Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አትላስ ሆቴል አካባቢ የተሳፈርኩበት ከቦሌ ወደ ካዛንቺስ የሚያመራው ሚኒባስ ታክሲ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እየደረሰ ሳለ፣ ‹‹…እየደረስኩ ነው አኢሴማ መዝናኛ ጠብቀኝ…›› የሚል ድምፅ ከመጨረሻ ወንበር ጥግ ተሰማ፡፡ በአርባዎቹ መጨረሻ ውስጥ ያለ የሚመስለው ጎልማሳ እንደገና፣ ‹‹… ካዛንቺስ 32 ቀበሌ ያለው አኢሴማ መዝናኛን አታውቀውም እንዴ… እየደረስኩ ነው መጣሁ…›› እያለ ከወዳጁ ጋር በስልክ ሲያወራ እኔ ደግሞ፣ ‹‹ወይ ጉድ በዚህ ዘመን አኢሴማን የሚያስታውስ ይገኝ…›› እያልኩ ከራሴ ጋር ማውጋት ጀመርኩ፡፡ በደርግ ዘመን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ)፣ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አኢወማ) የሚባሉ አደረጃጀቶች በዚህ ዘመን በትንሹም ቢሆን አስታዋሽ እንደማያጡ ብረዳም፣ ድንገት ታክሲ ውስጥ የአኢሴማ ስም ሲጠራ እኔ ደግሞ ወደ ወጣትነቴ ዘመን ነጎድኩ፡፡

እኛ የ1970ዎቹ ወጣቶች ደርግ ኢሕአፓንና መኢሶንን በየተራ ካስወገዳቸው በኋላ፣ በቀበሌዎቻችን በግዳጅ የተደራጀንበት አኢወማ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ያኔ የአኢወማ አባል ያልሆነ ወጣት ለትምህርት፣ ለውጭ ጉዞ፣ ለሥራና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የአኢወማን ይሁንታ ካላገኘ ዕድሉ ያመልጠው ስለነበር አባል መሆን የግድ ነበር፡፡ በአኢወማ ስብሰባዎችና በምሽት የጥናት ክበብ አለመሳተፍ ዋጋም ያስከፍል እንደነበረ አልረሳውም፡፡ ግዳጅ የበዛበት አባልነት ስለነበረው ወጣቶች በአኢወማ ደስተኞች አልነበርንም ማለት ይቻላል፡፡ እኛ የዚያ ዘመን ወጣቶች ባልበሰለ አዕምሮ የሶሻሊዝምን መፈክር አንግበን ሲከሽፍብን፣ ሙሉ በሙሉ ለምዕራባውያን ፕሮፓጋንዳ በመጋለጣችን የአኢወማ ነገር ይጎመዝዘን ነበር፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ ከቀበሌም ሆነ ከአኢወማ ጋር የነበረን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀበሌዎቻችንን ከሌላ አካባቢ ለመጡ አስተዳዳሪዎች ወይም ገዥዎች አሳልፈን እንድንሰጥ አድርጎናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከደርግ ውድቀት በኋላ ቀበሌዎቻችንም ሆኑ ሌሎች የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የሚመሩት በእኛ ሳይሆኑ፣ ከሌሎች አካባቢዎች በፖለቲካ ሹመት በሚመጡ ሰዎች እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ እኛ ከደርግ ጋር ተኮራርፈን አርቆ ማሰብ ስለተሳነን ቀበሌዎችን ስንሸሽ፣ ለስንት ነገር ሊጠቅሙን የሚችሉትን አኢሴማና አኢወማ ስናጥላላ በመጨረሻ ድርጅትም ሆነ መጠጊያ አልባ ሆነን ቀረን፡፡ በአጉል አራድነት ተጀቡነን ዛሬ ከመታወቂያ አቅም በገዛ ቀበሌያችን የሌሎችን ችሮታ እንጠብቃለን፡፡

እዚህ ላይ ለምን ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በክፍላተ ከተሞችና በወረዳዎች ውስጥ አመራር ሆኑ ወይም ተቀጣሪ ሆኑ የሚል ቅሬታ የለኝም፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው ቢሆን የሚኖርበትን አካባቢ አስተዳደር ሆነ አደረጃጀት እንደ ባዕድ ሲርቅ፣ የሚደርስበት ችግር ምን ያህል ሸንቋጭ እንደሆነ ለማስታወስ ፈልጌ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በካዛንቺሱ ሰውዬ የአኢሴማ መዝናኛ ቀጠሮ የሄድኩበት ትውስታ መለስ ሲልልኝ፣ ራሴን ጨምሮ ሌሎች አብሮ አደግ ጓደኞቼ ዛሬ የምንቆጭበት የያኔው ያልበሰለ ድርጊታችን እያብሰለሰለኝ ካዛንቺስ ወርጄ ወደ ጉዳዬ አቀናሁ፡፡

ማታ ቤት ገብቼ ይህ ጉዳይ ሊለቀኝ አልቻለም፡፡ እኛ በኢሕአፓ ላይ በተሰነዘረው ከባድ ምት ምክንያት በርካታ ታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በማለቃቸው፣ ኩርፊያችን ሥርዓቱ ላይ ቢሆንም ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን…›› አለች እንደተባለችው እንስሳ አገራችንን ማስታወስ ተስኖን ነበር፡፡ ከቤተሰብ ወደ ማኅበረሰብ፣ ከዚያም ወደ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ማደግ የነበረበት አስተሳሰባችን በመቀጨጩ፣ ቀበሌዎቻችንም ሆኑ አደረጃጀቶቻችን በጊዜው ‹‹ነፃ አውጭዎች›› በቁጥጥር ሥር ሲውሉና ሲበተኑ እንደ ሞኝ አጨበጨብን፡፡ ውሎ አድሮ ግን እኛው የዕርምጃው ሰለባ መሆን ስንጀምር ጊዜው ረፍዶ ነበር፡፡

አሁንም ከዚያ ባልተናነሰ ሁኔታ ውስጥ ያለን ይመስለኛል፡፡ የወጣቶችና የሴቶች ማኅበራት ወይም ሊጎች ተቋቋሙ ሲባል፣ እንደ ባይተዋር ከሩቅ አዳማጭ ሆነን ቀርተናል፡፡ ወረዳ ወይም ክፍለ ከተማ የምንሄደው ጉዳይ ሲገጥመን ብቻ ነው፡፡ ጉዳያችን ቶሎ እንዲያልቅም ለመማለጃ የሚሆን ጉቦ ጭምር ይዘን እንሄዳለን፡፡ ልጆቻችንማ የወረዳችንን በራፍ ዘልቀው ገብተው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እኛም ስብሰባ ሲጠራም ሆነ ለአካባቢ ጥበቃ ስንፈለግ የለንም፡፡ ችግር ገጥሞን ሄደን መፍትሔ ስንፈልግ ከምንገናኛቸው ሠራተኞችም ሆነ አመራሮች ጋር ለመግባባት ያዳግተናል፡፡

በቀደም አንዱ ወዳጃችን ለሚ ኩራ የሚባለው ጉደኛ ክፍለ ከተማን በተመለከተ አስገራሚ ነገሮች ሲነግረን ነበር፡፡ ይህ አዲስ ክፍለ ከተማ በእርግጥም ጉደኛ ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ ሙሉ አመራሩ ከዚህ ቀደም መበተኑን በሚዲያ ሰምቻለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ደግሞ የክፍለ ከተማው አመራሮች ‹‹ይቅርታ›› በመጠየቅ፣ ነዋሪዎችን በፍፁም ታዛዥነት ለማገልገል ‹‹ቃል ኪዳን›› መግባታቸውን እንዲሁ ከሚዲያ ተከታትያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ጉድ የሚሰማበት ክፍለ ከተማ አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ባላውቅም፣ ወዳጃችን የነገረን ነገር ግን የሚያሳዝን ነበር፡፡

አንዲት እህት ከአንድ ዓመት በፊት ከአሜሪካ መጥታ የሟች ወላጆቿን መኖሪያ ቤት በፍርድ ቤት አሳውጃ ባለመብትነቷን ታረጋግጣለች፡፡ የፍርድ ባለመብትነቷን ማረጋገጫ ይዛ ክፍለ ከተማ ሄዳ ፋይል ለማስወጣት ስትሞክር ግን ችግር ገጠማት፡፡ ፋይል ለማስወጣት 40 ሺሕ ብር ጉቦ ትጠየቃለች፡፡ በዚህ ብትል በዚያ ጉቦ ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ አቤቱታዋን የሚያዳምጥ ይጠፋል፡፡ ወደ ተለያዩ ኃላፊዎች ለመድረስ ያደረገችው ጥረትም ይከሽፋል፡፡ በመጨረሻ በድርድር 25 ሺሕ ብር ከፍላ ትገላገላለች፡፡ ‹‹ፈጣሪ ሁለተኛ እናንተ ዘንድ አይመልሰኝ…›› ብላ ነው ዕንባዋን እየረጨች ከክፍለ ከተማው የወጣችው ነበር ያለን ወዳጃችን፡፡

ሰሞኑን ደግሞ በየወረዳው ከቀበሌ መታወቂያ ጋር የሚነሳው ይኸው በሽታ ነው፡፡ አንዱ ነው አሉ፣ የካ አንደኛው ወረዳ ውስጥ መታወቂያ ለማግኘት 30 ሺሕ ብር አምጣ ሲሉት፣ ‹‹ዕድሜ ለብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በነፃ አሠርቻለሁ…›› ብሎ ጥሎ ሄደ የሚል መራራ ቀልድ ሰምቻለሁ፡፡ ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ መመሥረቱ እየተነገረና መራር ዕርምጃ ይወሰዳል እየተባለ ሲጠበቅ፣ ወረዳዎች ውስጥ የመሸጉ ነቀዞች ነዋሪዎች ላይ እየቀለዱ መሆናቸው ያንገበግባል፡፡ ጎበዝ አመራሩን መጨበጥ ባንችል እንኳ በድፍረት ነቀዞችን ማጋለጥ ለምን ያቅተናል?

(መክብብ ዳኛቸው፣ ከአዋሬ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...