Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበዝርፊያ አቀነባባሪዎች ላይ ትግል መጀመሩ እንደ አዲስ ምዕራፍ ይታይ!

በዝርፊያ አቀነባባሪዎች ላይ ትግል መጀመሩ እንደ አዲስ ምዕራፍ ይታይ!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

መንግሥት በምንገኝበት ወቅት ሙስናና ብልሹ አስተዳደር ሕዝብን ከማራቆቱ ባሻገር፣ ለአገራዊ አለመረጋጋቱም አሉታዊ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በየአካባቢው ያለው ጥገኛ መዋቅርና በሕዝብ ሀብት ምዝበራ ላይ የተሰማራው ስብስብ አገር ተረጋግቶ፣ ሥርዓት ሲቃና ሌብነቱ ስለሚጋለጥበት ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጨ ዕድሜውን ለማራዘም እደሚሠራ ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡ ዋነኛና ወቅታዊ ፈተና ለመሆኑም ብዙዎች ተስማምተውበት ያደረ እውነታ ነው፡፡

ይህን የዕድገት ፀርና የኢፍትሐዊነት በር የሆነ አሠራርና ተግባር በአገር ላይ ለማባባስ ተግተው ከሚሠሩት መካከል ደግሞ፣ ጉዳይ ገዳይና ሕገወጥ ደላሎች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡  መጀመርያ ከደላላ እንጀምር፡፡ በመሠረቱ በአሁኑ ወቅት አዲስ አባባን በመሰሉ ከተሞች ያለ ምንም ድካም፣ የንግድ ፈቃድ ወይም የግብር ሥርዓት በቀን እስከ አሥር ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን፣ በንፋስ አመጣሽ ገቢ ብዙዎቹን ወደ ገበያ ሰባሪና ጉዳይ ገዳይነት እየቀየረ የመጣ ዘርፍ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

- Advertisement -

አለፍ ሲል ደግሞ በደላላ ስም በተለይ በመሬት ዘርፍ መዋቅሩ በተደራጀ መንገድ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት የተዘረጋ፣ ጉዳይ ገዳይና አመቻች ኃይል መኖሩን መስማት ያስደነግጣል፡፡ እርስ በርሱ ተቆላልፎ ያለ እሱ ምንም ነገር የማይፈጸምበትና በእሱ ምክንያት ደሃው ይበልጥ እየጎበጠ፣ ሹመኛውና ጥገኛው ባለሀብት ተብዬ ስግብግብ ይበልጥ እየናጠጠ የሚቀጥልበትን፣ የራሱን ሥርዓት መፍጠር የቻለ ደላላ በአንድ ጊዜ የመጣ ባይሆንም ቢያንስ የ20 እና 30 ዓመታት ልምድ የዳበረበት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ሊገታው ግን ግድ ይላል፡፡

ከለውጡ ወዲህ በቅርቡ ጠንከር ያለ ትግል ሲጀመር በደላላና ጉዳይ ገዳይ ላይ ጭምር ማነጣጠሩ ይበል የተሰኘውም ለዚሁ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ያለውን ሰፊ መሬት፣ እንደ ሲሚንቶና ማዕድናት ያሉ ግብይቶችን ቀደም ሲል በመዋቅሩ ውስጥ የነበሩ፣ በፀጥታና መሰል ዘርፎች ለመንግሥት ቀረብ ያሉ ሰዎች ሁሉ ተሰግስገው ሲራኮቱበት መክረማቸውን መንግሥት በቂ መረጃ እንደደረሰውም ያሳያል፡፡ አንዳንዶቹ በመቶ ሚሊዮን የሚገመት ሀብት እንዳላቸው በዕግድ ወቅት የታየ መሆኑ  ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው፡፡ 

በአሁን ወቅት የአገሪቱን አንዳንድ ዘርፎችና እንቅስቃሴዎች ተቆጣጥሮ እንደፈለገው የሚያሽከረክረው ኃይል መዋቅሩን ብቻ ሳይሆን፣ ውስጥ አዋቂ ጉዳይ ገዳይና ደላላውን የያዘው ነው እየተባለ ነው፡፡ እየተነቃበት መሆኑ እንጂ የመሬትና የቤት ዋጋ እየተመነ፣ አስደንጋጭ በሆነ የምንዛሪ ተመንና የዋጋ ግሽበት ዜጋውን እያስጨነቀ ያለ ኃይለኛ ስብስብ ነው፡፡ ይህ ኃይል ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ በብሔርና በማንነት ጭምር እየተቧደነ፣ በነጠላ ሳይሆን በግብረ ኃይል የሚንቀሳቀስበት አቅም አደራጅቶ የሚገኝበት ሁኔታ ሊኖር መቻሉ ‹‹ወዴት እየሄድን ነው?›› የሚል ጥያቄ በየልቦናችን ማሳደሩ የታመነ ነው፡፡ እናም ትግሉ ጥብቅና በጥናት የታጋዘ ሊሆን ይገባዋል፡፡

አስቀድሞ ነገር ደላላን ማን ከሰው ቆጥሮት? ማን ፊት ሰጥቶት? ማን አይዞህ ብሎት?… ወዘተ ነው እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው? የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ብዙዎች  እስከምናውቀው ድረስ ደላላ በይፋ መታወቅ የጀመረው ከደርግ ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ ደርጉ ‹‹የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት›› በሚል አዋጅ የዜጎችን ሀብት ያላንዳች ርህራሔ ወረሰ፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ለተከራዮች ይዞታ ብሎ ሰጠ፡፡ አማላጅና ውስጥ አዋቂ ደላላ ብቅ ብቅ ያለውም ያኔ ነው፡፡

በጊዜው ደሃውና ጭሰኛው ቤት ቢያገኝም ላቡን አንጠፍጥፎ ያፈራው ባለይዞታ ደግሞ ባዶ እጁን አጨብጭቦ ቀረ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‹‹ቤት አለኝ… መሬት አለኝ…›› የሚል ሰው ጠፋ፡፡ በንጉሡ ጊዜ ቤት ለማከራየት እንኳ ደላላ አያስፈልግም ነበር፡፡ በየመንደሩ ‹‹የሚከራይ ቤት አለ›› ተብሎ በየመዝጊያው ላይ ይለጠፋል፡፡ አንኳኩቶ ገብቶ ቤቱን ዓይቶና ተስማምቶ መከራየት ብቻ ነበር፡፡ የቤት ኪራይ ‹‹ቅድሚያ ክፍያ›› የሚባል ነገር የለም፡፡ ቅድሚያ ክፍያ የመጣው ደላላ ከመጣ በኋላ ነው (ደላላ መኖሩ ባይጠለም ዋጋ ወሳኝና ገበያ ረባሽ እስኪሆን ዕድል ማግኘቱ ግን በየትኛውም መስክ ቢሆን ሃይ ባይ የሚፈልግ ነው)፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደላላው ገንዘቡን ይዞ መሄድ ስለሚፈልግና ወር ድረስ መጠበቅ ስለማይችል፣ ‹‹ቅድሚያ ተቀበሉ›› እያለ አከራዩን ሁሉ አስተማረው፡፡ ተከራዩ ገብቶ ወር ተቀምጦ በወሩ መጨረሻ መክፈል የነበረበት ባህል በደላላ ምክንያት ተሽሮ፣ ተከራይ ተበድሮና ተለቅቶ ቅድሚያ እንዲከፍል ተፈረደበት፡፡ ይህ ባህል እነሆ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ የኖርክበትን ሳይሆን ገና ወደፊት የምትኖርበትን መክፈል የጀመርከው በደላላ የተነሳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በላይህ ላይ የሚያከራየውና እያስወደደ የሚሸጠው ሁሉ ይኸው ኃይል ነው፡፡ ያውም አብዛኛው የኮሚሽኑን ይቀበላል እንጂ የመንግሥትን ድርሻ የሚሰጥበትን ሥርዓት ጨርሶ አያውቀውም፡፡

እንደዚያም ሆኖ በቀደመው ጊዜ ደላላ ቤት፣ መኪና፣ መሬት ለማሻሻጥ አንዳችም የጣልቃ ገብነት ሚና አልነበረውም፡፡ ቀድሞ ነገር ማን አስጠግቶት? ምን ጥልቅ አድርጎት? ‹‹የሚሸጥ ቦታ አለ›› የሚል ይለጠፋል፡፡ መኪና ላይ ‹‹ይሸጣል›› ተብሎ የባለቤቱ የቤት ስልክ ቁጥር ይጻፋል፡፡ አለቀ ደቀቀ፡፡ ሄዶ ተነጋግሮ መገበያየት ብቻ ነበር፡፡ ከደርጉ ወዲህ ግን ባለይዞታዎች/ባለሀብቶች ስለፈሩና ስለተሸማቀቁ የሚከራይም ሆነ የሚሸጥ ነገር አለን ማለቱን ተውት ይላሉ አንጋፋ ታዛቢዎች፡፡ ይኼኔ ነው ደላላና ጉዳይ ገዳዩ ቀዳዳ አግኝቶ እጁን አስገብቶ መፈትፈት የጀመረው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ደላላው የመሬት ሥሪቱን መረጃና ሕግጋት መያዝ ብቻ ሳይሆን ከውልና ማስረጃ አንስቶ እስከ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማና ከተማ ድረስ ባለው መዋቅር ውስጥ የራሱ ሰው እያበጀ ነገሮች በአቋራጭ እንዲያልቁ የሚሠራ ነው፡፡ አለፍ ሲልም ሕገወጡን ይዞታ ወይም ሰነድ አልባውን በጥቅም ትስስር ሕጋዊ እያደረገ፣ ካርታ እያስወጣ በሚሊዮን ብሮች የሚካፈልና ሕዝብን የሚያራቁት መሆኑ በሕዝብ መታወቅ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

አንዳንዱ ሳያርስ፣ ሳይማር፣ ሳይነግድ፣ ወይ ውርስ ሳያገኝ በአጭር ጊዜ ባለዘመናዊ ተሽከርካሪና ቤት ብቻ ሳይሆን የሚሊዮን ብር ባለአካውንት እንዴት ሊሆን ቻለ? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገው ይኼኔ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለባለሥልጣናት መግባቢያና እጅ መንሻ በሚሊዮን ብሮች ስጦታ እስከ ማቀበል የሚደርሱ መሆናቸውም ውስጥ ለውስጥ እየተነገረ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቀላል ቁጥር የሌለው ደላላና ጉዳይ ገዳይ በሕግ ጥላ ሥር ሲውል ትንፍሽ ያለ የጠፋው፡፡

ለነገሩ ቀደም ባሉት ዓመታትስ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርንና አሁን ድረስ መከራው እየተረፈን ያለውን ስደት ያባባሰው ማን ነበር? ደላላ መረቡን እያሰፋ በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ሽፋን ዜጎችን ወደ ዓረብ አገሮች በሕገወጥ መንገድ ጭምር የመላክ ሴራ ውስጥ አልገባም ነበር? የማያውቀውን አገር ‹‹ሥራ ሞልቷል… ገንዘብ ሞልቷል… እዚህ ሆነሽ በአሥር ዓመት የማታገኘውን እዚያ በስድስት ወራት ታገኛለች… ለቤተሰቦችሽ ትልኪያለሽ…›› እያለ በማማለል ስንቱን ዜጎች ለሰቆቃ ዳረገ? ሕገወጥ ደላላ ማለት ይኼ ነው ብላችሁ ተረዱልኝ፡፡

አሁን ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለጠጠ ዕቅድና በጋለ ፍጥነት እየተራመደ ለመሄድ ሲችል፣ በዘረፋና በአሻጥር እንዲበከል ከሚያደርጉ አካላት አንዱ ሆኗል፡፡ ጉዳይ ገዳዩና ሕገወጥ ደላላው በወቅታዊነት የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም፣ ባለ ገንዘቦችን ከላይኞቹ አመራሮች ጋር በማገናኘት ከቀበሌ እስከ ቢሮዎችና ሚኒስትሮች ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን ማቀባበል ጀምሯል፡፡

ዛሬ ዛሬ በደላላ ካልሆነ በቀር የሚፈጸም ጉዳይ ጠፋቷል የሚሉትም የበዙት ለዚሁ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በደላላ/ጉዳይ አስጨራሽ በኩል ሆነ፡፡ በደላላ በኩል መንቀሳቀስ ባህል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ደላላው የገበያው አድራጊ ፈጣሪ ለመሆኑ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የገጠመውን ግሽበት ማየት ይቻላል፡፡ ጉዳዩም በጣም ተራ ከሆነ የዕብደትና የቅጥፈት ተግባር ወደ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ድረስ መነጋገሪያ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ ሕዝቡ ግን ከልክ በላይ ተማረረ፣ በእጅጉ ተቸገረ፡፡

ደላላውን እዚህ ደረጃ ያደረሰው ምንድነው? ደላላውን ያጎለበተው የመልካም አስተዳደር ችግር መኖር ነው? ወይስ የመልካም አስተዳደር ችግርን የፈጠረው የደላላው መኖር ነው? ቃሉ ራሱ ተዘበራረቀ፡፡ መልካም አስተዳደር (Good Governance)፣ ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚሉ ቃላት አንድም ሦስትም እየሆኑ ሄዱ፡፡ አንዱ አንዱን እየጎተተ ያመጣል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ባለበት ሁሉ ሙስናና አቋራጭ መንገድ አሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔ አገኘ ማለት አብረው የሚመጡ ተያያዥ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ አገኙ ማለት ነው፡፡

በመጀመርያ የመልካም አስተዳደር ችግር በእርግጠኝነት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችል ችግር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነቱና ፅናቱ በእርግጥ ካለ የመልካም አስተዳደርን ችግር ያለ ጥርጥር መፍታት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጥገኞች መንግሥትን የጠቀሙና የቀረቡ መስለው፣ አሁን ባለው የማንነት ፖለቲካ ሰበብ ታዝለው፣ ሕግ፣  ሥርዓትና መርህን እየጣሱ የሚሠሩበት ውሽልሽል አካሄድ ካልታረመ ፍትሕና ብልፅግና ዕውን ሊሆን አይችልም፡፡ አገርንም ክፉኛ የሚያዳክም ድርጊት ነው፡፡

መልካም አስተዳደር ማለት እኮ ሌላ ነገር ሳይሆን በተቻለ መጠን በቅልጥፍና፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት ውሳኔን የማሳለፍና ተግባራዊ የማድረግ ሒደት ነው፡፡ ‹ውሳኔ› ሲባል ደግሞ ፍፁምነት ያለው፣ ስህተት የሌለበት፣ ትክክለኛ የሆነ ማለት ብቻ ሳይሆን ካሉት አማራጮች መካከል በተቻለ መጠን ከአገሪቱ አቅም፣ ከሕዝቡ ፍላጎት፣ ከሚጠበቀው የዕድገት ውጤት፣ ወዘተ ጋር ሲታይ/ሲመዘን ተገቢ የሆነውን ውሳኔ ለማሳለፍ የተሻለ ሒደትን የተከተለ አሠራር ማለት ነው፡፡

ይህን የአሠራር ሒደት ለመከተል ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው የመልካም አስተዳደር መርሆዎች አሉ፡፡ ለመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ዋናው የባህሪ መሣሪያ ‹‹ተጠያቂ›› የመሆን ባህሪ ነው፡፡ ተጠያቂነት ለመልካም አስተዳደር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ማለት የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት በሚያስተዳድሩትና በሚወክሉት ሕዝብ ስም ለሚያሳልፉት የትኛውም ውሳኔ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው፡፡ ግለሰቦች (ሙያተኞችና አመራሮችም) ባሳለፉት ውሳኔ ምክንያት ለተፈጠሩ ጉድለቶች/መስተጓጎሎች መጠየቅና መልስ መስጠት አለባቸው ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት መርህ ‹‹ግልጽነት›› ነው፡፡ ዜጎች የውሳኔ አሰጣጡን ሒደት አስፈላጊነትና ተመራጭነት መረዳትና መከታተል መቻል አለባቸው፡፡ ማለትም ዜጎች መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ እንዴትና ለምን እንደሆነ በግልጽ ማየት መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ ውሳኔ የተሰጠው በየትኛው መረጃ ላይ ተመሥርቶ፣ እነማንን አማክሮ፣ በየትኛው የሕግ አግባብ ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ ዜጎች በግልጽ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ዜጎች ይህን ካላወቁ ማንም ሹመኛ እንደፈለገው ውሳኔ እየሰጠ የሕዝቡን ፍላጎት ሊበጠብጥ ይነሳል፡፡ አገርም ይቃወሳል፡፡ ግልጽነት ያስፈልጋል መባሉ ለዚሁ ነው፡፡

     ሦስተኛው መርህ ‹‹ሕጋዊነት›› ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ሁሌም በሕጉ መሠረት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት፣ ወይም በአስፈጻሚ አመራሮች ወይም በክልሎች ደረጃ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የአሠራር ሒደታቸው በአገሪቱ ሕግጋት መሠረት የተከናወነ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ ወይም ስለተለያዩ ጉዳዮች ለምሳሌ ስለሠራተኛ አስተዳደር፣ ስለጤና፣ ስለትምህርትና ስለመሬት ይዞታ፣ ወዘተ በተመለከቱ ከወጡ አዋጆችና መመርያና ደንቦች ጋር የተጣጣሙ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን አሁን በዚህ ረገድ ችግር አለ፡፡ በለውጥ ስም ባልተጻፈ ሕግ ለማስኬድ መሞከር እየታየ ነው፣ ልክ ግን አይደለም፡፡

ማንም እየተነሳ ካሉትና ከታወቁት ሕግጋት ውጪ የየራሱን ሕግ እያወጣ (አንዳንዴ በጥገኛው ደላላና በባለሀብት ተፅዕኖ) ወይም የሕጉን ትርጉም እያጣመመ ወይም ሆን ብሎ እየጣሰ ውሳኔ ሊሰጥ፣ ወይም በሌላ አካል ላይ ተፅዕኖ በማሳደር እስከ ቀበሌና ወረዳ ድረስ እጁን እያስገባ የፈለገውን ሰው በዘመድ፣ በአገር ልጅነት ወይም በሌላ የጥቅም ግንኙነት ሊጠቃቀም አይችልም፡፡ ይህ ከታሪክ አለመማር ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ሁሉም ዜጋ አገሪቱ ከምታመነጨው በረከት እኩል ተጠቃሚ መሆኑን እያሰበ መወሰን አለበት፡፡

አራተኛው የመልካም አስተዳደር መርህ ምላሽ ሰጪ (Responsive) መሆን መቻል ያለበት መሆኑ ነው፡፡ እንደ ማዕከላዊም ሆነ እንደ ክልል መንግሥትነቱ ሁልጊዜም መጣር ያለበት የሁሉንም ኅብረተሰብ ጥያቄ ለመመለስ/ለማሟላት ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ጥያቄ ውስጥ የተለያዩ ተወዳዳሪ ፍላጎቶች ቢኖሩም፣ እነዚህን ፍላጎቶች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በተገቢው ጊዜ ውስጥ ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት መቻል አለበት፡፡ ምላሽ መስጠት ያለበት በወቅቱ ነው፡፡ ማጓተትና ማመላለስ አይጠበቅበትም፡፡ ጉዳይ ገዳይ ሊዳከም የሚችለው በዚህ ትጋት ነው፡፡

አምስተኛው የመልካም አስተዳዳር የውሳኔ ሒደት መገለጫ ሁሉንም ያቀፈና በእኩል ለመመልከት የመቻል ባህሪ ነው፡፡ በውሳኔ ሒደት ውስጥ የሁሉም ሕዝብ ፍላጎት መታየት ወይም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ወገኖች (ቡድኖች) በተለይ ተጎጂ ወይም ተጠቂ/ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች በውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ውስጥ የመሳተፍ ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በማንነት ላይ የተመሠረቱ ክልሎቻችን፣ በውስጣቸው ላሉ አናሳዎችና ዜጎች መብና ጥቅም ብሎም ግዴታ መከበር በታማኝነት ካልሠሩ አገር አለን ማለት አይቻልም፡፡

    በሌላ በኩል መልካም አስተዳደር ውጤታማ የሚሆነው ‹‹አሳታፊ›› ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ (ሕዝቡ) እሱንና አካባቢውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ውስጥ ሁሉ እንዲሳተፍ መደረግ አለበት፡፡ ሐሳቡን መስጠት መቻል አለበት፡፡ ችግሮቹን መግለጽ አለበት፡፡ ተገቢውን መረጃ ማግኘት አለበት፡፡ የውሳኔ ሐሳቦችን የማቅረብ ዕድል ሊያገኝ ይገባል፡፡ ጥቅማቸው በተሟላላቸውና በደላሎች በኩል ሳይሆን ድምፁ መሰማት ያለበት፣ በትክክለኛዎቹ ተወካዮቹ አማካይነት የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ አካል መሆን መቻል አለበት፡፡

አሳታፊነት ሲባል ደግሞ ለተወሰኑ ቀናት ሕዝቡን ሰብስቦ ማንጫጫትና ‹‹አሳትፈናል፣ አወያይተናል›› ለማለት ሳይሆን፣ ከልብ የሕዝቡን ሐሳብ እንደ ግብዓት በመውሰድ ለተግባራዊነቱ መትጋትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የአንድ አገር ዜጎች እንደ መሆናችን በአዲስ አባባ ከባንዲራ፣ ከመዝሙርና ከአከላለል ጋር እየተነሳ ያለውን ውዝግብ መጥቀስ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ‹‹የአሳታፊነት›› መግለጫ ሌሎች አካላትንም ለምሳሌ የተለያየ ሕዝብ አደረጃጀቶችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ የሰብዓዊ መብትና የዕንባ ጠባቂ አካላትን በተለይ ሚዲያውን ያጠቃለለ መሆን አለበት፡፡ ከእነዚህ አካላት የሚመጡ ሐሳቦች ለመልካም አስተዳደር መስፈን ታላቅ ግብዓት እንደሚሆኑ መታመን አለበት፡፡

በአጠቃላይ እንኳንስ ጥገኛውና ደላላው ክፉኛ እየተገዳደረው ያለውን ፖለቲካ  ኢኮኖሚ ቀርቶ፣ በየትኛውም የተረጋጋ አገረ መንግሥት ውስጥም ቢሆን ትችት አንቀበልም፣ ጉድለት የለብንም ማለት ለመንግሥት አይጠቀመውም፡፡ ማናችንም ‹‹ሙሉ በኩለሄ እንዳልሆንን እናውቃለን›› ብሎ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ራስን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ገንቢውን ትችት ሁሉ ሊያጠፋ እንደመጣ ተቃውሞ መቁጠር ግን ይበልጥ አጥፊ ነው፡፡ በመዋቅሩ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ ያለውን የገነገነ ጉዳይ ገዳይነትና ሕገወጥነትን መታገል የሚቻለው ቅድሚያ ትግልን ከራስ ከመጀመር ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...