Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የግብይት ሥርዓቱ ከተደራጁ ስግብግቦች ይፅዳ!

በዓላት በደረሱ ቁጥር የሸማቾች ዋነኛ ሥጋት ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ስለሚሆን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ኃላፊነት የተሞላበት ግብይት እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት ይጠበቅበታል፡፡ የበዓል ሰሞን ገበያ በርካታ ሸማቾች የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚዘዋወርበት በመሆኑ፣ ነጋዴዎች ከብዛት የተሻለ ትርፍ ስለሚያገኙ አላስፈላጊ ከሆነ የዋጋ ጭማሪ መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ የበዓል ገበያን ከሚረብሹ እንከኖች መካከል ዋነኛው የደላላ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በደላሎችና በተባባሪዎቻቸው የሚሠራጨው የዶሮ፣ የበግ፣ የፍየልና የዕርድ ከብቶች ዋጋ የበዓሉን ድባብ ከመረበሹም በላይ፣ ሸማቾችና ነገዴዎች ተሳስበው ግብይት እንዳይፈጽሙ ያግዳቸዋል፡፡ መንግሥት የአቅርቦት ሰንሰለቱ በደላሎች ጣልቃ ገብነት ሳይታወክ ግብይት እንዲከናወን የቁጥጥር ኃላፊነቱን መወጣት ሲገባው፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ገበያው ውስጥ እጁን እያስገባ የበለጠ ትርምስ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ አለበት፡፡ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ሊኖር የሚችለው የመንግሥት፣ የሸማቾችና የነጋዴዎች መስተጋብር በአግባቡ ሲኖር ነው፡፡ ገበያው ከስግብግነት መፅዳት የሚችለው አንዱ ለሌላው ሲያስብ ነው፡፡

ጤነኛ የሚባል የግብይት ሥርዓት ዋነኛ ተዋናዮቹ ማለትም ሸማች፣ ነጋዴና መንግሥት እየተናበቡበት በሥርዓት ይካሄዳል፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት በሚገባ ካልተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ ይታወካል፡፡ በተለይ ኢኮኖሚው በነፃ የገበያ ሥርዓት ይመራበታል በሚባልበት አገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ ከታወከ፣ በሥርዓተ አልበኞች ለመወረሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ሦስቱ አካላት ካላቸው ሚናና ኃላፊነት አንፃር የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ነጋዴዎች ጤናማና ፍትሐዊ በሆነ ውድድር መፎካከር አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በስፋት የሚታየው አልጠግብ ባይ ነጋዴዎችና ደላሎች የመወዳደሪያ ሜዳውን መውረራቸው ነው፡፡ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ አከፋፋይነትና በቸርቻሪነት ሥራዎች ውስጥ የተሰማሩ የተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ የምርትና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዋጋ እንደፈለጉ ይወስናሉ፡፡ የአቅርቦትና የሥርጭት መስመሮችን ይዘጋሉ፡፡ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ ይቆልላሉ፡፡ ሰላማዊና ጤናማ መሆን የሚገባውን የውድድር ሜዳ በማጣበብ ሕገወጥነትን ያሰፍናሉ፡፡ እነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የግብይት ሥርዓቱን ከዘመናዊ አሠራር ጋር በማጣላት ሸማቾችን ይበዘብዛሉ፡፡

እነዚህ ኃይሎች ኋላቀሩ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ዘለው ከገቡ ሕገወጥ ደላሎች ጋር በመመሳጠር፣ ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ ደላላ ትልቁን ሚና የሚጫወትበት ይህ ሥርዓተ አልባ የግብይት ሜዳ፣ በተጨማሪም ሥውር የንግድ ተዋንያንን ያሳትፋል፡፡ የመንግሥት ግብርና ቀረጥ ያልተከፈለባቸው ሸቀጦችን ገበያ ውስጥ የሚያስገቡት ሥውር ተዋንያን የሚደገፉት በደላላ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሥርዓተ አልበኞች ሕግና ደንብ አክብረው በሚሠሩ ታታሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠራቸውም በላይ፣ የሕዝቡን ኑሮ እያናጉ ነው፡፡ የነፃ ገበያ ሥርዓት ትርጉሙ ተዛብቶ ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥ በስፋት እየታየ ነው፡፡ አልጠግብ ባዮች በምግብ ምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰው ሠራሽ ጭማሪዎች ሲያደርጉ፣ መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ዕቃዎች ከሸማቾች ማኅበራት ሳይቀር በሕገወጥ መንገድ እያወጡ በተጋነነ ትርፍ ሲሸጡ፣ በኔትወርክ የተሳሰሩ ስግብግቦች ምርቶችን ሲደብቁ፣ ባዕድ ነገሮችን ምርቶች ውስጥ ሲደባልቁና እጅግ በጣም አሳፋሪ የሆነ የሚዛን ማጭበርበር ወንጀል ሲፈጽሙ እንዴት ጤናማ የግብይት ሥርዓት ይኖራል?

በኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓቱን አንቀው ከያዙት ችግሮች መካከል አንደኛው የአቅርቦት እጥረት ነው፡፡ የአቅርቦት እጥረት አንድም የተለያዩ ምርቶችን በበቂ መጠን አለማምረት ወይም አለማቅረብ ሲሆን፣ ሌላው በበቂ መጠን ያሉ ምርቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ሸማቹ ዘንድ ማድረስ አለመቻል ነው፡፡ የምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን ገበያው በሚፈልገው መጠን ባለማምረት ወይም ከውጭ ገበያ ባለማግኘት ምክንያት፣ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲጋለጡ መንስዔ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን በምታህል ትልቅና በበርካታ ፀጋዎች የተሞላች አገር የምግብ ምርቶች አቅርቦት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ አብዛኛው ሕዝብ ኑሮውን የሚገፋው በችግር ተቆራምዶ ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ በቂ ምርት በሚኖርበት ወቅት ደግሞ ሕገወጦች የአቅርቦት ሰንሰለቱን ስለሚቆጣጠሩት፣ ገበያው ውስጥ ሰው ሠራሽ እጥረት እንዲፈጠር ተደርጎ ዋጋ ይቆለላል፡፡ ይህንን የተለመደ ሥርዓተ አልበኝነት ፈር ማስያዝ የሚገባው መንግሥት፣ ጊዜውን አላስፈላጊ በሆኑ ድርጊቶች ስለሚያሳልፍ ዕርምጃ መውሰድ ሲጀምር በጥናት ላይ ተመሥርቶ ባለመሆኑ ገበያውን ያተራምሰዋል፡፡

መንግሥት በዓላት ሲደርሱ የቁጥጥር ግብረ ኃይሎች መሥርቶ ሥራ መጀመሩን ሲያስታውቅ፣ ይህ ሥራው የበዓል ሰሞን ዘመቻ ሳይሆን በተደራጁ መዋቅሮቹ አማካይነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ዘንግቶ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ገበያው ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ነጋዴዎችን በዚህ ዋጋ ሽጡ ወይም ሌላ ተግባር አከናውኑ ብሎ ከማዋከብ ይልቅ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን የደላሎችን ጣልቃ ገብነት ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ያለ ምንም ከልካይ እንዳሻቸው የሚፈነጩ ሕገወጥ የገበያ ተዋንያንን በማስወገድ፣ ፍላጎትና አቅርቦት ተጣጥመው ግብይቱ ጤናማ ሆኖ እንዲከናወን መሥራት ግዴታው ነው፡፡ ሸማቾች አንድን ምርት ሊገዙ ሲወጡ ገበያው ውስጥ የተለያዩ ዋጋዎች የሚጠሩ ከሆነ፣ ግብይቱ እየተመራ ያለው በሥርዓተ አልበኞች እንደሆነ ማንም አይስተውም፡፡ ስለዚህ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ከሕገወጥ ደላሎችና ቢጤዎቻቸው ፀድቶ ነጋዴዎችና ሸማቾች በፍትሐዊ የግብይት ሥርዓት እንዲገናኙ፣ ከማንም በላይ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት መታወቅ አለበት፡፡ ለበዓል ሰሞን ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜው ሥራው ይሁን፡፡

ፍትሐዊና ጤናማ የግብይት ሥርዓት በሌለበት ዋናው ተጎጂ ሸማቾች ናቸው፡፡ በአገራችን ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራት ወይም ወኪሎች ስለሌሉ፣ ሸማቾች የአልጠግብ ባዮች ሰለባ ናቸው፡፡ በንግድ ማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግና ሥርዓት ጠብቀው ሸማቾችን የሚያገለግሉ ያሉትን ያህል፣ በስግብግብነት የሚመዘብሯቸው ሞልተዋል፡፡ ሸማቾች ገበያው ውስጥ ሲገቡ ለመብቶቻቸው የሚከራከሩ ወኪሎች ስለማይኖሩዋቸው ለብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ጥራታቸው ለተጓደሉ ምርቶች የተጋነነ ዋጋ ሲጠየቁ፣ በሚዛን ሲዘረፉና የተለያዩ እንግልቶች ሲደርሱባቸው እንቢተኛ ለመሆን አቅም የላቸውም፡፡ ይህንን ችግር ተረድቶ ከጎናቸው የሚቆም ስለሌለ የአልጠግብ ባዮች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ የተደራጁ ስግብግቦች በሚፈጥሩት ወከባ ምክንያት ስለማይረጋጉ የተጠየቁትን ሳይወዱ በግድ ይከፍላሉ፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ኋላቀር በመሆኑ መተማመኛ የላቸውም፡፡ ወቅታዊ የተብራራ መረጃ ስለማያገኙና ገበያውን ውዥንብር ስለሞላው የተጠየቁትን ከማድረግ ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት አቅማቸው የኮሰመነ ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር መራመድ ያቃተው የግብይት ሥርዓት በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም፡፡ ጤናማና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር የግብይት ሥርዓቱ ከተደራጁ ስግብግቦች ይፅዳ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአብዮቱ ያልተዘጉ ዶሴዎች

‹ዳኛው ማነው› ሒሳዊ ንባብ - ሐሳብና ምክንያታዊነት በዚያ ትውልድ...

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

በዚያን ሰሞን የሹክሹክታ ወሬ ደርቶ ነው የሰነበተው፡፡ የአገራችን ልጆች...

በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያ

‹‹ድንጋይ ላይ ሠርተን እንዴት ነው ውጤት እንድናመጣ የሚጠበቀው?›› የኦሊምፒክ አትሌቶች በደረጀ...

በአዲስ አበባ የታቀደ ጥቃት ማክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

በኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የተጠረጠሩ መያዛቸው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...