Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአማራ ክልል በዋግ ሕምራ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከ67 ሺሕ በላይ ዜጎች  ለከፋ...

በአማራ ክልል በዋግ ሕምራ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከ67 ሺሕ በላይ ዜጎች  ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው ተሰማ

ቀን:

በአበበ ፍቅር 

በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ በዋግ ሕምራ ልዩ ዞን በፃግብጅና አበርገሌ  ወረዳዎች ከ67,000 በላይ  ዜጎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን፣ የፃግብጂ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ወረዳዎቹ ካሁን በፊት በአማራ ክልል አስተዳደር ሥር የነበሩ ቢሆንም፣ የአገው ሸንጎ ኃይሎችና የሕወሓት ታጣቂዎች ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጣጥረዋቸዋል ሲሉ የፃግብጅ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ንጉሡ ደሳለኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፣ ታጣቂዎቹ እስካሁን ሁለቱን ወረዳዎች ለቀው እንዳልወጡና በዚህም ለማኅበረሰቡ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡

አካባቢው ወደ ነበረበት አስተዳደር መመለስ አለበት በሚል ለመንግሥት  በተደጋጋሚ  ጥያቄ  እንዳቀረቡ  የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ በክልሉ መንግሥት በኩል  በሰላም ስምምነቱ መሠረት ‹‹ችግሩን በውይይት ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጧል›› የሚል  ምላሽ  ከመስጠት  የዘለለ መፍትሔ  እስካሁን  አልተገኘም  ብለዋል፡፡

‹‹በዚህም በሁለቱ ወረዳዎች  የሚገኙ  ከ67 ሺሕ  በላይ  የሚሆኑ ዜጎች  በከፋ ረሃብና የጤና እክል ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን አካባቢው በሕወሓት ታጣቂዎች ሥር ቢሆንም፣ መንግሥት በከፋ ችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች ዕርዳታን ማድረስ አለበት የሚል ጥያቄን እንደ ወረዳ  ያቀረብን ቢሆንም፣ ዕርዳታው በታጣቂዎቹ እጅ ስለሚገባና ለኅብረተሰቡ በቀጥታ   መድረስ ስለማይችል፣ አሁን ምንም ዓይነት የመድኃኒትም ሆነ የምግብ ዕርዳታ  ማቅረብ  እንደማይቻል ነው በመንግሥት በኩል ምላሽ የተሰጠው፤››  ብለዋል፡፡

ለሁለት ዓመት በጦርነት ቀጣና ውስጥ የነበረው  የፃግብጂ  ወረዳ  በመድኃኒት  እጥረት ብቻ 232 ሰዎች ሕይወታቸውን  ያጡ  መሆናቸውን፣ ከወሊድና  ተያያዥ  ችግሮች ጋር  ተያይዞ  20  የሚደርሱ  እናቶች  መሞታቸውን  አቶ  ንጉሡ  ገልጸዋል፡፡ 48  ነፍሰጡሮች በኅብረተሰቡ  ትብብር  በቃሬዛ  ወደ  ሰቆጣ በመሄድ  የሕክምና  ዕርዳታ  በማግኘት በሰላም መውለዳቸውን አክለው ተናግረዋል፡፡ 

በሌላ በኩል በአበርገሌና በፃግብጅ ወረዳዎች ባሉ አዋሳኝ የትግራይ   አካባቢዎች ተመሳሳይ የፀጥታ ሁኔታ ባለበት በንድ ወገን በኩል ዕርዳታ እየደረሰ  እንደሆነ  ለማወቅ መቻሉን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ለተመሳሳይ ችግር ተመሳሳይ    መፍትሔ  ሊሰጥ  ይገባል  ብለዋል፡፡

 ከዚህ በተጨማሪ በነበረው ጦርነት በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ መሆኑንና በተፈጠረው ሰላም  ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ መሆናቸውን፣ በሁለቱ ወረዳዎች ግን ተመሳሳይ መፍትሔ  ባለመገኘቱ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ እንዳልተቻለ አቶ ንጉሡ ተናገረዋል፡፡

 በወለህ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች፣ በተለይም ከሦስተኛው ዙር ጦርነት በኋላ ምንም ዓይነት ድጋፍ    እንዳልተደረገላቸው የመጠለያ ጣቢያው አስተባባሪ ወ/ሪት ሸዋዬ በድሉ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

   ‹‹አሥር ቀበሌዎችን ወክዬ ቅሬታ ሰሚ ነኝ፤›› ያሉት ወ/ሪት ሸዋዬ፣ ባሉበት የመጠለያ ጣቢያ ከ5,000 በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸው፣ አሁን ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡

  በዚህም በርካታ ሰዎች በከፋ ረሃብ ውስጥ እንደሆኑና በቂ የሕክምና አቅርቦት ባለመኖሩ በፅኑ ሕመም ላይ እንደሚገኙ አስተባባሪዋ ተናግረዋል፡፡

 ችግሩ ለእናቶችና ሕፃናት በጣም የከፋ ሆኗል ያሉት ወ/ሪት ሸዋዬ ለአቅመ ደካሞችና በሕመም ላይ ያሉ ዜጎች ችግሩን መቋቋም አልቻሉም ብለዋል፡፡

  መጪው በዓል እንደ መሆኑ ምንም ነገር በሌለበት ሁኔታ በዓልን ማሳለፍ እጅግ የሚያስከፋ ነው ያሉት በመጠለያ ጣቢያው ከሦስት ለጆቻቸው ጋር የሚኖሩት     ወ/ሮ በላይነሽ ተሰማ ናችው፡፡

 መንግሥት በሌሎች አካባቢዎች እንዳደረገው አካባቢያቸውን ሰላም አድርጎ  ‹‹ወደ ቀዬአችን እንድንመለስ›› ቢያደርግ ሲሉ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡     

  ለችግሩ መስፋፋትና ዘላቂ መፍትሔ ማጣት እንደ ምክንያት ያነሱት የፃግብጅ  ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሡ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ  ድርጅቶች፣ እንዲሁም በባለሀብቶች አማካይነት ለተፈናቃዮች ተሰብስቦና ተከማችቶ  የነበረው የዕርዳታ እህልና ቁሳቁስ፣ በሦስተኛው ዙር በነበረው ጦርነት ሙሉ በሙሉ  በመዘረፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከሦስተኛው ዙር ጦርነት በኋላ መንግሥትም ሆነ ባለሀብቶች ሲያደርጉት የነበረውን ዕርዳታ በመቀነሳቸው፣ በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ዜጎች ለከፋ ችግር  መጋለጣቸውን አብራርተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን አፋጣኝ መፍትሔ በመፈለግ፣ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...