱ ወይም ሌላው የስምምነቱ ተዋዋይ ወገን ወይም ሁለቱም ተስማምተው ስለሕገ መንግሥቱ መከበር ‹‹ሲስማሙ›› እየሰሙ እርር ድብን የሚሉ ወገኖችም፣ ስምምነቱን ሰላም ከሚነሱት/ከሚነፍጉት መካከል ናቸው፡፡ ሲጀመር ጦርነት የተከፈተበትና ሦስት ጊዜ ወረራ ያጋጠመው ለውጥ የመጣው፣ ኢትዮጵያን እውነትም እንደ ሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ፌዴራላዊና ሪፐብሊክ አደርጋለሁ ብሎ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ እንዲያከብር ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ አውታረ መንግሥቱን፣ ከእነዚህም መካከል ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት ዓምዶችን ከፓርቲ ገለልተኛ አድርጎ ማቋቋም ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን በመሰለው የለውጥ ጅምር ላይ ተመሥርቶ ሰላምንና ዴሞክራሲን የማደላደል ዘላቂ የማድረግ ሥራዎች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህ ሒደትም ሕገ መንግሥቱን ከምር የማወቅ፣ በዚያም ላይ የተመሠረተ የማሻሻልና የእኔ የሚሉትን የበላይ ሕግ የማውጣት ዕርምጃ ይከተላል፡፡

በእኛ አገር ውስጥ ሁሉም ከሞላ ጎደል ሁሉም ስለዴሞክራሲ ሲምልና ሲገዘት ይሰማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ የሚል ቅፅል ወይም ‹‹ማንጠልጠያ›› የሌለው የፖለቲካ ድርጅትም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ዴሞክራሲያችን ግን ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋም ግንባታ የሚል አቋም ድረስ ያስማማል ወይ? የሚል ጥያቄ አሁንም እንደተደቀነበት ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ስለታጠቀ ፓርቲ፣ ትጥቅ ስለሚፈታ ፓርቲ የሚወራባት አገር አትሆንም ነበር፡፡ ወይም የኢፌዴሪ የመከላከያ ኃይል አንድና አንድ ብቻ ነው የሚል ስምምነት መፈረም ድረስ መከራ ባላየን ነበር፡፡ በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸምና አተገባበር ሒደት ውስጥ፣ እንዲሁም በሒደቱ የተለያዩ ፌርማታዎችና መድረኮች ላይ አለመግባባት፣ ጭቅጭቅና ‹‹ንጭንጭ›› ጭምር ከሚፈጥሩት ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ፣ ወይም በተለይ ሁለቱ የውጭ ኃይልና የአገር መከላከያ ሠራዊት ያልሆነ ኃይል የሚባሉት ናቸው፡፡ ይህ ናይሮቢ አንድና ናይሮቢ ሁለት የጽሑፍ ስምምነት/ሰነድ ውስጥ በስም መጥራትን እንኳን የፈራ ስያሜ የሚናገረው ስለኤርትራና ስለአማራ ክልል ኃይል ስለመሆኑ በሹክሹክታ ሳይሆን በግልጽ የሚነገር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የኤርትራው ነገር ለጊዜው ይቆይና ስለሌላው ‹‹Non ENDF›› (የአገር መከላከያ ሠራዊት ያልሆነ) ኃይል አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተን እንነጋገር፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት/ኃይል አንድና አንድ ብቻ ነው ብሎ ታግሎ፣ ይህንንም የታሪካዊው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሪ ድንጋጌ ያደረገ አገራዊ ርብርብ፣ እንዲሁም በስምምነቱ አንቀጽ 8.3 የተመዘገበውን ድል ያስመዘገበ ትግል የመከላከያ ሠራዊት ያልሆነ ኃይል ለጊዜው ከክልሉ ይወጣል መባሉን ለምን ይፈራል? ለጊዜው የሚለውን ቃል አጽንኦት የሰጠሁት በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ያለ የአስተዳደራዊ ግዛት ውዝግብ፣ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚስተናገድ ስምምነቱ ስለሚወስንና እስከዚያ ድረስ ያለው ጉዳይም የዚህ/የዚያ ክልል ሳይባል የፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን ሆኖ ስለሚቆይ ነው፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 8.3 የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎችም የፌዴራል የደኅንነት አካላት በትግራይ ውስጥ በአገሪቱ የአየር ግዛት የበረራ ደኅንነትና ፀጥታ፣ በሁሉም የፌዴራል ፋሲሊቲዎች፣ ኢንስቲትዩሽኖችና እንደ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ አውራ ጎዳናዎችና የመሳሰሉ ዋና ዋና ከፍተኛ ‹‹ኢንፍራስትራክቸሮች›› ላይ ሙሉና ወሳኝ ቁጥጥር አለው፣ ይህንንም ይወስዳል፣ ይረከባል ይላል፡፡

ከሥር ከመሠረቱ የአገር የመከላከያ ሥልጣን የፌዴራሉ መንግሥት ነው የሚልና የክልል የዚህ አቻ ሥልጣን ከፖሊስ ሥልጣን በላይ አይዘልም የሚል ዓይነት ድንጋጌ ያለው ሕገ መንግሥት አፈር ድሜ በልቶ፣ ኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ የውስጥ ወረራ እንዲያጋጥማት ሆና ዝርክርኳ ወጥቶ፣ በታየበት ሁኔታ ውስጥ ሕወሓት ትጥቅ ይፈታል ከሚል አሸናፊነት ፊት ለፊት ስለሌላ ክልል ታጣቂ፣ ስለጥምር ኃይል ማውራት ራሱ ሕገ መንግሥታዊነትን ማደላደል፣ ለሕገ መንግሥታዊነት መታገል አይደለም፡፡

ክልሎችን እሳትና ጭዳቸው እንዲወጣ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፌዴራል አባላት አከፋፈለን የየብቻ የመሬት ቅርጫ ማረጋገጫ፣ የተወሰነ ማኅበረሰብ ርስት አድርጎ ‹‹መውሰድ›› ያመጣው ከሕገ መንግሥት ይልቅ የፖሊሲ ድጋፍ ያለው እጅግ በጣም ሥር የሰደደና የገነተረ እምነት ነው፡፡ በዚህ ላይ ብሔረሰባዊ የፓርቲ አደረጃጀት ፓርቲውን የጭቆና መሣሪያ አድርጎ እርፍ አለ፡፡ የብሔር ፓርቲ የጭቆናና የአድልኦ መሣሪያ የሆነበትም ምክንያት በአደረጃጀቱና በዓላማው ዓይነተኛ ማኅበረሰቡን የእኔ ብሎ ሌላውን ስለሚያገልና ስለሚያንጓልል ነው፡፡ በብሔረሰብ መደራጀት እንደ ብዙኃን ማኅበር መብት ነው፡፡ በፓርቲነት በብሔር ተደራጅቶ ብሔረ ብዙነት ባለበት አካቢያዊም ሆነ አገራዊ የሕዝብ ጥንቅር ላይ በገዥነት መውጣት ግን መብት ሊሆን አይገባም፡፡

የክልሎች አሸናሸንና አወቃቀር፣ እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ፓርቲነትና ገዥነት ተደጋግፈው በየክልሉ ሕዝብን ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ለመከፋፈል መዘዝ ሆኑ፡፡ እንዲህ ያለ አደረጃጀት ደግሞ ሲታጠቅ (ፓርቲና መንግሥት በተደበላለቀበት፣ የፓርቲና የትጥቅ ነገር መሠረታዊ ዕልባት አግኝቶ በማያውቅበት ሁኔታ ውስጥ) ከሕገ ማስከበር ዓውድና ግቢ ወጥቶ እኛና እነሱ እያለ እንዴት አድርጎ ደም እንዳፋሰሰ ብቻ ሳይሆን፣ የአገርን የመከላከያ ኃይል እንደምን አድርጎ እንደዘነጣጠለ ኢትዮጵያና ጥቅምት 23/24 ቀን 2013 ዓ.ም. ቋሚ የዓይን ምስክሮች ናቸው፡፡ እና እንደ ትግራይ ክልል ወይም እንደ ትግራይ ክልል ፓርቲ ወይም እንደ ሌላ መታጠቅ የሚቀናበትም፣ ሕገ መንግሥታዊም አይደለም፡፡ ጥምር ኃይል እያልንና የሕወሓትን ‹‹ልምድ› እያየንና በእሱም እየጎመዠን ከስያሜ የመጀመረ ጉዞና መንገድ ሁሉ መታረም ያለበት ስህተታችንና ጥፋታችን ነው፡፡

ለሰላም ስምምነቱ ሰላምታም ሰላምም ለመስጠት አልችልም ያለ አተያያችን በታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የመቀሌ ጉዞ ላይም አጋልጠናል፣ አጋልጦናል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተመራው የፌዴራሉ መንግሥት የልዑካን ቡድን የዚያን ዕለት የውሎ ገባ ጉዞና ጉብኝት አንዳንዶች፣ እንዲሁም ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ራሳቸው ‹‹አፍ እንዳመጣ›› ተናግረው እንዳስመሰሉት የናይሮቢ ሁለት ተከታይ ወይም ቀጣይ የድርድርና የውይይት ጉዞ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት፣ ሁለቱም ወገኖች ‹‹በቅን ልቦና›› ነገር ግን ዝም ብለው (አሁንም እደግመዋለሁ) ‹‹አፍ እንዳመጣ›› እንዳሉት፣ ያለ ምንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያካሄዱት ድርድርና የደረሱበትም መቀሌ አንድ የሚባል ‹‹ሰነድ›› የለም፡፡ ፕሪቶሪያ፣ ናይሮቢ አንድና ናይሮቢ ሁለት የሚባለውን ዓይነት ማለቴ ነው፡፡

የመቀሌው የፌዴራል መንግሥቱ የልዑካን ቡድን ጉዞ በእርግጥም በገዛ ራሱ ምክንያት ደፋርና ለጋስ ዕርምጃ ነው፡፡ ከአደጋና ከሥጋት ነፃ የሆነ መደበኛ መተማመኛ አለው የማይባል ደፋርና ቁርጠኛ ዕርምጃ ብቻ ሳይሆን፣ ፈረንጆች እንደሚሉት ማግነመስ  ነው፡፡ የውል ስምምነቱ ግዴታ የሚያደርጋቸውን ዕርምጃዎች ከመፈጸም በላይ ‹‹ከእኔ ይቅር››ም ከእኔ ይምጣም ብሎ ከፍ ያለ ግዳጅ የተቀበለ ተነሳሽነት ነው፡፡ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ናይሮቢ ሁለት ተፈርሞ፣ ታኅሳስ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. እሑድ ‹‹የናይሮቢ ሁለትን ተከትሎ የሰላም ሒደቱን ዛሬ ገምግመናል›› ማለትን ያህል ብቻ (የዓብይ አህመድ የትዊተር/የፌስቡክ ገጽ ጭምር) ዜና ሰምቶ፣ የታኅሳስ 17 ቀን ሰኞ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ‹‹ድንገተኛ›› ጉብኝትና ውጤቱንም ዓይቶ የሕወሓትንም አፀፋዊ ምላሽ ሳያደንቁና ሳያመሠግኑ ማለፍ በጭራሽ አይቻልም፡፡ የዘወትርና የዕለት ተዕለት የተዋዋይ ወገኖች የስምምነት ግዴታና ግዳጅ አፈጻጸም ከሚጠይቀው በላይ እጅግ በጣም የሚያኮራ (ሪስክም ያለበት) ጀብዱ ነው፡፡ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ናይሮቢ የተፈረመው የክትትል፣ የማረጋገጫ፣ የተገዥነት ሜካኒዝሙ ‹‹ተርምስ ኦፍ ሪፈረንስ›› ሰነድ የሚመለክተውና የሚገዛው በዋናው ስምምነት በአንቀጽ 3 እና 6 የተወሰኑትን ግጭትን በቋሚነት የመግታትና ትጥቅ የማስፈታት (DDR) ድንጋጌዎችን ነው፡፡ የሰኞ የታኅሳስ 17 ቀን ጉብኝት ግን በራሱ በሁለቱ ወገኖች የግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ በራሱ ብዙ ነገሮችን የናደ፣ የፈታና ያቀራረበ ነው፡፡

ይህ ዓይነት በጎና ደግ ነገር በታየበት አጋጣሚ ውስጥ ግን በሁለቱም ወገኖች ወይም ጎራዎች ያሉ ሰዎች የልባቸውን ሲናገሩ፣ ግዳጃቸውን ወይም ግዴታቸውን ሲወጡ የፈጸሟቸውን ወይም ፈጸሙ የተባሉትን ‹‹አፍ እላፊዎች›› እያነሱ ያዙኝ ልቀቁኝ ያሉ፣ ስምምነትና ድርድር ብሎ ዝም ፕሪቶሪያ ቀረ ብለው የተቆጡ፣ መቀሌ የተገኘው ቡድን አፀፋዊ መልስ አልሰጠም ብለው የከለሱ፣ ከዚህም በላይ በዚህ የመንግሥት ተነሳሽነት ውስጥ ብዙ ዕንከኖች ያወጡ ሞልተዋል፡፡ ጥያቄው ግን እነዚህ ‹‹እንከኖች›› የአገርን ህልውና ከአደጋ ለማዳን በምናደርገው ርብርብ ውስጥ አንድ ላይ እንዲደረብ የተደረገው ሥርዓት የመገንባት፣ ገለልተኛ ተቋም የማነፅ፣ ዴሞክራሲ የማደላደል ሥራው አካል አይደለም ወይ? ደግሞስ ዕንከኖቹ ‹‹ከተፈቀደው ቶለራንስ›› ወይም ከሚታገሱት በላይ ነው ወይ? (ከንፁህ ወርቅ ወይም ከብር ወይም ከመደብና ከሌሎች ማዕድናት የሚሠሩ ገንዘቦች እንኳን ‹‹የሚፈቀድ ልዩነት›› አላቸው ብዬ ነው)፡፡

የፕሮቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ደግሞ ከየት እንደመጣ፣ ከምን ዓይነት ፍዳ፣ ግፍ፣ መከራ፣ ደም ዕንባ፣ የሰው ሥጋና አጥንት ውስጥ ተፈልቅቆ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውጪ እንኳን ስንት ‹‹አንተ››/‹‹አንቺ››፣ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› ዓይተናል፣ ሰምተናል፡፡ ከዚህ ሁሉ አዘቅት፣ የቀብር ጉድጓድ እወጣለሁ ያለ ትግል ለምን ተኩሎ፣ ተሸልሞና ተጊጦ አልወጣም ማለት ትግሉን ራሱን መካድ ነው፡፡ ብዙ የምንነጋገርባቸው፣ በሰከነና በሠለጠነ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ውስጥ የምንፋለምባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አንድ ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ይህ ቦታ የየትኛው ክልል ነው የሚለው ውዝግብ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ለማየት የድሬዳዋን ከተማ ራሱን ምሳሌ አድርገን እንመልከት፡፡ ‹‹የድሬዳዋ ከተማ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ወደ የክልላቸው ይዞታ እንዲካለል በወቅቱ አንስተውት የነበረው ጥያቄ በሕግ መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ፣ በመንግሥት በተወሰነው መሠረት ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ለፌዴራል  መንግሥት ተጠሪ ሆኖ ሲተዳደር የቆየ ከተማ ነው››፡፡ ይህ የእኔ ቃል አይደለም፡፡ የሐምሌ 23 ቀን 1996 ዓ.ም. አዋጅ (የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር) ቃል ነው፡፡ ድሬዳዋ ዛሬም ችግሩ ከተነሳ 30 ዓመታት፣ ችግሩን በሕገ መሠረት እፈታለሁ ከተባለ ደግሞ ከ19 ዓመታት በኋላ መልስ አላገኘም፡፡ ለድሬዳዋ ችግር መልስ የሚገኘው መጀመርያ መልስ የምናፈላልግበትን የማዕቀፍ ግቢ ስንወስን ነው፡፡ በአንድ አገር ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ነው ድሬዳዋ ‹‹የዚህ›› ወይስ ‹‹የዚያ›› ክልል የምንለው? ወይስ የአገሮች አገር በሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ? መጀመርያ ከዚህ ደዌያችን መዳን አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ዕዳ ‹‹ገብስ›› ነው፡፡ የትግራይንና የአማራን ክልሎች ካላፋጀሁ የሚለው አንገብጋቢ ችግርም ይህን ያህል አገራዊ ትዕግሥትና ምክክር ይፈልጋል፡፡  

ሌላው የሚያቃጥለንና የሚያንገበግበን ጉዳይ የኤርትራ ድጋፍና ዕገዛ ‹‹ወረራው ኃይል›› መባሉ ነው፡፡ የኤርትራ ኃይል ወይም ጦር (ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ) ወራሪ ነው ወይስ አጋር? የጦር ጓደኛ? መመለስ ያለበት ስምምነቱ ውስጥ ተብራርቶ በተወሰነውና በተመለከተው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አንድ ብቻ ነው፣ አገር የመከላከል የመንግሥት ሥልጣን የፌዴራሉ መንግሥት ብቻ ነው በሚለው ማዕቀፍና ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍና ባለው መርህ መሠረት ነው፡፡ ይህንን በየቦታውና በየክልል፣ በየውጊያው ጎራና በየተዋጊው ውስጥ የአገር ግንዛቤ፣ ንቃትና ፖለቲካ ለማድረግ ጊዜም ትዕግሥትም ይፈልጋል፡፡ ትዕግሥት እያጣን፣ ቅደም ተከተል እያጠፋን ሰላም እየነሳን፣ ሰላምታ እየነፈግን አላስቆም አላስቀምጥ የምንለው ይህንኑ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...