በመንግሥታዊ ተቋማትና በልማት ድርጅቶች ሥር የሚገኙ ይዞታዎች መረጃቸው በማዕከል ባለመደራጀቱ ሕገወጥ ሥራዎች ሲከናወንባቸው ቆይተዋል፡፡ መሬትን ለራሳቸው ጥቅም የሚያውሉ ግለሰቦች መበራከታቸውም በተደጋጋሚ መነገሩም አልቀረም፡፡ ይህን አገራዊ ችግር ለመቅረፍ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፖሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡
የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሳ መኰንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ የሆኑ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ይዞታዎቻቸው የሚመዘገብበት በማዕከል የተደራጀ የመረጃ ቋት እንዲኖር ኮርፖሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡
በማዕከላዊነት የሚደራጀው የመረጃ ቋትም በመንግሥት ሥር በሚገኙ ተቋማት ውስጥ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዳይካሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ ከስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የከተማ አስተዳደሩን ያማከለ ሥራ መሥራቱን፣ በከተማዋ ምን ያህል ይዞታዎች አሉ፣ ማነው የያዛቸው፣ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ የሚለውን የማጥራት ሥራ መለየቱን ወ/ሮ ሌንሳ አክለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሁለተኛው ዙር መረጃን የማጥራት ሥራ በሐረር፣ በድሬዳዋና በሶማሌ ክልል መጀመሩን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ በአጠቃላይ እስካሁን 8,683 የሚሆኑ ይዞታዎች መኖራቸውን ከዚህ ውስጥ የ917ቱን መረጃ የማጥራት ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
በተቋማት በኩል የሚሠሩ ሕገወጥ የመሬት ወረራዎችንን ለማስቆምም ያስችላል የተባለው መረጃን በቴክኖሎጂ ታግዞ የማደራጀትና የማጣራት ሥራ በጅግጅጋ ከተማ መጀመሩን ገልጸው፣ በቀጣይ በሌሎች የክልል ከተሞች ላይ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡
በተቋማት በኩል የተጣራ የመረጃ ቋት አለመኖር ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ወደ ተቋማት በመሄድና ሌሎች መረጃዎችን በመያዝ የማጥራት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
ከየተለያዩ ተቋማት መረጃ ሲሰባሰብ፣ ለምን መረጃው እንደሚሰበሰብና ካርታው እንደሚሠራ በተቋማት በኩል በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ፣ ለማስረዳት የሚወስደው ጊዜ ከፍተኛ መሆኑንና በሥራቸው ላይ ተግዳሮት እንደሆነም አክለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የፌደራል ተቋማት ይዞታዎችን መረጃ ማስተካከል፣ የለሙ፣ ያለሙና በመልማት ሒደት ላይ ያሉ ይዞታዎችን ማወቅና ያልለሙ ይዞታዎችን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ልማት ማስገባት መሆኑን ወ/ሮ ሌንሳ አስረድተዋል፡፡
የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ፣ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን በበኩላቸው፣ የመንግሥት ይዞታዎች የመሬት አጠቃቀምና የመሬት ምዝገባ ምን ይመስላል? ምን ያህል ተጠቅመውበታል የሚለውን አሠራር በካርታ የማመላከት ሥራ ተቋሙ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሶማሌ፣ በድሬዳዋና በሐረሪ ውስጥ የሚገኙ የ126 ተቋማት መረጃ መሰብሰቡን፣ መረጃውም የከተማ አስተዳደሩን ተቋማት አለማካተቱን ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ ተቋማት 2162 ሔክታር መሬት በካርታ መሸፈኑንና አብዛኞቹ ተቋማትም ያላቸውን መሬት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በሦስቱ ከተሞች የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በርካታ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ እስካሁንም ከ67 በላይ ተቋማት በመረጃ ቋት መያዝ እንደተቻለ አክለዋል፡፡
የስፔስ ሳይንሰና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አማካሪ ቱሉ በሻ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ተቋማቸው መረጃዎች ከተጠናቀሩ በኋላ ካርቶግራፊን በመጠቀም የመሬት አጠቃቀም ካርታዎች የሚመረቱ ይሆናል፡፡