Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በሕግና በሥርዓት መኖር የአገር ባህል ይሁን!

ኢትዮጵያውያን እንደ እምነቶቻቸውና ልማዶቻቸው በዓላትን ሲያከብሩ ቅድሚያ የሚሰጡት፣ አንዳቸው ለሌላው አለኝታነታቸውን ለሚያሳዩበት መተሳሰብና መደጋገፍ ነው፡፡ በበዓላት ሰሞን ከዘመድ፣ ከጎረቤትና ከወዳጅ ጋር የሚደረገው መገባበዝ ብቻ ሳይሆን፣ ያላቸው ለሌላቸው ለማካፈል የሚያደርጉት ርብርብ ለዘመናት በትውልዶች ቅብብሎሽ የተወራረሰ አኩሪ የጋራ እሴት ተጠቃሽ ነው፡፡ በዓላትን ተንተርሰው የሚመጡ ወጪዎችን በመጋራትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት እርስ በርስ ለመደጋገፍ የሚያሳዩት ትብብር በዚህ ትውልድም በመቀጠሉ ሊያኮራ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት አርዓያነት ያለው የጋራ ማኅበራዊ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ተሿሚዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ሌሎችም ሕዝቡን መምሰል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያዩ ማንነቶችና መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም፣ በዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴቶቹ አማካይነት በመተሳሰብ አንድ ላይ ለመኖር ተቸግሮ አያውቅም፡፡ በዕድር፣ በዕቁብ፣ በደቦ፣ በቅርጫ፣ ወዘተ የኑሮ ተግዳሮቶችን ለማሸነፍ አንድ ላይ መኖር የሚችልበት ሕዝባችን፣ ችግሮች ሲያጋጡሙም በምሥጉን አገር በቀል የሽምግልና ሥርዓቶቹ መፍታት ልማዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገነባውም በዚህ ዕሳቤ ላይ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መኖር ጠቃሚ ነው፡፡

በሕዝብና በመንግሥት መካከል እንደ ጥሩ መገናኛ ድልድይ የሚያገለግለው መተማመን ነው፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እየዳበረ የሚሄደው መንግሥት በቅርበት ሲያዳምጠው ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ ሳይችል ሲቀር ግን ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ዘመን በበርካታ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው ያለው፣ መንግሥት በተቻለው መጠን የሕዝብን አመኔታ እንዴት እንደሚያገኝ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ማናቸውም ፖሊሲዎች ሆኑ ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት፣ የሕዝቡንም ሆነ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ይሁንታ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ አለበት ሲባል ምሁራንን፣ ተማሪዎችን፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ ነጋዴዎችን፣ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ነፃና ዴሞክራቲክ በሆነ መንገድ መነጋገር ለሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ግብዓት ለማግኘት ከመርዳቱም በላይ፣ የሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያረጋግጣል፡፡ በነፃነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው በሕግና በሥርዓት እንዲኖሩና መንፈሳቸው እንዲነቃቃ ያደርጋል፡፡

የአገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ከአገር ጥቅም በፊት የማንም አይቀድምም፡፡ የአገር ጥቅም ከምንም ነገር በላይ ይበልጣል፡፡ ይህ ሳይከበር ሲቀር ችግር ይፈጠራል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት መገለጫ ከሆኑት ውስጥ አንደኛው የአገርን ዕድሎች ማደናቀፍ ነው፡፡ ዜጎች በተሰማሩባቸው መስኮች በሕጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው ሀብት ሲያፈሩም ሆነ የሥራ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የመንግሥት ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እሴት በመጨመር ለአገር ዕድገት የሚበጁ ፕሮጀክቶችን የሚመሩ ዜጎች፣ በሰባራ ሰንካላ ምክንያቶች ሥራቸው ሲስተጓጎል ይታያል፡፡ ለአገር የሚበጁ ፕሮጀክቶች ሲስተጓጎሉና አቤቱታዎች ሲቀርቡ አዳማጭ ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ፣ ከግል ጥቅማቸው በላይ ማሰብ የተሳናቸው ኃይሎች የያዙትን ሥልጣን ያላግባብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አገሬንና ወገኔን ልጥቀም ብሎ ለልማት የተሠለፈው ኃይል ወደ ጎን እየተገፋ፣ በጥቅም ግንኙነት የተሳሰረው ኃይል አገር እያጠፋ ነው፡፡ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሕግና በሥርዓት አገር ያስተዳድሩ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ራሳቸውን ያድሱ፡፡ ከጥላቻና ከጨለምተኝነት አስተሳሰብ ወጥተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይንቀሳቀሱ፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በኃላፊነትና በያገባኛል መንፈስ ይነጋገሩ፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆን ስለሌለበት፣ የመነጋገሪያው መድረክ በአስቸኳይ ሥራውን ይጀምር፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው ወይም የሚጠበው በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባህሪ ምክንያት ስለሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ቀናነት ሲባል ሁሉም ለሰጥቶ መቀበል መርህ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን በጠላትነት እየተያዩ በአንድ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ስለማይቻል፣ ራሳቸውን ለመልካም ነገር ያዘጋጁ፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና አገር እየመራ ስለሆነ፣ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ እነሱን ያገለለና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚያጠፋ ጉዞ ጠቃሚ አለመሆኑን ይረዳ፡፡ በአገር ጉዳይ የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋልና፡፡ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ በሕግና በሥርዓት ለመንቀሳቀስ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ ለአገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የበለጠ ጎልቶ የሚታየው በሥነ ምግባር ሥራውን ሲያከናውን ነው፡፡ ከሥነ ምግባር አፈንግጠውና የኅብረተሰቡን ባህላዊ እሴቶች ንደው በሕዝብ ላይ አደጋ የደቀኑ ወገኖችን የማረቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ብዙኃኑ በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በሚሠሩበት አገር ውስጥ ከመጠን በላይ በሆነ ራስ ወዳድነት ውስጥ የተዘፈቁትን፣ የግብይት ሥርዓቱን መላቅጡን በማጥፋት ጤናማ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርጉትን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግድ ማኅበራትም ሆነ በንግድ ምክር ቤቶች አማካይነት ሊታገላቸው ይገባል፡፡ ምርት በመደበቅ፣ የግብይት ሰንሰለቱን በማዛባት፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት በመፍጠርና የሕዝቡን ሕይወት በማናጋት ላይ የሚገኙት እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች አንድ መባል አለባቸው፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ሹማምንትን በሙስና በመበከል የግብይት ሥርዓቱን እያጠፉት ስለሆነ የንግድ ማኅበረሰቡ ይንቃ፣ ይታገላቸው፡፡ በዚህም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ያሳይ፡፡ ጤናማና ፉክክር ያለበትና ለሁሉም የተመቻቸ ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ እንዲፈጠር የበኩሉን ይወጣ፡፡ ይህንን በስኬት ከተወጣ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ትልቅ ስጦታ እንደሰጠ ይቆጠራል፡፡ የመስጠትና የማካፈል በጎ ተግባር ተባባሪ ይሆናል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡ ለሕግና ለሥርዓት መከበር ትኩረት ይስጥ፡፡

ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ከሚነሱት መካከል ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ አዝጋሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩና ጥያቄዎች ሲቀርቡ በወቅቱ ምላሽ ባለመገኘቱ ምክንያት፣ አላስፈላጊ ግጭቶች ተነስተው ሕይወት ይጠፋባቸዋል፡፡ ከዚያ በመለስ ዜጎች ለራሳቸውም ሆነ ለአገር የሚጠቅሙ ተግባራትን ለማከናወን ሲነሱ ድጋፍና ማበረታቻ ከመስጠት ይልቅ፣ ደንብና መመርያን ሰበብ በማድረግ እንቅፋት ፈጣሪዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር የግልጽነት፣ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መርህ መጥፋት ነው፡፡ በሥልጣን ያላግባብ መገልገልና በማናለብኝነት የሚፈጸሙ ድርጊቶች በስፋት ይታያሉ፡፡ ሙስና የበላይነት ይዟል፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ሲባል ከሚሰሙ ዲስኩሮች በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔ አጥቷል፡፡ በብሔር፣ በጥቅማ ጥቅምና በመሳሰሉት ሕገወጥ ትስስሮች ምክንያት በዜጎች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ እኩይ ድርጊቶች ተወግደው በሕግ የበላይነት ላይ መተማመን ካልተቻለ አገሪቱ የሕገወጦች መፈንጪያ ትሆናለች፡፡ ሕገወጥነትን መዋጋት የሚቻለው ቆፍጠን ያለ ዕርምጃ ለመውሰድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መኖር የአገር ባህል ይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...