አንበሳ ኢንሹራንስ አቶ አብርሃም መርሻን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በማጨት ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ጥያቄ ይሁንታ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡
አንበሳ ኢንሹራንስ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ በነበሩት ነጋሲ ዮሴፍ (ዶ/ር) ምትክ አዲስ ያጫቸውና ሹመታቸው በብሔራዊ ባንክ የፀደቀው አቶ አብርሃም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሥራቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጋሲ (ዶ/ር) ከለቀቁ በኋላ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እስኪመደብ ድረስ ኩባንያው በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲመራ ነበር፡፡
አዲሱ የአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም መርሻ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ ከኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራር ደረጃ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዳገለገሉ ታውቋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የንብ ኢንሹራንስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
የኢንሹራንስ ሙያቸውን በኢትዮጵያ መድን ድርጅት የጀመሩት አቶ አብርሃም፣ አሁን ከሚለቁበት ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከምሥረታው ጀምሮ ለ20 ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሲያገልገሉ መቆየታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ላለፉት ሦስት ደግሞ ዓመታት በንብ ኢንሹራንስ የኦፕሬሽንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል፡፡
አቶ አብርሃም የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ማኅበርንም በፕሬዚዳንት እንደመሩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ አንበሳ ኢንሹራንስ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ15 ዓመት የዘለቀ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ መድን ዘርፍ 464 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ በማግኘት በዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ከታክስ በፊት ብር 63.9 ሚሊዮን ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ ኩባንያ ነው።