Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአተገባበር መጣረስ የፈተነው የትምህርት ሥርዓት

የአተገባበር መጣረስ የፈተነው የትምህርት ሥርዓት

ቀን:

በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች በመስፋፋታቸው የተማሪ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፣ የትምህርት ጥራትና ብቁ ዜጋን የማፍራት ጉዳይ ዛሬም ክፍተት አለበት፡፡ ከትምህርት ሥርዓት እስከ ትግበራ፣ ከመማር ማስተማር ሒደቱ እስከ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና ዘርፉን ተብትበው የያዙ የተለያዩ ችግሮች የተማሪ ብቃትን ፈትነዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት፣ በሌሎች ተቋማትና በተማሪዎች መመረቂያ ጽሑፍ የተሠሩ ጥናቶችም የትምህርት ሥርዓቱ ብቃት ያለው ተማሪ ማፍራት እንዳልቻለ ሲጠቁሙ ከርመዋል፡፡ ችግሩን ይቀርፋል የተባለ ሥርዓተ ትምህርት ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ መተግበር የጀመረ ቢሆንም፣ የመማር ማስተማር ምኅዳሩ ዛሬም ከችግር አልፀዳም፡፡

የብቁ መምህራን እጥረት፣ ድንገተኛ የፖለቲካ አጀንዳዎች በትምህርቱ ላይ ጣልቃ መግባት፣ የግብዓት እጥረትና ሌሎችም የዘርፉ ችግሮች ሆነው ቀጥለዋል፡፡

- Advertisement -

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋምና በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ለስድስት ዓመታት ተሠርቶ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው በተማሪዎች የማንበብ ችሎታ ላይ አተኩሮ በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት፣ ችግሮችና መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነው ጥናትም የዘርፉን መሠረታዊ ችግሮች ይፋ አድርጓል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር በላይ ሐጎስ (ዶ/ር) የጥናቱ አስተባባሪ ናቸው፡፡

ተቋሙ ከሚያደርጋቸው የተለያዩ ጥናቶች አንዱ ‹‹በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓትን በማሻሻል የትምህርት ብቃትን ማረጋገጥ ይቻላል፤›› በሚል እ.ኤ.አ. በ2017 የተጀመረውና በታኅሣሥ 2022 የተጠናቀቀው የትምህርት ሥርዓቶችን ለማሻሻል ምርምር የሚሠራው የራይዝ (Research on Improving Systems of Education) ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡

የጥናቱ መነሻ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ትምህርት፣ ዕውቀትና ክህሎት ሳያገኙ የሚቀሩበት ምክንያት ምንድነው? የሚለው መሆኑን የጥናቱ አስተባባሪ ይናገራሉ፡፡

እንደ ዶ/ር በላይ አገላለጽ፣ ችግሩ ከትምህርት ሥርዓት ይመነጫል፡፡ ግብዓት ቢጎድል የመማር ሥርዓቱ ቢስተጓጎልም ይህ ትልቅ ጥያቄ አይደለም፡፡

ትምህርትን በተመለከተ ማኅበረሰቡ ለመንግሥት በሰጠው ሥልጣን ልክ መንግሥት እየሠራና ተጠያቂነቱን እየተወጣ ነው? መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ለሚመራው አካል (ትምህርት ሚኒስቴር) የትምህርት ጥራትን አረጋግጥልኝ ብሎ በሰጠው ኃላፊነትና ተጠያቂነት መጠን ትምህርትን የሚመራው አካል እየፈጸመ ነው? ይህ አካል ለትምህርት ቤትና ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚሠሩ አካላት ኃላፊነትና ተጠያቂነትን አስተላልፎ እየተተገበረ ነው? የሚሉት መሠረታዊና ያለምንም መስተጓጎል ሊተገበሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ይህ አንደኛው አካሄድ ሲሆን፣ ሌላው በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ግንኙነት ነው፡፡ የመንግሥትና የመንግሥት አስተዳደር፣ የአስተዳደርና የሠራተኞች ፖለቲካዊ ግንኙነትና የሕዝብ ድምፅ/ፍላጎት ተፈጻሚነት ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡

በትምህርት ሥርዓቱ የተሰጠው ትምህርትና የተገኘው ውጤት ተጣርሷል ወይ? የሚለው ሲታይም፣ ሕዝቡ የሚፈልገው ልጆቹ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ቢሆንም በታቃራኒው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በትምህርት ስርአቱ ውስጥ መጣረስ አለ፡፡ ለዚህም ከሁለተኛ ክፍል 68 በመቶ እንዲሁም ከሦስተኛ ክፍል 51 በመቶ ተማሪዎች ዜሮ አንባቢ ሆነው መገኘታቸው ማሳያ ነው፡፡ ጥናቱ ማንበብ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ መጻፍና ማስላትም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ራይዝ በ2014፣ በ2016፣ 2018 እንዲሁም በ2021 ካስጠናው ውስጥ የ2021 ውጤት በጣም የዘቀጠ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ኮቪድ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ ቢችልም ብቸኛ ሊሆን እንደማይችል የጥናቱ አስተባባሪ ይገልጻሉ፡፡

ተማሪዎቹ ሁለተኛ ክፍል ላይ 68 በመቶ፣ ሦስተኛ ክፍል ላይ 51 በመቶ ማንበብ የማይችሉ ቢሆንም፣ የትምህርት ሥርዓቱ ወደ አራተኛ ክፍል እንዲያልፉ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ሌላው የትምህርት ሥርዓት መጣረስ ማሳያ ነው፡፡

ተማሪዎች አጥርተው እንዲያልፉ፣ ዕውቀት እንዲጨብጡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ቢፈለግም፣ የትምህርት ሥርዓቱ የትምህርት ጥራትን አስጠብቃለሁ ቢልም፣ የትምህርት መሠረት በሚጣልባቸው በእዚህ የትምህርት ደረጃዎች ተማሪዎች ዕውቀት ሳይጨብጡ ከክፍል ክፍል እንዲሸጋሩ ተደርጓል፡፡ ይህ ሥርዓቱ እርስ በርሱ የማይጣጣም መሆኑን ያሳያል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰትም 8ኛና 12ኛ ክፍልን ሳይጨምር ሁሉም ተማሪ ወደሚቀጥለው ክፍል ተዛውሯል፡፡ ይህ ከትምህርት ሥርዓቱ የተጣረሰና ለትምህርት ብቃትና ጥራት ትኩረት ያልሰጠ ውሳኔ ነበር፡፡

የትምህርት ርዕሳነ መምህራን ከብቁ መምህራን ውስጥ በመምህራን ተመልምለውና ተመርጠው መቀመጥ ሲገባቸው በዚህ መልኩ አለመተግበሩም ለብቃት ቦታ እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡

የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ላይ የሚቀመጡ ኃላፊዎችም ከሙያ ውጭ የግብርና፣ የፋርማሲና የሌላ ምሩቃን እንዳሉበት ጥናቱ ሲሠራ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ነገር ግን በቦታው ላይ ኃላፊ ሆኖ መቀመጥ ያለበት መምህር ሆኖ ያለፈ ወይም በትምህርት አስተዳደር የተማረ ነው፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች እንዲያፈራ፣ ብቃት ያላቸው ሠራተኞችን መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የተለየ አካሄድ ለብቃት፣ ለመብቃትና ለመሻሻል ያለውን ዋጋ የሚሸረሽር ነው፡፡

የራይዝ አጠቃላይ ዕሳቤ ሥርዓቱ በራሱ የሚጣረስ ከሆነ ለማከም እንደማይቻል ነው፡፡ በተደጋጋሚ በትምህርት ዙሪያ ውይይት ሲደረግ ‹የምንሠራው የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ነው ነገር ግን ማምጣት አልቻልንም› ተብሎ ሲነገር የሚደመጠውም ሥርዓቱ ስለተጣረሰ ነው፡፡ 

ዶ/ር በላይ፣ ‹‹አዎ አሁንም አይመጣም፡፡ የትምህርት ጥራት የሚመጣው የትምህርት ሥርዓቱን ከላይ እስከ ታች ያሉ አካለት ተናበው ሲተገብሩትና ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፣ ግንባር ቀደም ሆነው ማነቃነቅ ሲችሉ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ለዚህ እንደ ምሳሌ ያነሱትም የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የተሰጠበትን አካሄድ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ ትምህርት ሚኒስቴርና ታች ድረስ ተነቃንቆ ነበር፡፡ አካሄዱን በመቀየርም ትልቅ ለውጥ መጥቶ በስኬት ተጠናቋል፡፡ ይህንን ያመጣው ከላይ እስከ ታች ተናቦ መሥራቱ ነው፡፡

ወደ መምህርነት ሲመጣም ማንም መምህር መሆን ይችላል የሚል አመለካከት ስህተት ነው፡፡ መምህር ለመሆን የመጀመርያው መሥፈርት ፍላጎት ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ቢያንስ አማካይ ውጤት ያለው መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን መጻፍ የማይችሉ፣ ፊደል የማይለዩ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ማን አደረገው ሲባል መልሱ ሥርዓቱ ነው፡፡ በመሆኑም መምህራንን መውቀስ ተገቢ አይደለም፡፡

እንደ ጥናቱ ብቃት የሌላቸው ተመዝነው ዝቅተኛ ውጤት ያመጡ መምህራን የሚወቀሱትም ሥርዓቱ ስለከተታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ሥርዓቱና መሥፈርቱ ተጣጥሞ መሄድ አለበት፡፡ ጥቃቅን ነገሮችን በማሟላት በመማር ማስተማር ሒደቱ ለውጥ ሊያመጣ ቢችልም ትልቅ አጀንዳ የሆነው የሥርዓት መጣረስ ካልታረመ ችግሩ ሊቀረፍም ሆነ ብቁ ተማሪ ለማፍራት አይቻልም፡፡

የትምህርት ሥርዓትን የፖለቲካ አጀንዳና ፖለቲካው ለትምህርት ሥርዓቱ ትልቅ ቦታ መስጠት አለበት ያሉት ዶ/ር በላይ፣ አገር የሚገነባው ብቃት ያለው ዜጋ ሲኖር፣ በሁሉም ዘርፍ ፖለቲካ ውስጥ የሚገባው ዜጋ ብቁ ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩትም ብቁ ሆነው አገርን ማሳደግ ሲችሉ በመሆኑ ከታች ጀምሮ የሚተገበረው የትምህርት ሥርዓት ብቃት ያለው ተማሪ ማውጣት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ላለፉት 80 ዓመታት የትምህርት ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል ጥናት የተደረገ መሆኑን በማስታወስም፣ ከ1933 ዓ.ም. ጀምሮ ኢሕአዴግ እስከሚገባ ድረስ (1983 ዓ.ም.) የተማሪ ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ አጀንዳ ትምህርት ቤት ማስፋፋት፣ ተማሪ በብዛት መቀበልና 25 በመቶ በጀት ለትምህርት ማዋል ጥሩ ጎን ቢሆንም በቂ አልነበረም፡፡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት የመጨረሻ ግብ ባለመሆኑ ከመጡ በኋላ ዕውቀት ይዘው መሄድ አለባቸው የሚለው ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በ2000 ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያላቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥር 11,490 ሲሆን፣ ይህ በ2021 ወደ 36,492 አድጓል፡፡ የመምህራን ቁጥርም ከ15,777 ወደ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ግቡ ቁጥር ላይ ማቆም የለበትም፡፡

መሆን ያለበት እያንዳንዱ ልጅ ትምህርት ቤት እስከመጣ ድረስ አጥርቶ ለዕድሜውና ለከፍሉ የሚጠበቀውን ብቃት ይዞ መሸጋገር አለበት፡፡ ልጆቹን እየተገፉ ክፍል ቢቆጥሩም ተጎዱ እንጂ ጠቃሚ ውጤት አላመጡም፡፡

ጥናቱ የሚያመላክተውም፣ የትምህርት ሥርዓቱ እርስ በርስ በተለይም በተልዕኮ መጣረስ ትልቁ ለትምህርት ማሽቆልቆል ምክንያት ነው፡፡ 68 በመቶ ማንበብ ለማይችሉት የሁለተኛ ክፍልና 51 በመቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ስለመኖራቸው ማንም ተጠያቂ የሚሆን የለም፡፡ አስተማሪ ሆነ ከላይ እስከ ታች ያለው የመማር ማስተማር ሒደቱ ተዋናይን ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር የለም፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ምን ማስተካከያ ይደረግ?

እንደ ዶ/ር በላይ፣ መጀመርያ ኃላፊነት መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመርያውን ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ እሳቸው ጥራት ያለው ትምህርት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላ ሪፖርት አልፈልግም ማለት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ከታች እስከ ላይ ያሉ አካላት ሌትና ቀን መትጋት ይጀምራሉ፡፡

ትዕዛዙ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጣ የትምህርት ዘርፉን የሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር ይህንኑ ያንፀባርቃል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ይተገብራሉ፡፡ ተማሪዎችም ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ያገኛሉ፡፡ ወላጆችም ትክክል አይደላችሁም ብለው ለመጠየቅ ዕድል ያገኛሉ፡፡

መንግሥት ለትምህርት ሚኒስቴር የሰጠሁህን ኃላፊነት ወደ ታች አውርደህ አሳየኝ ማለት አለበት፡፡ ይህን ያህል ተማሪ አለ፣ ይህን ያህል አልፏል፣ የሴቶችና ወንዶች ቁጥር ይህን ያህል ነው የሚሉና በቁጥር የታጀቡ ሪፖርቶች ቢያስፈልጉም ወሳኝ ስላልሆኑ ጥራት ላይ ያተኮረ ሪፖርት መቅረብም አለበት፡፡ ለዚህ ሥርዓቱ ተናቦ መሄድና ተጠያቂነትን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት ቁርጠኝነትም ያስፈልጋል፡፡ ቁርጠኝነቱ ደግሞ ከላይ እስከ ታች መሆን አለበት፡፡

ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉት ትምህርቶች መሠረት የሚጣልባቸው ናቸው፡፡ ተማሪዎች ማንበብ፣ መጻፍ፣ ማስላት የሚችሉበት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ይህንን ያልቻሉ ተማሪዎች ወደፊትም ብቁ ለመሆን ይቸግራቸዋል፡፡ በመሆኑም የመጀመርያዎቹ የትምህርት መቀበያ ዕድሜዎች ላይ ጠንካራ መሠረት መጣል አለበት፡፡ በዚህ ወቅት እንደ ዋዛ እየተገፋ የተማረ ተማሪ ብዙ እያወቀ አይሄድም፡፡ በመጀመርያዎቹ የመማሪያ ዕድሜዎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፣ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገቡ ዝቅተኛዎቹም እንደዚያው ይዘልቃሉ፡፡ በሕይወታቸው ላይም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቅድመ መደበኛ እስከ የመጀመርያዎቹ አራት ዓመታት ኢንቨስት ማድረግ ይገባል፡፡

የተማሪዎችን ችሎታ በየጊዜው መለካትም ያስፈልጋል፡፡ መለካት ሲቻል ችግሮችን እየፈቱ መሄድ ይቻላል፡፡ በዚህ በኩል ጥሩ ዕድገት አለ፡፡ መረጃውም የተገኘው ከትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ነገር ግን ለክተን ምን አገኘን? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ምን ለውጥ አመጣን? የሚለው መታየትና በቀጣይ ችግሮችን ለመቀነስ መሠራት አለበት፡፡

አሠራሮች አለመጣረሳቸውን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ ከላይ እስከ ታች ያሉ የትምህርቱ ዘርፍ አካላት ቋንቋቸውን አንድ አድርገው የልጆች ብቃት ማዳበር ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ ገንዘብ ሆነ የሰው ኃይል መመደብ ያለበት ለተማሪዎች ብቃት መሆን አለበት፡፡

መምህራንን ማገዝም ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል፡፡ ሥርዓቱ ከመምህራን ጎን መቆም አለበት፡፡ መምህራንን ማንቋሸሽ፣ ተፈትነው ወደቁ እያሉ ማጣጣል ሳይሆን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ መውቀስ ማቆም አለበት፡፡ ምክንያቱም መምህራን በራሳቸው ሳይሆን በሥርዓቱ ምክንያት ነው ክፍተት የተፈጠረባቸው፡፡ ሲስተሙ ከልክሎ ቢሆን እዚህ ችግር ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡

ብዙዎቹም የብቃት ሥልጠና ቢሰጣቸው የሚስተካከሉ ናቸው፡፡ አስተማሪዎችን ሁሌ ተከታትሎ ችግራቸው ምንድነው እንዴት ይቀረፍ? የሚለው ላይ መሠራት አለበት፡፡ እነሱን ማገዝ ማለት የትምህርት ብቃትን ማገዝ ነው፡፡

ከሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም ሥራ መሠራትም አለበት፡፡ ለምሳሌ ቆላና ደጋ ላይ ተመሳሳይ አሠራር አዋጭ አይሆንም፡፡ እንደየአካባቢ ተጨባጭ ሁኔታ ለማስማማት የሚችል የድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡

የተማሪዎች የማንበብ ክህሎት ማሽቆልቆልን የጠቆመው ጥናት፣ ለችግሩ መንስዔ ያለውን የሥርዓተ ትምህርት አተገባበር መጣረስ ሊስተካከል የሚችልበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡  ዶ/ር በላይ እንደሚሉት፣ ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ ጥናቱን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ለመፍትሔው መጠቀም ይቻላል፡፡ ትርጉም የሚሰጥና ለውጥ የሚያመጣ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ መሬት ማውረድ ያስፈልጋል፡፡

ከጥናቱ አካል አንዱ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለየቱ ነው የሚለው ነው፡፡ ትምህርት ነው ወይስ የአለቃ ትዕዛዝ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት? ይህ ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ለአለቃ ትዕዛዝ ነው፡፡ የዕለትና የደራሽ ጉዳይ ነው ቅድሚያ የሚያገኘው፡፡ ያልታሰበ ነገር መጥቶ ጊዜና ጉልበትን ይወስዳል፡፡ ይህ አንዱ የመጣረስ መገለጫ ነው፡፡ ድንገት ለሚመጡ ጉዳዮች የሚሠራ ሌላ አካል መኖር አለበት፡፡ ያልታሰበ አጀንዳ ይነሳና ያለውን የአሠራር ሥርዓት ይረብሸዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰዎች መቀያየርም የዘርፉ ፈተና ነው፡፡ ጥናቱ በተሠራበት ዓመታት ከርዕሰ መምህር፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ትምህርት ሚኒስቴር ብዙ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ተቀያይረዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ራይዝ ጥናቱን ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እንኳን አምስት ሚኒስትር ተፈራርቆበታል፡፡ ይህ የአጠቃላይ ሥርዓቱ ነፀብራቅ ነው፡፡

ሥርዓቱ እንዴት የተረጋጋ መሆን ይችላል?

እንደ ራይዝ ፕሮጀክት፣ የትምህርት ሥርዓቱ በቋሚ ጸሐፊ መመራት አለበት፡፡ የፖለቲካ ሹማምንቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናውን ሥራ የሚሠራ ግን በቋሚ ጸሐፊ (ሴክሬታሪ) የሚመራ አደረጃጀት ያስፈልጋል፡፡

ይህ በዕውቀት ላይ መሠረት አድርጎ የሚሰጥ ኃላፊነትና አሠራር ፖለቲካው የቱንም ያህል ቢቀያየር የሚቀያየር አይሆንም፡፡ በፓርቲ ሰዎች መቀያየር ምክንያት የትምህርት ሥርዓቱ መረጋጋት አልቻለም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሚኒስቴሮች በቋሚ ጸሐፊ ቢመሩ ይመከራል፡፡ ይህ ብዙ መበጣጠስንና ተከታታይነት ማጣትን ያስቀራል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በተማሪዎች የንባብ ክህሎት ማነስና መፍትሔ ዙሪያ ከክልልና ከተማ አስተዳድር አካላት ጋር መምከሩን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡

በሚኒስቴሩ የትምህርት ቋንቋዎች ልማት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ሐረጓ ማሞ፣ የተማሪዎች የንባብ ክህሎት ማነስ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተሄደበት ያለውን ርቀት እንደሚያስተጓጉልም ገልጸዋል፡፡

የንባብ ክህሎት እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ መሆኑንም ገልጸው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ራይዝ ጥናቱን ያካሄደው በስምንት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 168 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ በአማራ፣ ቤንሻንጉልና ጉሙዝ፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ (በሁለተኛው ዙር አልተካተተም) ሲዳማ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች የሚገኙ 9,000 ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...