Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች ካፒታል የማሳደግ ውሳኔና ተግዳሮቱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በካፒታል ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የ2014 የሒሳብ ዓመት ሪፖርታቸውን ይፋ ባደረጉባቸው ጠቅላላ ጉባዔዎች ጎን ለጎን፣ አስቸኳይ ጉባዔ በማካሄድ የካፒታል ማሳደግ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ መፈቀዱን ዋና ምክንያት በማድረግ፣ ካፒታቸውን ለማሳደግ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች በጠቅላላ ጉባዔ አዎንታዊ ምላሽ አግኝተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ወሮች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ካደረጉ ባንኮች 14ቱ በተለያየ መጠን ካፒታላቸውን ለማሳደግ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ እነዚህ ባንኮች በጥቅል ያደረጉት ጭማሪ ከ165 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ካፒታል ለማሰባሰብ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ያመለክታል፡፡ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ የሚጠበቅባቸው ባንኮች በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ካፒታል ለማሟላት የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ የአገሪቱ ባንኮች በቀጣይ አምስት ዓመታት ወደ 200 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ አክሲዮኖችን በመሸጥ ካፒታላቸውን ያሳድጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ሁለቱን የመንግሥት ባንኮችን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ የተከፈለ ካፒታላቸው 199.06 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ወይም ወደ 140 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የግል ባንኮች ነው፡፡ ስለዚህ የግል ባንኮች ካፒታላቸውን ለማሳደግ ያሳለፉት ውሳኔና የብሔራዊ ባንክን መመርያ ለማሟላት የሚያካሂዱት የአክሲዮን ሽያጭ ካፒታላቸውን ከእጥፍ በላይ የሚያሳድጉ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች 2014 መጨረሻ ላይ ከደረሱበት የ199.06 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ውስጥ፣ 30 በመቶው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የልማት ባንክ በመሆኑ የግል ባንኮች ይደርሱበታል የተባለው ካፒታል ላለፉት 27 ዓመታት ይዘውት የነበረውን የተከፈለ ካፒታል በአምስት ዓመት ውስጥ በእጥፍ የሚሳድግም ነው፡፡ ካፒታላቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ ካሳለፉ ባንኮች ውስጥ አዋሽ ባንክ አንዱ ነው፡፡ አዋሽ ባንክ እስካሁን የነበረውን የ12 ቢሊዮን ብር ካፒታል በአንድ ጊዜ 43 ቢሊዮን ብር በመጨመር 55 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

ከአዋሽ ባንክ ሌላ ዘመን ባንክ ከአምስት ቢሊዮን ወደ 15 ቢሊዮን፣ ኅብረት ባንክ ከአምስት ቢሊዮን ወደ 20 ቢሊዮን፣ ወጋገን ባንክ ከአምስት ቢሊዮን ወደ 20 ቢሊዮን፣ አንበሳ ባንክ ከ5 ቢሊዮን ወደ 20 ቢሊዮን፣ እናት ባንክ ከ2.7 ቢሊዮን ወደ አምስት ቢሊዮን፣ ኦሮሚያ ባንክ ከአምስት ወደ 25 ቢሊዮን ብር፣ አማራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ ካፒላቸውን ለማሳደግ ውሳኔ ካሳለፉ የግል ባንኮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በባንኮቹ ውሳኔ መሠረት ይህንን ተጨማሪ ካፒታል ለማሟላት የሰጡት የጊዜ ገደብ ከስድስት ወራት እስከ ሰባት ዓመት ይደርሳል፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ተጨማሪውን ካፒታል በአምስት ዓመት ለማጠናቀቅ ውሳኔ ማሳለፋቸው በቀጣዮቹ ዓመታት ከፍተኛ የባንክ አክሲዮኖች ሽያጭ የሚፈጽሙበት ወቅት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 ባንኮች ለሚጠብቃቸው ውድድርም ሆነ አገልግሎታቸውን ለማሳደግ ካፒታል ማሳደጋቸው መልካም ቢሆንም፣ በአንድ ላይ በዚህን ያህል ደረጃ ካፒታላቸውን ለማሳደግ የወሰኑት ውሳኔ ምን ያህል ይሳካላቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው ጎምቱው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደግ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን በአንዴ ይህ ሁሉ ባንክ ካፒታሉን በዚህ ደረጃ ለማሳደግ ሲነሳ እንዴት ያሳኩት ይሆን? የሚል ጥያቄ እሳቸውም እየጫረባቸው ነው፡፡

‹‹ባንኮቹ የካፒታል ዕድገት እያወጁ መሆኑ የደቦ ሥራ ይመስላል፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ዋና ሥራው ያለው ካፒታል ማሳደጉ ላይ ሳይሆን፣ ወደ ጎን በመመልከት አገር ውስጥ ያሉትን ባንኮች አንዱ ከሌላው ጋር በመነጋገር ተዋህዶ አብሮ እሴት መፍጠር ነው፡፡ መሆን ያለበትም ይሔው ነው የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ተዋህደው ካፒታላቸውን ከፍ በማድረግ መሥራት እንጂ ሁሉም በየፊናው የካፒታል ዕድገት ማወጁ ብቻ ስኬት ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡

‹‹ካፒታል ለማሳደግ ማወጅ ቀላል ይሆናል፤›› የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ነገር ግን ይህ ካፒታል ይገኛል አይገኝም? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ስለመሆኑ ያስባሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እስካሁን ጥሩ ደቪደንድ የከፈሉና ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው ባንኮች ያቀዱትን ካፒታል ማግኘት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የባንኮች የካፒታል ማሳደግ ውሳኔን አሁን ሲያዩት ግን ‹‹ጡሩምባ ተነፍቶ ካፒታላችሁን ካላሳደጋችሁ ትዘጋላችሁ የተባሉ ይመስላሉ፤›› በማለት በወረቀት ላይ ካፒታል አሳድጉ ማለት በተግባር ገንዘቡን ያገኙታል ማለት ያለመሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ባንኮቹ ካፒታል ለማሳደግ እንደ ምክንያት ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ከውጭ ባንኮች ጋር የተያያዘ ቢሆንም አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣  ‹‹የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ግፊት እየተደረገ ያለው እንዲህ ያለ ጥቅም ይሰጠናል በሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ሲመጡ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ስለሚመጡ ሰቅዞ የያዘንን የውጭ ምንዛሪ ችግር ትንሽ ያሽለዋል የሚል አመለካከት የገፋፋን ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔያቸው ላይ የካፒታል ማሳደግ ውሳኔ ያሳለፉት ጥቂት ባንኮች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ዳሸን፣ ንብ፣ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ፣ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያና አዲስ ኢንተርናሽና ባንኮች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህ ባንኮች መካከል ዳሸን ባንክና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል በላይ የተከፈለ ካፒታል ያላቸው ናቸው፡፡

ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉ አዳዲስ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የአምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ለማሟላት በተጠሰጣቸው የገቢ ገደብ  የሚሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ አንዱ ሲሆን ባንኩ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ (ሰኔ 2018) ድረስ አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መሙላት ካልቻለ ከሌላ ባንክ ጋር ተዋህዶ ለመቀጠል የሚዘጋጅ መሆኑን አሳውቋል፡፡ እንደ አዲስ ባንክ ሁሉ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ እንደሚሠሩ ያስታወቁ ባንኮች፣ እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም. ድረስ በአማካይ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ካፒታል ማሰባሰብ ስለሚጠበቅባቸው በቀጣይ ተከታታይ ዓመታት ካፒታላቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉት ርብርብ እስከ 200 ቢሊዮን ብር የሚደርስ አዲስ ካፒታል መሸጥ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ግን የሚናገሩት እንደርስበታለን ብለው ያሰቡት የካፒታል መጠን ከፍተኛ የሚባል ያለመሆኑን ነው፡፡ እንዲያውም የባንኮች ካፒታል አሁን ከሚባለው በላይ መሆን አለበት፡፡ አሁን ተበታትነው እያሳደጉ ያሉት ካፒታል ብዙ ቢመስልም ከዶላር አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ለየብቻቸው ሆነው እያሳደጉት ያለውን ካፒታል ማሰባሰብና ወደ ውህደት መሄድ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ በመግለጽ የአቶ ኢየሱስ ወርቅ ሐሳብን ይጋራሉ፡፡

ይህንን የካፒታል ማሳደግ ተግባራቸውን ግን በአምስትና በስድስት ዓመት ሳይሆን በአንድና በሁለት ዓመት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ካልቻሉ ሊገጥማቸው የሚችለው ውድድር ከባድ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ የተለየ የባንክ አገልግሎት (ስፔሻላይዝድ) ካደረጉ ባንኮች ውጪ ያሉ በቶሎ ተዋህደው ጠንካራ ባንክ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡

‹‹ስለዚህ በእኔ በኩል ከካፒታል ማሳደግ ባለፈ ባንኮች አጠገባቸው ካሉ ባንኮች ጋር እየተወያዩ አሁን ያሉ ባንኮች ተዋህደው ወደ ከአምስት እስከ ስምንት ባንኮች ቢሆኑ በጣም ጥሩ ነው፤›› ብለው የሚያምኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ መልካሙ ነገር ይህ ነው ብለዋል፡፡ ባንኮቹ ይህንን ያህል ካፒታል ለማሰባሰብ እንዴት ይቻላቸዋል የሚለው ደግሞ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸው ባንኮች አክሲዮናቸውን ለራሳቸው ባለአክሲዮኖች መሸጥ ዕድል ያላቸው ቢሆንም፣ አነስተኛ ካፒታል ያላቸው የሚፈልጉን ካፒታል ለመሙላት ለአዳዲስ ባለአክሲዮኖች መሸጥ ግድ እንደሚሆንባቸው አቶ ኢየሱስ ገልጸዋል፡፡

ባንኮቹ በቀጣይ ተከታታይ ዓመታት ካፒታላቸውን እያሳደጉ መሄዳቸው ሌላ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይህም ባንኮች እስካሁን ሲያገኙ የነበረውን ያህል የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ከዚህ በኋላ ላያገኙ ይችላል የሚል ነው፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ካፒታል ባደገ ቁጥር ቢያንስ ካፒታሉን ለማሟላት የተሰጠው የጊዜ ገደብ እስኪጠናቀቅ ድረስ እስከዛሬ ያለውን ያህል የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ባለአክሲዮኖች አያገኙም፡፡ ድርሻው በጣም ይቀንሳል ብለዋል፡፡ ሌላው ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያም በዚህ ጉዳይ የሚስማሙ ሲሆን፣ አሁን ባንኮች ያደረጉት የካፒታል ዕድገት ተገቢ ቢሆንም፣ የትርፍ ክፍፍል ድርሻ ላይ ግን ቅናሽ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ባንኮች ካፒታል ማሳደግ ግድ የሆነባቸው መጪውን ውድድር በማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ አሁን የደረሱበት የብድር መጠን ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የብድር ጣሪያ ምጣኔ ጋር እየተቀራረበባቸው ስለመጣ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት የግድ ካፒታላቸውን መጨመር ስላለባቸው ነው ይላሉ፡፡

በተለይ ትልልቅ የሚባሉ እንደ አዋሽና አቢሲኒያ ባንኮች በሪፖርታቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት፣ ካፒታል የማሳደጉ ካስፈለገበት ምክንያት አንዱና ዋነኛው ብለው የጠቀሱት ይህንን የብሔራዊ ባንክ መመርያ መተላለፍ ስለሚኖርባቸው ባንኮች እያሳዩ ያሉት ዕድገት የግድ ካፒታል መጨመር ስላለባቸው ነው ተብሏል፡፡

አቶ ዘመዴነህም አሁን እየተደረገ ያለው ካፒታል የማሳደግ እንቅስቃሴ ብቻውን ግብ እንደማይሆን ነው የገለጹት፡፡ ይህንን እንቅስቃሴያቸውን ባንኮቹ እርስ በርሳቸው ተዋህደው የካፒታል መጠናቸውን ቢያንስ ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችሉት ሲዋሃዱ ብቻ በመሆኑ፣ አሁን ያላችሁ ባንኮች አራትና አምስት ሆነው ወደ ውህደት መግባት እንደሚኖርባቸውም ያምናሉ፡፡ በአፍሪካ ሦስተኛው ትልቅ ኢኮኖሚ የሆነውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማስቀጠል የእነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ጥንካሬ ወሳኝ በመሆኑ የውህደት ጉዳይ ግድ መሆኑን አውቀው፣ ከወዲሁ በቶሎ በዚህ ጉዳይ ላይ መሥራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ከአንድ ወይም ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የካፒታል ገበያ ስለሚጀመር ባንኮቹ የዚህ ዋነኛ ተዋንያን ስለሚሆኑ የሚፈልጉትን ካፒታል በካፒታል ገበያ አክሲዮን ሽያጭ ሊያገኙ የሚችሉበት ዕድል ያለ ስለሚሆን ይህንን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አቶ ዘመዴነህ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉ ባንኮች 30 ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ መንግሥታዊ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የግል ናቸው፡፡ አጠቃላይ የሀብት መጠናቸውም በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 2.5 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች