Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዲጂታል አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ፍልሰት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

የዲጂታል አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ፍልሰት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተነገረ

ቀን:

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት፣ ወደ ርዕሰ ከተማዋ አዲስ አበባ የሚደረገውን የሕዝብ ፍልሰት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው በኢትዮጵያ የቀጣይ 30 ዓመታት ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ለመምከር ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ወደ ሥራ የገባው ‹‹ኢትዮጵያ 2050›› የተሰኘ የባለሙያዎች ስብስብ፣ በማዕድን ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በውይይቱ የፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች፣ተመራማሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 ‹‹ኢትዮጵያ 2050›› ኢኒሼቲቭ በዋናነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2050 ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን 200 ሚሊዮን አኃዝ ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ መስኮች ማለትም የትምህርት፣ የውኃና ኢነርጂ አቅርቦትና የኢንዱስትሪ ልማትን ጨምሮ በሌሎች መሠረታዊ ዘርፎች ሙያዊ ዕገዛ፣ እንዲሁም ጥናታዊ ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን በጋራ ያሰባሰበ መሆኑ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዩናይትድ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢንሼቲቩ አንደኛው ሊቀመንበር ተስፋዬ ወርቅነህ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል? በዚህ ወቅት ያሉት መደበኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ዲጂታላይዜሽን እንዴት ይሄዳሉ? በሚሉት ላይ የፖሊሲ ግብዓት ለመሰብሰብ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ወቅት በአገሪቱ በተለይም መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ከማስተሳሰር አኳያ ትንንሽ ጅማሮዎች የሚታዩ ቢሆንም፣ ይህንን አቀናጅቶ በዲጂታል አገልግሎቶች ተደራሽነት ላይ መሥራት ከተቻለ በገንዘብ፣ አካባቢን በመጠበቅ አቅምን በማሳደግና ጥራት ያለው ሰነዶችን በማሰናዳት ወደ ተሻለ አቅጣጫ መሄድ እንደሚቻል ተጠቅሷል፡፡

ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው የሕዝብ ፍልሰት የሚመነጨው በተለይም ከቴክኖሎጂ አንፃር የተሻለ ፍሰት ስላለ ነው ያሉት ተስፋዬ (ኢንጂነር)፣ ከዚህ አንፃር የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነቱን በማስፋት ሌሎች ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ሳተላይት ከተሞች እንዲፈጠሩ በማድረግ የሕዝብ ፍልሰቱን መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂን በተለይም ወደ አምራች ዘርፉ ከማስገባት አንፃር ሁለት ነገሮችን ጠንቅቀው የሠሩ አገሮች ዕድገታቸው ወጥነት እንዲኖረው ማድረግ ችለዋል፡፡የመጀመሪው ግልጽ የሆነ የፖሊሲ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው ወደ ተግባር ማስገባታቸው ሲሆን፣ ይህንን ደግሞ በተቋም ማደርጀት ዕድገትን ቢያንገራግጭም እንኳን ዘላቂ ልማትን የሚያመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግብርና ላይ የተንጠለጠለ ኢኮኖሚና ዕድገት እንደነበራት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በተመሳሳይ የአመራረት ሒደት የቆየውን ዘርፍ ለማዘመን የአምራች ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ መዘመን የግድ ነው ብለዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የዜጎችን መሠረታዊ የኢኮኖሚና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፍላጎቶችንና ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን ወስዳለች ብለዋል፡፡

ለአብነትም በዝግጅት ላይ የሚገኘው የ‹‹ስታርት አፕ›› አዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ወቅት በርካታ የስታርት አፕ ድርጅቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ፣ ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትር ደኤታዋ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2050 ወይም አስቀድሞ በእጥፍ ያድጋል የሚለውን ትንበያ መሠረት በማድረግ በሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ በእጅጉ መሥራት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያስታወቁት ወ/ሮ ሁሪያ፣ በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እንዴት አቅምን በማቀናጀት ያልተጣጣመውን የግብርና፣ የአምራች ኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ፣ እንዲሁም የዲጂታል አገልግሎቶች ማሻሻል ይቻላል በሚለው ላይ መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ 2050›› ኢንሼቲቭ ሊቀመንበር ተስፋዬ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂን ከተግባር ጋር ለማቆራኘትና ወደ ፖሊሲ መቀየር የሚችል ግብዓት ለመስጠት በተዘጋጀው ፎረም የተገኙትን ውጤቶች፣ ተሞክሮዎችንና የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለዚህ ዓላማ ተብሎ ለተቋቋመው ክፍል ይቀርባሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...