Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የዋጋ ግሽበትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነጠላ አኃዝ መመለስ አይቻልም›› የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለረዥም ጊዜ ሲከተለው የነበረውን የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኃዝ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት የመሳካቱ ዕድል እየተመናመነ በመምጣቱ፣ የመንግሥትን ዕቅድ በድጋሚ ለመከለስ መገደዱ ታወቀ፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ባለሁለት አኃዝ ዋጋ ግሽበት ከመመዝገብ አልፎ፣ የዋጋ ግሽበት ላለፉት 12 ወራት ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ መቆየቱ የመንግሥት የነጠላ አኃዝ ዕቅድ እንዳይሳካ አድርጎታል፡፡

በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት፣ የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተጠቁሟል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት ፍቃዱ ድጋፌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዋጋ ግሽበትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በነጠላ አኃዝ ማድረግ የማይቻል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው በኅዳር ወር የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 35.1 ሲሆን፣ ይህም ባለፉት ስድስት ወራት ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነው፡፡ ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች በተለይም በትግራይ ክልል የታየው የዋጋ ግሽበት ከአንድ ሺሕ በመቶ በላይ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCAA) ጨምሮ፣ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተራድኦ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳን በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ጦርነት በሰላም መቋጨቱ የዋጋ ግሽበትን ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃና በአገር ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ከባቢ ሁኔታ፣ መንግሥት ጥብቅ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ እንዳይተገብር እንዳደረገው አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡  

ምክትል ገዥው እንደሚሉት፣ የብሔራዊ ባንክ የዚህ ዓመት ዕቅድ የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት ከፍ እንዳይል ማድረግ ሲሆን፣ በመካከለኛ ዘመን (ማለትም ከሦስት እስከ አራት ዓመት ውስጥ) ቁጥሩን ወደ ነጠላ አኃዝ ለማውረድ ታስቧል፡፡

በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ከተሞች ያለው የገበያ ሁኔታ እንደሚያሳየው፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች አሁንም ዋጋቸው መጨመሩን ቀጥሏል፡፡

ከውጭ የሚገቡ እንደ ዘይትና ስኳር ከመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦችና አልባሳት፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚመረቱ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች (ጤፍን ጨምሮ) ባለፉት ሁለት ወራት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ መሰል የዋጋ ግሽበት የሚከሰተው በአቅርቦት በኩል ባሉ ተግዳሮቶች የተነሳ ነው ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር አሁንም ድረስ ላለው የአቅርቦት ከፍተት ምክንያት መሆኑን አቶ ፍቃዱ ያወሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሌላኛው ለዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር በላይ ለመሆኑ እንደ ምክንያት በተደጋጋሚ የሚነሳ ነው፡፡ በተለይ ነጋዴዎች በተለምዶ ጥቁር ገበያ ተብሎ የሚጠራው የትይዩ ገበያው የውጭ ምንዛሪ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዋጋ መተመናቸው ግሽበቱን እንዳባባሰው አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በትይዩ (ጥቁር ገበያ) እና በባንኮች መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ገበያ ልዩነት ከ75 በመቶ በላይ ነው፡፡

ይህንን ልዩነት ለማጥበብ መንግሥት ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እስካለፈው  በጀት ዓመት መጨረሻ ለመተግበር አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ የመንግሥት የውጭ ምንዛሪ ክምችት በታሰበው ልክ ባለማደጉ ሊራዘም ችሏል፡፡

በዚህ ረገድ የተደረገ የፖሊሲ ለውጥ ካለ ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ፍቃዱ፣ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንዴት ይመራ የሚለው ቀጣዩ አገር በቀል ሪፎርም አጀንዳ ላይ እንደሚመለስ ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ እየተረቀቀ ያለው ሁለተኛው አገር በቀል ሪፎርም አጀንዳ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ እንደተናገሩት፣ ነፃ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የመከተሉ ጉዳይ የመንግሥት ዋነኛ ግብ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች