Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሲንቄ ባንክ ለሕንፃ ግንባታዎች 55 ቦታዎችን ተረከበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 371.6 ሚሊዮን ብር አትርፏል

የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም በሚል ይታወቅ የነበረውና ወደ ባንክ የተሸጋገረው ሲንቄ ባንክ አገልግሎቱን ለማስፋትና የቋሚ ሀብት መጠኑን ለማጠናከር ያግዙኛል ያላቸውን ሕንፃዎች ለመገንባት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ ከተማ 55 ቦታዎችን መረከቡን አስታወቀ።

ተቋሙ ወደ ባንክ ከተሸጋገረ የመጀመርያውን ጠቅላላ ጉባዔ ሰሞኑን ያካሄደ ሲሆን፣ በጉባዓው ላይም ለአገልግሎትና የቋሚ ሀብት መጠኑን ለማጠናከር ያግዙኛል ያላቸውን ሕንፃዎች ለመገንባት 55 ቦታዎችን እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ በእጁ ማስገባቱን አስታውቋል።

የሕንፃ ግንባታ ቦታዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 54 ከሚሆኑ የተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎች የወሰደ መሆኑንም የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቶሎሳ ገደፉ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ 

ባንኩ ለሕንፃ ግንባታ ከተረከቧቸው 55 ቦታዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አካባቢ ባለ 15 ወለል ሕንፃ እየገነባ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ቶሎሳ ገልጸዋል።

አክለውም ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የመገንባት ዕቅድ እንዳለው የገለጹ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ለህንፃ መገንቢያ ከተረከባቸው ቦታዎች ውስጥ በተመረጡ ዋና ዋና ከተሞች ላይ ከፍታ ያላቸውን ሕንፃዎች ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት እያስጠና እንደሆነ ተናግረዋል።

ባንኩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ በባንክ ደረጃ አገልግሎት የጀመረው በ2014 የሒሳብ ዓመት ሲሆን፣ ሥራ በጀመረበት በዚህ የሒሳብ ዓመት በፋይናንስና በኦፕሬሽን ሥራዎች ያሳየው ጅማሮ ይበል የሚያሰኝና ለባንኩ የወደፊት ጉዞ መሠረት የጣሉ መሆናቸውን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

የስንቄ ባንክ የ2014 ሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባንክ ከመሆኑ በፊት ወይም የብድርና ቁጠባ ተቋም ከነበረበት የ2013 ሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ጋር ተነጻጽሮ የቀረበ ነው። 

በዚህም መሠረት ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘቡ 10.28 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የብድርና ቁጠባ ተቋም ከነበረበት የመጨረሻው ሐሲብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ69 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ ያስረዳል።

ሲንቄ ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 3.97 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር የሰጠ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የባንኩን የብድር ክምችት 17.82 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተሰጠው ብድር ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ28.87 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያመለክታል፡፡ የባንኩ የብድር ሥርጭትን በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንዳመለከቱት አብዛኛው ብድር በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች የተሠራጨ ነው፡፡ የባንኩ የተበዳሪዎች ቁጥርም ከ748 ሺሕ በላይ የደረሰ መሆኑን የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳብው፣ ይህ ቁጥር በአገሪቱ ከሚገኙ ጠቅላላ ባንኮች አላቸው ተብሎ ከሚነገረው የተበዳሪዎች ብዛት አንፃር ሲታይ በእጥፍ የሚበልጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ባንኩ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት 2.78 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው ገቢ ጋር ሲነፃፀርም የ20 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የዓመቱ ጠቅላላ ወጪ ሆኖ የመዘገበው ደግሞ 2.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ወጪ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ37.2 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡ ለባንኩ የወጪ ዕድገት ዋነኛው ምክንያት ባንኩ ከብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክነት ሲሸጋገር ከፍተኛ የደመወዝ ማሻሻያ ማደረጉ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ በርካታ ቅርንጫፎችን ወደ አዳዲስ ሕንፃዎች እንዲዘዋወሩ መደረጉ፣ አዲስና ዘመናዊ የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር መገዛቱ፣ የብራንዲንግ ሥራና መሰል በርከታ ወጪዎች በመፈጸማቸው ባንኩን ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጉ ተገልጿል።

የባንኩ አጠቃላይ ገቢና ወጪዎች ተሰልተውም በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 371.6 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል። ከታክስ በፊት የተመዘገበው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ34 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 560.7 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ባንኩ ከማክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ የተሸጋገረበት ዓመት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የወጣው ከፍተኛ ወጪ ለትርፉ መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የሲንቄ ባንክ ጠቅላላ ሀብት መጠኑ 20.54 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም የ28.1 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ጠቅላላ ካፒታሉ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአምስት በመቶ ዕድገት በማሳየት በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ 8.09 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉም የስድስት በመቶ ዕድገት በማሳየት 7.45 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ 

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ቅርንጫፎች ቁጥር 404 የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 134 የባንክ ቅርንጫፎችና 270 የማክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኩን የአገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው ከዚህም በኋላ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ቅርንጫፎች ለመክፈት ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ ተበዳሪዎች ቁጥር ይህንን ያህል ለመድረሱ ዋናው የብድርና ቁጠባ ተቋም ሆኖ በቆየባቸው ጊዜያት በክልሉ በርካታ አነስተኛ ተበዳሪዎችን ይዞ በመቆየቱና አሁን ወደ ባንክ ሲሸጋገርም እነዚህን ተበዳሪዎች ይዞ በመቀጠሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ሲንቄ ባንክ መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን ለማስፋት እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትን መጀመር ሲሆን በዚሁ መሠረት ባንኩ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቋል፡፡ ለዚህም የስዊፍት (SWIFT) ኮድ ሲንቄታ (SINQETAA) አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ በዩሮኤዥያ አካባቢዎች ከሚገኙ የተለያዩ ባንኮች ጋር ለመሥራት የሚያስችሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማመቻቸቱን ያመለከቱት አቶ ገደፋ ከዚህም በተጨማሪ ከታወቁ ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን ትስስር በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡ 

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ለሰፊው ኅብረተሰብ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ባንኩ የሸሪአን ሕግ መሠረት ያደረገ የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆንና ክፍተት የሚታይባቸው የሥራ ዘርፎች እንዲጠናከሩ እንዲሁም የተሳለፈ የሥራ ሒደት እንዲሰፍን በጥናት ላይ የተመረኮዘ አዲስ መዋቅር ተዘርግቷል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በገበያው ውስጥ ተፎካካሪ ለመሆንና የሠራተኞችን ተነሳሽነት ለማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ የደመወዝ ማሻሻያም የተደረገ ሲሆን የካበተ የባንክ ልምድና ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞችም በመሳብ ባንካችን የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ ተሠርቷል፡፡ 

ባንኩ ሽግግር ሙሉ ለማድረግና የተሟላ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የተሠራ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ ከሦስተኛ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን በዚህም ረገድ ከቴሌ ብር፣ ደራሽ እንዲሁም ኢሲኤክስ ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጅት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ 

ሲንቄ ባንክ ከብድርና ቁጠባ ተቋምነት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ ፈቃድ ካገኙ አምስት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ወደ ባንክ ከተሸጋገረ በኋላ የባንኩ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት አድርጎ አቶ ነዋይ መገርሳን መሰየሙ ይታወሳል፡፡ አዲስ ባዋቀረው ቦርድ ደግሞ አቶ ቶሎሳ ገደፋን የቦርድ ሊቀመንበር እንዲሁም የቀድሞውን ጄኔራል ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶን ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ በመሰየም የባንክ ሥራውን እንደጀመረ ታውቋል፡፡ 

በ2014 መጨረሻ አጠቃላይ ሲንቄ ባንክ የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር የ14 በመቶ ዕድገት በማሳየት 6921 ሊደርስ ችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች