Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ለተቸገሩ ሕፃናት የደረሰው ድርጅት የገጠመው ፈተና

አባቶቻቸው የጠላትን ወረራ ሲከላከሉ ለተሰዉባቸው ልጆች የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሕፃናት አምባ በእንክብካቤ አሳድጎና አስተምሮ ለቁም ነገር እንዳበቃቸው የትናንት ትዝታ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የቀድሞ ሠራዊትን እና በአምባ ውስጥ ያሉ ሕፃናት እንዲበተኑና አምባውም አገልግሎቱን እንዲያቆም ማድረጉም ይታወሳል፡፡ የተበተኑ ሕፃናትም ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለውና አድገው የራሳቸውን ኑሮ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በትምህርት ላይ ያተኮረው ‹‹አምባ ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማኅበር››ን አቋቁመው ወደ ሥራ ከገቡም ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ አቶ ይታገሡ ጌትነት የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምባ ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማኅበርን ለማቋቋም ያነሳሳችሁ ምክንያት ምንድነው? በየትኛው የትምህርት ደረጃ ላይ ነው ማኅበሩ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው?

አቶ ይታገሡ፡- ማኅበሩን ለማቋቋም ያነሳሳን ዋናው ምክንያት ሕፃናት አምባ በቆየንባቸው ዓመታት ውስጥ እያለበሰ፣ እየመገበና እያስተማረ ያሳደገንና ለቁም ነገር ያበቃንን ማኅበረሰብና አገር ውለታ ለመክፈል ነው፡፡ በትምህርት ላይ ትኩረት ያደረግንበትም ምክንያት እንደ አልባሳትና ምግብ ጊዜያዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ ትምህርት ነገንም ይሠራል ከሚል እምነት ተነስተንም ማኅበሩ ትምህርት ላይ የበለጠ እንዲሠራ አድርገናል፡፡ አምባ ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማኅበር በ2001 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ በ2002 ዓ.ም. ደግሞ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጠው፡፡ ማኅበሩ በትምህርት ላይ ያለው የትኩረት አቅጣጫ በጣም ከተቸገሩ ቤተሰብ ተወልደው ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ ነገር ግን በምንም ዓይነት መንገድ የትምህርት ዕድል ያላገኙ ሕፃናት ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማስተማሩን ሥራ የትነው የጀመራችሁት?

አቶ ይታገሡ፡- የማስተማሩን ሥራ የጀመርነው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አንቆርጫ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በዚህም የመጀመርያውን ሥራ የጀመርነው አንዲት ሁለት በሁለት በሆነች ጠባብ ቤት ውስጥ 80 ሕፃናትን ተቀብለን ፊደል በነፃ በማስቆጠር ነው፡፡ ለቤቱም በወር 300 ብር በዓመት ደግሞ 3,600 ብር ኪራይ እንከፍል ነበር፡፡ ሕፃናቱ ፊደል መቁጠር ብቻ ሳይሆን ልብስ፣ ለትምህርት የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች፣ ቁርስና ምሳ በነፃ ይሰጣቸው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በዚሁ ቤት ውስጥ ተወስናችሁ ቀራችሁ ወይስ ሌላ አማራጭ ቤት ፈልጋችሁ ተዛወራችሁ?

አቶ ይታገሡ፡- የሕፃናቱ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ቤቱም ለመማር ማስተማር ሥራ ብቁ ባለመሆኑ በአቅራቢያው በሚገኘውና አምስት ክፍሎች ያሉት ሌላ ቤት ውስጥ ተዛውረን ገባን፡፡ የሕፃናቱም ቁጥር ወደ 120 ከፍ አለ፡፡ ይህም በመሆኑ ፊደል ከማስቆጠር ተላቅቀን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አቋቋምን፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ ለሰባት ዓመታት ያህል ቆየን፡፡ የሕፃናቱም ብዛት ከ200 በላይ ሆነ፡፡ ከእነዚህም መካከል 20 ከመቶ ያህሉ አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርቱን የሚከታተሉ ሕፃናትም በጣም ችግረኛ ከሆኑ ቤተሰብ የመጡ ናቸው፡፡ ትምህርት ብቻ ሳይሆን እንደ መጀመርያዎቹ ሕፃናት ቁርስና ምሳ ያገኛሉ፡፡ አልባሳትና የትምህርት መገልገያ መሣሪያዎችም በነፃ እየተሰጣቸው ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለቤት ኪራይ በየዓመቱ 240,000 ብር እንከፍል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን የምትሸፈኑበት ምን ዓይነት የገቢ ምንጭ ቢኖራችሁ ነው?

አቶ ይታገሡ፡- ፊደል የማስቆጠር ሥራ ገና እንደጀመርን አዲስ አበባ የሚገኙ ልዩ ልዩ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያደርጉልን ጠይቀን ነበር፡፡ በዚህም የጣሊያን ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር እንደሚሰጠን ቃል ገባልን፡፡ የተለገሠውንም ዕቃ እኛ ዘንድ ይዘው የመጡት ከጣሊያን በየሁለት ዓመቱ እየመጡ በጣሊያን ትምህርት ቤት በኮንትራት የሚያስተምሩ ጣሊያናውያን መምህራን ነበሩ፡፡ መምህራኑም ያለንበትን ሁኔታና ሕፃናቱም የሚማሩበትን ቤት ዓይተው በጣም አዘኑ፡፡ ከዚህ የተሻለ ሌላ ቤት ፈልጋችሁ ግቡ፣ ኪራዩንም እኛ እንከፍላለን ብለው በገቡልን ቃል መሠረት አሁን አለንበት ቤት ውስጥ ተከራይተን ለመግባት በቃን፡፡ በቃላቸውም መሠረት የቤት ኪራዩን ለሰባት ዓመታት ያህል ሲከፍሉልን ቆዩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለትምህርት የምትቀበሏቸው ሕፃናት በጣም ችግረኛ ከሆኑ ቤተሰብ የመጡ ለመሆናቸው ማረጋገጫችሁ ምንድነው?

አቶ ይታገሡ፡- ትምህርት ማስተማር የጀመርነው በቅድሚያ ከበጎ አድራጎት ማኅበራትና ድርጅቶች ኤጀንሲና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ጋር ስምምነት ከተፈራረምንና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሕጋዊ ዕውቅና ካገኘን በኋላ ነው፡፡ ሕፃናቱን ከችግረኛ ቤተሰብ መርጦ የሚያቀርብልን የወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ሲሆን፣ እኛ ደግሞ በእያንዳንዱ ሕፃን ቤት እየተዘዋወርንና በአካል እየተገኘን የቤተሰቡን ሁኔታ እናጣራለን፡፡ በዚህ መልክ ተጣርተው የመጡትን እየተቀበልን የትምህርቱ ተቋዳሽ እናደርጋለን፡፡ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን የተከታተሉት የመጀመርያዎቹ ሕፃናት በአሁኑ ጊዜ የመጀመርያ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኪራይ ነፃ የሆነ ቤት አግኝታችሁ የመማር ማስተማሩን ሥራ በተመቻቸ መልኩ እያከናወናችሁ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

አቶ ይታገሡ፡- አምስት ክፍሎች ባሉት ቤት ውስጥ ለአሥር ዓመታት ከሠራን በኋላ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ትምህርት ቤታችን ጎብኝተው ነበር፡፡ ያለንበት ሁኔታ ምቹ አለመሆኑን በመገንዘብ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ቤት ተዛውረን እንድንሠራ የቃል ትዕዛዝ ሰጡልን፡፡ ይህም ቤት ሰባት ክፍሎችና አንድ ሰፊ አዳራሽ እንዲሁም ሰፊ ግቢ አለው፡፡ ዙሪያውም በቀጭን ሽቦ ታጥሮ ያለምንም ሥራ ለስምንት ዓመታት ያህል ተዘግቶ ነበር፡፡ ባለንብረቱም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ቤቱን እንድንገለገልበት ከንቲባው ለባለሥልጣኑ የሰጡት የቃል ትዕዛዝ ነበር፡፡ እኛም በትዕዛዙ መሠረት በ2012 ዓ.ም. ገብተን የመማር ማስተማሩን ሥራ ተያያዝነው፡፡ አሁን ላይ ባለሥልጣኑ ቤቱን ለቅቀን እንድንወጣ ጠይቆናል፡፡ በዚህም በድንጋጤ ተውጠናል፡፡ ምክንያቱም ሕፃናቱ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፡፡ ድጋፍና ዕርዳታ በማጣትም አልባሌ ቦታ ይውላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሕፃናቱ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት እንዲያገኙ አድርጋችኋል፡፡ ይህም አንድ ጠንካራ ሥራ ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ የሕፃናቱ ወላጆችን ከድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ያደረጋችሁት ጥረት ይኖር ይሆን?

አቶ ይታገሡ፡- የሕፃናቱ እናቶች አንድም በልመና አንድም ማገዶ እየለቀሙና እየሸጡ በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን፣ ልጆቻቸውንና በአጠቃላይ ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩና እየረዱ ናቸው፡፡ ከዚህ ዓይነት ችግር ተላቀው ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ አመቻችተናል፡፡ በፀጉር ሥራ፣ በምግብ፣ በባልትና በልዩ ልዩና ጥቃቅን ሙያዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ እናቶችም በቀሰሙት ሥልጠና ተጠቅመው የራሳቸውን የገቢ ምንጭ በመፍጠር ከችግራቸው ለመላቀቅ የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥትና ከማኅበረሰቡ ምን ዓይነት ድጋፍ ትፈልጋላችሁ?

አቶ ይታገሡ፡- በቃል ትዕዛዝ ብቻ ስንገለገልበት የቆየነውን ቤት እንድንለቅ ተጠይቀናል፡፡ በዚህም የተነሳ የማንወጣው ችግር ውስጥ ገብተናል፡፡ ከችግረኛ ቤተሰብ የወጡና እያስተማርናቸውና እየተንከባከብናቸው ያሉት ሕፃናትም ዕጣ ፈንታ ያሳስበናል፡፡ በአካባቢያቸው ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት ስለሌለ ለከፋ ችግር ይዳረጋሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ለጎዳና እንዳይዳረጉ እንሠጋለን፡፡ የእኛም ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ችግር ለመላቀቅ ማኅበረሰቡ፣ መንግሥት፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም ለወገን ተቆርቋሪ የሆኑ ግለሰቦች ድጋፍና ዕርዳታ እንዲያደርጉልን እንማፀናለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...