Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሃይማኖት አባቶች ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሚናቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል!

የሃይማኖት አባቶች ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሚናቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል!

ቀን:

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

  1. እንደ መንደርደሪያ

እ.ኤ.አ. በ2015 በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላምን ለማስፈንና ግጭቶችን ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎችን ሚና በተመለከተ ከኢጋድ አባል አገሮች የተውጣጡ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች፣ ‹‹IGAD Countries Religions Leaders Consultation on the Welfare of the Region›› በሚል መሪ ቃል የተሳተፉበት አንድ ስብሰባ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ነበር፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ ‹‹Peace and The Human Race›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው የሚከተለውን ሐሳብ አንስተው ነበር፣ ይህን የብፁዕነታቸውን ሐሳብም ለጽሑፌ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ወደድኹ፡፡

ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደገለጹትም፣ ‹‹ሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት ጎልቶ በሚታይበት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው ሕዝቧ አማኝ በሆነባት አገር የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት፣ ግጭቶቹ አስከፊ ወደሆነ ደም መፋሰስና ጦርነት እንዳያመሩ በሰላምና በዕርቅ እንዲቋጩ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡

ታሪካዊ አብነቶችን በማንሳትም፣ ‹‹የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በተለይም ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን የሚገኙትን ሦስቱን ታላላቅ ሃይማኖቶችን ጁዳይዝምን፣ ክርስትናንና እስልምናን በሰላም ተቀብላ ያስተናገደች፣ የዘር/የብሔር/የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ ወዘተ. ልዩነት ሳያግዳት፣ ከፍ ባለ ሰብዓዊነትና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ ‹ሰላምና ፍትሕ› በፅናት የቆመች አገር መሆኗን ለዓለም ያሳየች ናት፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡

ስለሆነም ይላሉ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እነዚህን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ መልካም እሴቶቻችንን ከፍ በማድረግ እኛ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች፣ በአገራችን ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናና በአጠቃላይም በአፍሪካና በመላው ዓለም ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩና የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ምልክት (Symbol) እንድትሆን በማድረግ ረገድ ደግሞ፣ የሃይማኖት ተቋማት የነበራቸውና አሁንም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን አቡነ ያዕቆብ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው አስምረውበታል፡፡

በዚህ የብፁዕነታቸው ሐሳብ መንደርደሪያነት ወደ ዛሬው ጽሑፌ ዋና ሐሳብ ላምራ፣

  1. ግጭቶችን በመፍታት ረገድ የሃይማኖት አባቶችን ሚናን ማጠናከር

‹‹Throughout history, religious leaders have had a significant role to play in the protracted nature of conflicts between Ethiopia’s diverse identities.›› (International Journal of Peace and Development Studies)

ግጭቶችና አለመግባባቶች በየትኛውም ዓለም ውስጥ የነበሩ፣ ያሉና፣ ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ የተግባር ውጤቶች መሆናቸው አሻሚ ጉዳይ አይደለም። ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ ለግጭቶቹ መነሻ ተደርገው የሚሰጡት ምክንያቶች፣ በቅርፅም በይዘትም የሚቀየሩበት ሒደት በጣም ለየት ያለ የመሆኑ እውነታ ነው ሥጋታችንን ከፍ የሚያደርገው፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገራችን ብሔርን/ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን፣ የተፈጥሮ ሀብትን፣ ወዘተ. መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ በዚህም በርካታ ወገኖቻችን ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በነጋ ጠባ እንድንፈራና እንድንሠጋ የሚያደርጉን አሁንም ድረስ ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሔ ያልተበጀላቸውና ደም አፋሳሽ ለሆኑ ግጭቶች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከፊታችን ተደቅነውብን አሉ፡፡

ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምንም እነዚህን መሰል ግጭቶች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም ግጭቶቹ ከመባባሳቸውና ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት አንዳች መፍትሔን የሚያመላክቱ፣ በሕዝቦች መካከል ዕርቅና ሰላምን በማስፈን በማኅበረሰቡ መካከል ላቅ ያለ ክብርና ሥፍራ የሚሰጣቸው የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን ቁልፍ የሆነ ሚና በማጠናከር ረገድ፣ ለውይይት የሚረዳን ጥቂት ሐሳቦችን ለመጨመር ወደድኩ፡፡

ብሪጊት ብሮክ (ፕሮፌሰር) የተባሉ የግጭት አፈታት ምሁርና አጥኚ እ.ኤ.አ. በ2001 በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርሲቲ ‹በዕርቅና በሰላም› ጉዳይ በተካሄደ አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ፣ ‘‘Indigenous Conflict Resolution in Africa’’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣

‹‹የአፍሪካ አገሮች ያሉባቸውን የእርስ በርስ አለመግባባትና ግጭቶች ለማስወገድ የምዕራቡ ዓለም በሚያስቀምጠው መፍትሔ ሐሳቦች ብቻ ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ የረጅም ዘመናት ታሪክና ጥልቅ የሆነ መሠረት ወዳላቸው ወደ ራሳቸው ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና መፍትሔዎች ማተኮር አለባቸው፤›› ብለው ነበር፡፡

የፕሮፌሰር ብሮክ መፍትሔ ሐሳብ ኢትዮጵያ የዓለማችን ታላላቅ የሆኑ ሃይማኖቶች መሠረት በመሆኗ፣ አብዛኛው ሕዝቧም ሃይማኖተኛ፣ የረጅም ዘመን ታሪክና ሥልጣኔ ባለቤት፣ አብሮ በሰላም የመኖር ጠንካራ ባህል ባዳበረ ማኅበረሰብ መካከል በእጅጉ ተቀባይነት ያለውና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሔ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ በሃይማኖቶቻችንና በባህላችን ውስጥ ለዘመናት ተከብረው የዘለቁ፣ የአብሮነት፣ የዕርቀ ሰላም እሴቶቻችን ዛሬ ዛሬ እዚሁ አፍንጫችን ሥር እየተዳከሙ መሆናቸውን እያየን ነው፡፡

እንደ አገርና እንደ ሕዝብ በሰላምና በወንድማማችነት መንፈስ አስተሳስረውን የቆዩት በእጅጉ ልንኮራባቸውና ልንጠብቃቸው የሚገቡን የሰላምና የዕርቅ መሠረት የሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እየተናዱብን ስለመሆናቸው፣ በርካታ ማሳያዎችን መጥቅስ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ለሃይማኖቱና ለባህሉ ከፍተኛ ግምትና ቦታ በሚሰጥ እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር መንግሥት፣ ሕግ፣ የፍትሕ ተቋማትና የፀጥታ ኃይሎች ብቻቸውን ፍትሕን፣ ዕርቅንና ሰላምን ያሰፍናሉ ማለት ብዙ ርቀት ሊያራምደን እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡

የሃይማኖት ተቋማት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭቶችን በመፍታት፣ ሰላምንና ዕርቅን በማስፈን ረገድ ያላቸው ሚና እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይሁን እንጂ አገራችን አሁን ካጋጠማት ፖለቲካዊ ቀውስና የሰላም መደፍረስ አንፃር፣ የሃይማኖት አባቶች የሚገባቸውን ሚና በቅጡ እየተወጡ ነው ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እዚህም እዚያም አንዳንድ ሙከራዎች እንዳሉ ባይካድም ውጤታማነታቸውን፣ ሊኖራቸው የሚችለውን ዘላቂነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን በተመለከተ ግን ብዙዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በእርግጥም የረጅም ዘመናት የሃይማኖት ታሪክ፣ ጠንካራ የሆነ የሃይማኖትና የባህል እሴቶችን እንዳዳበረ ሕዝብና አገር ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ተገቢና አሳማኝ ነው፡፡

ምንም ይሁን ምንም ግን የሃይማኖት አባቶች በአገራችን የሚከሰቱ ግጭቶችን በማብረድና መፍትሔ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ አይካድም፡፡ ‹‹Minority Rights Group International›› የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት፣ በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ አገሮች የሚነሱ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት በአገር፣ በአኅጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሞከሩ ያሉ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና ዕርቀ ሰላምን ለማውረድ እየተደረጉ ያሉ ምዕራባዊ/ዘመናዊ ተኮር ጥረቶች በዋነኛነት ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች የተመለከተ ነው፡፡

ግጭትና አለመግባባት በሰፈነባቸውና አንዳንዴም እነዚህ አለመግባባቶችና ግጭቶች ተባብሰው ወደ እርስ በርስ ጦርነት በሚያመሩባቸው ማኅበረሰቦች መካከል፣ የቆዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ተገቢው ትኩረት በመነፈጋቸውና ይህን ሊፈጽሙና ሊያስፈጽሙ የሚችሉ በማኅበረሰቡ መካከል የታፈሩ፣ የሚፈሩና የሚከበሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰቡ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በሚገባ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ አለመቻሉ ወይም ጭራሹን ባለመፈለግ በተለያዩ ደረጃዎች መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ የፍትሕ አካላትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የግጭቶቹን ምንጭ ከሥሩ ለማድረቅና ለመፍታት እያደረጉት ያለው ሙከራ እምብዛም ስኬታማ እንዳልሆነ ነው፣ ይህ ሪፖርት ይፋ ያደረገው፡፡

ሪፖርቱ ለማሳያነት ከተጠቀመባቸው አገሮች መካከልም በሰሜናዊ ኡጋንዳ በካራሞጃ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረና አካባቢ በሚኖሩ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚነሱ ግጭቶችን በዋቢነት ያነሳል፡፡ በእነዚህ አካባቢ የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት መንግሥትም ሆነ በሰላምና በግጭቶች አፈታት ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የእነዚህ ሕዝቦች ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት ባላማከለ መንገድ የሚወስዷቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች አቅመ ደካማና ዘላቂነት የሌላቸው ጊዜያዊ ብቻ እንደሆኑ ነው የሚገልጸው፡፡

የ‹ማይኖርቲ ራይት ኢንተርናሽናል› ሪፖርት በማጠቃለያውም

በእነዚህ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት የቆየው ባህላዊው የግጭት አፈታት ዘዴና የሃይማኖት አባቶችን ሊኖራቸው የሚችለውን ጉልህ ሚና ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ባህላዊ የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከዘመናዊው አኗኗር ዘዴ፣ ወቅታዊ ከሆነው የፖለቲካ ሥርዓትና ከመንግሥታዊ የፍትሕ ተቋማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመፍትሔ አካላት የመሆን ትልቁ ፋይዳቸው እየተዘነጋ እንዳለ ነው የደመደመው፡፡

ስለሆነም መንግሥትና የመንግሥት አካላት የሚወስዷቸው ፖለቲካዊ መፍትሔዎችና ዕርምጃዎች በራሳቸው በቂ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምንም በአገራችን በተለያዩ ክልሎች የሚከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችን ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም ለአፍሪካና ለመላው የሰው ልጆች ኩራት የሆኑና እንደ አገርና እንደ ሕዝብ በፍቅር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ በሰላምና በአብሮነት መኖር እንችል ዘንድ በአገራችን ለዘመናት የኖሩት የግጭት አፈታትና ዕርቀ ሰላም የማውረድ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መልካም የሆኑ እሴቶቻችን ተጠናክረው የአንድነታችን ውበት፣ ጌጥና ሽልማት ሆነው ይቀጥሉ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ጉልህ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉት ይገባል እላለሁ፡፡

በመጨረሻም በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ያከበርነው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሰላምና ዕርቅ የተሰበከበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ የሰማይ ሠራዊት መላዕክትና እረኞች በአንድነት ሆነው፣ ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ!›› ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ! በማለት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና ዕርቅ መደረጉን የምሥራች የሰበኩበት ነውና የፈጣሪ፣ የአምላክ ፍፁም ሰላም በኢትዮጵያ፣ በምድራችን ይሰፍን ዘንድ በመመኘት ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ሰላም!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...