በእንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)
ከሰሞኑ አዲስ አበባ በመገናኛ ብዙኃን በፖለቲከኞች፣ በመንግሥት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳ ብትሆንም ከአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ የባለቤትነት ወይም እኔ ላስተዳድራት ጥያቄ ደርግ ከወደቀበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ አንዳንድ ጊዜ በግላጭ አንዳንዴ በህቡዕ አጀንዳ ከመሆን የዘለለችበት ወቅት አልነበረም፡፡ ችግሩ ምናልባትም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴራሉ መንግሥት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ እስከ ሚደርስ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ ብይን ለመስጠት ሳይሆን፣ በፌዴራል መንግሥታት ዋና ከተሞች (Federal Capital Cities) አስተዳደር ከፌዴራሊዝም መሠረታዊ መርሆዎች፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና ከአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አንፃር ያለውን ሁኔታ በገንቢ መንገድ ለውይይት ማቅረብ ነው፡፡ ጽሑፉም የምሠራበትን መሥሪያ ቤት አቋም፣ ወይም የትኛውንም ጎሳ፣ ሃይማኖት ወይም ፖለቲካ እንደማይወክል አንባቢያን ከወዲሁ እንዲረዱ እፈልጋለሁ፡፡
ስለፌዴራል ዋና ከተሞች አስተዳደር ከማንሳታችን በፊት አንባቢያን ስለፌዴራሊዝም የመንግሥት ሥርዓት ምንነት አዲስ ባይሆኑም፣ እንደ መንደርደሪያ ወይም እንደ ዳራ የፌዴራሊዝምን ጽንሰ ሐሳብና ምንነት ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፌዴራሊዝም ‘Foedus’ ከሚለው የላቲን ቃል የተወሰደ ሲሆን፣ ጥሬ ትርጉሙም የተለያዩ ቡድኖች አንድ ለመሆን የሚመሠርቱት ማኅበር ማለት ነው፡፡ ከ13ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ የኅብረተሰብና የመንግሥታት መስተጋብርን (State-Society Relationship)፣ የመንግሥታትን ሕገ መንግሥታዊ መዋቅርና የሥልጣን ክፍፍል በዘለለ የኅብረተሰብ መዋቅራዊ መስተጋብርን የሚያጠና ዘርፍ ሆኗል፡፡
ስለዚህ ፌዴራሊዝም ማለት፣ “The system of government which operates in a country which is a federation of semi-autonomous provinces or states, with a central federal government linking 2them together (Political dictionary) ይሆናል፡፡
ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ እንደምንረዳው አንደኛው የሥርዓተ መንግሥት ዓይነት (Federalism Vs. Unitary State) መሆኑን፣ በአንድ አገር ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ በከፊል ሙሉ ሥልጣን ያላቸው መንግሥታት መኖራቸውንና አንድ ማዕከላዊ መንግሥት እንደሚያስተሳስራቸው እንረዳለን፡፡ የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቋንቋ፣ በጎሳ፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖት በመልክዓ ምድር ተከፋፍለው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ብዝኃነታቸውን ጠብቀው፣ የጋራ መንግሥት መሥርተው እንደ አገር ለመቀጠል አማራጭ ሥርዓተ መንግሥት መሆኑን ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ነው፡፡
በአንፃሩ የፌዴራሊዝምን ሥርዓተ መንግሥት የሚተቹ አካላት የማዕከላዊ መንግሥትን ያዳክማል፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በመልክዓ ምድር የተከፋፈለ ኅብረተሰብ (Divided Society) ይፈጥራል በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም የትኛውም ሥርዓተ መንግሥት የራሱ የሆነ ውስንነቶች ቢኖሩትም፣ መንግሥታት የመረጡትን ሥርዓተ መንግሥት በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋል ከቻሉ ተሻጋሪ አገረ መንግሥት ይመሠርታሉ፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራሊዝምን ሥርዓተ መንግሥት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ከቻሉ አገሮች መካከል ስዊስና አሜሪካ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ለምሳሌ ሦስቱ የአልፓይን ማኅበረሰቦች በ13ኛው ክፍለ ዘመን የስዊስን ኮንፌዴሬሽን በመመሥረት ሉዓላዊ ግዛት መሥርታለች፡፡ አሜሪካም ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ነፃነቷን ካረጋገጠች በኋላ እ.ኤ.አ. በ1787 የዴሞክራሲ መርሆችን ታሳቢ በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው የፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት መሥርታለች፡፡ ዛሬ በውል የሚታወቁ እንደ ዓለም አቀፍ የፌዴሬሽን ፎረም (Forum of Federations) 25 የሚጠጉ በፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት የሚተዳደሩ አገሮች አሉ፡፡ በአገራችንም በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንደሚመሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እንደሆነ፣ ከተደነገገበት ጊዜ አንስቶ በፌዴራል ሥርዓተ መንግሥት በመተዳደር እስከ ውስንነቱ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ ዛሬ ላይ እያጋጠመን ላለው ችግር ይህ ጸሐፊ እምነት ፌዴራሊዝምን የተረዳንበት፣ የተረጎምንበትና ተግባራዊ ለማድረግ የተከተልነው አቅጣጫ መሠረታዊ ስህተት ነበረው ብሎ ያምናል፡፡ የችግሩ መነሻም በአገራችን ጥበብ ለጥበበኞች እንደሚባለው፣ ፖለቲካውም ለፖለቲከኞች አለመሆኑ በምክንያትነት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የአገራችን የፌዴራሊዝም አተገባበር ላይ ባለመሆኑ አንባቢያን ግን በአጀንዳው ዙሪያ ሊወያይበት ይገባል፡፡
- የፌዴራል መንግሥት ዋና ከተሞች ቅርፀ መንግሥት (Types of government for federal capitals)
ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት የሚከተሉ አገሮች ዋና ከተማቸውን ለማስተዳደር ወይም ለመምራት በርካታ ተግዳሮቶች የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ ዲግሪው እንደ ደረሰበት የዕድገትና የአስተሳሰብ ደረጃ የሚወሰን ቢሆንም፣ በዚህ ዘርፍ ጥናት ካደረጉ ምሁራን መካከል (Donald C. Rowat) የፌዴራል መንግሥታት ዋና ከተማቸውን ለማስተዳደር (How their federal capitals should be governed) የሚያጋጥማቸው ችግሮች ከሦስት ጉዳዮች እንደሚመነጩ ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመርያው የፌዴራል ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ትልልቅ ከተሞች የሚያጋጥማቸው ችግር በቂ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ካለመቻል የሚመነጭ ሲሆን፣ ሁለተኛው ሁሉንም የፌዴራል ዋና ከተሞች የሚያጋጥማቸው የዋናው ከተማው ነዋሪዎችን ፍላጎት ከአጠቃላይ የአገሪቱ ዜጎች ፍላጎት ጋር ማጣጣም አለመቻል ነው፡፡ ማለትም ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች አዲስ አበባ የመኖር መብት ስላላቸው የመኖሪያ ቤት ወይም ቦታ ፍላጎት የሚያሳድሩ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የዋና ከተማው ነዋሪዎችም ተመሳሳይ ፍልጎት አላቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን ፍላጎት ማጣጣም ካለመቻል የሚመነጭ ችግር ነው፡፡
ሦስተኛው የፌዴራሊዝም ሥርዓተ መንግሥት ተፈጥሮአዊ ባህሪ የሚመነጭ ችግር ሲሆን፣ ይህም የፌዴራል መንግሥት ዋና ከተማዋን የመቆጣጠር ፍላጎት መኖር ወይም የከተማው ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መኖር ወይም ዋና ከተማው የሚገኝበት መንግሥት (በእኛ ክልላዊ መንግሥት) ተፅዕኖ በፌዴራል መንግሥቱ መከልከል (Preventing the capital from being dominated by one of the states) In our case from the Oromia National Regional State) ተብለው የተለዩ ሲሆን፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፌዴራል መንግሥታት ዋና ከተሞች በሦስት ዓይነት መንግሥታዊ አደረጃጀቶች የሚከፈሉ መሆኑን ኃይለየሱስ ታዬ (ቀን አልተመለከተም) እና ሌሎች ጸሐፍት ያመላክታሉ፡፡
እነሱም አንደኛው ሞዴል (The Federal District Model) የሚባል ሲሆን፣ አብዛኛው የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች በተለይ ብዝኃ ጎሳ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ማንነት፣ ያላቸው ሕዝቦች የሚጠቀሙበት ሞዴል ነው፡፡ ይህ ሞዴል ዋና ከተማው በፌዴራሉ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ፣ የፌዴራል መንግሥት በሚያወጣቸው ሕጎች የሚተዳደር ነገር ግን የራሱ አስተዳደር ያለው የፌዴራል አባል መንግሥታትን በጋራ ለማስተዳደር ዕድል የሚፈጥር (Shared Rule) የከተማ መንግሥታዊ አደረጃጀት ነው (ለምሳሌ አቡጃ፣ አዲስ አበባ፣ ብራዚሊያ፣ ቦነስአይረስ፣ ካንቤራ፣ ካራካስ፣ ኢስላማባድ፣ ኳላላምፑር፣ ሜክሲኮ ሲቲና ዋሽንግተን ይጠቀሳሉ)፡፡
ሁለተኛው ሞዴል (The Member State – City State Model) ራሱ ዋናው ከተማው የፌዴራሉ አባል መንግሥት የሚሆንበትና ከሌሎች የክልል መንግሥታት ጋር እኩለ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው በመሆኑ፣ እንደ ዋና ከተማነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ክልል መንግሥታትም ተደራቢ ሚና አለው (ለምሳሌ በርሊን፣ ብራሰልስ፣ ሞስኮና ቪየና)፡፡
ሦስተኛው ሞዴል (City in A Member State) ሲሆን፣ ይህ ሞዴል ዋና ከተማው በሚገኝበት የክልል መንግሥት ሥር የሚተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ ተግባራትን የሚያከናውን ነው፡፡ ከተማው በሚገኝበት ክልል ተፅዕኖ ሥር የሚወድቅ በመሆኑ፣ የፌዴራሉ አባል መንግሥታት ፍላጎት የማያንፀባርቅ ከፍተኛ የበጀት እጥረት የሚገጥመውና የከተማውም ወሰን በውል ስለማይታወቅ፣ ለታክስ አሰባሰብና መንግሥታዊ ተግባራትን (State Function) ለመከወን ይቸገራል፡፡
በዚህ ንድፈ ሐሳባዊ ማዕቀፍ መሠረት ኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ በአንደኛው ሞዴል ሥር የምትወድቅ ስትሆን፣ መሠረታዊ እውነታዎች ምን ነበሩ የሚለውን ጉዳይ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንፃር በወቅቱ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አሁን የያዘውን ቅርፅ ይዞ ከመውጣቱ በፊት ተነስተው የነበሩ ጉዳዮችን ማየት ጠቃሚ በመሆኑ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ከሕገ መንግሥትና ከአዲስ አበባ ቻርተር አንፃር
በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 የፌዴራል ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ እንደሆነችና ተጠሪነቷም ለፌዴራሉ መንግሥት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም በሕገ መንግሥቱ ከተካተቱት ነጥቦች መካከል የአዲስ አበባና የኦሮሚያን ግንኙነት የሚመለከተው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሲሆን፣ አከራካሪ የነበረው ጉዳይ ሚያዝያ 14 ቀን 1986 ዓ.ም. በተካሄደው የስብሰባ ቃለ ጉባዔ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚለው ቃል ይግባ ወይስ አይግባ የሚለው ሐሳብ ነበር፡፡ መግባት የለበትም የሚሉ ወገኖች መከራከሪያቸው አዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በአገልግሎት አቅርቦት፣ እንዲሁም ከተማውንና ክልሉን የሚያገናኙ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በሚመለከት በሁለቱም ወገን የጋራ ጥቅም ስላላቸው (Mutual Benefit) ጥቅማቸውን በጋራ ትብብር ያስጠብቃሉ የሚሉ ነው፡፡ በሌላ ወገን ሰብሳቢውን ጨምሮ ምንም እንኳን አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ፣ በአገልግሎት አቅርቦት በተለይም እንደ ውኃና መሬት ባሉ የተፈጥሮ ሀብቶችና በበርካታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስለሚተሳሰሩ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ጥቅም ስለሚኖረው ይህ ጉዳይ በሕግ እንዲወሰን ሐሳብ ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ የተወሰነ መሆኑን ከቃለ ጉባዔው መረዳት ይቻላል፡፡
እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም ከተሞች ከሚገኙበት አጎራባች አካባቢዎች በእንግሊዝኛው (Suburbs or Peripheries) ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት መካከል በርካታ የሚነሱ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ እነሱም አሉታዊ ወይም አዎንታዊ የጎንዮሽ ውጤት (Positive And Negative Externalities) አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ አዎንታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ፣ አሉታዊ ጉዳትም አለው፡፡ ለምሳሌ በአገራችን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ትልልቅና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ነው የሚገኙት፡፡ ይህን ጥቅም ሐዋሳ ወይም ጅማ አላገኙትም፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አባባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች የአንድ ካሬ የመሬት ዋጋ (Value) ከደብረ ብርሃን ወይም ከፍቼ የአንድ ካሬ መሬት ዋጋ ልዩነት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ከመሠረተ ልማትና ከገበያ አንፃርም ብዙ ጠቀሜታዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ በአንፃሩ የአዲስ አበባ የጎንዮሽ ዕድገት በዙሪያው ያሉ አርሶ አደሮችን ከማፈናቀሉም በላይ፣ ከከተማው የሚወጣው የቆሻሻ ፍሳሽ በዙሪያዋ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚፈጥረው የጤና ቀውስ መኖሩ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖራቸውን ግንኙነት በሕግ መወሰኑ ተገቢ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ሕግ ለምን ማውጣት እንዳልተቻለ መረጃ ባይኖርም፣ ይህን ሕግ የማውጣት ሥልጣን የአዲስ አበባ ወይም የኦሮሚያ ክልል ባለመሆኑ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ እንደሚወስን ተቀምጧል፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሌላው ጉዳይ የአዲስ አበባ ማንነትን ከመወሰን አኳያ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብትና በፌዴራል ፓርላማ የከተማው ነዋሪዎች እንዲወከሉ ይደነግጋል፡፡
የኢፌዴሪን ሕገ መንግሥት መሠረት አደርጎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 በግልጽ እንደሚያስቀምጠው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለውም ከተዘረዘሩት የከተማ አስተዳደሩ ዓላማዎች ውስጥ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት የሚኖሩበት የባህላቸው መገለጫ እንድትሆን የማድረግ ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በሌሎች ክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥት ውስጥ የማይገኝ፣ ነገር ግን አዲስ አበባ የሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ማንነት መገለጫ መሆኗን የሚያስረዳ ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩን የሥራ ቋንቋም በተመለከተ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ይሁን የከተማ አስተዳደሩ ቻርተር የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ ቢያስቀምጥም፣ ሌሎች ተጨማሪ የአገሪቱን ቋንቋዎች መጠቀም የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ በመሠረቱ ቋንቋ ለልዩነት መንስዔ ሊሆን አይገባም፡፡ ምክንያቱም አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገር አንድ አገር አይፈጥርም፡፡ የተለያዩ ቋንቋዎች መኖራቸውም አንድ አገር ከመሆን አያግዳቸውም፡፡ ይህ መርህ ቢሠራማ ትግራይና ኤርትራ ትግርኛ፣ ካናዳና ሰሜን አሜሪካ እንግሊዝኛ፣ ላቲን አሜሪካና ስፔን ስፓኒሽ በመናገራቸው አንድ አገር በሆኑ ነበር በአንፃሩ በህንድ ከ179 እሰከ 188 ቋንቋ መናገራቸው 179 ወይም 188 አገር አላደረጋቸውም፡፡
ስለዚህ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ብዝኃነት አንድ ለመሆን ወይም ለመለያየት ምክንያት አይሆንም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሊረዱት የሚገባው ጉዳይ ልዩነቶች መኖራቸውን ተቀብለን፣ በልዩነት ውስጥ አንድ የሚያደርጉን በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ተገንዝበን፣ ሁሉንም ነገር በፖለቲካ ዓይን ከማየት በሰውኛ በማየት አንድነቷ የጠነከረ ዴሞክራሲያዊትና ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ መሥራት ይጠበቃል፡፡ መሪዎችም ሕዝቡን እንድንመራ እግዚአብሔር የመረጠን መሆኑን አውቀን፣ ለሁሉም የሰው ልጆች ቢቻል በዓለም አቀፋዊ ወንድድማችነት መርህ መሠረት አገራችንንና ሕዝባችንን ልንመራ ይገባል፡፡
አመሠግናሁ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡