በአልጄሪያ አዘጋጅነት ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ውድድር ሊጀምር ጥቂት ቀናት ይቀሩታል፡፡ በሻምፒዮናው ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የአገር ውስጥ ልምምዱን አጠናቆ፣ ቀሪ ልምምዱን በሞሮኮ ለማድረግ ወደ ሥፍራው ያቀናል፡፡
ታኅሣሥ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ልምምዱን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ ከሚያደርገው የስምንት ቀናት ዝግጅት በዘለለ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ለቻን ሻምፒዮና የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ሞሮኮ ላይ የሚያደርገው የዋሊያዎቹ ስብስብ፣ በሁለት ቀናት ልዩነት የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ከሞሮኮ ጋር የሚያደርግ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ጨዋታውን ታኅሣሥ 29፣ ሁለተኛው ጨዋታውን ከሁለት ቀናት በኋላ ጥር 1 ቀን ያደርጋል፡፡
በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክና ሊቢያ ጋር የተደለደለው በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 26 ተጫዋቾች በመያዝ በአልጀሪያው ሻምፒዮና ላይ ይካፈላል፡፡
ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአልጄሪያ አራት ከተሞች የሚከናወነው የቻን ሻምፒዮና ቀድሞ የወጣው መርሐ ግብር ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት መጀመሪያ ይፋ በሆነው መርሐ ግብር መሠረት፣ በመክፈቻው ዕለት ሊደረግ ታስቦ የነበረው የኢትዮጵያና የሞዛምፒክ ጨዋታ ወደ ጥር 6 ቀን መዘዋወሩ ተገልጿል፡፡ በመክፈቻው ዕለት አዘጋጇ አልጀሪያ ከሊቢያ በሚያደርጉት ብቸኛ ጨዋታ ሻምፒዮናው በይፋ ይጀምራል፡፡