Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየጃንሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናና በመወዳደሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተነ ያለው አትሌቲክስ

የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናና በመወዳደሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተነ ያለው አትሌቲክስ

ቀን:

አራት አሠርታት የሞላው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ 40ኛ ሻምፒዮናውን እሑድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በሱሉልታ ተከናውኗል። በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች ተካፋይ መሆን ችለዋል። በነፋሻማው አየር ንብረት የተካሄደው ሻምፒዮናው በ6፣ በ8 እና በ10 ኪሎ ሜትር ርቀቶች ላይ የክለብ፣ የክልል፣ የተቋማትና የግል አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ፡፡

በሻምፒዮናው በኦሊምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና፣ በአኅጉርና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመካፈል ልምድ ያካበቱ አትሌቶች ተሳትፈውበታል። በሱሉልታ ጃንሜዳ ውድድር በወንዶች የኦሊምፒክ የ10 ሺሕ ሜትር ባለ ድሉ ሰለሞን ባረጋ፣ የዶሃ ዓለም የ5,000 ሜትር ሻምፒዮናው ሙክታር እድሪስ፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስኬትን መጎናፀፍ የቻለው በሪሁ አረጋዊ ተካፍለውበታል፡፡

በሴቶች የዓለም የረዥም ርቀት ክብረ ወሰን ባለቤትና የ10 ሺሕ ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ባለድሏ ለተሰንበት ግደይ፣ መቅደስ አበበና ፅጌ ገብረ ሰላማ የመሳሰሉ አዋቂ አትሌቶች ደምቀውበት ውለዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ8 ኪሎ ሜትር፣ 6 ኪሎ ሜትርና በድብልቅ ሪሊ በሁለቱም ፆታ በተለያዩ አኅጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ ያካበቱ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር አድርገዋል፡፡ በተለይ በአዋቂ ሴቶችና በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነበር፡፡

በዚህም በሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ለተሰንበት ግደይ ከትራንስ ኢትዮጵያ 32፡21.55 አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ጌጤ ዓለማየሁ ከኦሮሚያ ክልል 35፡40.87 በመግባት ሁለተኛ እንዲሁም መቅደስ አበበ ከአማራ ክልል 35፡46.06 ሦስተኛ ስትወጣ፣ ጽጌ ገብረ ሰላማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ፎቴን ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ውዴ ከፋለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ ስድስተኛ ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በወንዶች 10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች በሪሁ አረጋዊ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 30፡44.20 በመግባት አንደኛ፣ ታደሰ ወርቁ ከኤሌክትሪክ 30፡53.09 ሁለተኛ፣ ጌታነህ ሞላ ከመቻል 30፡54.43 ሦስተኛ፣ ሞገስ ጥዑማይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አራተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ጭምዴሳ ደበሌ ከኦሮሚያ ክልል አምስተኛ እንዲሁም ኃይለ ማሪያም አማረ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ በአውስትራሊያ ኢትዮጵያን መወከላቸውን ያረጋገጡ አትሌቶች ናቸው፡፡

በሁሉም ርቀቶች ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች በአውስትራሊያ ባቱረስት ከተማ ለሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ይካፈላሉ፡፡

አውስትራሊያ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታስተናግዳለች። በኮቪድ-19 ወረርሽኝና አውስትራሊያ የጉዞ ገደቦች ምክንያት ሻምፒዮናው ለሁለት ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል፡፡

በመካከለኛና በረዥም ርቀት ላይ በመፎካከር የሚታወቁት የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ከ1981 እስከ 2017 መካከል የተደረጉትን የአገር አቋራጭ ውድድሮች በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

በወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ኬንያ ከ1986 እስከ 2013 ባደረጉት ተሳትፎ ለ18 ዓመታት ውድድሩን በበላይነት በማሸነፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሌለው ስኬት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ በሌሎች ርቀቶች ላይ ሁለቱ አገሮች በተፎካካሪነት እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

የጃንሜዳ ሻምፒዮናው ለበርካታ አትሌቶችም የውድድር አማራጭ ከመሆኑም በላይ፣ በተለይ ለዘመኑ የዓለም አቀፍ የጎዳና ሩጫ ራስን መፈተሻ ውድድር መሆን እንደቻለ ተገልጿል።

በተለይ በርካታ አትሌቶች የዕለት ተዕለት ልምምድ ማዘውተሪያ ሥፍራ በሆነችው ሱሉልታ ላይ ሻምፒዮናው መከናወን መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል። በአንፃሩ በሻምፒዮናው ወቅት በርካታ አትሌቶች ውደድሩን አቋርጠው ሲወጡ የተስተዋለ ሲሆን፣ በዕለቱ የነበረው ነፋሻማ አየርና የመሮጫው ሥፍራ አመቺ አለመሆን እንደምክንያት ተጠቅሷል።

ዓመታዊው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለዘመናት በጃንሜዳ መከናወኑ ቢታወቅም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥፍራው የተለያዩ ኩነቶችን እያስተናገደ በመምጣቱና ሥፍራው ለውድድር አመቺ ባለመሆኑ፣ ሻምፒዮናውን ወደ ሰሉልታ ለመውሰድ መገደዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣ ለጊዜያዊነት የአትክልት ተራ ሆኖ ማገልገሉን ተከትሎ፣ ዓመታዊ ውድድር ማድረግ አለመቻሉን አቶ ዮሐንስ ያብራራሉ፡፡ ሥፍራው ለአትክልት ገበያ እንዲውል ከተወሰነ በኋላ፣ በመሮጫ ሥፍራው ላይ የተደፋው ገረጋንቲ አትሌቶችን እንዳሻቸው እንዲሮጡ አለማስቻሉና የሚመለከተው አካል ሥፍራውን ለውድድር አመቺ እንዲሆን አለመደረጉን ያነሳሉ፡፡

ሥፍራው 39ኛውን የጃንሜዳ ውድድር ማስተናገድ ቢችልም፣ በርካታ አትሌቶችን ለጉዳት መዳረጉና የዓለም አትሌቲክስ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ለማሰናዳት ከሚያስችለው መሥፈርት ጋር በመጣረሱ ውድድሩን ወደ ሱሉልታ ለመወሰድ ገፊ ምክንያት እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከዚህም ባሻገር የጃንሜዳ ዙሪያ የተለያዩ ግንባታዎች እየተከናወኑ በመሆኑና የሥፍራው የባለቤትነት ጥያቄ በአዲስ አበባ ስፖርት ቢሮና በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል መውደቁ መፍትሔ ማጣቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዓለም አትሌቲክስ የሚያወጣውን የውድድር መርሐ ግብር ተከትሎ የአገር ውስጥ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮችን ለማድረግ በማዘውተሪያ ሥፍራ ዕጦት መመታቱን እንዲሁም አማራጮችን ማጣቱን ሲናገር ሰንብቷል። ውድድር ለማሰናዳትም ሆነ ልምምድ ለማድረግ የመሮጫ ትራኮች ከመጥፋታቸውም በላይ የረዥም ርቀት ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉ አትሌቶች ጭምር መቸገራቸው ሲነገር ከርሟል፡፡

በተለይ የማራቶን ልምምዳቸውን በአዲስ አበባ መውጫ ጎዳናዎች ላይ ከተሽከርካሪዎች ጋር እየተጋፉ ልምምድ ማድረጋቸው መዘውተሩን ተከትሎ፣ አትሌቶች ለመኪና አደጋ እየተዳረጉ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።

ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ስታዲየም በርካታ ሻምፒዮናዎችን ለማስተናገድ፣ እንዲሁም አትሌቶች በፈለጉት ሰዓት ልምምድ የሚያደርጉበት ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ስታዲየሙ ዕድሳት ላይ በመሆኑና ዕድሳቱ በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ በርካታ አትሌቶች ልምምዳቸውን ክፍያ እየፈጸሙ ለማከናወን ተገደዋል፡፡

የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርቡ ዕድሳቱ ተጠናቆ ለውድድር ክፍት እንደሚሆን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን፣ ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ይፈታዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...