Wednesday, May 22, 2024

ብልፅግና በእጅጉ እየተፈተነባቸው ያሉ ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው ብልፅግና አገር ማበልፀግ ዋና ዓላማው መሆኑን ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በራሳቸው በብልፅግና አመራሮች ጭምር ‹‹ከብልፅግና ጉዟችን የሚመልሰን የለም›› የሚል መፈክርም በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ በተጨባጭ ብልፅግና ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ጎዳና እንዴት ነው የሚወስደው የሚለው ብዙ የሐሳብ ትንተና፣ የርዕዮተ ዓለም ውይይት ብቻ ሳይሆን የፖሊሲና የዕቅድ ክርክሮችን ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብልፅግና ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት፣ ሚናን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ለመውሰድ በማሰብ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት አልፎም በየክልሉ ኮሚቴዎች እየተመሠረቱ ናቸው፡፡ በዚህ መነሻም የተለያዩ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ብልፅግና በእጅጉ እየተፈተነባቸው ያሉ ችግሮች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሲከታተሉ

በተለይ ገዥው ፓርቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት የሰጠ መሆኑን በአፅንኦት ለማሳየት፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሩት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተሳተፉበት ጠለቅ ያለ ማብራሪያ አንደኛው ገላጭ ሁነት ነበር፡፡  

‹‹እንደ ብልፅግና ያሉ ፓርቲዎችና ስብስቦች ዋና መሣሪያቸው ሐሳብ ነው፡፡ ሐሳብ መገደብ ወይም መጽሐፍ መደበቅ ከጀመሩ ብልፅግና አይረጋገጥም፤›› በማለት ከሰሞኑ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሰፊ ገለጻ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ‹‹ብልፅግና የሚረጋገጠው በከፍተኛ የሐሳብ ፍሰት ነው፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ፓርቲው አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ እነሱን እየተገለገለ እንደሚሄድ ነው ያስረዱት፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሰሞነኛ ማብራሪያ ስለሚመሩት ፓርቲ ብልፅግናና ስለመንግሥታቸው ብዙ የተባለበት መድረክ ነበር፡፡

በተለይ ፓርቲያቸው ብልፅግና በእጅጉ እየተፈተነባቸው ስላሉ ችግሮች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢሕአዴግ ተፈትኖ የወደቀባቸውና በሕዝብ ተጠልቶ ከሥልጣን ለመወገድ የተዳረገባቸው ምክንያቶች የብልፅግናም ፈተና እየሆኑ እንደመጡ በግልጽ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ሙስና፣ ምዝበራ፣ በሥልጣን መባለግና ንቅዘት ሲባሉ የቆዩ ከዘመነ ኢሕአዴግ ጀምሮ የተወረሱ ችግሮች የፖለቲካ ገበያ (Political Market Place) የሚል ጥቅል ትርጓሜ ተሰጥቷቸው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

‹‹ትልቁ የዚህ አገር ፈተና የፖለቲካው ገበያ ነው፡፡ መገረዝ ያለበት አስተሳሰብ እሱ ነው፡፡ ለብልፅግና ባለን ጉጉትና ሥራ ላይ እንቅፋት የሚሆን የፖለቲካ ገበያ በማንኛውም መንገድ መገረዝ አለበት፡፡ አደገኛና ጉዟችንን የሚያቆም ስለሆነ፡፡ የፖለቲካ ገበያው ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ የኢትዮጵያን ብልፅግና ጉዞ አደጋ ውስጥ ከቶታል፤›› በማለት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ስለፖለቲካ ገበያ ዘርዘር ሲያደርጉም በሕግ የሚከወን ፖለቲካ እንዳለ በመጠቆም፣ ሌላኛው የዚህ ተቃራኒ ደግሞ ‹‹በገንዘብና በጥቅም የሚሸቀጥ ፖለቲካ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሙስናና ምዝበራ በሥርዓቱ ላይ የደቀነውን አደጋ በሰፊው አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካ እንደ ቀሸጥ ለገበያ እየቀረበና ለግል ፍላጎት መጠቀሚያ እየሆነ ነው ብለው፣ ነገር ግን ፓርቲያቸው ብልፅግና ትልልቅ የሙስና ችግር ውስጥ የለም ብለዋል፡፡

‹‹በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ብልፅግናን ለሙስና የመጠቀም ችግር የለም፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ የሙስናው ደረጃ ትንንሽ (Petty Corruption) ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ትንንሽ ሙስናም ቢሆን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመው፣ ከዚህ በዘለለ ግን መዋቅራዊ ሙስና ወይም ‹ስቴት ካፕቸር›› የለም ሲሉ ነበር የተደመጡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞኑ ትንተናቸው የፖለቲካ ሸቀጥነትን አደገኛ ቢሉትም፣ ‹‹መዋቅራዊ ሙስናን ግን ገና ያልደረስንበት ችግር ነው፤›› ብለውታል፡፡ የሁለቱ ነጥቦች ዝምድናም ሆነ ልዩነት በእሳቸው ማብራሪያ ብዙም ሳይጠቀስ ነው የታለፈው፡፡ እዚህ ላይ የኢሕአዴግን ውድቀት ያፋጠነውና እሳቸው የሚመሩት ብልፅግና በቦታው እንዲተካ ያደረገውን መሠረታዊ ምክንያት መከለስ ጠቃሚ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የዛሬ ሁለት ዓመት ባሳተሙት ሁለተኛ የመደመር መጽሐፋቸው ‹‹የመደመር መንገድ›› ላይ ከገጽ 162 እስከ 163፣ መንግሥታቸው የመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸውን ልክ እንደ ፍኖተ ካርታ (ማኅበራዊ ኮንትራት) እንደሚቆጥረው ገልጸው ነበር፡፡

‹‹መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረበውን የፓርላማ ንግግር እንደ የመጀመርያው ዕቅድ ሊወሰድ ይችላል፤›› በማለት ነበር ‹‹በመደመር መንገድ›› መጽሐፋቸው የከተቡት፡፡

በዚያ ንግግራቸው ደግሞ፣ ‹‹መሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ አገራችንን ከሁለት አሥር ዓመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት፣ በሁሉም መስክ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ሕገ መንግሥታዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል፡፡ ያሳካናቸው በርካታ ስኬቶች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ ያለባቸው በርካታ ችግሮችም አሉ፤›› በማለት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) በመጋቢት 24 ቀን ንግግራቸው ሙስናና ምዝበራን በተመለከተ ያነሱበት መንገድ ደግሞ ከሁሉ ጠንከር ያለ ነበር፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው፡፡ ሙስናን ፀረ ሙስና ተቋምን በመመሥረት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተናል፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ፡፡ ትናንት የተፈጠረን ሀብት ከሌላው በመቀማት ሒሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም፡፡ ገበታው ሰፊ በሆነበትና ሁሉም ሠርቶ መበልፀግ በሚችልበት አገር፣ ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ነጥቆ ለመውሰድ የሚያስገድድ ቀርቶ የሚያሳስብ ምንም ምክንያት የለም፤›› በማለት ሰፊ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ የዕጦትና የመነጣጠቅ አስተሳሰቦችን በመተው በጋራ ለመበልፀግ እንዘጋጅ የሚል ጥሪም አቅርበው ነበር፡፡

ሁሉንም በጋራ አበለፅጋለሁ የሚለው የዓብይ (ዶ/ር) ብልፅግና በኢሕአዴግ ወንበር ከተተካ እነሆ አራት ዓመታት አለፉ፡፡ ይሁን እንጂ በብዙዎች እምነት ብልፅግናው ሳይሆን፣ በኢሕአዴግ ዘመን ሕዝብን ሲያስመርር የዘለቀው የሙስና አባዜ ተመልሶ አገራዊ ችግር ሲሆን ነው የታየው፡፡

አንዳንዶች በኢትዮጵያ የታየውን ለውጥ (ሪፎርም) ከተለያዩ አገሮች የፖለቲካ ሽግግር ጋር አዛምደው ያቀርቡታል፡፡ ዓብይ ሰይድ የተባሉ አንድ ጸሐፊ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እ.ኤ.አ. በ1997/98 በኢንዶኔዥያ ከተፈጠረው የፖለቲካ ሽግግር ጋር ሊነፃፀር የሚችል እንደሆነ ከትበዋል፡፡

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ አደረገ እንደሚባለው ሁሉ፣ በኢንዶኔዥያም ፕሬዚዳንት ሱሀርቶ አገሪቱን በመቀየር የሚወደሱ የፖለቲካ መሪ እንደነበሩ ጸሐፊው ይጠቅሳሉ፡፡

የገነቡት ኢኮኖሚና ያስመዘገቡ ዕድገት ከብዙኃኑ ኢንዶኔዥያዊ ይልቅ ጥቂቶችን ብቻ ከበርቴ ያደረገ ነበር፡፡ ከስድስት ልጆቻቸውና ቤተሰባቸው፣ እንዲሁም ከጦር መሪዎችና ባለሥልጣናት ጋር ተሻርከው የአገሪቱን ሀብት ሲዘርፉ ለ32 ዓመታት ኖሩ፡፡ በአጠቃላይ የፕሬዚዳንት ሱሀርቶ ቤተሰብ ከ35 ቢሊዮን ዶላር በላይ የአገር ሀብት መመዝበሩ ይነገራል፡፡ ሱሀርቶ በ1997 ዓ.ም. የኢኮኖሚ ቀውስ መከሰቱን ተከትሎ ተቃውሞ በረታባቸው፡፡ በተቃውሞ ተገደውም ሥልጣን ለቀቁ፡፡

በኢንዶኔዥያ የመጣው ለውጥ ‹‹ሪፎርማሲ›› የሚል ስም ወጥቶለት መላው ኢንዶኔዥያዊያን አገራቸው እንደሚቀየር ብዙ ተስፋ አደረጉ፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡ የተጠበቀውን ሳያመጣ ቀረ፡፡ በሱሀርቶ ዘመን የተዘረፈውን የአገር ሀብት ማስመለስም ሆነ ዘራፊዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ ሳይቻል ቀረ፡፡ ከኢንዶኔዥያ ኢኮኖሚ ዛሬም ቢሆን 70 በመቶውን የሚያንቀሳቅሱት የሱሀርቶ ዘመን ከበርቴዎች ናቸው፡፡ ሱሀርቶ ከሥልጣን ከተወገዱ፣ እንዲሁም ከሞቱ ብዙ ዓመታት ቢቆጠሩም ልጆቻቸውና ቤተሰባቸው ዛሬ ከ15 እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ፣ በሁሉም የኢኮኖሚ መስክ የሚሠሩ ፈርጣማ ከበርቴዎች ሆነው መቀጠላቸውን ይህ ጽሑፍ ይዘረዝራል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የሕዝቡን ብሶትና ቁጣ ያናረ ብለው የገለጹት ሙስናና ምዝበራ ዛሬም ድረስ የሥርዓቱ አደጋ ሆኖ መቀጠሉን፣ በተደጋጋሚ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩት ተደምጠዋል፡፡ ይህን አደጋ ግን መዋቅራዊ ችግር ነው ብለው ለመግለጽ ግን የተቸገሩ ይመስላል፡፡ ፓርቲያቸው ብልፅግና በፖለቲካ ገበያ ሽሚያ እየተፈተነ መሆኑን ያስረዱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ሥልጣን ለግል ጥቅም ማካበቻነትና መነገጃነት እየዋለ መሆኑን በግልጽ ነው የዘረዘሩት፡፡ ይህንን ቢሉም ግን ከትልልቅ (Grand Corruption) ይልቅ ትንንሽ (Petty Corruption) መከላከል አስፈላጊ መሆኑን ነው አተኩረው ሲናገሩ የተደመጠው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -