Monday, February 26, 2024

ሙስና በአገር ላይ የደቀነው ሥጋትና የሚስተዋሉ ተቃርኖዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከመንግሥት ግዥና ሽያጭ ጨረታዎች ጋር፣ እንዲሁም ከመሠረተ ልማትና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ከ40 እስከ 50 በመቶ በጀት ለብክነት እንደሚጋለጥ አንድ የ2014 ዓ.ም. ጥናት ይጠቁማል፡፡ በ2014 ዓ.ም. አገሪቱ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድባ እንደነበር ለአብነት የሚያነሳው ጥናቱ፣ ይህ ማለት እስከ 250 ቢሊዮን ብር ለብክነት መዳረጉን ያስረዳል፡፡ ይህ መሰሉ ጥናት የተጋነነ ሊመስል ቢችልም፣ በሙስናና በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት እንደምታጣ ይነገራል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት የቀረበ አንድ ጥናት ደግሞ በኢትዮጵያ ብልሹ አሠራር፣ ሙስናና ምዝበራ ባይኖሩ ኖሮ አገሪቱ በምን ደረጃ ልታድግ እንደምትችል ይጠቅሳል፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ሥር የተቀመጠውን የሕፃናት ሞት የመቀነስ ግብ ለማሳካት 13 ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ የሙስና አንዱ መገለጫ የሆነው ሕገወጥ የገንዘብ ፍልሰት ባይኖር ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ይህን ግብ በዘጠኝ ዓመታት ማሳካት ትችል ነበር ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2011 ዓ.ም. የሕፃናት ሞት በ5.3 በመቶ እየቀነሰ ነበር፡፡ አገሪቱ በሕገወጥ የገንዘብ ፍልሰት ወንጀል ባትጠቃ ኖሮ፣ የሕፃናት ሞት ዓመታዊ ቅነሳ 7.58 በመቶ በሆነ አኃዝ የሚመዘገብ አገራዊ የልማት ስኬት ይሆን እንደነበር ነው የአፍሪካ ኅብረት በጥናቱ ያመለከተው፡፡

ሙስና በኢትዮጵያ የልማት እንቅፋት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ አገሪቱን ከድህነትና ከኋላቀርነት እንዳትላቀቅ ማድረጉም ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የችግሩን ስፋትም ሆነ ችግሩ የደቀነውን አገራዊ ሥጋት በተመለከተ ብዙም መግባባት አይታይም፡፡

ሙስና የሥርዓቱ አደጋ ነው የሚለው አባባል ተደጋግሞ ቢደመጥም፣ በምን ያህል ደረጃ ለሥርዓቱ ፈተና እንደሆነ ማስቀመጥ ላይ የሚያግባባ መረጃ ሲሰጥ አይታይም፡፡

በኅዳር ወር መግቢያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ሙስና የአገርን አንጡራ ሀብት በልቶ ባዶ የሚያስቀር ነው ብለው ነበር፡፡ ‹‹በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎችና ባለሀብቶች ከዋልጌ ባለሥልጣናት ጋር ሲገጥሙ፣ እንዲሁም ከእነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዙ ዜጎች ሲሠለፉ ሙስና የተባለው ነቀዝ አገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል፤›› በማለትም ተናግረው ነበር፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ሲቀጥሉም፣ ‹‹ሙስና አገርን ሊያፈርስ የሚችል የደኅንነት ሥጋት መሆኑን ያስመሰከሩ አገሮችን በዘመናችን ዓይተናል፤›› ብለዋል የአደንዛዥ ዕፅ፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድና የንግድ ማጭበርበር ሙሰኞች ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ እንደሚጠቀሙም ዘርዝረዋል፡፡ በዓለማችን የተጀመሩ ጦርነቶች እንዳይጠናቀቁ፣ ግጭቶች እንዳይበርዱ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሙሰኞች መሆናቸውንም ዓብይ (ዶ/ር) ጠንከር ባሉ ቃላቶች ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹ሙስና ዛሬ የአገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል፤›› ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ሁሉ አስገዳጅነት ብሔራዊ ኮሚቴ በማዋቀር የፀረ ሙስና ትግል ለማካሄድ መንግሥታቸው መቁረጡን ገልጸው ነበር፡፡

ብሔራዊ ኮሚቴው መቋቋሙን በተከተሉ ቀናት የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ብዙ ተስፋ ያሳደረ ይመስል ነበር፡፡ በየክልሎቹ ኮሚቴ የማዋቀር ዕርምጃም ሲካሄድ ሰነበተ፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥም በተለያዩ ባለሥልጣናት ላይ በተለይም ዝቅ ባሉ የመንግሥት የኃላፊነት እርከን ላይ ባሉ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ሲነገር ነበር፡፡ ይህ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሄዶ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችን ወደ ማካተት ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ ግን ነገሩ በዚያው የቆመ መስሏል፡፡

ይህ ጅምር የሙስና ትግል በተጀመረ በአንድ ወር ልዩነት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስደንጋጭ ንግግር ሲናገሩ ተሰማ፡፡ ታኅሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የወላይታ ሶዶ የዳቦ ፋብሪካ ለማስመረቅ የተገኙት ዓብይ (ዶ/ር) እጅግ ከፍተኛ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ነበር ስለሙስና ያነሱት፡፡ ‹‹ትናንትና ተሳስታችሁ፣ በስህተት ሰርቃችሁ ሀብት ያከማቻችሁ ሰዎች ካላችሁ መፍትሔው ቀላል ነው፡፡ ብዙ ዳቦ ፋብሪካ ስለምንፈልግ፣ ብዙ ትምህርት ቤት ስለምንፈልግ፣ ፋብሪካዎቹን ከሠራችሁ ሰላም ይመጣል፤›› በማለት መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ ግርምት የፈጠረ ነበር፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ ‹‹ስረቁ ግን ስትሰርቁ እንዳትያዙ፤›› ብለው መናገራቸውን በማስታወስ፣ በርካቶች የዓብይ (ዶ/ር) ንግግርንም ሌብነትን ከማበረታታት ጋር አገናኝተውታል፡፡ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ሲቋቋም ብዙ ማበረታቻና ድጋፍ ያሳዩ አንዳንድ ወገኖች፣ መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉ እየከበደው መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ማሳያ ለመሆኑ ሲያወሱ ሰንብተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ ለሚዲያ ባለሙያዎች ሙስናን በተመለከተ ሥልጠና የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ያነሱት ጉዳይም ይህንኑ ግምት የበለጠ የሚያጠናክር ነበር፡፡

‹‹በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ካሉ በርካታ የፀጥታ ችግሮች ጀርባ ሙስና አለ፤›› ሲሉ የተደመጡት ሚኒስትሩ የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ እንዲሁም ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው ሕገወጥ እንቅስቃሴ፣ አገሪቱን ለማያባራ ግጭት እየዳረጋትና በከባዱ እየፈተናት መሆኑን በሰፊው አስረድተዋል፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ተቋማትን መገንባትና ለአሠራር ምቹ ማድረግ ላይ መንግሥት ማተኮሩን ለገሰ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የመጠቀምን አስፈላጊነት የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ስለሙስናው ዓይነትና አድማስ ግን አከራካሪ ድምዳሜ ነበር ያስቀመጡት፡፡

‹‹በኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሙስና የለም፡፡ ስቴት ካፕቸር (State Capture) ተብሎ በሚገለጽበት ደረጃ ላይ የሙስና ችግር በኢትዮጵያ አይገኝም፤›› በማለት፣ ለሠልጣኝ የሚዲያ አካላት በጥቃቅን ሙስና (Petty Corruption) እንዲሁም በብልሹ አስተዳደር ችግሮች ላይ እንዲያተኩሩ ምክር ቢጤ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በየዕለቱ በየደረጃው ሕዝብን የሚያማርሩ እጅግ በርካታ የአገልግሎት ችግሮች ላይ ቢተኮር የተሻለ ነው፤›› ያሉት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ ሙስና (Grand Corruption) ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ብልሽቶችና አነስተኛ የሙስና ዓይነቶች ላይ እንዲተኮር የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሚኒስትር ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን ካልታሰረና ተጠያቂ ካልሆነ የፀረ ሙስና ትግል እየተደረገ አይደለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይፈጠር፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ የመንግሥታቸውን አቋም በግልጽ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ደግሞ በዚያው ሥልጠና ላይ ተገኝተው የነበሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር  ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ የበለጠ አጠናክረውታል፡፡ ‹‹ለመመርመር ጊዜ፣ ገንዘብና ብዙ አቅም ከሚጠይቁ፣ የደኅንነት ዋስትና አደጋን ከሚደቅኑ ትልልቅ ሙስናዎች  (Grand Corruption) ይልቅ፣ ሚዲያውም ሆነ ጋዜጠኞች በአነስተኛ ሙስና (Petty Corruption) ላይ ቢያተኩሩ አገሪቱ ብዙ ትጠቀማለች፤›› የሚል መልዕክት ነበር አቶ ፈቃዱ ያስተላለፉት፡፡

ከአንድ ወር በፊት ሙስና በአገር ደኅንነት ላይ እጅግ ከባድ አደጋ መደቀኑን ሲናገር የቆየው መንግሥት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል የአቋም ለውጥ ለምን አሳየ የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗል፡፡

የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፋይናንስና የሳይበርን ጨምሮ ሙስናን ለመታገያነት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የፍትሕና አስተዳደር ተቋማት ያሉት መንግሥት፣ እነዚህ ሁሉ እያሉ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ማዋቀሩ ለጉዳዩ የሰጠውን ክብደትና ትኩረት ማሳያ ነው ሲባል ነበር፡፡

በሙስና ላይ ማምረሩን ሲናገር የቆየው መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሬ አነስተኛ ሙስና ነው ለማለት የተገደደባቸውን ምክንያቶች፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናቱ ፍንጭ በመነሳት ከመገመት ውጪ የተጨበጠ ምክንያት ለማግኘት ከባድ ነው የሚመስለው፡፡

‹ተሳስቶም ይሁን የሰረቀ ዳቦ ቤት ይክፈት› የሚለው ገለጻም ሆነ፣ ‹ከብዙ የፀጥታ ችግሮች ጀርባ የሙስና ወንጀሎች አሉ› የሚለው ማብራሪያ የፀረ ሙስና ብሔራዊ  ኮሚቴ በተቋቋመ ማግሥት በአገሪቱ የተፈጠሩ ሁነቶችን ለመፈተሽ የሚጋብዙ ናቸው፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙንና አንዳንድ ዕርምጃ መወሰዱን ተከትሎ፣ በርካታ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በአገሪቱ አጋጥመዋል፡፡ በየትምህርት ቤቶቹ የደረሱ ግጭቶች፣ በየዩኒቨርሲቲዎቹ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ሌሎችም የፀጥታ ቀውሶች የፀረ ሙስና ዘመቻው የቀሰቀሳቸው ችግሮች ስለመሆናቸው ብዙ መላምቶች እያሰጡ ነው፡፡

አሁን መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ፍላጎቱም ሆነ ቁርጠኝነቱ ቢኖረው፣ ነገር ግን በተጨባጭ ሙሰኞቹን ተጠያቂ ለማድረግ አቅምና ጡንቻው እንዳነሰው የሚናገሩ እየተበራከቱ ነው፡፡ ሙስኞቹን መነካካት በተለይ ግዙፎችን የሙስና ሕዋሶች ለመበጣጠስ መሞከር የሚያስከትለውን የቀውስ አፀፋ ለመቋቋም መንግሥት በእጁጉ ተፈትኗል የሚለው መላምት በብዙዎች እየተነገረ ነው፡፡

መንግሥት ሙስና የሥርዓቱ አደጋ መሆኑን ለመረዳትም ሆነ በሙስና ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት በማሳየት ላይ ችግር የለበትም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሙሰኞቹን በተለይ ፈርጣማ ጡንቻ ያላቸው አሳ ነባሪዎቹን ለመዋጋት መንቀሳቀስ፣ ለሥርዓቱ የበለጠ ከባድ አደጋን የሚጋብዝ እንደሆነ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከደረሱ አጋጣሚዎች መንግሥት መመልከቱን የሚናገሩ እየበረከቱ ነው፡፡

በሌላም በኩል ጥቂት ይሁን እንጂ ሥርዓታዊ (መዋቅራዊ) ሙስናን ለፖለቲካ ትርፍ ማግኛ መንግሥት ይጠቀምበታል የሚል መላምት ሲሰጥም ይሰማል፡፡ መንግሥት በትንንሽ ሙስናና ሙሰኞች ላይ ይተኮር የሚለው፣ መዋቅራዊ የሆነው ሙስና ሳይቀረፍ ለሥልጣን ማራዘሚያ ለመገልገል በመፈለግ መሆኑን የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ ‹‹በኢትዮጵያ መዋቅራዊ ሙስና አለ ብለን እናምናለን፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ተቋም ገንብቶ አገር የመዝረፍ ዝንባሌ የለም የሚለውን ድምዳሜ መጋቢ ብሉይ ውድቅ ያደርጉታል፡፡

‹‹ሌላው ቀርቶ የእምነት ተቋማት ሳይቀሩ በሙስና ስለመዘፈቃቸው እኮ መንግሥት ሲነግረን ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ላይ ነበር ፖሊሶች፣ ዳኞችና ዓቃቤ ሕጎች በሌብነት ስለመዘፈቃቸው የተናገሩት፡፡ ለሙስናና ምዝበራ ያልዋለ ተቋም በኢትዮጵያ አለመኖሩን ራሱ መንግሥትም ያመነው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ እንደ ኢሕአፓ ግልጽና ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ መዋቅራዊ ሙስና በአገሪቱ አለ ነው የምንለው፤›› ሲሉም መጋቢ ብሉይ ይሞግታሉ፡፡

መንግሥት መዋቅራዊ ሙስና (State Capture) የለም፣ እንዲሁም ከከባድ የሙስና ወንጀሎች ይልቅ ሕዝብ ያስመረሩ ዝቅተኛ ሙስናዎችና የአስተዳደር ብልሽቶች ይተኮርባቸው ቢልም፣ ‹‹ሙስና የሥርዓቱ አደጋ ነው›› የሚለውን ድምዳሜ ደጋግሞ አስተጋብቶታል፡፡ በዚህ ደረጃ ዕውቅና የሰጠውንና የሥርዓት አደጋ ብሎ የበየነውን ይህን ችግር፣ በጀመረው ልክ በተጠናከረ ሁኔታ ለመዋጋት መንግሥት ጥረት ሲያደርግ አለመታየቱ ደግሞ ብዙ ጥያቄ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -