በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የተሞከሩ የሽግግር ፍትሕ ሙከራዎች መሳካት ባለመቻላቸው፣ እንዲሁም ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ያከበረ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት በማሰብ፣ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጀ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የተረቀቀውና ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማግኘት ታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የሽግግር ፍትሕ ሙከራዎች የነበሩ ቢሆንም በፖሊሲ የተደገፉ ባለመሆናቸው ግባቸውን ያልመቱና ውጤት ያላመጡ መሆናቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ሰነድ ያስረዳል፡፡
የተለያዩ የዓለም አገሮችን ተሞክሮ በግብዓትነት ያካተተው ረቂቅ ሰነዱ፣ አገሮች ክስና ቅጣት ላይ ትኩረት በመስጠት ጊዜያዊ ልዩ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም፣ እንዲሁም አጥፊዎች በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤቶች እንዲቀርቡ የማድረግ ተሞክሮ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ብታልፍም በተሟላ ሁኔታ የሽግግር ፍትሕ አላባዎች ተተግብረው አያውቁም፤›› ሲል የነበረውን ተሞክሮ ያስረዳል፡፡
ረቂቅ ሰነዱ በተጨማሪ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የነበሩት የሽግግር ሒደቶች ሲደረጉ ተከናውነው የነበሩ ‹‹ጉልህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በደሎችና ጭቆናዎች መንስዔ፣ ምንነት፣ ዓይነትና የጉዳት መጠን›› በበቂ ሁኔታ አለማጣራት፣ እንዲሁም ለተከናወኑ ጥፋቶች የተጠያቂነትና የይቅርታ ሒደት አለማካሄድ እንደነበረ ይገልጻል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወል ሡልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለሽግግር ፍትሕ መቋቋም አንደኛውና የመጀመርያው ተግባር፣ አሁን እየሆነ ያለው ረቂቅ የአቅጣጫ ሰነዱን ጨርሶ ለአስተያየትና ለሕዝብ ውይይት ማቅረብ ነው። ‹‹በረቂቅ ሰነዱ ላይ የተካተቱት ሐሳቦች አሁን እንዳሉ የሚፀድቁ ሳይሆኑ፣ ከሕዝብ ውይይት በኋላ በሚነሱ ሐሳቦች ላይ ተመርኩዞ የተሻሉ የሚባሉት ሐሳቦች ተወስደው ይፀድቃል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
ሰነዱ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ያሉትን የሽግግር ፍትሕ ሙከራዎች በዝርዝር ያስረዳል። የደርግ መንግሥት በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ትክክለኛ የሽግግር ፍትሕ አተገባበርን ተግባራዊ አለማድረጉ አንደኛውና የመጀመርያው ክፍተት እንደሆነ ያስቀመጠው ሰነዱ፣ በኢሕአዴግ ዘመንም የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናትን በመልካም የፍትሕ ሥርዓት ለመዳኘት ተሞክሮ በተወሰኑ ጉድለቶች ምክንያት የተሟላ የሽግግር ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይጠቅሳል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የመጣውን ለውጥ ተከትሎም መንግሥት ጥሩ ዕርምጃዎች መውሰዱንና ‹‹ለደረሱ በደሎች እንደ መንግሥት በይፋ ይቅርታ የጠየቀ›› መሆኑን ያብራራል፡፡
ሆኖም በዚህኛው መንግሥት የተደረገውን የሽግግር ፍትሕ ሙከራ ጉድለቶችን ሲዘረዝር ሦስት ማሳያዎችን አቅርቧል፡፡ እነሱም የወንጀል ክሶችን፣ የምሕረትንና ተቋማዊ አደረጃጀት በማለት ጉድለቶችን ጠቅሷል፡፡
አንደኛው የጉድለት ምንጭ የሆነው የወንጀል ክሶችን በሚመለከት ሰነዱ በዝርዝር ካስቀመጣቸው ጉድለቶች መካከል፣ ‹‹በአመዛኙ ክሶች የቀረቡት ሊከሰሱ ከሚገባቸው መካከል ማማረጥ የሚመስል መሆኑ›› አንደኛው ሲሆን፣ ረዥም የፍርድ ሒደት ደግሞ ሌላኛው እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሁለተኛውና ምሕረትን በሚመለከት ሰነዱ ካስቀመጣቸው ጉድለቶች መካከል የምሕረት ሒደቱ ሲካሄድ ተጎጂዎችን የመካስና ይቅርታ የመጠየቅ ሒደቶች አለመኖራቸው፣ እንዲሁም በምሕረት አዋጁ ‹‹ተጠቃሚ ሆነው ከእስር የተለቀቁ ሰዎች ባለፉት አራት ዓመታት በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ተመልሰው መሳተፋቸውና በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የታለመውን ግብ ያላሳካ መሆኑ›› ይገኙበታል።
ሦስተኛውና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በሚመለከት የተጠቀሰው ዋነኛ ጉድለት፣ በ2011 ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ፍትሕን በሚመለከት የሚጠበቅበትን ዓላማ ሳያሳካ የተሰጠው ሦስት ዓመት በማለቁ በ2014 ዓ.ም. መፍረሱ እንደሆነ ይገልጻል። የኮሚሽኑ አመሠራረት አገር አቀፍ የሕዝብ ምክክር ስላልተካሄደበት፣ ‹‹ግልጽነት የጎደለውና ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ›› የሆኑ ኃላፊነቶች ስለተሰጠው፣ እንዲሁም ደግሞ የኮሚሽነሮቹ አመራረጥ ግልጽነት የጎደለውና ከእነሱም መካከል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ይገኙ የነበሩ መኖራቸው ከኮሚሽኑ ጋር በተያያዘ የተጠቀሱ ጉድለቶች ናቸው።
የሽግግር ፍትሕ በግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፉ እንዲመራ ሰነዱ ምክንያቶችን ሲያስቀምጥ ዋነኛው የተሟላ የፍትሕ ሥርዓትን መተግበር ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ ‹‹ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሥልታዊና መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ›› በመፈጸማቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ለውጡ በ2010 ዓ.ም. ከመጣ ወዲህም ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አለመረጋጋት፣ ግጭቶችና የእርስ በርስ ጦርነት›› መቀጠላቸውንና ዜጎችም ‹‹ለሞት፣ ለስደትና ለንብረት ውድመት እየተጋለጡ›› መሆኑን ያስነብባል፡፡
ይህን የሽግግር ፍትሕ ሒደት ለማሳካትና ተግባራዊ ለማድረግ፣ እንደ አማራጭ የተቀመጠው እንደኛው ‹‹የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን›› አቋቁሞ እውነትን የማጣራት ተግባር ለእሱ መስጠት መሆኑን ሁለተኛው ደግሞ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ወይም በቅርቡ ለተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመስጠት እውነትን እነሱ እንዲያጣሩ ኃላፊነት መስጠት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ለመተግበር የተወጠነውን የሽግግር ፍትሕ ሒደት ከተለያዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ለማስተባበር በረቂቁ ከቀረቡ በርካታ ስያሜዎች በአንደኛው ላይ ተመርኩዞ ኮሚሽን እንደሚቋቋም ረቂቅ ሰነዱ ይጠቁማል። ሒደቱም የተሟላ እንዲሆንና ኃላፊነት የሚኖርባቸውን የተለያዩ ተቋማትን በመሰብሰብ ፖሊሲውን በባለቤትነት እንዲያስፈጽም ደግሞ፣ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ አስተባባሪ ቦርድ (ምክር ቤት) ማቋቋምም አስፈላጊ መሆኑ በሰነዱ ተካቷል፡፡