Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አዲሱ ዲጂታል ግዥ የጨረታ ውድድሮችን በተለያዩ መንገዶች መዝጋትንና ስርቆትን ይከላከላል›› አቶ ሐጂ ኢብሳ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

ለረዥም ዓመታት ባሳለፉበት የገንዘብ ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊነት ስልካቸውንም ሆነ ቢሮዋቸውን መረጃ ለሚፈልጉ ጋዜጠኞች ሁሉ ክፍት በማድረግ የሚታወቁ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደነበሩ በሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ አቶ ሐጂ ኢብሳ አሁን ወዳሉበት የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ሲመጡ የገጠማቸው ችግርና ለመቀየር የተገደዱበትን ነገር ከመግለጽ በተጨማሪ፣ ተቋማቸው ከዓምና ጀምሮ ስላስጀመረው የዲጂታል ግዥ ሥርዓት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አዲሱ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሙስና፣ ምዝበራና ብልሹ አሠራርን ከመከላከል ጀምሮ ኢትዮጵያን ወደ ሥልጡን አገር ለማሸጋገር መሠረት እንደሚሆን አቶ ሐጂ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ የዲጂታል ግዥ ጀምራችኋል፡፡ ከጽንሰ ሐሳቡ በመነሳት ስለአሠራሩ ምንነት ቢያብራሩልን?

አቶ ሐጂ፡- እንደሚታወቀው ከአገሪቱ በጀት 70 በመቶ ለግዥ ነው የሚውለው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ አገሮች በጣም ብዙ ግዥ የሚያካሂደው መንግሥት ነው፡፡ ለግዥ ደግሞ የሀብት፣ የጊዜና የጉልበት ብክነት ደጋግሞ ያጋጥማል፡፡ ይህ ችግር ይጥፋ ስላልን ብቻ የሚጠፋ ባለመሆኑ በ2011 ዓ.ም. ጥናት አስጠናን፡፡ ያደጉ አገሮች ይህን በሽታ እንዴት አለፉት ብለን ተሞክሮዎችን አፈላለግን፡፡ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ በአጠቃላይ የሰባት አገሮችን ተሞክሮ አጥንተናል፡፡ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement/e-GP) እየተባለ የሚጠራው የግዥ ሥርዓት በካናዳ ነበር እ.ኤ.አ. 1991 ለመጀመርያ ጊዜ የተተገበረው፡፡ ካናዳ በዚህ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ሙስናን ተከላክላበታለች፡፡ ለግዥ ከሚመደበው ወጪ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን በዚህ መንገድ ነው ከሙስና ነፃ ያደረጉት፡፡ ደቡብ ኮሪያና ሰሜን ኮሪያም የተሻለ ተሞክሮ ያገኘንባቸው አገሮች ናቸው፡፡ ብዙ አገሮች የሙስና ተጋላጭነትን በዚህ አሠራር ቀንሰዋል፡፡ ይህ የዲጂታል ግዥ ሥርዓት የፋይናንስ ኦዲት ለመሥራት የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ረገድ ሥራ ያቀላል፡፡ የተደራረበ የኦዲት ሥራን ያቀላል፡፡ አሠራሩ ያለ ዕቅድ የሚደረግ ግዥን የሚያስቀር ነው፡፡ የታቀደን የግዥ ዕቅድም እንዳይፋለስ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ በአራተኛው ሩብ ዓመት የታቀደ ግዥን በአንደኛው ሩብ ዓመት ላይ እንዳይካሄድ ያደርጋል፡፡ አሠራሩ የግዥ ዕቅድ እንዲኖር የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፣ ያልተፋለሰ የግዥ ሥራ እንዲካሄድም የሚጠቅም ነው፡፡

በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ዓመቱን ዝም ብሎ ተቀምጦ ግንቦትና ሰኔ ላይ የዓመት ግዥ የመከወን ልማድ አለ፡፡ ስም ባልጠራም እስከ 80 በመቶ ግዥውን በአራተኛው ሩብ ዓመት ካልገዛሁ ያለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ገጥሞኛል፡፡ ለምሳሌ ይህ ተቋም ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትራክተሮችን እገዛለሁ ቢልህ ግዥውን መከልከል ከባድ ነው፡፡ መጪው ክረምትና የእርሻ ሥራ የሚኖርበት በመሆኑ ወጣቶቹን በደልክ ማለት ነው፡፡ ሒደቱን እየጠላኸውና እያመመህም በዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ግዥውን ወደ መፍቀድ ልትገባ ትችላለህ፡፡ አዲሱ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ግን ይህን የሚያስቀር ነው፡፡ ድንገተኛ ግዥ ለማድረግ ዕቅድን ተመልሶ መከለስ ይጠይቃል፡፡ አንደኛ፣ ሁለተኛም ሆነ ሦስተኛ ሩብ ዓመት ያቀድከውን የምትገዛበት ነው፡፡ አራተኛ ሩብ ዓመት ግን ለቀጣይ ግዥ ሥራዎችህን የምታቅድበትና የፋይናንስ ኦዲትህን የምትዘጋበት የበጀት ዓመት ነው፡፡ የተሳኩና ያልተሳኩ የግዥ ሥራዎችን የምትገመግምበት ነው፡፡ ወሳኝ የሚባሉ ግዥዎች በሙሉ በሦስቱ ሩብ ዓመት ማለቅ አለባቸው፡፡ ጥቃቅን ግዥዎች በአራተኛው ሩብ ዓመት ቢከናወኑ ይሻላል፡፡ ነገር ግን በጀት ዓመት መዝጊያ ላይ ለግዥ መዋከብን ይህ አሠራር ያስቀራል፡፡ ለምሳሌ ሶፍትና ስክሪብቶ የበጀት ዓመቱ ሲያልቅ ገዝቶ ለሠራተኛ የማደል ልማድ ይታያል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሲጽፍ ለቆየ ሠራተኛ በሰኔ ወር 12 ስክሪብቶዎች ማሸከም እንዲሸጠው ካልሆነ በስተቀር ምን እንዲያደርገው ነው፡፡ የደንብ ልብስ ያውም ጥራቱ የወረደ በበጀት ዓመት መዝጊያ ላይ ይታደላል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲጂታል ግዥ ትግበራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ሐጂ፡- በኢትዮጵያ በጀት ማለት ግዥ ማለት ነው፡፡ ወደ 70 በመቶ በጀት የሚውለው ለግዥ ሲሆን፣ ሌላው ትልቅ በጀት የሚፈስበት ደመወዝ ወይም መደበኛ አገልግሎት ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያሉ ዘርፎች በጀታቸው በንፅፅር አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ በጀትን ለመቆጠብም ሆነ የአገርን ሀብት ከብክነት ለመከላከል፣ ውጤታማ የአሠራር ሥርዓትን የተከተለ የግዥ ሒደት ማበጀት ግዴታ ነው፡፡ ይህ የዲጂታል ግዥ ሥርዓት የሚተገበረውም ለዚህ ሲባል ነው፡፡ ዓምና ዘጠኝ ተቋማት ነበሩ ወደዚህ ሥርዓት የገቡት፡፡ ዘንድሮ ወደ 74 አድርሰናል፡፡ ከየካቲት ጀምሮ ሥልጠና የምንጀምር ሲሆን፣ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ 169 መሥሪያ ቤቶች ወደ ዲጂታል ግዥ ሥርዓት እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ ትንሽ የሚያስቸግሩት ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፣ በተለይ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከኔትወርክና ከሌሎች መሠረተ ልማቶች ጋር በተያያዘ ሊቸግራቸው ይችላል ብለን እንጠብቃለን፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ሁሉም የፌዴራል ተቋም ወደ ዲጂታል ግዥ ሥርዓት እንዲጠቃለሉ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በሁለትና በአምስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበር አልመናል፡፡

በአዲስ አበባ በዘጠኝ ቢሮዎች ጀምረናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሐዋሳ እየሄድን ነው፡፡ የሲዳማ ክልል ኃላፊዎች ለመተግበር ቃል ገብተዋል፡፡ ድሬዳዋ ላይ እንዲጀመር ተነጋግረናል፡፡ ባህር ዳርም በቅርብ ጊዜ እንጀምራለን፡፡ በጥቂቱ ጀምረን እያሰፋን መሄድ ነው ዕቅዳችን፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የሚተገብረውን ዲጂታል የበጀት ሥርዓት (Integrated Financial Management Information System/IFMIS) መጀመርያ የተቀበሉት ጥቂት ነበሩ፡፡ በሒደት እንዳየነው ግን ብዙዎች እየተገበሩት ነው፡፡ እኛም ቀስ በቀስ እያለማመድን ሁሉንም ለማስገባት ነው ዕቅዳችን፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴሩ IFMIS የመንግሥት ተቋማትን በጀት፣ ግዥና ፋይናንስ ክዋኔ ብቻ የተመለከተ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡ የእኛ ኢጂፒ (eGP) ግን መላው የንግዱን ማኅበረሰብም ያካተተ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 30 ሺሕ ንግድ አንቀሳቃሾች አሉ ይባላል፡፡ እኛ እስካሁን ወደ 6,000 መዝግበናል፡፡ ከትልልቁ ንግድ አንቀሳቃሽ ጀምሮ እስከ ሱቅ በደረቴው ጭምር በዚህ ሥርዓት ውስጥ ገብቶ የሠለጠነ አገር መሆን ነው ፍላጎታችን፡፡  ከአፍሪካ ሞሮኮ ይህን ግብ አሳክታለች፡፡ ደቡብ አፍሪካም እንደዚሁ አሳክታለች፡፡ ኡጋንዳ ከእኛ አሥር ዓመታት ቀደም ብላ ጀምራዋለች፡፡ እኛ ከአፍሪካ ስድስተኛ ነን፡፡ በዲጂታል ግዥ ሥርዓት ረገድ ፈጣን ለውጦች ለማድረግ ነው እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዲጂታል አሠራሩ በግዥ ሥርዓቱ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል?

አቶ ሐጂ፡- የዚህ ኤሌክትሮኒክ ግዥ መጀመር አንደኛ ዲጂታል በመሆኑ የወረቀት ብክነትን ያስቀራል፡፡ ሁለተኛ የትራንስፖርት ወጪን ይቀንሳል፡፡ ቤት ተቀምጦ ወይም በማንኛውም ቦታ ሆኖ ልጫረት ያለ ሁሉ በሞባይል ስልኩ መጫረት ይችላል፡፡ የቢሮ ሰዓት አለፈ ወይ ሱቅ ተዘጋብኝ ሳይባል በማንኛውም ሰዓት መሳተፍ ይቻላል፡፡ ካለበት ቦታ ሆኖ ሁሉንም የጨረታ ሒደት መከታተል ያስችላል፡፡ ባለህበት ሆነህ ጨረታ ታስገባለህ፣ አሸናፊውን ማወቅ ትችላለህ፣ ውል ትዋዋላለህ፣ ቅሬታ ታቀርባለህ፣ በአጠቃላይ በተቀላጠፈ ሁኔታ መገልገል ትችላለህ፡፡ ተጫራቹና አጫራቾች ሳይተዋወቁና ሳይገናኙ ሥራቸውን እንዲሠሩ የሚያስችል ነው፡፡ ውል ገብቶ እስከ 30 በመቶ ዕቃውን ሲያቀርብና ቀብዱን ሲወስድ ሊሆን ይችላል አሸናፊው የሚታየው እንጂ፣ ተጫራች ለጨረታ ሒደት ላይ ታች መመላለሱን አሠራሩ ያስቀራል፡፡  ነባሩ ጨረታ በሁሉ መንገድ ንክኪ የበዛው ሲሆን፣ አዲሱ ግን ከንክኪ ነፃ ነው፡፡ የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ ወዘተ ተወላጅ እየተባለ በክልል፣ በብሔር ወይም በዝምድና ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚተው የጨረታ ሒደት በአዲሱ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ይቀራል፡፡ ዲጂታል ጨረታው እንኳን ኢትዮጵያዊ የአገሩ ነዋሪ ቀርቶ፣ የውጭ ዜጋም ቢሆን ከፈለገ ከመላው ዓለም ሊወዳደርበት የሚችል ነው፡፡ ማንም ሰው በመሆኑ ብቻ በዚህ የቴክኖሎጂ ጨረታ እኩል ይሳተፋል፡፡

በበፊቱ የጨረታ አሠራር ጨረታ ተብሎ ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ፣ መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ውድድሩን የመዝጋት አሻጥር ሊደረግበት ይችላል፡፡ ጨረታ ተብሎ ለሦስት ቀን የጨረታ ሰነድ ይሸጥና ከዚያ አሞናል ወይም ስብሰባ በሚል ቢሮ ዘግቶ ከርሞ፣ ውስን ቁጥር ያላቸው ተጫራቾች ብቻ እንዲወዳደሩ ማድረግ የተለመደ ነበር፡፡ ጨረታ ብለው መጀመርያ ክፍት አድርገው በመጨረሻ ግን ሦስት ሰዎች ብቻ ተወዳደሩ ብለው ወደ ፕሮፎርማ ግዥ ሊወስዱትም ይችላሉ፡፡ ጨረታ አምስት ተወዳዳሪ ከቀረበበት ውስን ጨረታ ነው፡፡ አብዛኛው ግን ውስን እያለ ሦስት ሰዎች የተወዳደሩበት ጨረታ ያመጣል፡፡ ሦስት ሰዎች ከቀረቡ እኮ ፕሮፎርማ ግዥ ነው፡፡ የጨረታ ሰነድ የሚሸጠውን የቢሮ ሠራተኛ ሆን ብሎ ሌላ አገር በመላክ፣ ወይም ቢሮ በሰበብ አስባቡ በመዝጋት ውድድርን ማፈንና ጨረታን ለራስ ጥቅም ለማዋል መሞከር የተለመደ አሠራር ነው፡፡ ተጫራቾችን ማንከራተት የታወቀ ልማድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲያውም ለዘመዱ ሰጠው ነው የሚባለው፡፡ አዲሱ አሠራር ይህን ሁሉ ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡

ከአፍሪካ ስድስተኛው አገር ነን እዚህ ውስጥ በመግባት፡፡ ከእነ ደቡብ አፍሪካ ጋር በዚህ ዘርፍ መሠለፍ ቀላል አይደለም፡፡ ደቡብ አፍሪካም የዛሬ 20 ዓመት በ2002 ነው አሠራሩን የጀመረችው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ አንደኛ ናት ሲባል ግዥዋን በሙሉ ተቆጣጥራዋለች ማለት ነው፡፡ እኛ ዘግይተን ብንጀምረውም ሒደቱ እንቅፋቶችን እያለፈ ያድጋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሥራው በመጀመሩ ትልቅ ዕርምጃ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከተለመደው ኋላ ቀር አሠራር የመንግሥት ተቋማትን አላቆ ወደዚህ ለማምጣት ብዙ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በለመድኩት ልግዛ፣ የለመድኩት ነው የሚመቸኝ፣ ተጫራች አይመዘገብልኝም፣ ኔትወርክ ያስቸግራል፣ ሙያተኛ የለኝም፣ ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ይደረደራሉ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በሚኒስትሮች ያስደውላል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ በተለመደው መንገድ እንድገዛ ፍቀድልኝ የሚልም አለ፡፡  አዳዲስ ነገር ሲመጣ ለመቀበል መቸገር ሁሌም የአፍሪካ ችግር ነው፡፡ እኛም ዘንድ ይህ ይስተዋላል፡፡ የሚዲያ አካላት ይህን ግልጽና ብዙ ብልሹ አሠራርን የሚከላከል አሠራር በደንብ ብትሠሩበት መልካም ነው፡፡ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም ለግዥ የሚመደብለት በጀት ይታወቃል፡፡ ግዥ በተጠየቀ ቁጥር ግን በጀት የለኝም የሚለው ብዙ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የተቋም አመራሮችን ወይም ኃላፊዎችን የሚጠቅም ነገር ለመግዛት በጀት ችግር አይታይም፡፡ ለወሳኝ ተቋማዊ ሥራ ሲሆን ግን በጀት የለም ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ አሠራር በግዥ ሒደት የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል ምን ውጤት ይኖረዋል?

አቶ ሐጂ፡- ይህ አሠራር በተለያዩ አገሮች ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እጅግ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርተውበታል፡፡ አካላዊ ንክኪ ሳይኖር በርቀት ሥራን መከወን ማስቻሉ ተመራጭ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያ በዓመት 7.8 ሚሊዮን የወረቀት ዶክመንት ክምርን ለመቀነስ የቻለችው በዚህ ሥርዓት ነው፡፡ ህንድ ሳይታቀድ ለሚካሄድ ጨረታ ይወጣ የነበረን 560 ሺሕ ዶላር ማስቀረት ችላለች፡፡ እንግሊዝ ደግሞ ለእያንዳንዱ ግዥ ይወጣ የነበረን 41 ዩሮ ከየግዥው ላይ መቀነስ ችላለች፡፡ አውስትራሊያ ወደ 178 ሚሊዮን ዩሮ ጣሊያን ደግሞ 67 ሚሊዮን ዩሮ ከግዥ ሒደት ማትረፍ ችለዋል፡፡ ደቡብ ኮሪያ በአጠቃላይ እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ባንግላዴሽ ደግሞ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከግዥ በጀቷ ስድስት በመቶ የሚሆን ሀብትን ማትረፍ ችለዋል፡፡ በህንድ 135 ቀናት ይፈጅ የነበረ ግዥ ወደ 35 ቀናት ማጠር የቻለው በዚህ የቴክኖሎጂ ግዥ ነው፡፡ በኖርዌይ የግዥ ሒደትን ጊዜ 40 በመቶ አሳጥሮታል፡፡ በደቡብ ኮሪያ ደግሞ 30 ሰዓት የሚፈጅ ግዥ ወደ 30 ደቂቃ ያጠረበት ውጤት መጥቷል፡፡  አዲሱ ዲጂታል ግዥ መስረቅን ይከላከላል፡፡የጥራት ደረጃ ራሱ ስለሚሰጥ ከደረጃ በታች የሆነ ግዥ እንዳይካሄድ ይከላከላል፡፡

ለምሳሌ ኮንስትራክሽን ላይ ብዙ ጊዜ ይገጥም የነበረ የግዥ ጥራት ጉድለትን መከላከል በሚያስችል መንገድ ነው ሥርዓቱ የተዘረጋው፡፡ ቅድመ ትንበያ ተደርጎ የግንባታ ጨረታ ይወጣል፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ገበያ ለመስበር ሲባል ለምሳሌ አንድ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ግዥን በአንድ ሚሊዮን ብር አቀርባለሁ የሚል ሊመጣ ይችላል፡፡ ተጫራቾቹ በቴክኒክ ምዘናው እኩል ሆነው ሳለ ነገር ግን በዋጋ እጅግ ሊራራቁ ይችላሉ፡፡ በጨረታ ሒደት ደግሞ ዋጋም አንዱ መወዳደሪያ ስለሆነ፣ መንግሥታችንም ደሃ ነውና ዝቅ ያለ ዋጋ ያቀረበውን እናሳልፍ ሊባል ይችላል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግን ይህንን ከልክለናል፡፡ ምክንያቱም ዋጋ እያወረዱ መሥራት የሚችሉ ሰዎችን ከገበያ ውጪ አድርገው ገብተው በድርድር ዋጋ ካልጨመራችሁልኝ የሚሉ ዕቃና አገልግሎት አቅራቢዎች በኮንስትራክሽን ብቻ ሳይሆን፣ በብዙ ዘርፎች እየበዙ መጥተዋል፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪዎችን በዋጋ ማውረድ ጥሎ ከገበያ በታች በሆነ ገንዘብ ለመሥራት ይዋዋላል፡፡ ነገር ግን ሥራውን ሳይሠራ ለተቋም ሠራተኞች ጉቦና ማባበያ በማቅረብ ዋጋ አስጨምሩልኝ ወደ ማለት ይገባል፡፡ ለግዥ ኮሚቴዎች የተወሰነ በማስጨበጥ ሥራውን ስወስድ የሲሚንቶ፣ የአሸዋና የብረት ዋጋ ዝቅተኛ ስለነበር ግንባታውን እንድጨርስ ዋጋ ጨምሩልኝ የሚል ተቋራጭ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የበዛ ሲሆን፣ ይህ ልማድ ደግሞ በሌሎች ዘርፎችም መታየት ጀምሯል፡፡

ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር በጀመርነው አሠራር ውጤታማ የሆኑ ተቋራጮች ብቻ እንዲፎካከሩ የማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተናል፡፡ በስድስት ወራትም ይሁን በአንድ ወይ በሁለት ዓመታት በተሰጠው ጊዜ ገደብ ሥራን ጨርሶ የሚያስረክብ ተቋራጭ ነው የምናበረታታው፡፡ በበጀትና በጊዜ ብክነትና መጓተት የሚፈጥሩ ተቋራጮች ግን ከጨዋታው ውጪ ነው የሚሆኑት፡፡ ለዩኒቨርሲቲዎች እንጀራ አቀርባለሁ ብሎ ተጫርቶ ዋጋ ሰብሮ ገብቶ ዋጋ ጨምሩልኝ የሚል ሁሉ እየገጠመን ነው፡፡ ለምሳሌ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲታይ የአንድ እንጀራ ዋጋ ስምንት ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በአራት ብር አቀርባለሁ የሚል ተጫራች ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ አቅራቢ አሥር ብር ብለው ካቀረቡ ተጫራቾች ጋር በቴክኒክ እኩል ተወዳዳሪ ቢሆን፣ ዋጋው ስላነሰ ብቻ እሱ ጨረታውን ሊወስድ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ ብዙ ተወዳዳሪዎችን ጥሎ ገብቶ ለሁለት ወራት ለዩኒቨርሲቲው እንጀራ አቅርቦ ዋጋ ጨምሩልኝ ወደሚል ድርድር ሊገባ ይችላል፡፡

በዚህ የተነሳ በአማካይ ከተቀመጠው ዋጋ አምስት በመቶ ከፍና ዝቅ ብሎ ዋጋ ከቀረበ፣ ጨረታው እንዲሰረዝ ዳግም እንዲካሄድ የሚያስገድድ አሠራር ፈጥረናል፡፡ ለምሳሌ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለኮንስትራክሽን ሥራ ጨረታ ወጣ፡፡ አማካይ ዋጋው ተብሎ የተቀመጠው እስከ 110 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ አንዱ ተጫራች ግን 159 ሚሊዮን አቀረበ፡፡ አንደኛው ደግሞ 59 ሚሊዮን አቀረበ፡፡ በማንኛውም ጨረታ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበውን መውሰድ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን እስከ 60 በመቶ ተጫራቾችን የምታወዳድረው በቴክኒክ ነው፡፡ ቴክኒኩን ደግሞ ሁለቱም እኩል አለፉ፡፡ ነገር ግን በ159 እና በ59 ሚሊዮን ብር መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ ሁለቱም ከአማካይ ዋጋ የሰፋ ልዩነት አላቸው፡፡ እኛ ጋ ይህ ነገር ሲመጣ ሌላ ጨረታ ይውጣ ብለን ውድቅ ነው ያደረግነው፡፡ ሌላ ጨረታ ወጥቶ ካልተሳካስ ከተባለ ግን መፍትሔው ጥሩ ሥራ ለሚሠሩ ተጫራቾች ሥራውን መስጠት ነው የሚሆነው፡፡ በገቡት ቃል መሠረት በተባለው ጊዜና በተቀመጠው በጀት ሥራን ጨርሰው የሚወጡ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች ሞልተዋል፡፡ ለእነሱ መስጠት በመንግሥት ላይ የሚጨምረው ምንም ጫና የለም፡፡ በሰዓቱ ጀምረው በሰዓቱ የሚጨርሱ ሊመሠገኑ የሚገባቸው ተቋራጮች አሉ፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ከአምስት እስከ አሥር ዓመት የዘገዩ ፕሮጀክቶችን አጥንቶ፣ መንግሥት ለእነዚህ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ መክፈሉን አረጋግጦ ነበር፡፡ ውል የገቡበት ሳይሆን በመዘግየታቸው ብቻ ያስወጡት ወጪ ነው፡፡ ይህ ብር እኮ ዛሬ የአገራችን ትልልቅ ክልሎች በጀት እንደ ማለት ነው፡፡ ምን ያህል ዋጋ አገሪቱ እንደከፈለች ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ያለ ዕቅድና ያለ በጀት ፕሮጀክት ለማከናወን የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣል፡፡ አንዳንዱም ደግሞ እንትን ዞን ላይ ይተግበር፣ እከሌ አካባቢ እየተባለ እየጮኸ ነው ተብሎ ብቻ ይላካል፡፡ ለሕዝብ ቃል ይገባል፣ በጀት የለውም፣ ጥናት የለውም፣ መቼ እንደሚጠናቀቅም ሆነ ውሉ አይታወቅም፣ ነገር ግን የመሠረት ድንጋይ ይቀመጣል፡፡ ድንጋዩ ለአሥር ዓመታት ባዶውን ይቀመጣል፡፡ ከዚያ አንድ ዞን በሙሉ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ይታመሳል፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱንም ወደ ሌላ ቀውስ ይወስዳል፡፡ ለዚህ ሲባል ፕሮጀክቶችን በተመለከተ አሁን ጥብቅ ጥንቃቄና ቁጥጥር እያደረግን ነው፡፡ ከኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ጋር በጣም ተቀራርበን እየሠራን ነው፡፡ በጣም ጥሩ የሠሩ ተቋራጮችን እያበረታታን ነው፡፡ ዋጋ ሰብሮ የሚገባና ሳይሠራ ዋጋ ጨምር የሚል አጭበርባሪ በሩ እየተዘጋበት ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ አዲስ ፋሽን እየጀመሩ ነው፡፡ የብር ዋጋ እየወረደ በመሆኑ በዶላር ውል ይገባልን የሚሉ መጥተዋል፡፡ ዶላር እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ብር ደግሞ በተቃራኒው ይወድቃል በሚል ትንበያ በዶላር ታስቦ ይከፈለን የሚሉ ብልጦች መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ሲመጡ ተቋሙን ይገጥሙት የነበሩ ችግሮች ምን ነበሩ?

አቶ ሐጂ፡- ዋናው ችግር ሥርዓት አለመዘርጋቱ ነው፡፡ ቢኖርም በነባሩ ወይም በማኑዋል የግዥ ሒደት ነው፡፡ ግዥ በማኑዋል ሲሆን ደግሞ በትዕዛዝ የሚፈጸሙ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ከኦዲት ጋር የተገናኙ ችግሮችም በተደጋጋሚ ያጋጥማሉ፡፡ እኔ ከመጣሁ የለወጥኩት ብዬ የማስበው ኦዲተሮች የትም ቢሄዱ፣ አንድም ብር ከማንም ሳይቀበሉ የኦዲት ሥራቸውን እንዲሠሩ ማድረግን ነው፡፡ የመንግሥት የውሎ አበል ሥርዓት በራሱ ጊዜ የሚሻሻል ቢሆንም፣ ነገር ግን አይበቃንም ብለው ኦዲተሮች ለሥራ በሄዱበት ቦታ ኦዲት ከሚያደርጉት አካል አበል የሚቀበሉ ከሆነ ሥራቸውን በሀቀኝነት ለመሥራት ይቸገራሉ፡፡ ኦዲተር ለሥራ ሲሰማራ ኦዲት የሚደረገው ተቋም አልጋ፣ ምግብ፣ መኪናና ሌላም ጥቅም ካመቻቸለት በየትኛው ሀቀኝነት ነው ሥራውን በትክክል ሊሠራ የሚችለው? ስለዚህ ኦዲተሮች ከማንም አበል እንዳይቀበሉ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህም ሆኖ ለፓርላማው በሚቀርቡ የኦዲት ሪፖርቶች ግን የኦዲት ጉድለት ችግሮች ሁሌም ተደጋግመው ነው የሚነሱት እኮ?

አቶ ሐጂ፡- ተሰብሳቢና ተከፋይ የሚባሉ የኦዲት አያያዞች ላይ ችግር ማጋጠሙ የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ከኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ተጠራቅመው የመጡ ያልተወራረዱ የኦዲት ጉድለቶች ጭምር መንግሥት እስኪሰርዛቸው ድረስ ተከማችተው ነበር፡፡ አበልም ይሁን ሌላ በሰነድ መቅረብ ያለበት ገንዘብና ንብረትን ሳያወራርድ አንድ ግለሰብ ቢሞት ወይ ደብዛው ቢጠፋ ተከማችቶ የመንግሥት ዕዳ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ለሥራ ሄጄ በአበል አንድ ወር ቆይቼ እንደተመለስኩ ሳላወራርድ ብሞት፣ እኔ የሞትኩበት ተቋም ተሰብሳቢ አለ እየተባለ ኦዲት ላይ ይጻፍለታል፡፡ ተቋም ለረዥም ጊዜ ይኖራል፣ ግለሰብ ግን በድንገት ቢሞትና ሒሳቡን ለማወራረድ የሚያስችል በቂ ሀብትና ንብረት ትቶ ባያልፍ የኦዲት ሥራን ያወሳስባል፡፡ ተሰብሳቢ ኦዲት እየተባለ ቁጭ ያለ ብዙ አለ፡፡ ችግር በየዘርፉ አለ፡፡ ነገር ግን ከራስ ጀምሮ ሀቀኛ መሆን ነው መፍትሔው፡፡ አበል ተቀበልክ ማለት ትክክለኛ የኦዲት ግኝት ለማምጣት መቸገር ያመጣል፡፡ አዲሱ ኤሌክትሮኒክ ግዥ ግን አበል የከፈለው ተቋም ጭምር ነው መክፈሉን በአኃዝ እንዲያረጋግጥ የሚያስገድደው፡፡ ለኦዲተር እከሌ ይህን ያህል አበል ከፈልኩ የሚለውን ሪፖርት አቅርቦ ነው ሒሳቡ የሚወራረድለት፡፡ ዲጂታል ስለሆነ እያንዳንዱ የመንግሥት ወጪና ገቢ በቀላሉ ይሰበሰባል፡፡ አሠራሩ ውጤታማ እንዲሆን አጋዥ ይፈልጋል፡፡ ሚዲያዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ ቢደግፈው፡፡ በተለይ በከፍተኛ አመራርነት ላይ ያሉ ቢያግዙት፡፡ ሚኒስትሮች፣ ኮሚሽነሮች፣ ዳይሬክተሮችና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ቢረዱት ነው የምንለው፡፡ ይህ አሠራር አዋጪ ነው፣ ለአገር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለው ቢይዙት ለማደግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አስገዳጅ በሆነ መንገድ ለመተግበር አቅዳችኋል?

አቶ ሐጂ፡- ያው ዞሮ ዞሮ ግዴታ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ መጀመርያ ግን ማሳየትና ጠቀሜታውን ማስገንዘብ አለብን፡፡ ዓምና ዘጠኝ ተቋማትን ያውም ለምነንና አባብለን የሙከራ ሥራ ጨረስን፡፡ ዘንድሮ 74 ተቋማት ላይ አስጀምረናል፡፡ ወደ 60 በሚሆኑት ላይ የተሳካ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የቀሩት አንዴ በማኑዋል ሌላ ጊዜ በዲጂታል ግዥ በማድረግ ገባ ወጣ እያሉ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ሥራው ሰፍቷል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁሉንም የመንግሥት ተቋም ወደ ማዳረሱ እንሄዳለን፡፡ አልገባም የሚለው በመገለል ብቻውን ይቀራል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር ግዥ ማከናወን አይደለም በጀት አይለቅለትም፡፡ ለምሳሌ አሁን ከዩኒቨርሲቲዎች ውጪ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች በገንዘብ ሚኒስቴር IFMIS ሥርዓት ነው በጀቱን የሚያገኙት፡፡ የመንግሥት ግዥም ቢሆን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በዘረጋነው ኢጂፒ (eGP) የግዴታ መካሄድ እንደሚጀምር ጥያቄ የለውም፡፡ በ60 አገሮች የማማከር ሥራ የሠራ አንድ ህንዳዊ አማካሪ እኛ ዘንድ መጥቶ በአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ወደ 73 ተቋማት እንደ ደረስን ስነግረው ተደነቀ፡፡ ሌላው ጋ እዚህ ደረጃ ለመድረስ 15/20 ዓመታት ይፈጃል ነው ያለው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር IFMIS በ2003 ዓ.ም. ነው የተጀመረው፡፡ ዛሬ 12 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ እኛ ዓምና ነው የጀመርነው፡፡ ነገር ግን በሚቀጥለው ዓመት IFMISን እናልፈዋለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደ IFMIS ያልገቡ ተቋማትን እኛ እያስገባን ነው፡፡ ሥራው በጣም እየፈጠነ መሆኑን ይህ አንድ ማሳያ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሥርዓቱን በሙሉ አቅም ለመተግበር በቴክኖሎጂም ሆነ በሰው ሀብት በኩል አስቻይ ሁኔታዎች አሉ?

አቶ ሐጂ፡- ቴክኖሎጂው አለ፡፡ ሰውም ቢሆን ማሠልጠን ነው፡፡ በየዓመቱ እስከ 150 ሺሕ ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲ ይወጣሉ፡፡ አሠራሩን እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ወጣቱ ከሠለጠነ ደግሞ ቴክኖሎጂው የራሱ በመሆኑ ለትግበራ አይከብድም፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ኮንፍረንሶች የጀመርነውም ለዚያ ሲባል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአጋር አካላትስ ሚና? ለምሳሌ እንደ የመረጃ መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ድጋፍ አስፈላጊ ነው?

አቶ ሐጂ፡- ልክ እንደ ዲጂታል ባንክ፣ ኢንሹራንስና ሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት ሁሉ ኢንሳ ለዚህ ሥራም ዋና መሠረት ነው፡፡ ከኢንሳ ጋር የጋራ ኮሚቴ አለን፡፡ የሳይበር ደኅንነቱን በሙሉ አስተማማኝ የሚያደርገው ኢንሳ ነው፡፡ የኢንሳን ይሁንታ ሳያገኝ ይህ ሥራ ዕውን አይሆንም፡፡ መላው የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሳተፍበት ትልቅ የግዥ ሥርዓት ዕውን የሆነውም ኢንሳን በመተማመን ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ተማምኖ የሚሸጥበትና የሚገዛበት ገበያ ከተበላሸማ ሥራው አይሳካም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለአገር ውስጥ ዕቃና አገልግሎት አቅራቢዎች በአዲሱ አሠራር የተለየ ቦታ ተሰጥቷል?

አቶ ሐጂ፡- ለአገር ውስጥ ተወዳዳሪ እስከ ሦስት በመቶ የተሻለ ዕድል እንዲሰጥ አስቀምጠናል፡፡ በማምረቻ ዘርፍ ለተሰማሩ ደግሞ እስከ 20 በመቶ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ግን ደግሞ ለአገር ውስጥ አምራቾችና አቅራቢዎች ተብሎ ገበያው ዝግ አይደረግም፡፡ ውድድር ለዕድገት መሠረት ነው፡፡ እስከ መቼ ገበያን ዘግተን እንዘልቃለን? የአገር ውስጥ ተወዳዳሪዎች ከውጭዎቹ ጋር አቅማቸውን ሲፈትሹ ነው ማደግ የሚችሉት፡፡ የተለየ ለሚባሉ ለአነስተኛና ለጥቃቅን ዘርፎች ማበረታቻ ሊደረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለአገር ቤት ቅድሚያ በሚል ዋጋም፣ ጥራትም ሆነ አገልግሎትም መስዋዕት የሚያደርግ ግዥ እንዲደረግ መፍቀድ ውድድርን ያቀጭጫል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...