Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተሽከርካሪዎችንና ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን ለማስወገድ ጨረታ ያወጡ የመንግሥት ተቋማት ሒደቱን እንዲያቋርጡ ታዘዙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ለአቅላጭ ፋብሪካዎች ያለ ቫት የሚሸጥበት አዲስ ዋጋ ወጥቷል

ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ለማስወገድ ጨረታ ያወጡ የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ የጨረታ ሒደቱን እንዲያቋርጡ ታዘዙ።

የጨረታ ሒደት የጀመሩትም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት በተቋማቸው የሚገኙ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ያለ ጨረታ ማዕድን ሚኒስቴር ለሚደለድላቸው የአገር ውስጥ ብረት አምራች ኢንዱስትሪዎች መንግሥት ባወጣው አዲስ ዋጋ እንዲሸጡ ታዘዋል።

በገንዘብና በማዕድን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተደረገው የዋጋ ማሻሻያ ከታኅሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተገበር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በጨረታ ሒደት ላይ የሚገኝ የየትኛውም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወይም የመንግሥት ተቋማት የጨረታ ሒደት ተቋርጦ አዲስ ሥራ ላይ እንዲውል በተወሰነው ማሻሻያ መሠረት ይከናወናል ተብሏል።

በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ በማዕድን ሚኒስቴር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ የማያገለግሉ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ለብረት አቅላጭ ኢንዱስትሪዎች የሚሸጡበት ዋጋ ተከልሶ የነበረ ሲሆን፣ ለብረት አምራቾች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚወስነው ዋጋና የማዕድን ሚኒስቴር በሚደለድለው የብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ኮታ መሠረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ቁርጥራጭ ብረቶቹን ሲወስዱ መቆየታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውሷል፡፡

ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎቹ የትራንስፖርትና የሌሎች ተያያዥ ወጪዎችን በተመለከተ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግላቸው ለማዕድን ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፣ ፋብሪካዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ጥሬ ዕቃ እንዲያገኙና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ጥያቄያቸውን መነሻ በማድረግ የዋጋና የሌሎች ወጪዎች ማሻሻያ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

በአዲሱ የዋጋ ማሻሻያ መሠረት ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በኪሎ 51.25 ብር የሚቀርቡበት ዋጋ በ39 ብር የተተካ ሲሆን፣ በውዳቂ ብረታ ብረትነት የሚወገዱ ተሽከርካሪዎችንና ማሽነሪዎች ደግሞ ይሸጡበት ከነበረው 51.25 ብር የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎባቸው በ39 ብር በኪሎ ይሸጣሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ቁርጥራጭ የሆኑ ስቲል ብረታ ብረቶችን በኪሎ 64 ብር እንዲያስረክቡ የተገለጸላቸው መሥሪያ ቤቶች በአዲሱ ማስተካከያ በ48 ብር ሲያስረክቡ፣ በኪሎ 51.75 ብር ሲሸጡ የቆዩትን የካስት አይረን ብረቶች ደግሞ በ39 እንዲሸጡ መወሰናቸው ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኪሎ 120 ብር ይሸጡ ተብሎ ዋጋ የወጣላቸው ቁርጥራጭ አልሙኒየሞች፣ ከታኅሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ90 ብር እንዲሸጡ ተወስኗል፡፡

ብረት አቅላጭ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውስጥ ከሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ቁርጥራጭ ብረቶችንና ማሽሪዎችን ሲገዙ፣ ከላይ በተተመነው ዋጋ መሠረት የሚገዙ ሲሆን፣ ከ100 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ከሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የሚገዙ ቁርጥራጭ ብረቶች የዋጋ ማሻሻያ እንደተጠበቀ ሆኖ ቁርጥራጭ ብረቶቹን ለመለየት፣ ለመቁረጥ፣ ለመሰብሰብ፣ ለማስጫን፣ እንዲሁም ለትራንስፖርት ከ0.009 ሳንቲም እስከ አምስት ብር ከሰማንያ ሳንቲም ብር ተቀናሽ እንደሚደረግላቸው ታውቋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ምንጮች ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ አገሪቱ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር እያወጣች የብረታ ብረት ውጤቶችን ከውጭ ትገዛለች። የመንግሥት ንብረትን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ገንዘብ ሚኒስቴር በመሆኑ ቁርጥ ዋጋ እያወጣ ለብረት ኢንዱስትሪዎች እንዲያስረክቡ እየተደረገ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያሉ 29 የብረት ኢንዱስትሪዎች የወዳደቁ ብረቶችን እንዲረከቡ ይደረጋል። ነገር ግን አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ነገሩን ባለመረዳት የወደቁትን ብረቶች ለመስጠት ፈቃደኛነት አይታይባቸውም ያሉት ምንጮች፣ መንግሥት አሁን ባለበት ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ብረት ከውጭ ለማስገባት አቅም ስለሌለው፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ አገልግሎት የማይሰጡ ብረታ ብረቶችን ለአገር ውስጥ ብረት አምራቾች የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው ቁርጥ ዋጋ እንዲሸጡ ተወስኗል።

በእነዚህ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኘው አገልግሎት የማይሰጡ ብረታ ብረቶችና ተሽከርካሪዎች፣ ለአገር ውስጥ ብረት አምራቾች ለሁለት ዓመት ግብዓት የሚበቃ እንደሆነም ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር በመንግሥት በኩል ቁርጥራጭ ብረትን በቀጥታ ግዥ እንዲሸጥ የተወሰደው ዕርምጃ የሚበረታታ መሆኑን ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የብረት ኢንዱስትሪዎቹ በተናጠል የመንግሥት ተቋማት በሚያወጧቸው ጨረታዎች በመሳተፍ በተበጣጠሰ መንገድ የሚያገኙትን ግብዓት፣ ተቀናጅቶ መቅረቡ ጥቅሙ በርካታ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች