Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፀደይ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ 24.5 ቢሊዮን ብር ደረሰ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከብድርና ቁጠባ ተቋምነት ወደ ባንክ የተሸጋገረው ፀደይ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና የ2015 የሒሳብ ዓመት ትርፉን ወደ 1.66 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱን አስታወቀ፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው የ1.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የሦስት በመቶ ዕድገት እንዳሳየ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባቀረቡ ሪፖርት አመልክተዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የሚባል ብድር ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማበደር እንደቻለ የተገለጸ ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት 27.6 ቢሊዮን ብር አድርሶታል ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ገዱ ሪፖርት ይህ የብድር ክምችት ከቀዳሚው ዓመት የ29 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ከዕቅዱ አንፃር ደግሞ የስምንት በመቶ ብልጫ አለው፡፡

ከተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድም በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 24.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ12 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ተገልጿል፡፡

ባንኩ የዘረጋውን ጠንካራ የብድር ክትትል ሥርዓት በመጠቀም የተበላሹ የብድር መጠኖች በጦርነቱ ምክንያት ከፍ እንዳይሉ ማድረግ መቻሉን የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ የተበላሸ የብድር ምጣኔ የብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ወለል ሳይበልጥ ጤናማ የብድር አስተዳደር ማረጋገጥ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ ገቢን ከማሳደግ አንፃር ውጤታማ ክንውን እንደነበርውና ከቀዳሚው ዓመት የስምንት በመቶ ዕድገት ማሳየቱን፣ እንደሁም የዕቅዱን 83 በመቶ በማስመዝገብ አምስት ቢሊዮን የሚሆን ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ባንኩ ለዓመቱ ከያዘው የወጪ ዕቅድ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ወጪ ያስመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪ ከቀዳሚው ዓመት የ25 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 3.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አቶ ገዱ ገልጸዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥም ሆነው አበረታች ውጤት ማስመዝገባችን የገለጹት አቶ ገዱ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነትና በየአካባቢው የነበሩ ሰዎች መፈናቀልና ግድያ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የኑሮ ውድነት ትልቅ መሰናክሎችን ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የባንኩ ሠራተኞችና ደንበኞች በሞት እንዳጡና 162 ቅርጫፎች ተዘግተው መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡   

የባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት ዕቅድና ግብን በተመለከተ አቶ ገዱ በዝርር ባቀረቡት ሪፖርታቸውው አዲስ 9.3 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 33.9 ቢሊዮን ብር ማድረስ አንዱ ነው፡፡

ከዚህ ሌላ የብድር ክምችቱን 37.7 ቢሊዮን ማድረስና ዓመታዊ የባንኩ ገቢም 7.55 ቢሊዮን እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የባንኩን አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር ወደ 13 ሚሊዮን ከፍ የማድረግ ዕቅድ መያዙንም በዚሁ ሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡ ፀደይ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 44 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2015 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ይህንን የሀብት መጠን 59.8 ቢሊዮን ብር ያደርሳል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች አንድ መቶ አዳዲስ ቅርንጫፎችን የመክፈት ዕቅድ ያለው ፀደይ ባንክ፣ የእነዚህ ቅርንጫፎች መከፈት አጠቃላይ 571 ቅርንጫፎች እንዲኖሩት ያስችላል፡፡

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አሁን ፀደይ ባንክ) ከ26 ዓመት በፊት በ1988 ዓ.ም. ሲቋቋም በሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ነበር፡፡ በወቅቱ ተቋሙን ባለአክሲዮን ሆነው የመሠረቱትም የአማራ ክልላዊ መንግሥት፣ የአማራ መልሶ ማቋቋም ማኅበር የአማራ ልማት ማኅበር ጥረት ኮርፖሬትና የአማራ ልማት ማኅበር ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ከ10 እስከ 35 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ይዘው ነው፡፡

40 ሠራተኞች ይዞ ሥራ የጀመረው ተቋሙ አሁን ላይ አጠቃላይ የሠራተኞቹን ቁጥር ከ12,200 በላይ ማድረስ ችሏል፡፡

ፀደይ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ እየገነባ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታውን አጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል፡፡

ይህ 36 ወለል ያለው ሕንፃ በአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ መንደር እየተባለ በሚጠራው ሰንጋ ተራ አካባቢ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ ግንባታው ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፀደይ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 7.7 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ 

ፀደይ ባንክ ከብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ መሸጋገሩን ይፋ ባደረገበት ወቅት 12 ሚሊዮን ቆጣቢዎችንና አንድ ሚሊዮን ተበዳሪዎችን ይዞ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የብድርና ቁጠባ ተቋሙ 471 ቅርጫፎች የነበሩት ሲሆን፣ በ148 ቅርንጫፎቹ የባንክ አገልግሎቱን በማስጀመር የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል የቻለ ባንክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች