Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች ምላሽ ያልሰጠ በመሆኑ፣ አገሪቱ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

ምሁራኑ ይህን ምክረ ሐሳብ ያቀረቡት፣ ‹‹ፌደራሊዝምና ጎሳዊ አደረጃጀት፣ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ምን ትምህርት ተገኘ?›› በተሰኘ ርዕስ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ባሰናዳው የምሁራንና የባለድርሻ አካላት የውይይት መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወይም ‹‹ጎሳዊ›› አደራጃጀት ከተጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው ብለዋል፡፡ ፌደራሊዝሙ ታስቦ የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የውስጥ አስተዳደር፣ የተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎችን መብት፣ ልማትና ዕድገት በአገሪቱ ውስጥ ካለው ከአጠቃላይ አሠራርና አደረጃጀት ጋር ከፍ ለማድረግ ታስቦ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህ እንዳለ ሆኖ ፌደራሊዝሙ በጥሩ ውይይትና አስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ጥቅም አንፃር በደንብ የተሸፈነ ሳይሆን በአብዛኛው የኢትዮጵያን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ፍላጎት ለማስከበር በሚል በችኮላ የተቀመረ መሆኑን ያስረዱት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ በዚህም ምክንያት ውሎ አድሮ በድንበር፣ በጎሳዊ አደረጃጀቶች፣ እንዲሁም በማንነት ጥያቄ ላይ በርካታ አለመግባባቶች መከሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በተረቀቀበት ወቅት በተለይም ከአንቀጽ 39 እና 47 ድንጋጌዎች ጋር ተያያዘው የነበሩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች፣ ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ በእጥፍ አስቸጋሪ ሆነው መቅረባቸውን ያዕቆብ (ዶ/ር)  ለማሳያነት አቅርበዋል፡፡

እንደ ፖለቲካ ተመራማሪው እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለሁሉም በሚመች፣ አገረ መንግሥቱንና የአገሪቱን ጥንታዊነት ባገናዘበ፣ ለኅብረተሰቡ በየደረጃው አስፈላጊ በሆነ፣ ነፃነትን፣ ዴሞክራሲን፣ እንዲሁም ለሥራና ለአሠራር አመቺ በሆነ አስተዳደር (የፌዴራል ሊባል ይችላል ወይም በሌላ ዓይነት መንገድ) አማራጭ መቀመር ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን የሚያደራጁበትና ከኢትዮጵያም ነፃ ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ ተፈቅዶላቸዋል በሚል መደንገጉን፣ ድንጋጌው አፈጻጸም በመፈለጉ በአንቀጽ 47 ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ራሱን ካለበት ክልል ነፃ ለማውጣት ወይም ለመግለጽ ከፈለገ ነፃ የመውጣት መብትና አሠራር መደንገጉ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን የፌደራል ሥርዓት የሚወስኑ፣ የአስተዳደርና የአሠራር፣ የሕግና የልማት አደረጃጀቶችን የወሰኑ ማዕከላዊ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሆናቸው በመድረኩ ተብራርቷል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች አንፃር በትክክለኛ ግንዛቤ የተጤነ አይመስልም ያሉት ያዕቆብ (ዶ/ር)፣ ሕገ መንግሥቱን የጻፉ ሰዎችና ያፀደቁት ኃይሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክና የኅብረተሰብ መስተጋብር፣ ባህልና የሕዝቡን በርካታ ዘመናት አብሮ የመኖር፣ አንዱ ከሌላው ጋር በቅርብ መዛመድ በደንብ አለማጤናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ተቋቁሞ አዲስ ሥርዓት ከተበጀ በኋላ በርካታ ችግሮች በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰታቸውን፣ እነዚህም ማንነትን፣ ድንበርን፣ የአስተዳደር ግድፈትን የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ በርካታ ጥያቄዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ሊመለሱ ያልቻሉና ይህም ጥያቄዎቹን መመለስ ሌላ ብዙ ችግር ሊፈጥር ይችላል በሚል ለረዥም ጊዜ በጥያቄነት የቆየ ጉዳይ መሆኑን የፖለቲካ ተመራማሪው አስታውቀዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አስናቀ ከፍአለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ፈዴራሊዝም ከሌሎች አገሮች ፌደራሊዝም ለየት የሚለው የመገንጠል መብትን በሕገ መንግሥት በማረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከ30 ዓመታት በኋላ የፌደራል ሥርዓቱ የብሔር ብሔረሰብ ወይም ጎሳዊ በመሆኑ  ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ዓይተናል፤›› ያሉት አስናቀ (ዶ/ር)፣ አንዳንዶች ችግሩ የአፈጻጸም እንጂ ሥርዓቱ በራሱ ችግር የለውም የሚል አስተሳሰብ እንደሚያራምዱ አክለዋል፡፡ በአንፃሩ ያዕቆብ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሐሳብ ሥርዓቱ ከአመሠራረቱ ጀምሮ ችግሮች ስላሉት፣ ይህንን ቆም ብሎ በማሰብ የተሻለ አደረጃጃት እንዴት ነው የሚመጣው? የምክክር ኮሚሽኑም ሆነ ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሠሩ ይገባቸዋል የሚለውን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩትና ከጉድገቨርናንስ አፍሪካ የተወከሉት ዘሪሁን መሐመድ (ዶ/ር)፣ ፌደራሊዝም ያሉት ጥሩ ጎኖች እንደተጠበቁ ሆነው ነገር ግን በጎሳ ላይ ሲመሠረት ያለውን ችግር ሲጠቁሙ፣ ባለፉት 30 ዓመታት የተገኙት ልምዶች ተወስደው ከዚህ ተጠቃሚ የሆነ ሰፊ ክፍል መኖሩን ተናግረዋል፡፡ መልሶ እንደ አዲስ የሚተከል ነገር ዋጋ የሚያስከፍልና ደም አፋሳሽ ሊሆን የሚችል በመሆኑ፣ የቱ ጋ አጣጥመን መሄድ አለብን? የሚለው ጉዳይ ሰፊ ውይይት የሚያስፈልገው መሆኑን ዘሪሁን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ያዕቆብ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለብቻዋ የምትኖር ሳትሆን ከጎረቤቶቿም ሆነ ከዓለም ጋር መሳ ለመሳ ቆማ ጂኦ ፖለቲካዋንም አስማምታና ቀምራ አስተዳደሯን በሚገባ መሥራትና ውጤታማ ማድረግ ስላለባት አንድነቷን፣ ሉዓላዊነቷን የግዛትም ሆነ የአገሪቱ የክብር ጉዳይ ሳይነካ ለወደፊት ማሰብና ለዚህ የሚሆን ሕገ መንግሥት ማበጀት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽን ከሚሠራባቸው የአጀንዳ ሐሳቦች በየቦታው የሚነሱትን ጥያቄዎች በመንግሥት ውሳኔና በሕግ ማዕቀፍ ለወደፊትም ጥያቄዎቹ መፍትሔ አግኝተው፣ ኅብረተሰቡ ዳግም በማይቸገርበት ሁኔታ እንዲሠራበት የሚያደርግ ሊሆን እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...