Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንግሥት በሚያውቃቸው ደላለሎች ሕዝብ መማረር የለበትም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የግብይት ሥርዓት ብልሽት እንደ ምክንያት ከምንጠቅሳቸው ተዋንያን መካከል ደላሎች በቀዳሚነት ይቀመጣሉ፡፡ ለኑሮ ውድነትና ለዋጋ ንረት የደላሎች እጅ ሚና ቀላል ላለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የሕዝብና የአገር ዋነኛ ሀብት ተደርጎ የሚወሰደውን መሬት በረቀቀ ዘዴ ከሹመኞች ጋር ተቧድነው የሚቸበችቡት እነዚሁ ደላሎች ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መሬት በደላሎች እጅ ገብቷል፣ ስለዚህ መሬት የመንግሥት መሆኑ ትርጉም አጥቷልና ቢያንስ የከተማ መሬት የግል መሆን አለበት፤›› ማለታቸውን ልብ ይሏል፡፡ ይህ በደላሎችና በሹመኞች ቅንጅት የሚፈጸም ዘረፋ ግዥው ፓርቲ የሥልጣኔ መሠረት ነው የሚለውን የመሬት ፖሊሲ ጭምር ለመቀየር እንዲስብ አስገድዶታል ማለት ነው።

የምርቶች ከገበያ መጥፋት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች እጥረት መፈጠር፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ንረት መፈጠርና ከሌሎች የገበያ መዛባቶች ጀርባ ደላሎች መኖራቸው በገሀድ እየታየ ነው። 

የቤት ኪራይ ተወደደ ሲባል ገበያው የፈጠረው ብቻ አይደለም፡፡ በተከራይና በአከራይ መካከል ዘወትር ደላሎች የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ የሚፈጠር ጡዘት ስለመሆኑ እኔንና እኔን መሰል ተከራዮች ምስክሮች ነን፡፡ የአንድን ተከራይ በማፈናቀል የቤት ኪራይ ዋጋ ጨምሮ ለሌላ ግለሰብ እንዲከራይ በማድረግ የሚወስዱትን ኮሚሽን እያሳደጉ በሰው ሕይወት የሚቀልዱ ናቸው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን ዋጋ የሚወስኑትም እነዚሁ ደላሎች ናቸው፡፡ ዲዛየር የተባለው የቤት መኪና ዋጋ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ መወደዱ ሲደንቀን፣ ከሰሞኑ ደግሞ የዚሁ የቤት መኪና ዋጋ በአስገራሚ ሁኔታ የማሽቆልቆሉ ምክንያት የደላሎች ሚና መሆኑ ግልጽ ነው። ገበያውን ይዘውሩታል የሚለው አይገልጻቸውም። ከሲሚንቶ ምርት እጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጀርባ የደላሎች፣ የሹመኞችና የአምራቾች ትስስር እንዳለም እናውቃለን።

አርሶ አደሮች ጥረውና ግረው ያመረቱትን አትክልትና ፍራፍሬ ሁሉ ማሳው ድረስ ሄደው ‹‹በዚህ ካልሸጥክ አንረከብህም›› የሚሉ እነዚሁ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች በከተማ ገበያዎች ዋጋ የሚወጣላቸው አሁንም ደላሎች በምንላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ የሚተመነው በደላሎች ነው፡፡ ደላሎች የማይገቡበት ገበያ የለም፡፡ ስለዚህ ገበያው በአመዛኙ በደላላ የሚዘመር መሆኑ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡

ደላሎች በመሃል ሆነው ዋጋ ወሳኝ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የማያዙት ባለሥልጣን የለም። ደላሎች በእያንዳንዱ ግብይት መሃል ሆነው በሚያደርጉት ቅብብሎሽ የሚያገኙት የ‹‹ኮሚሽን›› ክፍያ ተደማምሮ የሚፈጠረው የዋጋ ንረትና ሸክሙ የሚያርፈው ሸማቹ ላይ ነው፡፡

ስለዚህ ደላሎች የማይገቡበት ጉዳይ የለም፡፡ ከገበያ ቀመስ ጉዳዮች ወጣ ካልንም፣ ለሕዝብ ግልጋሎት የተቋቋሙ ተቋማት ውስጥም ደላሎች እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ እዚህ አካባቢ ያሉት ደላሎች መጠሪያቸው ለየት ብሎ ‹‹ጉዳይ ገዳዮች›› ይባላሉ፡፡ ኅብረተሰቡ እነዚህ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎቶችን ያለ ችግር የማግኘት መብቱ ቢሆንም፣ በእነዚህ ‹ጉዳይ ገዳዮች› እና በተቋማቱ ሠራተኞች መካከል በሚፈጠር ግንኙነት ዜጎች ጉዳያቸውን በቀጥታ ሳይሆን በጉዳይ ገዳዮች በኩል እንዲፈጸም በማድረግ፣ ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎትም ጠንቅ ሆነዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎቶች ያለ ጉዳይ ገዳዮች አይከወንም፡፡ ስለዚህ ደላሎች በዚህች አገር ሁሉ ነገር ውስጥ አሉ ካልን ሁሉ ነገራችን እየተበላሸ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ አብዛኛው ከድለላ ጋር የተያያዘ ሥራ ከሕጋዊነት የራቀ ነው፡፡ እጅግ የበዛ ገንዘብ የሚገኝበት ግን ደረሰኝ የማያውቀው ገንዘብ የሚንቀሳቀስት ነው፡፡ 

በተለይ የከተማ መሬት፣ ቤትና ተሽከርካሪ ሽያጭ ደላላ ያልነካው የለም፡፡ እያንዳንዱ ሽያጭ ደላሎች ከሁለት ወገን የሚጨልፉት ገንዘብ ግብር አያውቀውም፡፡ ስለዚህ ሕግ የማያውቀው በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ቅብብሎሹ ብዙ ነው፡፡ ደላሎች ለዚህች አገር የግብይት ሥርዓት መበላሸትና ለዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ችግር ፈጣሪነታቸው መንግሥት ዕርምጃ ለምን አይወስድባቸውም ሲባል የሚንቀሳቀሱት በሕገወጥ መንገድ በመሆኑ እነሱን ለመቅጣትም ሆነ ከግብይት ሰንሰለት ውስጥ ለማስወጣት አስቸጋሪ ነው የሚል እምነት ያላቸው ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ይህ አመለካከት ግን ስህተት ስለመሆኑ የተረዳሁት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወጣ የተባለው መረጃን ካየሁ በኋላ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል የተላለፈው መረጃ በሦስት ዘርፎች የተሰማሩ ደላሎች ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ማድረጉን የሚጠቁም ነው፡፡ 

በእህል፣ በቁም እንስሳትና በአትክልትና በፍራፍሬ የተሰማሩ ስምንት ሺሕ በላይ ናቸው የተባሉ ደላሎች ፈቃድ ተሰርዟል፡፡ ‹‹ደላሎች የገበያውን ዋጋ ከማናር በዘለለ ምንም የሚጨምሩት እሴት የለም፤›› የሚለው የሄው መረጃ ሚናቸውን በማጤን ፈቃዳቸው እንደተሰረዘም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ደላሎች የገበያውን ዋጋ ከማናር በዘለለ ምንም የሚጨምሩት እሴት የለም፡፡

በአንፃሩ ግን እነዚህ ደላሎች ከተጠቀሱት ሦስት ዘርፎች ውጪ ባሉ በሌሎች ቋሚና ተንቀሳቃሽ ዘርፎች ብቻ ተወሰነው የማገናኘት ሥራ እንዲሠሩ መወሰኑን መረጃው ይነግረናል፡፡

እንደ ሸማች ይህ መረጃ ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ‹‹ለካስ እስካሁን ስንበዘበዝ የነበረው ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው መንግሥት በሚያውቃቸው ደላሎች ነበር?›› እንድንል የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ እስካሁን እነዚህ ደላሎች መንግሥት የሚያውቃቸው ፈቃድ የሌላቸው ሆነው ለቁጥጥር ያስቸገሩ ይመስለን ነበር፡፡ አሁን የተነገረን ግን ደላሎች እየፈጠሩ ያሉት ችግር በመንግሥት ዕውቅና የሚፈጸም አስመስሎታል፡፡ 

‹‹በየግብይት ቦታው ደላሎች ችግር እየፈጠሩ ነው፤›› በሚል ከኅብረተሰቡ የሚሰማውን ሮሮ እያደመጠ ዝም ብሎ ቆይቶ ‹‹ደላሎቹን እኮ እውቃቸዋለሁ ፈቃድ አላቸው፤›› ሲለን ማስገረሙ አልቀረም፡፡

ደላሎች እየፈጸሙ ያሉትን ሕገወጥ ተግባር ከታች እስከ ላይ ያለ ባለሥልጣን ነጋ ጠባ ሲደሰኩርና ደላሎችን ከግብይት ሥርዓት ውስጥ ማስወጣት ካልተቻለ ችግሩ ይብሳል ሲባል የችግሩ ፈጣሪዎች በስም የማይታወቁ የመንግሥት መዝገብ የማያውቃቸው መስሎን ነበር፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ የሚታወቁ ከሆነ እነርሱን ለመቆጣጠር ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው? ያልተገባ ጥቅም እያገኙ ገበያውን እያወኩና ለሸማችና ተገልጋይ የምሬት ምንጭ ሆነው ከሚያገኙት ገንዘብ ግብር ይከፍሉ ነበር? 

በአንድ በኩል ግን ሚኒስቴሩ ዕርምጃ የዘገየ ቢሆንም መልካም ነው፡፡ ፈቃድ ያላቸው ደላሎችን ያህል ግን ፈቃድ በሌላቸው ሕገወጦች ቁጥር የትየለሌ መሆኑን ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ ቢዘገይም የሚኒስቴሩ ዕርምጃ መልካም የመሆኑን ያህል ዕርምጃው ያስገኘውን ውጤትም በተግባር ማየት እንፈልጋለን፡፡ 

መንግሥት በሚያውቃቸው ደላለሎች ሕዝብ መማረር የለበትም፡፡ ደላሎች ላይ ቁጥጥሬን አጠብቃለሁ ማለቱ ግን ይደገፋል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት