Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንበሳ አውቶቡስ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም አሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ድርጅቱ የበጀት እጥረት እንዳለበት ገልጿል

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች ለአንድ ዓመት የቆየው የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄያቸው እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱን ተናገሩ፡፡

በድርጅቱ ሥር 1,900 አባላትን በማቀፍ የተቋቋመው የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር፣ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ በድርጀቱ መፍትሔ ባለማግኘቱ ጉዳዩ ታኅሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ አድርጎ ነበር፡፡ በድርጅቱ ተቀጥረው ከሚሠሩት 4,000 ሠራተኞች ውስጥ የተወሰኑት የደመወዝ እርከን ጭማሪ ሲጠይቁ መቆየታቸው ተገልጿል።

ማኅበሩ ከድርጅቱ ጋር ለአንድ ዓመት የቆየ ክርክር ካደረገ በኋላ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሠራተኞቹ ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡

ችሎቱ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ያለውን የሁለት እርከን ደመወዝ ጭማሪና የቤት ኪራይ ክፍያ ድርጅቱ እንዲጨምር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ድርጅቱ የፍርድ ቤት ውሳኔውን እስካሁን ተፈጻሚ ማድረግ አለመቻሉም ተገልጿል፡፡ ለሠራተኞቹም የ2014 ዓ.ም. የደመወዝ እርከን ጭማሪና የቤት ኪራይ ብቻ መጨመር እንደሚችል፣ ነገር ግን የ2013 ዓ.ም. የደመወዝ የእርከን ጭማሪ (Back Payment) ማድረግ አልችልም ማለቱን፣ የማኅበሩ ሊቀ መንበር ወ/ሮ ለምለም ገብረ እግዚአብሔር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹እኛ የ2013 ዓ.ም. የእርከን ጭማሪ ጨምሮ የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ እንፈልጋለን። በሕግ በኩል ሄደን ተፈርዶልናል። በወቅቱ በ2013 ዓ.ም. ተጨምሮ ቢሆን ኖሮ ለሠራተኛው በጣም ይጠቅም ነበር። አሁን በድርጅቱ በኩል የተሰጠውን ምላሽ ሠራተኛው ራሱ እንዲወስን፣ ሠራተኞችና የድርጅቱ አስተዳደሮች እየተወያዩ ናቸው፤›› ሲሉ ወ/ሮ ለምለም አስረድተዋል።

የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ለገንዘብ ተቀባይ ከሚከፈለው ከ2,516 ብር ዝቅተኛ ደመወዝ ጀምሮ፣ በአመራር ደረጃ ለሚገኙት እስከ ሃያ ሺሕ ብር ድረስ ይከፍላል።

ለአውቶቡስ አሽከርካሪዎች እንደ የሥራ ልምዳቸው ከ5,663 ብር እስከ 8,000 ብርና ከዚያ በላይ ይከፈላቸዋል። ድርጅቱ ለሠራተኞቹ የሚያደርገው የደመወዝ እርከን ጭማሪ ከ100 ብር ጀምሮ ሲሆን፣ የቤት ኪራይና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም ጭማሪዎችን ያደርጋል። በድርጅቱ የተቀጠረ ሠራተኛ ዘጠኝ ወራት ከሞላው በኋላ የእርከን ጭማሪ የመጠየቅ መብት ያለው መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡

የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ባለፈው ሳምንት ጥቂት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ አስበው የነበረ ሲሆን፣ ከድርጅቱ ጋር ውይይት በማድረግ አድማው እንዳይካሄድ መደረጉን የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል።

በውይይቱም ላይ ድርጅቱ የበጀት እጥረትና የተለያዩ የብድር ጫና እንዳለበት ለሠራተኞቹ መገለጹን፣ ከሠራተኞቹ ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት በሒደት ላይ መሆኑን ከሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የሠራተኞቹን ጥያቄ መመለስ የሚችለው የድርጅቱ የቦርድ ውሳኔ ምን ላይ እንደደረሰ ለመረዳት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገበየሁ ዋቄ የእጅ ስልክ በመደወል መረጃ ቢጠየቅም፣ እሳቸው መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረው፣ መረጃዎችን በሕዝብ ግንኙነት በኩል ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍሉም ከላይ ከተጠቀሰው ውጪ ሌላ መረጃ እንደሌለው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች