Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስኳርና ዘይት ለመግዛት ረዣዥም ሠልፎች የተስተዋሉበት የበዓል መዳረሻ ገበያ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የፍጆታ ዕቃዎችን በዘመቻ ከማቅረብ ይልቅ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር መዘርጋት አለበት›› የኢኮኖሚ ባለሙያዎች

በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በበዓል መዳረሻ ሳምንት ባሉት የገበያ ቀናት፣ የፍጆታ ዕቃዎችን ለመሸመት በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሠልፈዋል፡፡

ሪፖርተር ለአብነትም በዘነበ ወርቅ፣ በመካኒሳ አቦ፣ በስድስት ኪሎ፣ በሾላ ገበያ፣ በገርጂ፣ በሜክሲኮና በካዛንቺስ አካባቢዎች ነዋሪዎች በሸማቾች ሱቆች የሚቀርቡትን፣ በተለይም እጥረት ተከስቶበታል የተባለውን ስኳር ጨምሮ ዘይትና የፉርኖ ዱቄት ለመግዛት የተደረገውን ረዥም ሠልፍና ትርምስ ለመታዘብ ችሏል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች ባሉት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ተፈላጊ የሆኑት የፍጆታ ዕቃዎች በአንዳንዶቹ ሱቆች ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ እየተሠራጩ ቢሆንም፣ በአንፃሩ እስካሁን ድረስ ‹‹የመሸጫ ዋጋ ባለመወሰኑ›› የምርት ሥርጭት ያልተጀመረባቸው ሱቆች መኖራቸውን ሪፖርተር ያነጋገሯቸው የሽያጭ ባለሙያዎችና ሸማቾች አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ የሚመራ የኢኮኖሚ ክላስተር ኮሚቴ የበዓል ፍጆታዎችን ለኅብረተሰቡ በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ታኅሳስ 24 ቀ ን 2015 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ፍላጎት ስለሚጨምር፣ የአቅርቦት ክፍተት እንዳይፈጠርና ኅብረተሰቡ ላልተገባ ዋጋ እንዳይጋለጥ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሠራ መሆኑን ሲገልጽ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የተዋቀረው የኢኮኖሚ ክላስተር ኮሚቴ ደግሞ የበዓል ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች በተመረጡ 126 የእሑድ ገበያዎችና በዓሉን ታሳቢ በማድረግ በተከፈቱ ባዛሮች ምርቶች እንዲቀርቡ ተደርጓል ብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርም ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ዘይት እንዲያገኝ በጅቡቲ ከሚገኘው ጎልደን አፍሪካ ካምፓኒ 43,037,412 ሊትር የፓልም የምግብ ዘይት ግዥ መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅቶች በላከው ደብዳቤ በአዲስ አበባና በክልሎች የፓልም ምግብ ዘይት የመሸጫ ዋጋ ተመን ልኳል፡፡

በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በሚሰጡት የኢኮኖሚ ትንታኔ የሚታወቁት አቶ ዋሲሁን በላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ‹‹መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በቅንጅት እየተሠራ ነው›› የሚል መግለጫ በየዓመቱ መስጠቱ፣ መንግሥት ሕዝቡን ‹‹ቢያንስ ለበዓል እንዳይከፋችሁ›› የሚል አንድምታ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

መሠረታዊ አቅርቦት ላይ መሥራት የሚቻል ቢሆን በዓመት ውስጥ የሚመጡ ጥቂት በዓላት የሚፈጥሩት የሸማችና የመንግሥት ጭንቀት ይቀንስ ነበር የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የማስታመም ዕርምጃ የለመደው የኢትዮጵያ ገበያ በበዓላት ወቅት የመንግሥትን ውስን የገበያ ጣልቃ ገብነትን ባይጠላም ሸማቹም ለበዓል ሸመታ ምክንያታዊ ለመሆን መጣር አለበት የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ሸማቹ በዓልን ከሃይማኖትና ሌሎች የባህል ጉዳዮች ጋር ስለሚያይዘው ገበያ ውስጥ ያለውን ዋጋ ተቀብሎ ስለሚገዛ፣ ሻጮች ዋጋ የመወሰን ዕድላቸው ወይም ፍላጎታቸው ከሌላው ጊዜ የበለጠ መሆኑን አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ይህንን በበዓል ወቅት የሚያይል ፍላጎትን ማወቅ፣ ሻጮች ገዥዎች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በማወቅ ዋጋ እንደሚጨምሩና ምርት እንደሚያከማቹ ታሳቢ በማድረግ እልባት ለመስጠት ከመንቀሳቀስ ባሻገር ሊኖር ይችላል የሚባለውን እጥረት አንዳንዴ እጅ በማስገባት ዋጋ የመወሰን፣ በተለያየ አካባቢዎች የገበያ ቦታ አማራጮችን ማስፋት የሚጠበቅበት ኃላፊነት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ለበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን የምርት እጥረት በተከሰተባቸው ወቅቶች እየታዩ ካሉ ልምምዶች ውስጥ ታሪፎች ላይ ለውጥ ማምጣት፣ ለሸማች ማኅበራት ከፍተኛ ብድር በማቅረብ ምርት ጨምረው ወደ መጋዘን እንዲያስገቡ ማድረግን የገለጹት አቶ ዋሲሁን፣ ነገር ግን ይኼ ጠቅላላ የገበያ ሁኔታውን ያስተካክላል ተብሎ እንደማይወሰድና የጥቂት ቀናት የሸማች ኅብረተሰብን ፍላጎት የሚያስታግስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ለማስተካከል እየሄደበት ያለበት ርቅት ውጤት አለማምጣቱን አመላካቹ ብዙ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ፣ ውጤት እንዳያመጣ ካዳረጉት ጉዳዮች ውስጥ የኑሮ ውድነት ልክ እንደ በዓል ወቅት ገበያ በዘመቻ ሳይሆን ተቋማዊ የሆነ ለውጥ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የግብይት ሁኔታው በሚያሳዝን ሁኔታ በሥርዓት አልበኝነት የተሞላ ነው ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ በነፃ ገበያ ሥርዓት የሚመራ ሳይሆን ጥቂቶች ምርት እየደበቁ፣ ዋጋ እየወሰኑ ምርት የሚያመጡበትና የሚያጠፉበት ሥርዓት የተንሰራፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘመቻ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ቀድሞውኑም ሲገለጽ የነበረ መሆኑንና ሰንበት ገበያ፣ ባዛርና ኤግዚቢሽን፣ እንዲሁም የበዓል ወቅት ተጠብቆ የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ይኼ ነው የሚባል ለውጥ አምጥተዋል ተብሎ የሚገለጽ አለመሆኑን የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጁ  ገልጸዋል፡፡

ጥቂቶች ዋጋን እንደ ልብ የሚወስኑበትን ገበያ፣ ጥቂቶች ምርት የሚደብቁበትን መስክ መንግሥት ሕግ የበላይነት ዕርምጃ ሳይወስድበት፣ የበዓል ወቅት በመጠበቅ ይህን ያህል ዶሮ፣ እንቁላል ይቀርባል ማለት ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ሥራ ተደርጎ እንደማይቆጠር አቶ ቁምላቸው ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ መንግሥት ከፕሮፓጋንዳ ሽፋን ውጭ በተገቢው መንገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት አይደለም በሚል የሚሞግቱት አቶ ቁምላቸው፣ የሕግ በላይነትን ከፖለቲካ፣ ከፍትሕ፣ ከፀጥታና ከደኅንነት አንፃር ብቻ ሳይሆን በንግድ ወይም በግብይት ሥርዓቱም ላይ ሊሰፍን ይገባል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ፍራንኮ ቫሉታ አማራጭ በራሱ ችግር የነበረው ሆኖ ሳይሆን ተቋማዊ አሠራር ደካማ በመሆኑ በፋይናንስ ተቋማትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አማራጩን ከዓላማ ውጭ በመተግበሩ መዘዝ ያመጣ መሆኑን በዋቢነት ያቀረቡት አቶ ዋሲሁን፣ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት አቅም መጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ ለገናና ጥምቀት በዓላት የተሻለ የፍጆታ ምርት አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መሆኑን ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ለሁለቱም በዓላት 60 ሺሕ ዶሮዎችና ስድስት ሚሊዮን እንቁላሎች በኤልፎራ፣ከባለድርሻ አካላትና በክልል የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት የሚቀርብ መሆኑን ገልጿል።

አራት ቋሚ የእንስሳት መሸጫ ማዕከላትን ጨምሮ በሚደራጁ ጊዚያዊ ማዕከላት በኩል 15 ሺሕ የእርድ እንስሳት እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑን የጠቀሰው ቢሮው፣ ፌቤላ 2.2 ሚሊዮን ሊትር፣ ጊፍቲ 800 ሺሕ ሊትር፣ የንግድ ሥራ ኮርፖሬሽን በሸማቾች በኩል 1.2 ሚሊዮን ሊትር በድምሩ 5.4 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ እንዲሁም ሰላሳ ሺሕ ኩንታል ስኳር ለገናና ለጥምቀት በዓላት የሚቀርብ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች