ከአንድ ሳምንት በፊት በምዕራባዊው የዘመን አቆጣጠር መሠረት 2022 ተሸኝቶ አዲሱ 2023 የገባበት ነበር፡፡ ዓምና በዓለም አትሌቲክስ መድረክ በተካሄዱት ውድድሮች በተለይም የቤልግሬዱ 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሩውዝ (ሩጫ፣ ውርወራ፣ ዝላይ) ከዋክብት አትሌቶች ከቶኪዮ ኦሊምፒክ እስከ ዳይመንድ ሊግ ባሉ ውድድሮች ባለድል የሆኑትን ያወዳደረበት መድረክ ነበር፡፡
ቤልግሬድ ያልተገመቱና ያልተጠበቁ ነገሮችን አስተናግዳለች፡፡ ለዓመታት ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቅ ኃያል የነበረችው አሜሪካ ተስፈንጣሪዎቹን አትሌቶችን ለያዘችው ኢትዮጵያ መንበሩን ማስረከቧ አንዱ ያልተገመተ ገጠመኝ ነበር፡፡ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. በቤልግሬድ የስፖርት፣ የባህል ኩነቶችና ሌሎች ፕሮግራሞች የሚካሄድበት ‹‹ስታርክ አሬና›› በሚሰኘው ዓለም አቀፍ አዳራሽ የተከናወነውን የዓለም ሻምፒዮና ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ በአራት ወርቅ፣ ሦስት ብርና ሁለት ነሐስ አውራ ሆና ስታጠናቅቅ፣ አሜሪካ በሁለተኛነት የፈጸመችው ሦስት ወርቅን ጨምሮ በ19 ሜዳሊያዎች እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚያው ዓመት በአሜሪካ ኦሪገን በተከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ ውድድሩን በ13 ወርቅ፣ 9 ብርና 11 ነሐስ ቀዳሚ ስትሆን፣ ኢትዮጵያ በ4 ወርቅ፣ 4 ብርና 2 ነሐስ ሁለተኛነቱን ስትጨብጥ፣ ጃማይካ በ2 ወርቅ፣ 7 ብርና 1 ነሐስ በሦስተኛነት ፈጽማለች፡፡
የዓምናውን ውድድሮች ውጤቶችን የመዘነው የዓለም አትሌቲክስ በየጊዜው እንደሚያደርገው፣ የዓመቱን የ2022 ምርጥ 10 አትሌቶች ከሩጫና ከሜዳ ተግባራት፣ እንዲሁም ምርጥ 10 የአትሌቲክስ አገሮች ብሎ ምርጫውን አከናውኗል፡፡ ለምርጫው ዋነኛው መለኪያ ያደረገው የኦሪገኑ የዓለም ሻምፒዮናን እንደሆነም ገልጿል፡፡
በዚሁም መሠረት በወንዶች 10ሩ ምርጥ የትራክ (የሩጫ) አገሮች ብሎ ከዘረዘራቸው በቀዳሚነት በ118 ነጥብ ያስቀመጠው አሜሪካን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ20 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ኬንያ (46 ነጥብ)፣ እንግሊዝ (28 ነጥብ)፣ ካናዳ (24 ነጥብ) ሆነዋል፡፡ ጃማይካና ዑጋንዳ እንደ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ነጥብ 5ኛ ሆነዋል፡፡ በ8ኛነት ኖርዌይና ስፔን (17 ነጥብ) ሲቀመጡ ደቡብ አፍሪካ (12 ነጥብ) 10ኛነቷን ጨብጣለች፡፡
በሴቶች ምድብ ጃማይካ (75 ነጥብ) መሪነቱን፣ አሜሪካ (74 ነጥብ) ሁለተኛ ስትሆን ኢትዮጵያ (60 ነጥብ) ሦስተኛነትን አግኝታለች፡፡ ተከታታዮቹን እስከ አሥረኛ ያሉትን ደረጃዎች እንግሊዝና ኬንያ (39 ነጥብ)፣ ኔዘርላንደስ (20 ነጥብ)፣ ናይጄሪያ (13 ነጥብ) ካዘኪስታን (12 ነጥብ) ባሃማስ (10 ነጥብ) አግኝተዋል፡፡
በ1,500 ሜትር የ2022 ምርጥ 10 አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ግማሾቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሁለተኛነትን ያገኘችው ጉዳፍ ፀጋይ (3፡54.21) ስትሆን ቀዳሚዋ ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፕዬጎን (3፡50.37) ናት፡፡ ከ4ኛ እስከ 6ኛና 10ኛ ደረጃን የያዙት ድርቤ ወልቴጂ (3፡56.91)፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ (3፡56.94)፣ ሒሩት መሸሻ (3፡57.30) አክሱማይት እምባዬ ናቸው፡፡