Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዴት እንግባባ?

ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ ልንንደረደር ነው። ወያላው ያለ ከልካይ ያሻውን ይዘላብዳል፡፡ “ምን አፍሽን ታሾይብኛለሽ? ትጥቁን የፈታ አማፂ መሰልኩሽ?” ይላታል ራሱ ጎትጉቶ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ቦታ የሰጣትን ጭምት። “አንተም እዚያ ደረጃ ደርሰህ ነበር ወይስ እንደ እነሱ መሆን አምሮህ ነው?” ስትለው ተበሳጭታለች። “ኧረ እናንተ ሰዎች በፈጣራችሁ ተው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ይኼን ምናምንቴ ነገር ጎትታችሁ ልታመጡብን ነው?” መሀል መቀመጫ ላይ ጥቁር ባርኔጣ ከደፋ ጎልማሳ አጠገብ የተቀመጠች  ወይዘሮ ትቆጣለች። “ታዲያ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ተጨፋጭፈን ሲደክመን ስለትጥቅ መፈታት እንጂ ስለጦርነት ብናወራ አያምርብንም…” ይላል ጎልማሳው። “ታዲያ ይኼ መሠልጠን ነው መሰይጠን እንጂ…” ወይዘሮዋ ታቀባብላለች። “ለሰላም ስምምነቱ ግምገማ አልተሰበሰብንም እባካችሁ…” ወያላው ነገር ያጦዛል። “ደግሞ ብለህ ብለህ ወደ እኛ ዞርክ?” ሲለው ጎልማሳው ወያላው ተገላመጠ። ነገር ተጀመረ ማለት ነው!

“አንተ ይህንን ነገር መቆስቆስ ተው ብልህ አልሰማ ብለሃል፣ ቆይ ብቻችንን እንገናኝ…” ብሎ ሾፌሩ የወያላውን ቀልብ ይገፈዋል። ይኼን ካለ በኋላ ሬዲዮን ይከፍታል። ሰዓቱ የዜና ነው። “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰላም ስምምነቱ መሠረት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ዕፎይ ማለታቸው እንዳስደሰታቸው ተናገሩ…” ሲል ዜና አንባቢው፣ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የነዋሪዎቹን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የትግራይ ነዋሪዎች እንዲደሰቱ ያድርግ…” ሲል አንዱ ተረበኛ ተናገረ። “ኧረ ዜና እንስማበት…” ሲል ጎልማሳው፣ “አትሰማም እንዴ? አሁን እስኪ ማን ይሙት በወገኑ ሰላም ማግኘት ማን ይከፋዋል ብለው ነው ይህንን ዜና የሚሉት…›› የሚለው ሌላ ነገረኛ ነው፡፡ “ይኼንንስ ማን አየብን? ቢያንስ ሒደቱን እያየን አፋችን አንድ እየሆነ በመምጣቱ ፈጣሪን እናመሥግን…” የምትለው ደግሞ አንዲት ለግላጋ ናት። እውነቷን ነው!

ጉዟችን ተጀምሯል። ዓይናችን በተራው ጣራና ጌጡን ሲያማትር አንድ ጥቅስ አነበብን። ‘ሥራ ለፈታ ሰው ያንን ቲቪ አውሰው…’ ይላል። “እኔ እኮ እዚህ አገር በሰው ምርጫና ዓይን ዕጣ የሚያወጣው አልበዛባችሁም?” ትላለች አንዷ። “ዓይቶ ማለፍ እያለና ሰምቶ መቻል ሳለ አንቺስ ምን ነዳጅ ያስጨርስሻል? ያውም ጠፍቶ ላልጠፋ ነዳጅ ለመሠለፍ?” ይላታል ከጎኗ። ጎልማሳው ደግሞ፣ “ሲቸግር ምን ታድርግ? ይኼው አሁን እኔ የምጓዘው ለሽምግልና ነው። ድምፃቸው የማይሰማ የነበሩ ባለትዳር ናቸው። ስንቱን ክፉ ጊዜ ያሳለፉ። ካልጠፋ ነገር በምን ተጣሉ አትለኝም? በዚህ በመከረኛው ቲቪ፡፡ ባል እራት አቅርቢ ሲላት፣ እሺ አለችው። እሺ ብላው ቆማለች። እንደገና እራት ሲል ሄዳ ወጡን ብቻ አመጣች። ደግሞ በዚያው ቆማ ቀረች። እሱ ርቦታል። አድርጎት የማያውቀውን ተነስቶ በጥፊ መታት፡፡ ይኼው ልጆቿን ትታ ትናንት ከትናት ወዲያ ማታ እንደ ወጣች አልተመለሰችም…” ሲል ተሳፋሪው ወደ አለመደማመጥ ባህሉ ተጣደፈ። የነገር መነሻው ይህም አይደል!

 “ደግ አደረጋት…” ሲል አንዱ፣ “ምን ማለት ነው ደግ አደረገ? እሱ ወጥና እንጀራ ለማቅረብ አንሶ ነው? ነውር አይደለም እንዴ? ያውም በዚህ በሠለጠነ ጊዜ?” ትላለች ነገር ቆስቋሻ። ከሾፌሩ ጀርባ ካሉት አንዱ ደግሞ፣ “ምን ማለት ነው በዚህ ጊዜ ማለት? መጽሐፍ ሚስት ፈቃዷ ወደ ባሏ ነው አይልም እንዴ?” ብሎ ነገር ሲያከር፣ “እሱ ይውደዳት፣ እንደሚሰበር እንቁላል ይንከባከባት እንጂ ካሻው ያቅምሳት…›› ይላል ብሎ ከጎኑ ያሉትን ሰቅዞ መያዝ። ታክሲያችን በተደበላለቀ ስሜት ስትናጥ በአንዴ ለዛዋ ጠፍቶ እጅ እጅ አለች። የዘመኑ ሰው ምን ነክቶት ነው እንዲህ የጉልበተኞች ጠበቃ የሆነው ያሰኛል፡፡ ከአስገድዶ ደፋሪና ከተራጋጭ መከላከል ይሻላል ወይስ ማበር አያሰኝም ትላላችሁ፡፡ መስኮት ተከፍቶባቸው የሚታገላቸውን ንፋስ ለመከላከል የሚታገሉ አዛውንት ጨዋታ ያነሳሉ። “አዳሜ እንዲህ የሆድሽን አውጥተሽ እያራገፍሽ የመናገር ነፃነት ታፍኗል እያልሽ ‹አሳይለም› ትጠይቂያለሽ፡፡ ወየውልሽ እያንዳንዳሽ፣ በፍርድ ቀን የምትመልሽውን አዘጋጂ…” አሉ። “እኔ የሰማሁት ግን የመንቀሳቀስ እንጂ የመናገር ነፃነት ችግር አለ ሲባል አይደለም…” አለች እዚያው ቅርባቸው። “የተጻፈ ሕይወት እየኖራችሁ ማነው አትንቀሳቀሱ ያላችሁ በፈጠራችሁ?” አዛውንቱ ነገሩን ማጠጠርና ማዋዛት ይዘዋል። “ምነው አባት ሕገ ሰማይና ሕገ መንግሥት ከተለያዩ ቆዩ እኮ…” ሲላቸው ደግሞ ያ አጭሩ ነገር ጫሪ፣ “እሱንማ መርጣችሁ ነዋ። የሰው መንግሥት ድሮም ወጉ የሰው ነው። ምነው ግን የዛሬ ልጆች ይኼ ዓይነቱ ማስተዋል ርቋችሁ ከእባብ ዕንቁላል የዶሮ ጫጩት ትጠብቀላችሁሳ? ደግሞ ይኼንንም ፌስቡካችሁ ላይ ለቅልቁና አነካኩኝ አሉዋችሁ…” ሲሉ ተሳፋሪዎች ሳቁ። ከሳቁ በኋላ ግን መፖሰቱ አይቀርም፡፡ ነገረኛ ሁሉ!

ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “ዘመኑ የመነካካት ነው አባት። ሳይነካኩ መኖር ከብዷል…” ሲላቸው ደግሞ፣ “ኧረ እኔስ የከበደኝ ሌላ ነው…” ብለው ልብ አንጠልጥለው ዝም አሉ። “ይንገሩና!” ጎልማሳው ወተወታቸው። “አትኖረው ይመስል ምኑን ልንገርህ?” አሉት። “እሱን እኮ ነው የምልዎት…” ሲላቸው፣ “ምን ይላል ሰውዬው? የራሴን ሐሳብ መልሰህ እየነገርከኝ ነው ‘እሱን እኮ ነው የምልዎት’ የምትለኝ? አዲስ ሐሳብ ሳታፈልቁ አዲስ ራዕይ ሳትቀርፁ ነው ታዲያ ማይኩ የጥቂቶች ብቻ ሆነ ብላችሁ የምትጮሁት? ለመቃወም ለመቃወምማ ሰይጣንም ይቃወማል እኮ? ቀናነትን በጠማማነት ለማሸነፍ የመረጠው የትግል ሥልት ግን የት አደረሰው? የትም…” እያሉ ያሻቸውን ነካክተው ጠያቂና ሞጋቾቻቸውን ዝም አሰኙ። መቼም ዕድሜ የጠገበ ሰውና ሥርዓት ዝም የሚያሰኝበት ነገር አያጣም፡፡ ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው በፈገግታ ታጅቦ በሞባይል ስልኩ እያሰላ መልሳችንን ያድለናል። “ኧረ ይቆጥርብሃል ብዙ አትጠቀም…” ይለዋል አንዱ። ወያላው፣ “እኔን ነው?” ይጠይቃል። “ለአንተም ለሞባይልህም የተላለፈ መልዕክት ነው። ቴሌ ካልጻፈው በቃ መልዕክት አናነብም አይደል?” ይላል መጨረሻ አካባቢ ሌላው። “ምነው የእናንተ ቤት አከራይ ቴሌ ነው እንዴ መብራት አጥፉ ብሎ የሚልክባችሁ?” ጎልማሳው ነገሩን ወዳመጣው ተሳፋሪ ዞሮ ጠየቀ። “እሱስ ለጨዋታ አልኩት እንጂ ሁላችንም በየቤታችን መብራት እልም ሲልብን እኮ አድብቶ ነው…” ማለት። “አድብቶ ስትል?” ከጎኔ ያለችው በጥያቄ ማፋጠጥ። “እንጀራ ልንጋግር ስንል፣ ገና ቁሌት ስናቁላላ፣ ሞባይላችን ቻርጅ አድርጉኝ ከማለቱ ነዋ…” አላት። “ይቅርታ አድርግልኝ አሁን ከጠቀስካቸው ነገሮች ሁሉ አድብቶ የሚያስብል ነገር አላገኘሁም…” አለው ከወደ ጋቢና። “እንዴ መብላት የህልውና ማገር እንደሆነ ለማስመስከር ተደራጅተን ማብሰል ሊኖርብን ነው? ዘንድሮ እኮ የተናጠል መብት አላዋጣም ጎበዝ…” አለ ሰውዬው። ትንተና ሲጀመር እንዲህ ነው አሉ!

“ስንቱ የመብራት መቆራረጥ ንግዱንና ሥራውን እያስተጓጎለበት፣ ግፋ ቢል ፌስቡክ ከፍቶ የሚፈዝበት ስልኩ ቻርጅ ሲጨርስ መብራት ሄደብኝ ብሎ ሰው የአገሩን ደካማ ጎን አጋልጦ ይሰጣል?” ስትለኝ ከጎኔ ሰውዬው ሰምቷት ኖሮ፣ “እሱስ ልክ ነሽ። ከመብራት መቆራረጡ በላይ እርስ በርሳችን የጋራ ችግራችንን በተመለከተ የአቋም መዋዠቅና መቆራረጥ እያለ፣ እኔም ሰው አገኘሁ ብዬ ይኼን መናገር አልነበረብኝም…” ብሎ በነገር ጎሸማት። ‹‹እንዲህ ተፋጠን መሽቶ እየነጋ የኃይል መቆራረጥ ችግር በአንድም በሌላ ካላቆራረጠን እንላቀቃለን ታዲያ? ይኼን ሰምታችሁ መስመሩን ቆራርጡት አሉዋችሁ በገና በዓል ደግሞ…›› ሲሉ የምንሰማቸው ወይዘሮዋን ነው፡፡ ሁሉም ተራው ሲደርስ መናገሩ አይቀርም ማለት ነው፡፡ ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋና ጎልማሳው በአንድ አንድ ተዛምደው ስለጥቁሩ ባርኔጣ ይነጋገራሉ። “ምነው የቅርብ ሰው ነው?” ሲሉ ወይዘሮዋ ሐዘን ላይ እንደከረመ ጎልማሳውን ይጠይቃሉ። “የለም፣ ማንም አልሞተም። ብቻ ወሬ የሚገለው በዛ። በሆነ ባልሆነው ባልተጨበጠ ትርክት ገደል የሚገባው ላቀ…” ካለ በኋላ፣ “እና ይኼ እኔ የጀመርኩት አዲስ ምልክት ነው። የሰው ልጅ አዕምሮን የመሰለ አስገራሚ ነገር ተሠርቶ ተሰጥቶት፣ በተለይ በተለይ እኛ ዘንድ የምንጠቀምበት የሚያመነጨውን አመክንዮ ሳይሆን ስሜቱን ብቻ ነው። ለዚህ ነው የእስካሁኑ ይበቃል፣ የኑሯችን መጎሳቆልና መጥቆር ምክንያቱ ጭንቅላታችንን ልክ እንደዚህ ጥቁር ባርኔጣ የተኮፈሰበት የጥመት አስተሳሰብ ነው ለማለት ነው…” ብሎ ኮራ ብሎ እንደ መደላደል ሲያደርገው፣ “ወይ ጉድ በደቦ እየጨፈለቀ ገደለን እኮ? እኛ እኛ እያልን በፍረጃ የምንገጫጨው እኮ ከከተማችን የትራፊክ አደጋ ባሰ…” ትላለች ከወዲያ። ከወዲህ ምን ይባል ደግሞ!

መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ደግሞ በአንድ ድምፅ ‘ላይክ አድርገነዋል’ ብለው ጎልማሳውን ጫር ሲሉት፣ “እንደ አሜሪካ የማያጠፉትን እሳት የሚጭሩ ዘንድሮ መግቢያ ቀዳዳቸውን አውቀነው…” ብላ ከጋቢና ሌላዋ ታስተጋባለች። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው ከሐሳብ ይልቅ ስሜት የሚሰጠውም የማይሰጠውም ጭፈራና ዘፈን ብቻ ጎላ ብሎ በሚደመጥበት ጎዳና ሿ ብለን ፈሰን ትርምሱን ተቀላቀልን። የተቀላቀለው በዝቶ ኩልል ባዩ ኩሉን መጠበቅ አቅቶት ያልሆነውን ሲሆን፣ በመመሳሰል ጎዳና የምናትመው አሻራ አስጨፍልቆ ሊያፈራርደን ደግሞ ሌላ ፌርማታ ይጠራናል። በምልክት ወይም በዜማ ካልተግባባን ምን ቀርቶልን ይሆን? ለመሆኑ እንዴት እንግግባ! መልካም በዓል! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት