Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአንድ አራት ነጥቦች

አንድ አራት ነጥቦች

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

አንባቢያን ከልባቸው እንዲያውቁልኝ የምፈልጋቸው ጥቂት ሁነኛ ነጥቦች አሉኝ፡፡ ነጥቦቹ አዲስ አይደሉም፡፡ ብዙ ሐተታ የሚሹ አይደሉምና ሳላንዛዛ ላስቀምጣቸው፡፡ 

1ኛ/ ሀ) ሕወሓት ወደ ሰላም በመምጣቱ እናደንቃለን፡፡ የአገዛዝ ተግባሩ ግን መድበስበስ የለበትም፡፡ ለዕርቅም የሚበጀን እውነት እውነቱን መነጋገር ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕወሓት ቡድን ገና ከመነሻው ሌላ የፖለቲካ ቡድን በትግራይ እንዳይንቀሳቀስ የማጥፋት ተግባር ውስጥ ሲገባ፣ የትግራይ ሕዝብን ህሊና የብቻ ‹‹ርስቱ›› አድርጎ መቁጠሩ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ የትግራይን ሕዝብ አዕምሮ እንደ ማሳ ንብረቱ እንደፈለገው እያረሰ፣ የፈለገውን የሚዘራበት አድርጎ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡ ይህን የማሟላት ተግባሩም ከራሱ ድርጅታዊ ቅስቀሳ (ዘፈን፣ ጋዜጣ፣ ሬዲዮ) ውጪ ሌላ ዓይነት ሐሳብ የሕዝብ ጆሮ ዘንድ እንደይደርስ፣ ከደረሰም ልብ ውስጥ ውሎ እንዳያድር የማድረግ ጥረቱ፣ ‹‹አምስት ለአንድ›› በሚባል መዋቅር ሰውን በሰው እስከ መጠፈር ሄዷል፡፡ ጥፈራው ከመሥሪያ ቤት እስከ መኖሪያ ሠፈር ብሎም እስከ ቤተሰብ ድረስ እንዲረዝም ተደርጎ ቆይቷል፡፡ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ለውጥ ወደዚህ በኢትዮጵያ አያሌ አካባቢዎች ጥፍነጋው ውልቅልቁ ቢወጣም፣ የትግራይ ሕዝብ ግን ጥርነፋና የጥላቻ ውስወሳ ጠንክሮበት መነጠልንና ጦርነትን ‹‹ጥቅሜ›› እስከ ማለት ድረስ ተገዶ ነበር፡፡

እንደ ማንኛውም ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎትና ትግል መብት የለሽነትና ድህነት ከተንሰራፈበት የተዋረደ ኑሮውና ከጦርነት መላቀቅ ቢሆንም፣ ገዥዎቹ ይህንን ግብ ሲያገለግሉ አልኖሩም፡፡ የእነሱን የፖለቲካ ፕሮጀክትና ጦርነት የሕዝብ ተጋድሎ እያሉ ሕዝብ ላይ ሲጭኑ (ሕዝቡን ሲገለገሉበት) ነው የኖሩት፡፡ እነሱ ተጋድሎህ ነው/ዓላማህና ጥቅምህ ነው ያሉትን መቃረን ትግራዋይ የመሆንና ያለ መሆን፣ ትግራይን የመካድና ያለ መካድ ተደርጎ ይፈረጃል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በዚህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ተይዞ በስብሰባ መዋቅር፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚመጣ የሕወሓት ፕሮፓጋንዳ የሚግተውን ሁሉ ቢወድም ባይወድም (ከሃዲ ላለመባል) የእኔ እንዲል ተገዶ ኖሯል፡፡ የጥላቻና የበቀል አጠባ ህሊናው ላይ የወረደበትና የጦረኝነት ማገዶ የሆነውም በዚህ ዓይነት ግነዛ ተይዞ ነበር፡፡

ጦረኞቹ የሰሜን ዕዝ ላይ ዘግናኝ ነውር የፈጸሙበትና በመብረቃዊ ምት አወራረድነው የሚል ፉከራ ትን ያላቸው ሰዓት፣ ወደ አውሬነት የወረዱበት ሰዓት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ብዙ ብዙ ውለታ ለትግራይ የዋለ ሠራዊትን ለማረድ ያልተመለሱና መላ ኢትዮጵያን መከላከያ የለሽ የማድረግ በደል የፈጸሙ ሰዎች፣ ለቀሪው ሕዝብ ደግ ሐሳብና ርኅራኄ ይኖራቸው ነበር ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ በየትኛውም የዓለም ክፍል ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ጅልነት ነው፡፡ እናም አገራዊ ህልውናን ለማትረፍ በጊዜው ፈጥኖ ባለ በሌለ ኃይል መነሳት በጣም ትክክል ነበር፡፡ ጦርነት ከፋቾቹ በዚያን ጊዜ ስሜታቸው ለማንም እንደማይመለስና እንደማያዝን ለማየትም ሩቅ ጊዜ አልወሰደም፡፡ ከመቶ ሺዎች እስከ ሚሊዮን የሚደርስ የትግራይ ሰው አልቋል የሚለው ወሬ ይጋነንም አይጋነንም፣ የትግራይ ሰው ከሕፃን እስከ ሽማግሌ ያለ በቂ ሥልጠናና መሣሪያ እስከ ሦስት ዙር ወረራ በገፍ የገባበት ሁኔታ በራሱ የትግራይ ሰው ነፍስ እንደ ባሩድ አሻሮ እንደተቆጠረ ይጠቁማል፡፡ የትግራይ ሰው የቴክኖሎጂ መመጣጠን በሌለበት ጦርነት ውስጥ ገፍ በገፍ የተደፋውም፣ የቴክኖሎጂ ብልጫን በሰው ማገዶ ብዛት በማቻቻል ሥሌት ነበር፡፡ ይህም ሰው እንደ ባሩድ አሻሮ የመቆጠሩ ሌላ ጠቋሚ ነው፡፡ የትግራይ ሰው በዚህ ዓይነት ሒሳብ በገፍ መርገፍ ብቻ አልነበረም የደረሰበት፡፡ የትግራይ ሰው ጥላቻና በቀል እየተጋተ ምንም ሃይማኖትና ጨዋነት የሌለው ይመስል፣ ለወረራ በዘመቱ ሰዎቹና ታዳጊዎቹ አማካይነት በወገን ላይ ይቅርና በጠላት ላይ እንኳ የማይፈጸም ግፍ እንዲፈጽም ነበር የተደረገው፡፡ በነውር ሠሪነት ሰውን ማቆሸሽ ሌላ በደል ነው፡፡ አፋርና አማራ ውስጥ እስከ አዲስ አበባ መዳረሻ ድረስ እንዲያ ያለ አይደረግ ነውር በወገን ላይ መደረጉ ሌላ በደል ነው፡፡ ሲቪል ተቋማትንና የተራ ነዋሪዎች ንብረትን በዝርፊያና በውድመት ከመመንጠር ታልፎ ጭፍንና ዘግኛኝ ጥቃቶች በታዳጊዎችና በአዛውንቶች፣ ይባስ ብሎም በእንስሳትና በተክሎች ላይ የተፈጸመው ምን ባጠፉ? ምንም፡፡ ለምን ታዲያ? እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ የተካሄደው ግፍ ለሌላው ወገን የተላከ መልክዕት ነበረው፡፡ እናንተም አውሬያችሁ ወጥቶ ከትግራይ ውጪ በሚኖሩ የትግራይ ሰዎች ላይ ጭፍን ጥቃት እንድትፈጽሙ ተጋብዛችኋል የሚል፡፡ ለምን? የትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር አንደኛውን እንዲበቃቃ፡፡ የንጠላ ፕሮጀክትን ለማሳካት ሲባል የዚህ ዓይነት የመስዋዕትነት ግብዣ ማቅረብ ከጭካኔም ጭካኔ ነበር፡፡

አሁንም ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወደ እዚህ ይቃወሙናል/ያጋልጡናል የሚሏቸውን ሰዎች ስለማሰራቸው እየሰማን ነው፡፡ ከእንግዲህ ግን ከሕወሓታዊ አቋም የተለየ አቋም ይዞ በትግራይ መንቀሳቀስ በክህደት የሚፈረጅበት ምዕራፍ እየተዘጋ ነው፡፡ ሌላ ሐሳብ የያዘ ሰው/ቡድን እንደ ጠላት የሚሳደድበትና የሚዳፈንበት ምዕራፍ እያከተመ ነው፡፡ በአፈናና በማወናበድ የተካኑት አሮጌ ገዥዎች ዛሬም ከቀዘፉትና መሪህ ነን ብለው ሊፈናጠጡት ከቻሉ የትግራይ ሕዝብ ዕርም እስከ መብላት ድረስ በቁሙ አልቋል፣ ወይም ለዚህ ጊዜ የሚሆኑ ልሂቃን አጥቷል ያሰኛል፡፡ አንዳንድ የሕወሓት ቁንጮዎች እንደሰማናቸው ዛሬም ለሕዝብ ሲሉ እንደተዋጉና ያንን ሁሉ ሰው የማገዱበትን ጦርነት ተገደው እንደገቡበት ያለ ኃፍረት ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያለ ንግግር ፀፀትና ኃፍረት የማይነካካንና ወደፊትም የማንታረም ነን ከማለት ቁጥር ነው፡፡ እነሱ ጎበጡም ተገትረው ቀሩም ግን፣ ከእንግዲህ ለዚህ ዓይነት ሰዎች የሥልጣን ፈረስ መሆን ይቅርና፣ ፀፀት የለሽ ቅጥፈታቸውን ቆሞ ማዳመጥ እንኳ የውርደት ውርደት ነው፡፡ ግድ መሆን ያልነበረበትን የመቶ ሺዎች መስዋዕትነት የብልጣ ብልጥነት መዘባነኛ እንዲሆን መፍቀድም ነው፡፡ ከእንግዲህ የብሶት ረመጥን በሆድ ይዞ ሕዝብ የሚኖርበት ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ተሟላ የሚባለውም ያለ ፍርኃት በነፃነት የልቡን መተርተር የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ ሲገባ፣ የልቡን በመተርተሩም የደኅንነት አደጋ የማይደርስበት ሲሆን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ሐሳቦችን መስማትና ማማረጥ ሲችልና ያለ አፈና ያዋጣኛል ያለውን ቡድን መምረጥ ሲችል፣ መርጦ የሰቀለውንም ማፋጠጥና ከዚያም አልፎ በድምፁ መሳብ የሚችልበት ጉዞ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ ለትግራይ እንዲሆን የምንሻው በመላው ኢትዮጵያ እንዲሆን የምንሻው ነው፡፡

ለ) ሕወሓት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የከፈተውና ወደኋላና ወደፊት እያለ ሁለት ዓመት ያቆየው ጦርነት፣ በገዛ አገር ላይ የተከፈተ የወረራ ጦርነት ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል፡፡ አዎ፣ የጥላቻንና የጭካኔን ጣሪያ የነካ፣ ወገኔ ሳትልና ምንም ሳታስቀር ዝረፍ፣ አውድም፣ አቃጥል የሚል ምሪት የነበረው ጦርነት ነበር፡፡ በጥላቻ እየተወሰወሰ፣ በእህል ውኃ ገመድና በከሃዲነት ውንጀላ ተጠፍሮ የትግራይ ሕዝብ የተጋፈጠበትን ጦርነት አንዳንዶች ጁንታው ጦርነቱን ‹‹ሕዝባዊ አደረገው›› እያሉ ሲገልጹት ነበር፡፡ የሕወሓት ጦር የሕዝብ ማዕበል አዎ ነበረበት፡፡ ግን ሕዝብ ወዶ የገባበት አልነበረም፡፡ ጦርነቱ የሕዝብ ጦርነት (Popular/Peoples’ War) አልነበረም፡፡ ጦርነቱ የሕዝብ ዓላማ፣ የሕዝብ ጥቅምና ነፃ ተነሳሽነት የተቆናጠጠ አልነበረም፡፡ በአገር ላይ (በሰሜን ዕዝ የገዛ ወገን ላይ፣ በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ…) የተካሄደ የጥፋት ጦርነት ነው፡፡ የአገር መከላከያን ማረድ፣ አፋርና አማራ ውስጥ የሰዎችን ኑሮ ማውደምና ዘግናኝ ግፍ መፈጸም የትግራይ ሕዝብ ጥቅም አልነበረም፡፡ ሕወሓት የከፈተውን የግፍ ጦርነት የመከተውና የተቀናቀነው ጦርነት ግን አገራዊ ህልውናን የማትረፍና ግፍን የመተናነቅ ጦርነት ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ተመፃዳቂ የሚኖርበት ጦርነት አልነበረም፡፡ በሁለት በኩል የተላለቁት የአንድ አገር ልጆች ከመሆናቸው አኳያ፣ ጦርነቱን እርስ በርስ የተደረገ አሳዛኝና አሳፋሪ ጦርነት ነበር ብንለው ይገባዋል፡፡

ነገር ግን ‹እርስ በርስ›ን ‹ሲቪል ጦርነት› በሚል ትርጉም ወስደን ተሳስተን እንዳናሳስት መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ሲቪል ጦርነት ሕዝብ ለሕዝብ ወደ መፈሳፈስ የተሸጋገረበት ጦርነት ነው፡፡ ማንም ጀመረው ማን ሕዝብ ከሁለት በኩል ገንፍሎ የገባበትን መሰያየፍ ማስቆም ከባድ ነው፡፡ ምሬትና ቂሙም በቀላሉ አያቀራርብም፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት በጎንደር በትንሽ ሰበብ በውስን የክርስቲያንና የሙስሊም ምዕመናን ቱግታ የተለኮሰች ፀብ፣ ከጎንደር ተወንጭፋ ወራቤ ውስጥ እንደምን ለመቀጣጠል እንደሞከረች እናስታውሳለን፡፡ ያቺ እሳት በቶሎ ባይደረስባትና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፈጠረችው ተነካን ባይነት መሬት ላይ የመባዛት ዕድል አግኝቶ ቢሆን ኖሮ፣ እሳት ማጥፊያው ጭንቅ በሆነ ነበር፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ጦርነት በሁለት በኩል የዚያ ዓይነት ጅምላ ፀባይ ነው ያለው፡፡ ጦርነቱ ዓይነ-ስቡ ወደ ጠፋ የሕዝብ ለሕዝብ መተጫጨድ እንዲሸጋገር ታቅዶ ግን ተሠርቷል፡፡ አፋርና አማራ ውስጥ በሰዎች ላይ የተፈጸመው ነውር፣ ሕዝብ በአፀፋ ነውር እንዲጨማለቅ የተካሄደ ትክተካ ነበር፡፡ በፌዴራሉና በሌሎች ክልላዊ አስተዳደሮች ጥሪ የተነቃነቀው ሕዝብም ሆነ ሠራዊት ግን በትክተካው አልቀወሰም፡፡ የሕወሓት ሰርጎ ገቦች ውድመት እንዳያደርሱ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ከመውሰድ በቀር በየትም ሥፍራ የትግራይን ሰው በመብራት እየፈለጉ የመቅጠፍ ቁጣ ውስጥ አልገባም፡፡ በእስር የተንገላቱና በቅርብ ክትትል ውስጥ የነበሩ የትግራይ ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ፣ ከትግራይ ውጪ በሁሉም ሥፍራ የትግራይ ሰዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ነበሩ፡፡ በሥራ ገበታም ላይ ነበሩ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በሚመራው መንግሥትም፣ በፓርቲውም፣ በመከላከያውም ውስጥ ነበሩ፡፡ የፌዴራሉን መንግሥትና ኢትዮጵያዊነትን ደግፈው የሚንቀሳቁሱ የትግራይ ልጆች በኢትዮጵያም ውስጥ ከኢትዮጵያም ውጭ ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡

እናም ሕወሓት ጦርነቱን የሕዝብ ለሕዝብ ሊያደርገው ቢሞክርም አልሆነም፡፡ የቤተ እምነት ሰዎችን የፕሮፓጋንዳ አካሉ አድርጎ ‹‹የዓብይ መንግሥት የትግራይን ዘር ሊያጠፋ የተነሳ›› እንዳስመሰለ ቅስቀሳው ቢሆንማ ኖሮ፣ በጨካኝ የግፍ ጥቃቶቹ ሕዝብንና መንግሥትን ህሊና ለማሳጣት እንደተለፋው ልፋት ቢሆንማ ኖሮ፣ ከትግራይ ውጪ ባለ የኢትዮጵያ መሬት ያለ የትግራይ ሰው ባለቀ ነበር፡፡ ግን የፌዴራል መንግሥትም ሆነ ሌላው ሕዝብ በአፀፋ በቀል በትግራይ ሰው ላይ አልተነሳም፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በኩል የተካሄደው ጦርነትም አገርን እስከማፍረስ ድረስ የረዘመ ዓላማ የነበረውን የግፍ ወረራ የማስቆምና የማሸነፍ ነበር፡፡ በጦርነቱ ጊዜ ቤት እስከ መፈተሽና እስከማሰር የደረሰ ጥንቃቄ ባይወሰድ ኖሮ፣ እንደ እነ ኮምቦልቻ አዲስ አበባ በሰርጎ ገቦች አይሆኑ ሁኔታ በሆነች ነበር፡፡ የሕወሓት ካድሬዎች በብዙ ጥላቻና ማስፈራሪያ ቢጠቀጥቁትም የትግራይ ሰው ችግርንና የግዳጅ ምልመላን በመሸሽ ወደ አማራና አፋር ተሰድዷል፡፡ ይህንን ለማድረግ የደፈረውም ቢያንስ አስፈራሪውን ፕሮፓጋንዳ ቢጠራጠር ነው፡፡ ተሰዶ ሲመጣም ከበቀል ይልቅ ተካፍሎ፣ ነፍስን የማትረፍ መተሳሰብ ነበር ያጋጠመው፡፡ ይህ የሆነው ጦርነቱ ውል የሳተ ስላልነበረ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በገባበት ሥፍራ የትግራይ ሕዝብ ተመስገን እያለ የተቀበለውም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ውጊያ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ የግፍ ጦርነትን የማምከንና የትግራይን ሕዝብ ከዕገታ የማላቀቅ ውጊያ ስለነበረ ነው፡፡ ታኅሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመቀሌ ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ ገና ከማየቱ የመቀሌ ሕዝብ የተሰማው የደስታ ስሜት፣ ጦረኞች የለፉበትን ያን ሁሉ የጥላቻ ሥራ ገደል የሰደደም ነበር፡፡

የትግራይ የለውጥ ስኬት በፕሪቶሪያው ስምምነት ወደ መሬት መውረድ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብንና የኢሕወሓታዊ ፖለቲከኞችን ንቁ ሚና በእጅጉ ይፈልጋል፡፡ ታጣቂዎች በአግባቡ ትጥቅ መፍታታቸው፣ የጦር መሣሪያዎች ያለ ሸፍጥ መሰብሰባቸውና ሥውር የአፈና/የቅርጠፋ መረብ መበጣጠሱ የሚሳካው፣ እንዲሁም ለየትኛውም ቡድን ያላደረና ለሙያው የታመነ የአካባቢ ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ግንባታ እየጠራ የሚመጣው ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን በተራቡ ወገኖች ንቁ አጋዥነት ነው፡፡ እነዚህ ሒደቶችና ክንዋኔዎች ከተልኮሰኮሱ የትግራይ ሕዝብ ከስቀዛ መገላገል ይልኮሰኮሳል፡፡ ይህ እንዳይሆን የአዲስ ሕይወት ፖለቲከኞች ከወዲሁ ሕዝብ ውስጥ እየዘለቁ መሥራትና ሥውር የአፈና መረብ ሊዳፈረው በማይችለው ስፋት ሕዝብ የሆዱን ወደ መናገር መሸጋገሩ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕወሓታዊ አሮጌ አስተሳሰብንና አባልነትን ጥለው የሚወጡ አባላት መበራከት፣ አዲስ ትንፋሽ ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን መድረኮችና ከያኒያን የሚኖራቸው ሚና የዋዛ አይደለም፡፡ የእኔን ዕንባ ያንቸረፈፈው የጎይቶም ኃይለ ማሪያም፣ ‹‹ንአረር አይተፈጠርናን›› የሚል ዘፈን የትግራይን ሕዝብ ምን ያህል እንደሚፈነቅል መገመት ይከብዳል፡፡

2ኛ/ ከ1983 እና 1984 ዓ.ም. ወዲህ የብሔር ብሔረሰቦችን ያለፈ ጭቆና ስለማስወገድ ብዙ ሲወራ ቆይቷል፡፡ በየብሔሩ የተደራጁ ፓርቲዎች ዋናውን የፖለቲካ መድረክ እንዲይዙ ሆኗል፡፡  ‹‹ልዩ ልዩነት/ብዝኃነት ውበታችን›› ሲባልም ቆይቷል፡፡ ግን ብዝኃነት ውበታችን እንደሆነ ሁሉ፣ አብሮ መኖር የህልውናና የጥንካሬ ካስማችን መሆኑ ተጣምሮ ሲነገር አልነበረም፡፡ በዚያ ፈንታ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆየት የቢሻኝ ጉዳይ እንዲመስል በፈለጉበት ጊዜ መውጣት መብት ሆኖ እንዲታሰብ ተደረገ፡፡ ሕገ መንግሥቱም በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ላይ ተመሥርቶ ተቀረፀ፡፡ አገሪቱም የብሔር/ብሔረሰቦች ይዞታ ተደርጋ ተሸነሸነችና ለሕወሓት የታመኑ ብሔርተኞች አካባቢያዊ ይዞታቸው ነው በተባለው ሥፍራ ባንዲራ እያቆሙ ገዥዎች ሆኑ፡፡ ሽንሻኖው ማለቂያ የሌለው ችግር አስጀመረ እንጂ አላቃለለም፡፡ ይዞታ እያስወሰኑና ባንዲራ እያቆሙ የመግዛት ፍላጎት እዚያም እዚያም ተባዛ፡፡ ቆስቋሾቹ ደግሞ ብሔረሰባቸውን/ጎጣቸውን ጃኬት አድርገው አካባቢያዊ ጌታ መሆን የጠማቸው ‹‹ልሂቃን›› ናቸው፡፡ ጥማቱና እንቅስቃሴው ይኼው እስከ ዛሬ ድረስ አለ፡፡

ብሔር ብሔረሰቦች ከ1984 ዓ.ም. ወደ እዚህ ልዩ እንክብካቤና ሞገስ ያገኙ ያስመሰለ ግንዛቤም ተፈጥሯል፡፡ ይህንኑ ግንዛቤ በመመርኮዝ ብሔር ብሔረሰብነት በአፍ ሲሞገስ ቆይቷል፡፡ የግል መብት የተዘነጋ ወይም የተዳመጠ የመሰለው ደግሞ፣ ‹‹ዋናው የግለሰብ መብት ነው/የፖለቲካው ውል ዜግነት መሆን አለበት›› የሚል አቋምን ሙጥኝ ይዞ ቆይቷል፡፡ ሁለቱም ጥጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰውን ጉዳት አሟልተው አይናገሩም፡፡ ሕወሓቶችና ተቀጥላዎቻቸው በደም የተገኘ የሚሉት ሕገ መንግሥት፣ ከእነ አሸናሸኑና ከእነ ብሔርተኛ አገዛዙ የብሔር/ብሔረሰብ ጭቆናን በሌላ መልክ አባዛ እንጂ አላስወገደም፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነቶች ገና እኩልነት አልተቀዳጁም፡፡ ባለቤትና ባይተዋር/ሥልጣን ላይ የመውጣት መብት ያለውና የሌለው የሚል የፖለቲካ ግንኙነት ገና ዛሬም እንደተዘረጋ ነው፡፡ የብሔረሰባዊ ማኅበረሰቦች የህልውና መብትም ገና አልተሟላም፡፡ ብሔረሰባዊ ዳመጣ ከተካሄደባቸው ሥፍራዎች ዋናው ትግራይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወደ ከፋ ጥላቻና ጭካኔ የዘቀጠ ‹‹ብሔርተኛነት››  ብሔረሰባዊ ማንነት ላይ ጭፍን ጥቃት ሲፈጽም ያየነውና እያየን ያለነው ብሔር ብሔረሰብነት ‹‹እየተሞገሰ›› ነው፡፡

ብሔርተኛ ፖለቲካ ግለሰባዊ ሰውነትንም ከበፊቱ ይበልጥ ደፍጥጧል፡፡ ዛሬ ድረስ ግለሰቦች በግለሰባዊ ማንነታቸው ከመመዘን ይልቅ፣ በብሔረሰባዊ አመጣጣቸው የሚመዘኑ ናቸው፡፡ የሆነ ብሔረሰብ ግለሰባዊ ናሙና ተደርገው ይታያሉ፡፡ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የመጡ ሁለት ሰዎች ነገር ቢወራወሩና ቢደባደቡ ጥሉ የግለሰቦች ጥል ተደርጎ በመታየት ፈንታ፣ የሁለት ብሔረሰቦች ጥል ተደርጎ የሚቆጠረው ለዚህ ነው፡፡ ከተለያየ ብሔረሰብ የመጡ ግለሰቦችን ፀብ ተመርኩዞ ብሔሬ ተጠቃ በማለት ከተጣዮቹ ውጪ በሆኑና ፀቡን ባላገዙ (እንኳን ሊያግዙ ስለፀቡም ባላወቁ) ንፁኃን ላይ ጥቃት መፈጸም የሚመጣው ግለሰብነትን የብሔረሰብ ናሙና አድርጎ ከቆጠረ አስተሳሰብ ነው፡፡

ለብሔር መብትና እኩልነት እዋደቃለሁ ባዩ ብሔርተኛነት ሄዶ ሄዶ እንደምን በጥላቻና በበቀል ተጠምዶ፣ የሌላ ብሔረሰብ አባላትን በጭካኔ ለመመንጠር እስከ መፈለግ ሊዘቅጥና በደም ሊጨቀይ እንደሚችልም ስንመረምር እውነተኛ ተጋድሎው ለመብቶች መከበር፣ ለእኩልነትና ለፍትሕ ሆኖ አናገኘውም፡፡ በብሔርተኞች/ጎጠኞች የፖለቲካ ዳዊት ውስጥ የምናገኘው በደል ቆጠራን፣ ከዚሁ የሚሸመን ቂምን፣ ጠባብ የሥልጣን ስስትንና በዚሁ ስስትና ጥማት የሚመራ የመሬት ቆጠራን ነው፡፡ መሬት ተቀራምቶ ጠባብ ሥልጣናቸውን የመጨበጥ ትግላቸው የማይሰዋው ምንም ነገር እንደሌለ በተግባር ሲያሳየን ቆይቷል፡፡ እንደ ሰው በሕይወት የመኖር መብትን ሁሉ በጭፍንና በጨካኝ በቀል ደፈጣጠው ሕዝብን በሕዝብ ላይ አስነስቶ ለማፋጀት እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ በተግባር አስመስክረዋል፡፡ በጭፍን ማረድና ማሳረድ ለሕዝብ መብት ከመዋደቅ ጋር አይዛመድም፡፡ አንዱ ሌላውን ይጣላዋል፣ ይደመስሰዋል፡፡ በግፍና በጥላቻ እየዛቆኑ ለመብት መታጋል ብሎ ነገር የለም፡፡

በአጭሩ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጡ ሊያሳካቸው ከሚገባቸው ነገሮች መሀል፣ የማኅበረሰባዊና የግለሰባዊ ማንነቶች ህልውና በእኩልነት የመከበር ጉዳይ አለበት፡፡ በሁለት በኩል ላሉት ለእነዚህ ዕጦቶች ፖለቲካችንና አገራዊ ምክክራችን መፍትሔያቸውን ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አገር ውስጥ ማኅበራዊም ፖለቲካዊም ሰላም እንዳይኖር እጅግ መርዘኛ ነገር ሠሪዎች እንደ መኖራቸው፣ ይህ ቀላል ተግባር አይደለም፡፡

3ኛ/ ከኅዳር መገባደጃ እስከ ታኅሳስ መጀመሪያ በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ከኦሮሚያ ባንዲራና መዝሙር ጋር የተያያዘ ግርግር መደረግ ያልነበረበት ነበር፡፡ ማን ጀመረው? በምን ዓላማ? የሚል ነገር ውስጥ አልገባም፡፡ በየትኛውም ወገን በኩል ጉርምስናውን የጨረሰ ፖለቲካ ኖሮን ቢሆን ኖሮ፣ ከግርግር ይልቅ ተመካክሮ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ በተሠራ ነበር፡፡

ያለንበት ወቅትና ሁኔታ ሌላ የውዝግብ ልፊያ ሊታከልበት የማይገባ ነው፡፡ የማሸበር ሰቆቃና መፈናቀል ቀዘቀዘ ሲባል እየሞቀ፣ በዚህ ያዝኩት ሲባል በሌላ ሥፍራ ብቅ እያለ ያስቸገረበት ሁኔታ ዛሬም አብሮን አለ፡፡ ይህንን እሳት የሚሞቁና የተገኘችውን ሰበባ ሰበብ ሁሉ የጦዞ ሥዕል እየሰጡ ያለውን መንግሥት የኦሮሞም ሆነ የአማራ ጠላት ለማስመሰል፣ በተለይም የኦሮሞን የዕይታ አድማስ ከኢትዮጵያዊነት አውጥቶ በኦሮሚያ ውስጥ ለማኮማተር ሌት ተቀን ከሚሠሩ ቡድኖች ጋር ነው የምንኖረው፡፡ መረባቸው ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ነው፡፡ ክንዳቸው የመንግሥት ደጋፊ መስሎ እስከ መሸፈጥ የረዘመ ነው፡፡ ሌት ተቀን በሐሳዊ መረጃ የግዝገዛ ሥራ የሚያካሂድ ሚዲያ አላቸው፡፡ በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የታገለ መስሎት፣ ነገሮችን ያወሳሰበና ለሸኔዎች የፈረስነት አገልግሎት የሚሰጥ ሌላ ዓይነት ፅንፈኝነትም ብቅ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አገዳዎቹን ገና አላቀላጠፈም፡፡ ከሕወሓት ሰዎች አንዳንዶቹ በአዲስ አበባው ውዝግብ ውስጥ ምላሳቸውን ሲያጠቅሱም ታዝበናል፡፡ በዚህ ላይ የሰሜኑ ጦረኝነት ሽንፈት ደረሰበት እንጂ ፀፀትን ሲተነፍስ እየሰማን አይደለም፡፡ ፅንፈኛ ጎጠኝነትና ብሔርተኝነት ገና አልተሸነፈም፡፡ አምስት ዓመት ሊደፍን ያለው የለውጥ ጅምር ቢያንስ ሰላሳ ዓመት ከኖረ ክፍልፋይ አዕምሮ ጋር ነው የገጠመው፡፡ ፖለቲካችን ደግሞ ስክነት ገና ዳገቱ ነው፡፡ እናም ከአፍንጫ በማይርቁ ጀብደኛ ምላሶችና ድርጊቶች ኢትዮጵያዊ ማንነትና አካባቢያዊ ማንነቶች እንዳይመናቀሩ ተጠንቅቆ የሚተነኳኮሉንን ፅንፈኞች የማቃለል ተግባር አሁንም ተደቅኖብን ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ መላ ኅብረተሰብ ሰላምና ግስጋሴ እናስባለን የሚሉ ፖለቲካኞችንና ምሁራንን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ አንዳንድ የተሰሙና የሆኑ ነገሮችን እንነካካቸው፡፡ የአዲስ አበባ ብሔረ-ብዙ ሕዝብ አማርኛ በመናገሩ እንደ አማራ ተቆጥሮ እንደሆነም አላውቅም፣ አንዳንዶች ውዝግቡን አማራና ኦሮሞን የማጋጨት ፍላጎት ያለበት ነው የሚል የተሳሳተ ሥዕል ሲሰጡት ተሰምተዋል፡፡ በአፍ መፍቻ የመማር መብትንና ማንነትን የመደፍጠጥ እንቅስቃሴ የተነሳም ያስመሰለ ድስኮራ ተደጋግሟል፡፡ የኦሮሚያ መዝሙር ለኦሮሞም የማይመጥን ስለመሆኑ መጢቅ ትምህርት የሰጡንም ዶቅዶቄዎች ነበሩ፡፡ በግርግሩ የኢትዮጵያ ባንዲራም የኦሮሚያ ባንዲራም ወደ መሬት እንደተወረወሩ ተነግሯል፡፡ እነዚህን መሰሎቹ ነገሮች እንድንመናቀር ሌት ተቀን የሚሠሩትን ኃይሎች ይጠቅማሉ ወይስ የተባበረ ትግላችንን? ጥያቄው ለሁላችንም ነው፡፡

ውዝግብ የተነሳበት ጉዳይ ተሸፋፈነም ግልጽ በግልጽ ተነገረም በትንቅንቅ የሚገላገሉት ነገር አይደለም፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለ የመንግሥት አካል ሕግን እንዲያከብር ነቅቶ ከመጠበቅ ልምምድ አኳያ፣ ድርጊቱ የሕግ መሠረት እንደሌለው ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ባለንበት ደረጃ ያጋጠመን ችግር የሕግ አንቀጾችን መከታ በማድረግም ሆነ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ የሚቃለል አይደለም፡፡ ፍርድ ቤት፣ ‹‹የኦሮሚያን የባንዲራ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማከናወን የሕግ መሠረት የለውም›› የሚል መሳይ ብይን ቢሰጥና በዚያ መሠረትም ሆነ በመንግሥት ውሳኔ ድርጊቱ እንዲቋረጥ ቢደረግ፣ ምናልባት ውዝግቡ አጎንብሶ ያድር እንደሆነ እንጂ አይወገድም፡፡ የችግሩ አፈታት ሕግ ከማመሳከርና ወደ ፍርድ ቤት ከመሮጥ ይልቅ፣ አገራዊ መግባባትንና የመተሳሰብ ግንኙነት ግንባታን የሚሻ ነው፡፡

ችግሩ የሚፈታው ከመሬት ቆጠራ ይልቅ የሕዝብ ለሕዝብ ዝምድና ሲበልጥብን ነው፡፡ የትኛውንም ማኅበረሰብ ከእነ ቋንቋና ከእነ ባህሉ የእኔም የአንተም ብለን ስናምን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዥንጉርጉርነቶችን ሁሉ ለኢትዮጵያ ያለን ፍቅር ይዘቱ ሲያደርጋቸውና ሲናፍቃቸው ነው፡፡ በየአካባቢያችን ውስጥ ያሉ ሰዎችንና ማኅበረሰቦችን ያለ ማንጓለል የአካባቢያዊ ማንነታችን አካል) ስናደርጋቸው ነው፡፡ አካባቢያዊ ማንነቶችና አገራዊ ማንነት እርስ በርስ ሲገነባቡ ነው፡፡ በሁሉም ሥፍራ አነሰም በዛ የሰዎች መከበር፣ የዜጎችና የማኅበረሰቦች እኩልነት ፀሐይ ሲወጣላቸው ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የደረደርኳቸው ነጥቦች የመፍትሔው ልዩ ልዩ ገጽታዎች ናቸው፡፡ የተናገርኩት ነገር ቢኖር ችግሩ የሚፈታው መፍትሔ ሲያገኝ ነው ከማለት የራቀ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ወደ እዚህ ውጤት የሚያደርሱትን መንገዶች አውቆ በእነሱ ላይ መሥራት ነው፡፡

የብዙዎቻችን የአገር ፍቅር መናጨት የጥቃት መግቢያ መሆኑን፣ መተባበርና ትልቅ አገርነትም ጥንካሬ መሆኑን ሳያሰላስል ያውቃል፡፡ ነገር ግን የአገር ፍቅራችንና ኩራታችን ብዙ ጊዜ ‹‹እምዬ አገሬ፣ ዞሮ መግቢያዬ፣ እትብቴ የተቀበረብሽ፣ ወዘተ›› የሚሉ ዓይነት ድፍን ነገሮችን ይዞ የሚነድ ነው፡፡ የነዲዱ ማገዶዎች ከመላው ኢትዮጵያ ጋር በተራከቡ ሰፊ ዥንጉርጉር ልምዶች፣ ናፍቆቶችና አድናቆቶች የተሞሉ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ የትውውቅና የልምድ ውስንነት አንዱ ችግር ነው፡፡ ከዕድገትና ከልማት ጋር የሚመጣ የሰዎች ዝውውር መጨመር፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፊልሞች፣ ሚዲያዎችና ወደ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚደረጉ የበጎ ሥራና የብሔራዊ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ሁሉ ትውውቅን የማጎልበት ሚና ይጫወታሉ፡፡ የምንናገራቸው አገራዊ ቋንቋዎች በጨመሩ ቁጥርም ያንኑ ያህል የማኅበረሰባዊ፣ የሥነ ልቦናዊና የባህላዊ ዝምድናችን ፈትሎች ይበረክታሉ፣ ይወፍራሉ፡፡ 

ጉዳዩ ካለመተዋወቅ ወደ መተዋወቅ የማለፍና ትስስርን የመገንባት ብቻ አይደለም፡፡ አንዳችን ከሌላችን ጋር ምን ያህል እንደተወራረስን አለማወቃችንን የማወቅም ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ የሰዎች አሠፋፈር ይቅርና የሠፈርንበት መልክዓ ምድርም በዘመነ ዘመናት ውስጥ እየተለወጠ እዚህ የደረሰና ወደፊትም ለውጡ የሚቀጥል ነው፡፡ ዛሬ የምናቃቸው የዓለማችን የየብስ፣ የተራራዎች፣ የበረሃዎች፣ የባህርና የውቅያኖስ፣ የበረዶ ሥርጭቶች ጥንት እንደነበሩ ያሉ አይደሉም፡፡ የአሜሪካ አኅጉራትና የአፍሪካ ምድር ያልተበረቀቁበት ዘመን ነበር፡፡ የኤርትራና የዓረቢያ ምድር በባህር ያልተገመሰበት ጊዜም ነበር፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን፣ በፀሐያዊ ሥርዓታችን ውስጥ ያለ እንቅስቃሴ፣ በከርሰ ምድራችን ውስጥ ያለ እንቅስቃሴ፣ ሰዎች በምድር ላይ የሚያስከትሉት ለውጥ ሁሉ እርስ በርሱ በሚፈጥረው መስተጋብር የምድራችን ሁለመናዊ ባህርይ ከእነ አየር ንብረታችን መጪና ሂያጅ ነው፡፡

ከሥነ ምድራዊ ለውጦች በጣም በፈጠነ ደረጃ የሰዎች አሠፋፈር መጪና ሂያጅ ነው፡፡ በተፈጥሯዊ ነውጦችና ለውጦች ምክንያትም ሆነ በማኅበራዊ ቀውሶችና መሳሳቦች ምክንያት የሰው ልጆች ታሪክ ከሥፍራ ሥፍራ በመንቀሳቀስ (በፍልሰት፣ በስደት፣ በመውረርና በመወረር፣ በመበታተንና በመቀላቀል) የተሞላ ነው፡፡ ማኅበራዊ ጥንቅሮችም በረዥም ጊዜያት ውስጥ እየተዘናነቁ ከልዩ ልዩነት ወደ ተመሳሳይነት ተቀይረዋል፡፡ ተመሳሳይ የነበሩም ወደ ተለያየ ሥፍራ ተረጭተውና ከሌሎች ጋር ተቧክተው ወደ ልዩ ልዩነት ተፈላቀዋል፡፡ ተቧክተው አምሳያነት ያገኙትም እንደገና ታሪክ ሌላ ውጥወጣ ውስጥ እየከተተ ሲሠራቸው ኖሯል፡፡ ይህ ሒደት ልብ አንለው እንደሆን እንጂ ወይም የረጋ ይምስለን እንጂ ዛሬም ያለና የሚቀጥል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች አጠነቃቀርና ሥርጭትም ከዚህ ታሪካዊ ሒደት ውጪ የመጣ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የትኛውም ሥፍራ ዘንድ ብንሄድ ጥንት እንደተፈጠረ ያለ፣ ከአንድ ምድር ጋር ተሰፍቶ የኖረ ማኅበረሰብ የለም፡፡ ሁሉም ማኅበረሰቦች ወደውም ሆነ ሳይወዱ ከቦታ ከቦታ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ዛሬ የምናውቃቸው እንዲህ ያለ ባህልና ቋንቋ ያላቸው እያልን የምንቆጥራቸው ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ በተራክቧዊ ልውጠት የተገኙና በልውጠት ውስጥ እየኖሩ ያሉ ናቸው፡፡ የተራክቧዊ ልውጠት ውጤት ደግሞ ፊት ያልነበሩ ልዩነቶችን ማብቀል ብቻ ሳይሆን በመመሳሰል ማዛመድም ነው፡፡

ከዚህ ታሪካዊ እውነት አኳያ፣ የአንድ አገር አካል ሆኖ በተወሰነ የታሪክ ወቅት ውስጥ የተከናወነን የማኅበረሰብ ሠፈራ ዘለዓለም የነበረ አስመስሎ ወይም በእግዜር ስጦታነት ተርጉሞ ባለቤት ማድረግ፣ የሌላውን ታሪክ አመጣሽ ሠፈራ ግን በሰው ሠፈር መምጣት (ባዕድነት) ማድረግ ፍርደ ገምድልነት ከመሆኑም በላይ፣ የገዛ አገራዊ ሰላምን እየበጠበጡ መኗኗርን አስቸጋሪ ማድረግ ነው፡፡ ንቁሪያ ውስጥ የሚከቱን መሬት አምላኪዎችም ዓላማቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዳንኗኗር ማድረግ ሆኗል፡፡

እንዳዥጎረጎረን ሁሉ ያወራረሰን እንቅስቃሴ አመጣሽ ልውጠት፣ ባለሦስት ሰበዝ ዝምድናችንን ይነግረናል፡፡ አንደኛ/ዓይነተኛ በሆኑ የማኅበረሰቦቻችን ሥሪት ውስጥ ሌሎቻችንም ተቀምመናል፡፡ በኦሮሞነት፣ በአማራነት፣ በትግሬነት፣ ወዘተ፣ ወዘተ ውስጥ ሳይቀላቀል የቀረ የሌላ ማኅበረሰብ ሰው አለ ብሎ ማንም ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡ ሁለተኛ/በማኅበረሰቦች የእርስ በርስ ንክኪ ውስጥ በባህል በቋንቋና በአስተሳሰብ ብዙ ነገሮችን ተቀባብለናል፡፡ ከኤርትራ አንስቶ ወደ ትግራይ፣ ወሎና ጎንደር ብንጓዝ ብዙ የባህል መወራረስን እናገኛለን፡፡ በአዝርዕት፣ በሥራ ሥር፣ በእንሰት ባህል፣ በአስተራረስ፣ በሽመና፣ በቤት አሠራር፣ በምግብ ባህል፣ በአለባበስ፣ በሙዚቃ፣ ወዘተ ያለው መወራረስ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ሦስተኛ/የልዩነትና የመመሳሰል ገጽታዎች ያሉትን ዥንጉርጉርነታቸውን ይዘን የምንኖረው ኑሮ የጠርሙስ ውኃን መሳይ ነው፡፡ የጠርመሱ ውኃ የቅልመት ሽብርቁን የሚያገኘው ከአካባቢ ጋር ባለው መስተጋብር ነው፡፡ አካባቢውን ያንፀባርቃል፣ ከሙቀት ከብርሃንና ከጥላ መስተጋብር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የነገሮች የህልውና ኑሮም እንዲህ የተመረኳከዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለን የየትኛውም ማንነት ኑሮ እንደዚያው የተመረኳኮዘና አንዱ በሌላው ውስጥ የሚታይና የሚላወስ ነው፡፡ የህልውናችን መቀጠል ደግሞ እንደ መቋጫ ሆኖ፣ የተዘማመደ ዥንጉርጉርነታችሁን ተንከባክባችሁ ለጊዜ አመጣሽ መመናቀራችሁ መፍትሔ መፈለግና እንደ አገር መቆየት ይበጃችኋል ብሎ ይመክረናል፡፡

ይህንን በአግባቡ የተረዳን ከሆነ አፍ የፈታንበት ከምንለው ቋንቋ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ ተማሩ ስንባል፣ የባህል መጫን ደረሰብን የሚል ስሜት ሊፈጠርብን አይችልም፡፡ ማንነታችንንም ከአንድ ማኅበረሰባዊ ምንጭ ጋር ብቻ አናጣብቀውም፡፡ የትኛውንም የኢትዮጵያ ቋንቋ፣ ባህልና ማኅበረሰባዊ አካባቢ የእኔ የሚል ግንዛቤ ካለን ከአፍ መፍቻችን ውጪ የምንማረው ቋንቋ ባዕድ ሆኖ አይሰማንም፡፡ ከየትኛውም ብሔረሰባዊ ምንጭ ብንመጣ የተወለድንበትን፣ ያደግንበትንና ቋሚ መኖሪያችን ያደረግነውን የትኛውንም ሥፍራ ወንዜ ማለት አይጎረብጠንም፡፡ ብሔረሰባዊ አመጣጥን በማይጠቁም አኳኋን የባሌ ልጅ ነኝ፣ የጎሬ ልጅ ነኝ፣ የሐረር ልጅ ነኝ፣ ወዘተ ማለት በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ኑሮ ታሪክ ውስጥ እንግዳ አይደለም፡፡ ዛሬም በአካባቢ ልጅነት የአካባቢውን ባንዲራና መዝሙር የእኔ ብሎ መቀበል ከልካይ እስከ ሌለበት ድረስ ችግር አይደለም፡፡

ጊዜ አመጣሹ የዚህ አካባቢ ባለቤት እከሌ ማኅበረሰብ ነውና አንተ ከዚያ ማኅበረሰብ ባለመሆንህ ባይተዋር ነህ የሚል ማንጓለል ከልካይ ነው፡፡ ማንነትን ከብሔረሰብ አባልነትና የዚያ ብሔረሰብ መገኛ ከተባለ ሥፍራ ጋር አጣብቆ የሚያይ አስተሳሰብ ከልካይ ነው፡፡ የፊተኛው የአካባቢ ልጅነትን የሚፈቅደው መርጦ ነው፡፡ የኋለኛው ደግሞ የትም ተወልደህ ብታድግና ብትኖር መሠረታዊ ማንነትህ ብሔረሰባዊ ምንጭህ ነው ብሎ ብቸኝነትን ያጠብቃል፣ የተወለደበትንና ያደገበትን ሥፍራ የእኔ እንዳይል ያውካል፡፡ ከዚያም አልፎ ሄዶ በሌላ ‹‹ክልል›› ያለ የዚያ ብሔረሰብ ብጫቂ በጊዜያዊነት ያለ የሌላ ‹‹ክልል›› ልዑክ ወይም ኤምባሲ ነክ ማኅበረሰብ እንዲመስል ያደርጋል፡፡ እናም በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማርን ነገር መገኛዬ (ማንነቴ) ከተባለ “ክልል” ባንዲራና መዝሙር ጋር ያጎዳኘዋል፡፡ የዚህ ዓይነት መፈነጋገጥ እያለ አካባቢያዊነትንና አገራዊ መዘማመድን ተመጋገቢ አድርጎ መገንባት አይቻልም፡፡

አንጓላይና አግላይ ነገሮችን ነቅሰን እየጣልን አካባቢያዊና አገራዊ መዘማመድን የመገንባት ሥራ ውስጥ ከገባን፣ ከየትኛውም አካባቢና ብሔረሰባዊ ምንጭ የመጣ ኢትዮጵያዊ የሚኖርበትን አካባቢ ባንዲራና መዝሙር የእኔም ብሎ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ ጋምቤላ ውስጥ ዕትብቱ የተቀበረም ሆነ ኑሮውን የመሠረተ ኦሮሞ የኦሮሞ ልጅ ነኝ እንደሚል ሁሉ፣ የጋምቤላ ልጅነትንም መጎናፀፍ ያስፈልገዋል፡፡ አካባቢዎች ባንዲራና መዝሙር እስካላቸው ድረስም፣ ከየአካባቢ ባንዲራና መዝሙር ጋር አገራዊው ባንዲራና መዝሙር ተጣጥሞና ተጎዳኝቶ መከበሩም አግባብ ነው፡፡ አዲስ አበባ በፌዴራል ሥልጣን ማዕከልነቷም ሆነ የአገሪቱን አካባቢዎች አንደበቶችና የባህል ገጽታዎች በማንፀባረቅ የምትወክል ከተማ ከሆነች፣ የፌዴራላዊት ኢትዮጵያን ባንዲራ በሁሉም አካባቢዎች ባንዲራዎች ሞሽራ ብታውለበልብ ትንሿን ኢትዮጵያን ለሚወክሉ ነዋሪዎቿ አይከብዳቸውም፡፡ የፌዴራል ኢትዮጵያ ባንዲራ ብቻውን ቢውለበለብም አይጠባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያንም ሀብት ለመሆን የበቃ ነውና፡፡ በዚያ ባንዲራ ላይ ሙሉ ስምምነት እስከሚኖረን አገራዊ ባንዲራ አይኑረን አይባልም፡፡ ሁላችንን የሚያስማማ ለውጥ ልናደርግ ስንነሳ እንኳ የባንዲራው ዓድዋዊ ታሪክና የአፍሪካ ሀብትነቱ ያንኑ የሚያዳምቅ እንጂ፣ የሚያደበዝዝ ነገር እንዳናደርግ ይከለክለናል፡፡ ባንዲራው ይህን ያህል ጉልበት ካለው የምናደርገውን እስከምናደርግ ድረስ አክብሮ መቆየት እንደምን ይተናነቀናል፡፡ ይህንን ካጤንን አዲስ አበባ ውስጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያከበሩ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና በመማሪያ ቋንቋ አገራዊ መዝሙርን መዘመር አይጋጩም፡፡ ከዚህ የበለጠ የሚያግባባ ሌላ መፍትሔ ይኖር ይሆን? ዋናው ጉዳይ በቅጡ መክሮ መግባባት መቻል ነው፡፡ የአገራዊ ምክክራችን አንዱ ጉዳይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አገራዊ መግባባትን መፍጠር ነው፡፡

በአፍ መፍቻ ከመማር መብት ሳንርቅ አንድ ነገር እናጥራ፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ በመማር መብት ላይ አጠቃላይ መግባባት መኖሩን ተመርኩዘው አንዳንድ ፖለቲከኞች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርና በወላጆች ቋንቋ መማር መምታታት እንደሌለበት፣ በአዲስ አበባ ዓይነቱ ከተማ ውስጥ የተወለደ ልጅ በአማርኛ አፉን ከመፍታት እንደማያመልጥ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ መጀመሪያ ነገር አዲስ አበባ ኦሮሚኛና አማርኛ ተናጋሪነት ተቃቅፈውና ተሰባጥረው የሚነገሩበት ከተማ ነው፡፡ የሁለቱም ቋንቋዎች ተነጋሪነት የድምቀት ሥፍራዎች አሏቸው፡፡ ከሁለቱ ውጪ ሌሎች ቋንቋዎችም ትንንሽ መንደር ብጤ ፈጥረው የሚነገሩበት ሁኔታም አለ፡፡ ያም ባይሆን በቤትና በቤተ ዘመድ ተራክቧቸው ውስጥ ወላጆች አፍ መፍቻ ቋንቋቸውን በመጠቀም እናት ቋንቋቸውን ለልጆቻቸው የሚያወርሱበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ አኳኋን አፍ መፍታት የጀመረ ሕፃን ቢያንስ ከቤቱ ሲወጣ ደጅ የሚከበውን የንግግር ቋንቋ መልመዱ አይቀርም፡፡ ውጤቱም በአንድ ጊዜ በሁለትና በሦስት ቋንቋ አፍ የመፍታት ያህል ይሆናል፡፡ የዚህ ዓይነት አፍ አፈታት ባለበት ሁኔታ ሕፃኑ ከአንድ የበለጠ የመማሪያ ቋንቋ አማራጮች ያገኛል፡፡ ወላጆች በተለያየ ምክንያት የእነሱን አፍ መፍቻ ለልጃቸውም መፍቻ እንዲሆን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው፣ ቅድመና አንደኛ ደረጃ ትምህርትን ልጃቸው በማያውቀው ቋንቋ እየተማረ የወላጆቹን ቋንቋ እንዲቀስም ለማድረግ ቢጠቀሙበት በልጃቸው የዕውቀት ጉልምስና ላይ በደል ነው የሚፈጽሙት፡፡ የኢኮኖሚ አቅሙ ኖሮን ሁሉም ልጆቻችን አፍ በፈቱበት ቋንቋ አንደኛ ደረጃ ትምርታቸውን ቢማሩ እሰየው ነው፡፡ ይህ ቢሳካልን አንዳንዶች ኢትዮጵያችን አገራዊ የጋራ ቋንቋ የምታጣ ይመስላቸዋል፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ያለ ትምህርትን በጥሩ የእንግሊዘኛ አቅም መማር ቢቃናልን አገራችን በእንግሊዝኛ ተጥለቅልቃ የጋራ አገርኛ መግባቢያ የምታጣስ ይመስላቸው ይሆን? የጋራ አገራዊ ቋንቋችን ህልውና በዋናነት የሚኖረው ከትምህርት ቤት ውጪ ነው፡፡ በትልልቆቹ አማርኛና ኦሮሚኛ ተነጋሪነት ላይ ሌሎች ይታከላሉ እንጂ የትም አይሄዱብንም፡፡ ሰፊ ተነጋሪነታቸው፣ የሥነ ጽሑፍና የሚዲያ ቋንቋነታቸው ከመንግሥታዊ የሥራ ቋንቋነት ጋር ይቀጥላል፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ግንዛቤዎች በደንብ ከተጨበጡን ብዙ ውዝግቦቻችን ይቀላሉ፡፡ ጠባብ ዕይታዎችም አያምሱንም፡፡ “ማንነትህ ተካደ! መሬትህ ተወሰደ!፣ ወዘተ የሚሉ ጩኸቶች ብሔርኞች ሰዎችን ወደ ብሔርተኛ ጉድጓዳቸው የሚያስገቡባቸው ድጦች ናቸው፡፡ ከብሔርና የብሔር ከሚባል “ክልል” ውጪ ሌላ ማንነታችን እንዳይታየን ነው ብሔርተኞች የሚለፉት፡፡ እናም አንድ ማንነትን የማንነት ሁለመና አድርጎ ለሚወሰውስ ፖለቲካ ጆሮ መስጠት ሌላ ድጥ ነው፡፡ እዚህ ድጥ ላይ ወለም ዘለም ከተባለ መንሸራተት ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ በጠባብ ዕይታዎች ድጦች የመንሸራተትን ፈተና ለማዳከም በሰፊ ግንዛቤዎች ላይ መላልሶ መሥራት፣ ልምድና ተራክቦን ማስፋት ግድ ነው፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነትን ከቋሚ መኖሪያ አካባቢ ልጅነትና ከኢትዮጵያ ልጅነት ጋር አስማምቶ መያዝ ድጥን ለመከላከል ያስችላል፡፡ በዚህ ረገድ በስያሜ ጭምር ሁሉን አቃፊ የሆኑት አዲሶቹ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና የደቡብ ኢትዮጵያ ‹‹ክልሎች››፣ ከተለያየ ብሔረሰብ የተገኙ ሰዎቻቸውን በኢትዮ-ምዕራብና በኢትዮ-ደቡብ ልጅነት በማሸራረብ ፊት መሪና ምሳሌ ቢሆኑ ብለን እንናፍቃለን፡፡ ይህ እንዲቃና ደግሞ ፖለቲካችን አንጓላይነትን ለማራገፍ መሥራት አለበት፡፡ በአካባቢዎችና በፌዴራል ደረጃ የሚካሄዱ ፈርጀ ብዙ መስተጋብሮች መተሳሰብንና መሸራረብን ለመጥቀም መቻላቸውም ወሳኝ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ልጅነትም ወደፊት ተራክቧዊ ይዘቱ የሚበለፅግ ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ የአዲስ አበባ የሕንፃዎችና የመንገዶች ልማት አዲስ አበባ ውስጥ ጥርሴን ነቅያለሁ የሚለውን ሰው እንኳ የሚያደናግር ሆኗል፡፡ የኑሮ ውድነቱም ከሥራ ቦታ መልስ ኑሮን በመኖሪያ አካባቢ ውስን ዙሪያ ውስጥ የሚሽከረከር አድርጎታል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሠሩትን መናፈሻዎችን ለአንድ ጊዜ እንኳ ያልጎበኛቸውና በቴሌቪዥን እያየ አጀብ የሚለው ብዙ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ልማት የደቀቀ ኑሮን እያላወሰ ሲሄድና የመንፈስ ማደሻ ሥፍራዎች መገኛ በሁሉም አቅጣጫ ሲሠራጭ፣ ውድ ክፍያ የሚጠይቁት ሥፍራዎች በዓመት ለተወሰኑ ቀናት የነፃና የቅናሽ መርሐ ግብር አውጥተው መንታሎችን ሲያስተናግዱ፣ በሌላ ጎን ሰርክ በነፃና በአነስተኛ ክፍያ የሚያገለግሉ ሲለሙ፣ በአጠቃላይ በአገልግሎቶች ይዘትና በዋጋቸው አባባይነት የመሀል ከተማውን ሰው ወደ ገጠራማና ወደ ዳር አዲስ አበባ፣ የዳርና የገጠራማውን ነዋሪም ወደ መሀል የሚስቡ የመስተንግዶ ሥፍራዎች ሲበራከቱ የአዲስ አበባ ጣዕም ለነዋሪዎቿ እየታወቀ ይመጣል፡፡ ያኔ ደግሞ ፎቅ በተደቀደቀበት የአዲስ አበባ ክፍልና በሸገር ሰንሰለታዊ የከተሞች ልማት መሀል ያለው ነዋሪ የአካባቢ ልጅነቱ ከሁለት በኩል በሚመጣ መስተጋብር ድርብ ይሆናል፡፡

4ኛ/ ንቅዘት ጥቃቱ መመከቻ ሲያጣ፣ ሁሉን የሕይወት ዘርፍ ወርሮ ያነክታል፡፡ የሥራ ቅጥሮች፣ የሠራተኛ ዕድገቶች/ሹመቶችና ሌሎች የጥቅም ዕድሎች በፓርቲያዊም ሆነ በጎሳዊ/ጎጣዊ መረብ ውስጥ ከወደቁ፣ በአቋራጭ መክበር የሚሹ ሰዎች የትኛውንም የሥልጣን ተዋረድና የአሠራር ሥልት እያላሸቁ መጫወቻቸው ያደረጉበት ሁኔታ ከደራ፣ ያንን የሚቀይር ለውጥ ለማካሄድ ሳይደፍሩ ሙስናን ለመታገል መሞከር በጭቃ ውስጥ ሆኖ ከመታጠብ ብዙም አይርቅም፡፡ የንቅዝት ዋነኞቹ ነጋዴዎች ወይም አንቃዦች ከሁለት በኩል የሚመጡ ናቸው፡፡ ቀጥተኛ መንገዶችን በልዩ ልዩ ዘዴ በማሳበርና የሠራተኛን ጨዋነት በመበሳሳት የተካኑ ባለ ጉዳዮች ከአንድ በኩል ይመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በየመሥሪያ ቤት ውስጥ የማጎሳቆል ሥልቶችን ታቅፈው ሥልጡን ሙሰኞችንም ሆነ ያልተገሩ አገልግሎት ፈላጊዎችን የሚጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ በሁለቱ ተራክቦ የግለሰቦች ኪስ ይታለባል፡፡ የመንግሥት/የኅብረተሰብ ጥቅም በ‹እከክልኝ ልከክልህ› ይሰለባል፡፡ በሥራና በሰው ላይ የሚደርስ በደል ይባዛል፡፡ በሕግ ላይ መመካት፣ በሙያ ብቃት/በሥራ ትጋትና በውጤታማነት ላይ መመካት፣ በወሮታና በዕድገት ሥርዓቱ ላይ መተማመን ውልቅልቁ ይወጣል፡፡ እነዚህ እየነቀዙ የሚያነቅዙ የሁለት በኩል ኃይሎች ተራክቧቸው የሚቃናላቸው ለንቅዘት የሚስማማ አየር ንብረት እስካለ ድረስ ነው፡፡ በንቅዝት ነጋዴዎች ዘንድ ደንብና ሕግ ጥሶ ያልተገባ ጥቅም መለዋወጥ ነውር የለውም፡፡ ያለ እከክልኝ ልከክልህ የሥራ መስተጋብር አይገፋም የሚል እምነት መንሰራፋት ዋና አቅማቸው ነው፡፡ ይህን እምነት የሚያጠናክሩና ለዚህ እምነት ተሸናፊ የሚያደርጉ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ደጅ የሚያስጠና ዘረክራካ አሠራር፣ የሥራ መወዘፍ፣ በሥራ ገበታ የሠራተኛ መጓደል፣ የበደል አቤቱታ ሰምቶ የሚያቃልል አለመኖር፣ የአቤቱታ ሰሚ ክፍሉ በሥውር የንቅዘት መረብ መጠለፍ፣ የሥውሩ መረብ ቋንቋ አልገባው ያለን (ወደ አቋራጭ መንገድ አልታጠፍ ያለን) ባለ ጉዳይ በሕጋዊነት ስም ከፍተኛ ወጪ በማስከፈል በአቋራጭ ለሚመጡ ደግሞ መለስ ያለ ወጪ በማስከፈል ለልማድ ተሸናፊ የሆኑ ደንበኞችን ማበራከት፣ ሕግና ደንብ ተጥሶ ጉዳይ እንዲፈጸም የሚያደርግ የበላይ ትዕዛዝ መኖር፣ ዘፈቀዳዊ የሥልጣን አጠቃቀምን ዕንቢ ብሎ ለማጋለጥ የሚያደፋፍር ሁኔታ አለመኖር፣ ቢኖርም ለተወሰነ ጊዜ ሽርጉድ ተብሎበት ተመልሶ የሚላሽቅ መሆን፣ በአጠቃላይ ሥራ በቅልጥፍናና በጥራት መሠራቱን የመከታተልና ስኬታማነትን የመመዘን፣ እንከንንና እንከን ፈጣሪዎችን የመለየት፣ አቤቱታዎችን ወዲያው ለወዲያው የመስማት፣ ችግሮችንና ችግር ፈጠራዎችን የሚያቀልል ዕርምጃ ትኩስ በትኩስ መውሰድ የሁልጊዜ የሥራ አካል አለመሆን፡፡

አድራጊ ፈጣሪ ሥልጣንና የአሠራር ትብትብ ባለበት ሁሉ ንቀዝት መኖሩ አይቀርም፡፡ ከዚህ አኳያ ንቅዝት/ሙስና ረዥም ታሪክ አለው፡፡ በየትኛውም የኑሮ መስክ እንደ ወረርሽኝ የተዛመተው ግን በደርግ አገዛዝ ጊዜ ነው፡፡ ያኔ የነበረ ንቅዘት የተኛ ታካሚን መድኃኒት እስከ መመንተፍ ድረስና የከተማ አውቶቡስ ሳንቲምን ትኬት ባለመስጠት እስከ ማጭርበርበር ግጥጥ ብሎ ነበር፡፡ ዛሬ ያው ንቅዘትና ልሽቀቱ ከዚያን ጊዜው ትንሽ መለስ ያለ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሰብዕና፣ በሙያ ብቃትና ለኃላፊነት በመታመን ረገድ የደረሰው የስብራት ጥልቀት በዋዛ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ በአማኒያንና በቤተ እምነት መሪዎች ዘንድ የሚታየው የንቅዘት ስፋት፣ የፈጣሪን ትዕዛዞች እየጣስን በፆምና በፀሎት ፈጣሪን ማሞኘት አያቅተንም የሚል ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች የተፈጠሩ እስኪመስል ድረስ አስደንጋጭ ነው፡፡ አገሪቱ አሁን አለኝ በምትለው ከሥራ ገበታና ከሥራ ውጪ ባለ ‹‹የተማረ›› ኃይል ውስጥ ያለ የዕውቀት/የሙያ ብቃት ጉድለት (በሐሰተኛ ምስክር ወረቀት ከማጭበርበር፣ ከለብለብ ትምህርትና ከዕውቀት መንተብ ጋር የተያያዘ) እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ብቃት የለሾችንና ለኃላፊነት የማይታመኑ እየመነጠርኩ በደህነኞች ልተካ ቢባል ተፈላጊ ሰዎችን ከገበያ ለማግኘት መቻል የሚያጠራጥር ይመስላል፡፡ የተንሰራፋው የንቅዘት ንቃተ ህሊናና ዘልማድም አዲስ የሚመጡትን ሰዎች ለማላሸቅ ያለው ኃይል ከባድ ፈተና ነው፡፡ በመሆኑም እስከ ዛሬ የተሞከሩ ጥረቶችን ሲያመክን ቆይቷል፡፡ በዚያ ላይ ለሰላሳ ዓመታት የተሠራበት ብሔርተኛነት ለነቀዞችና ለአንቃዦች ጥሩ መሸሸጊያ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ የተነሳ ሙሰኞችን በሰፊው ለማበጠር እሞክራለሁ ማለት የንብ ቀፎ እንደ መንካት በደንብ ማሰብን የሚጠይቅም ነው፡፡ ሙሰኞች ሊያስነሱት ለሚችሉት ‹‹በብሔሬ ተገፋሁ›› የሚሉ ጫጫታዎችና ሰላም የማደፍረስ ተንኮሎች በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ንቅዘትን የመታገል ተግባርን ዛሬ ካሉብን ፈተናዎች ጋር በአግባቡ ካላገናዘብነው የሙሰኞች ደባ ከሙስና የዘለለ ጣጣ እስከ መፍጠር ሊሄድም ይችላል፡፡ በንቅዘት (ሙስና) ላይ የሚካሄደው ትግል ሁሉን የኅብረተሰብ ክፍል (ፓርቲዎችን፣ ምሁራንን፣ ሚዲያዎችን መንግሥትንና የሃይማኖት መሪዎችን ሁሉ አንድ ላይ ያስተባበረ እንቅስቃሴን ይሻል፡፡ ቀንደኛ አንቃዦችንና ነቀዞችን ከማስወገድ ጋር በልሽቀትና በንቅዘት የጎደፉን በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ማረቅ/ማከም ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ የሥነ ምግባር የዕውቀትና የሙያ ማካካሻ ሥልጠናን አዝሎ የሥራ ባህልን የቀየረ ተሃድሶ (የተራዘመ አብዮት) ውስጥ መግባት የሚሻ ይመስላል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                    ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...