Tuesday, November 28, 2023

ኢትዮጵያን የወረረው የፖለቲካ ገበያ ምንድነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፖለቲካው ገበያ ጽንሰ ሐሳብን ያመነጨውና አሁንም ድረስ በስፋት እየተመራመረበት የሚገኘው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) ነው። ፕሮፌሰር አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያን ጨምሮ የአብዛኞቹ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ፖለቲካን ጠንቅቆ ያጠና ተማራማሪ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቀድሞዋ ሱዳን የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተወከሉ ልሂቃን መካከል አንዱ ነበር። 

አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) በሱዳን የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ አገሪቱ በተደጋጋሚ በተመላለሰባቸው ዘመናት፣ ከተለያዩ የሱዳን የፖለቲካ ልሂቃን እየተገናኘ በሚወያይበት ወቅት፣ ልሂቃኑ በሱዳን ዳርፉር ተንሰራፍቶ ለነበረው ግጭት ዋነኛ ምክንያት ‹‹የፖለቲካ በጀት ነው፤›› የሚል ሐሳብ በተደጋጋሚ ከአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን በመስማቱ፣ የፖለቲካ ገበያ ጽንሰ ሐሳብን ለማመንጨት ቁልፍ ምክንያት እንደሆነው በጽሑፎቹ ይጠቅሳል። በሱዳን የተረዳው ሁኔታ፣ በሶማሊያም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችም ይስተዋል እንደነበርም ይጠቁማል። 

በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት መመራመሩን የቀጠለው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር)፣ የፖለቲካ ገበያ ሁኔታ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በሽታ ብቻ እንዳልሆነ ለመለየት ችሏል።

የፖለቲካው ገበያ ጽንሰ ሐሳብ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ የፖለቲካ ልሂቃን ጋር በመገናኘትና በመወያየት የመነጨ ቢሆንም፣ በእነዚህ አገሮች የታየው የፖለቲካ ገበያ ተሞክሮና ባህሪያት፣ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ በርካታ አገሮች ጋር የሚስማማ ሆኖ በመገኘቱ፣ ጽንሰ ሐሳቡ በዓለም አቀፍ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞች ወዲያውኑ ዕውቅና ማግኘቱን እ.ኤ.አ. በ2016 በጻፈው ማብራሪያ ይጠቅሳል። ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ያስተዋወቀው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) አሁንም በጉዳዩ ላይ በስፋት እየተመራመረበት ይገኛል።

የፖለቲካ ገበያ ምንድነው? 

ጽንሰ ሐሳቡን ያስተዋወቀውና ያበለፀገው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር)፣ የፖለቲካ ገበያ በግላዊ የፖለቲካ ግብይት ላይ የተመሠረተ የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን፣ የፖለቲካ አገልግሎት፣ አጋርነትና ተወዳዳሪነት በገንዘብ ወይም በቁሳዊ ሽልማት መለዋወጥ እንደሆነ ይገልጻል። አንድ የፖለቲካ ገበያ ተዋናይ የሆነ ሹመኛ ምን ያህል መክፈል እንዳለበት ከፖለቲካ ልሂቃኑ አባላት ጋር በመደራደር፣ በጥሬ ገንዘብ ወይም ሌሎች ጠቃሚ ሀብቶችን ለአብነት ያህል የፕሮጀክት ኮንትራቶችን ድጋፍ ለማግኘት፣ የምርጫ ድምፅ ለማሰባሰብ፣ ሕዝብ ለማፍራት ወይም ጎጂ ጥቃት ለማድረስ እንደሚያውላቸው ያስረዳል።

በዚህ የፖለቲካ ገበያ የተወረረ አገር፣ የአገር ግንባታና ተቋማዊ የፖለቲካ አስተዳደር ጅማሮዎቹ የመደናቀፍ ወይም የመቀልበስ አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችልም ይጠቁማል።

የፖለቲካ ገበያ በተለያዩ መንገዶች ሁከት የሚፈጥር እንደሆነ የሚገልጸው አሌክስ ዴዋል፣ ሁከት መቀስቀስ አንዱ የፖለቲካ መደራደሪያ ዘዴ ሲሆን፣ በፖለቲካ ገበያው የበታች ተጫዋች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳበት ወይም ዋጋውን ለመጨመር የሚሞክርበትና ገዥ ደግሞ የይገባኛል ጥያቄውን የሚከራከርበት ወይም ዋጋውን ዝቅ የሚያደርግበት ዘዴ እንደሆነ ያስረዳል። ብጥብጥ የተቀናቃኝን ወይም የይገባኛል ጥያቄ አቅራቢውን አካባቢ ለመጉዳት ወይም ለማጥፋት በመሞከር በገበያ ላይ ያለውን ዋጋ እንደሚቀንስም ይጠቁማል። ብጥብጥ ከስህተትም ሊነሳ እንደሚችል የሚገልጸው ተመራማሪው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር)፣ አንድ የፖለቲካ ንግድ ተዋናይ ተቀናቃኞቹን በተሳሳተ መንገድ በማንበብ ወይም በመረዳቱ ሁከት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ይገልጻል።

በፖለቲካ ገበያ ውስጥ ያለው የትጥቅ ግጭት፣ ከጥልቅ ጠላትነት ወይም ከማይታረቅ ልዩነት የመነጨ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የፖለቲካ ገበያ ውስጥ የሚሳተፉ ተገዳዳሪ ተዋናዮች ከሁኔታዎች ጋር አቋማቸው ተለዋዋጭ እንደሚሆን ይገልጻል። ‹‹የዛሬ ወዳጅ የነገ ጠላት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ የዛሬው ጠላትም የነገ አጋር ሊሆን ይችላል። በዚህ ምክንያት የፖለቲካ ልሂቃን ከግጭት ሜዳ ውጪ ወዳጃዊ ወይም ተግባቢ ሊሆኑ ይችላሉ፤›› ይላል።

በፖለቲካ ገበያ አመክንዮ፣ ሁከት በዋናነት የመደራደሪያ ዘዴ እንደሆነ የሚገልጸው ተማራማሪው አሌክስ ዴዋል፣ ነገር ግን ክፍያ ያልተፈጸመበት ሁከት ትክክለኛ ዋጋው የማይታወቅ ገንዘብ መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባ በሀተታው ያስረዳል። በፖለቲካ ገበያ ውስጥ በጣም ከባድ የሆኑ ሁከቶች ብዙውን ጊዜ የሚነሱት የፖለቲካ ንግድ ተዋናዮች በሚፈጽሟቸው ስህተቶች ምክንያት ሲሆን፣ ስህተቶቹ የሚታወቁት የተፈጠረው ጥቃት የበቀል አመክንዮ እየፈጠረ ግጭቱን በማባባስ መጠነ ሰፊ እንደሚያደርገው ያስረዳል። 

የፖለቲካ የገበያ ቦታ ከተቋማዊ ሙስና፣ በወንጀለኞች ተጠልፎ ከተያዘ የሌቦች አገዛዝ፣ የጦር አበጋዝነትና የጦርነት ኢኮኖሚዎች ጋር በቅርበት የሚዛመድ መሆኑንም ይጠቁማል። ሙስና ከፖለቲካ ገበያ ጋር የሚወዳጅ ቢሆንም ሁለቱ ግን የተለያዩ ባህሪ ያላቸው ክስተቶች መሆናቸውን ያስረዳል።

ለፖለቲካ ገበያ የሚውል በጀት በአብዛኛው ሕጋዊ የገንዘብ ምንጮች ላይ የሚመሠረት ሲሆን፣ አብዛኛው የገንዘብ ወጪ የሚከፈለውም ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የፖለቲካ ድጋፍ ወይም ጥቅም ለመሸመት ነው። በዚህም ምክንያት ሙስና የፖለቲካ ገበያ ወደ ተቋማትና ተቋማዊ ሥርዓት እንዲገባ የማመቻቸት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቁማል።

የክለፕቶክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት የተለመደ ትርጉም፣ የሌቦች አገዛዝ ሲሆን፣ ከፖለቲካ ገበያ አንፃር ያለው ፍቺና ባህሪ ግን በመጠኑ እንደሚለይ ይገልጻል። ይኸውም አቅርቦትና ፍላጎት የሚባሉትን የገበያ ዘዴዎችን በመጠቀም የሕዝብ የሥልጣን አካላትን ለስርቆት ምቹ በማድረግና ስርቆትን በእነዚህ ተቋማት በመፈጸም፣ የፖለቲካ ሥልጣንን መጨበጥ ወይም ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ መሆኑን ይገልጻል።

የኢኮኖሚ ወንጀለኞች በስግብግብነት ብቻ የሚነዱ ቢሆንም የፖለቲካ ገበያ የሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ ግን ባህሪና ግባቸው የተለየ ነው። በዚህ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ የሚፈጸሙ ኢኮኖሚያዊ ወንጀሎች የፖለቲካ ሹመትን ለማበልፀግ ብቻ የሚውል ነው። የፖለቲካ ንግድ ተዋናዮች በፖለቲካ ገበያ ውስጥ እንዲወዳደሩ ወይም እንዲወድቁ በሚያስገድድ ሥርዓት ውስጥ ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ያሳድዳሉ። ግባቸው ወይም የሚያሰሉት ትርፍ ሥልጣን በመሆኑ የሚያስተዳድሯቸውን አብዛኞቹን ፕሮጀክቶች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀሙባቸዋል። በተጨማሪም የግል ሀብት በማጠራቀም ወደ ፖለቲካው ለመግባትና ሥልጣን ለመያዝ እንደሚጠቀሙባቸው ያትታል።

የፖለቲካ ገበያ በብሔር ወይም በሃይማኖት ማንነት ላይ በቆሙ መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ከተንሰራፋ የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ይገልጻል።

የፖለቲካ ንግድ በኢትዮጵያ 

የፖለተካ ገበያ (The Political Market Place) የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ያመነጨውና ያበለፀገው እንዲሁም አሁን ድረስ በስፋት እየተመራመረበት የሚገኘው ፕሮፌሰር አሌክስ ዴዋል እ.ኤ.አ. በ2018 The Future of Ethiopia: Developmental State or Political Market Place በሚል ርዕስ፣ የኢትዮጵያን መፃኢ የፖለቲካ ሁኔታ የቃኘበት መጣጥፍ አቅርቦ ነበር። ይህ መጣጥፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቀድሞው ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ አሸንፈው ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት የቀረበ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሚከተሉት የአስተዳደር መርህን በመቃኘት በእሳቸው የፖለቲካ አስተዳደር ወቅት በኢትዮጵያ የPolitical Market place ሥርዓትን ሊያነግሥ እንደሚችል ሥጋቱን የገለጸበት ነው። 

አሌክስ ዴዋል (ፕሮፈሰር) ይህንን ሥጋቱን ከገለጸ ከአራት ዓመታት በኋላ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የፖለቲካ ገበያ በኢትዮጵያ መንስራፋቱን በይፋ ገልጸዋል።

ለገዥው ብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጻ ሲያደርጉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀየረ የብልፅግና ጉዞውን አደጋ ውስጥ የሚከት ልምምድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ወሮታል ሲሉ ተደምጠዋል።

ፖለቲካ በሁለት እንደሚከፈል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንዱ ሕጋዊ ፖለቲካ ሲሆን፣ ይህ በሕግ የሚወከን ፖለቲካ እንደሆነ አስረድተዋል። ሁለተኛው ደግሞ በገንዘብ፣ በጥቅም የሚከወን የሚሸቀጥ ፖለቲካ እንደሆነና ይህም የፖለቲካ ገበያ እንደሚባል ጠቁመዋል።

የፖለቲካ ገበያ ሁኔታ የተፈጠረበት አገር ውስጥ ፖለቲካ በሐሳብ ፉክክር የሚከወን መሆኑ ቀርቶ እንደማንኛውም Commodity ወይም ሸቀጥ የሚገዛና የሚሸጥ እንደሚሆን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ከአሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) ጽንሰ ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምተዋል።

በፖለቲካ ገበያ ውስጥ ፖለቲካ በገንዘብ የሚሸጥ፣ ኢ-መደበኛና በሚስጥር እንደሚከወን፣ ይህ ሁኔታ ሲፈጠርም ፖለቲካ ተገማች እንደማይሆን ገልጸዋል። 

‹‹የሚነገረው ፖለቲካና በተግባር የሚፈለገው የተለያዩ እንደሚሆኑ፣ በዚህም የግለሰቦች ጥቅምን በስውር የሚያገለግል፣ ለእያንዳንዷ ሁነት ትርፍ ያሰላና የመጨረሻ ግቡም ሥልጣን መቀራመት ይሆናል። በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ የፖለቲካ ገበያ ጋር ተሳስሮ የሚፈጸም ነው። ከአንድ ቦታ አጀንዳ ይሰጠዋል ተቀባይ ሆኖ ሳያውቀውም ሆነ እያወቀው የአጀንዳው ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፤›› ብለዋል። 

የፖለቲካ ገበያ ዓውድ በሦስት ነገሮችን እንደሚፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንደኛው ሙስና እንደሆነ፣ ሁለተኛው አመፅና ግጭትን የሚሻ ሲሆን፣ በዚህም የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የፖለቲካ ፍላጎትን እንደሚያስፈጽምና ሦስተናኛው ዓውድ ደግሞ አማፂን በማንቀሳቀስ ግጭት የሚቀሰቅስ እንደሆነ ገልጸዋል። በስተመጨረሻም የመንግሥትን ሥልጣን መቆጣጠር ይይዛል፣ የከፋ ሲሆን ደግሞ ተቋም በማፍረስ አገር እንደሚበትን አስረድዋል።

በኢትዮጵያ ሁኔታ የፖለቲካ ገበያ መገለጫ ከሆኑት  አንደኛው የብሔር ወይም የማንነት አክራሪነት መሆኑንና ይህ አክራሪነትም በኢትዮጵያ እጅግ የነገሠበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ጠቁመዋል። ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሁኔታ መገለጫ ሌብነት ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ አጀንዳን አውቆትም ይሁን ሳያውቅ በመቀበል በኢትዮጵያ ሰላምና ኅብረት እንዳይኖር የሚሠራበት አዝማሚያ እየነገሠ እንደሆነ ገልጸዋል። 

በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ብልፅግና ውስጥ ተቋማዊ ሙስና የለም። ነገር ግን ሌብነት አለ። ከመሬት ጋር የተገናኘ ሌብነት አለ፣ ኮንትራት የሚሸጡ ግለሰቦችና ጥቂት ቡድኖች አሉ፣ መታወቂያ ለመስጠትና በመሳሰሉት ገንዘብ እየተቀበሉ ሕዝብ ያማረሩ ሌቦችም አሉ። በሌብነት ያገኙትን ገንዘብ ተጠቅመው አክቲቪስት በመግዛት ሥልጣናቸውን የሚያደላድሉ ባለሥልጣናት አሉ። 

በመሬት፣ በብሔር በቡድን ተጠልፈናል። ይህ ሀኔታን መቀየር ካልቻልን መንግሥትን መቆጣጠር ይፈጠርና አገር ማፍረስ ይጀምራል። 

ፖለቲካ ውስጥ ሁልጊዜም የግለሰቦች ውሳኔ ይኖራል ነገር ግን ተቋማዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ተቋማዊ ሥነ ሥርዓትን ተከትሎ የማይወሰን ከሆነ ጥፋት እንደሚከተል የተጠቁስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ይህ ሁኔታ ሲከሰት ፖለቲካ ለግሰቦችና ለቡድኖች ጥቅም ብቻ እንደሚውል ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲገልጹም፣ ‹‹የእኛን አገር ሁኔታን አስፈሪ የሚያደርገው ተቋም የለም። አንድ የክልል ፕሬዚዳንት በራሱ ክልል ሆኗል። ሚኒስትር ከሆነም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በሙሉ በእጁ ይዞ ግለሰቡ በራሱ ተቋም ሆኗል። ይሄ አሠራር ካልተገራ ሄዶ ሄዶ ፖለቲካ ሸቀጥ ይሆንና ገንዘብ ያለው ሰው የፈለገውን ያደርጋል። ሀብታም ሚኒስቴር ይገዛል፣ ሚኒስቴር ፖለቲካን ለመሸቀጥ ዩቲዩበር ይገዛል። አንድ ሚኒስቴር አንድ ባለሀብትና አንድ ዩቲዩብር የፈለጉትን ያደርጋሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ አሁን እየሆነ ነው፤›› ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሰማራት ‹‹በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና›› በሚል ርዕስ ዙረያ የዩኒቨርስቲ መምህራንና አጠቃላይ የአገሪቱ ምሁራን በማወያየት ላይ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ምሁራንን እንዲያወያዩ ከተመደቡት መካከል የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ፣ በኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካ ገበያ እንዲበቅልና እንዲንሰራፋ ምቹ መደላድል እየፈጠሩ ካሉት አዝማሚያዎች መካከል አንዱ የነቀዙ ፖለቲከኞችና ነጋዴዎች፣ ለሌብነታቸው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር አክቲቪስቶችን በመግዛት ግጭትና የፖለቲካ ልዩነትን እየዘሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከሌሎች የፖለቲካ ልሂቃን ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር ንቅዘትና ሌብነታቸውን ለማስቀጠል እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም አክራሪንትን ለመፍጠርና ለማንሰራፋት አክራሪዎችን በገንዘብ እየደገፉ እንደሚገኙ ጠቀሙዋል።

እነዚህ ኃይሎች በፖለቲካ ገበያው ለመቆየት የትጥቅ እንቅስቃሴን በመደገፍ እንዲሁም አክራሪነትን መሠረት ያደረጉ ሹኩቻዎችን እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹እነዚህ ኃይሎች በፖለቲካው ውስጥ እጅግ ተፈላጊ መሆን ሲጀምሩ የውጭ ኃይሎች የእነዚህን የአገር ውስጥ ነጋዴዎች ታማኝነት በመግዛት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያስፈጽሙበት ሁኔታ ይፈጠራል፤›› ሲሉም ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

መፍትሔው ምንድነው?

‹‹ትልቁ የዚህ አገር ፈተና የፖለቲካ ገበያ ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ለብልፅግና ባለን ጉጉትና ሥራ ላይ እንቅፋት የሚሆን የፖለቲካ ገበያ በማንኛውም መንገድ መገረዝ አለበት። ምክንያቱም አደገኛ ስለሆነና ጉዟችንን ስለሚያቆም፤›› በማለት የመፍትሔ መንገዱን አስተዋውቀዋል።

መፍትሔውን ሲዘረዝሩትም፣ ባለሥጣናትንና ፖለቲከኛውን በባለሀብቶች ኪስ ውስጥ እንዳይሸጎጡና ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አሌክስ (ፕሮፌሰር) ዴዋል የፖለቲካ ገበያን በተመለከቱ የተለያዩ ትንታኔዎቹ የሚመክረው ግን የኃይል ወይም ሥር ነቀል የሆነ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የተጠና አካሄድን መከተል ተመራጭ እንደሆነ ይገልጻል።

አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር)፣ ሙስናን ለመቋቋም የሚረዱ ቴክኒካል መሣሪያዎች በመጠቀም ዕርምጃ መውድ ሙስናን መዋጋት ይችላል። ነገር ግን የፖለቲካ ገበያውን አያፈርስም። እንደ ማዕቀብ ወይም ክስ የመሳሰሉ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሙስናን፣ ሕገወጥ የፋይናንስ ፍሰትን፣ ወንበዴነትን ወይም የጦርነት አትራፊነትን መዋጋትና ወንጀለኞችን መያዝ ይችላል፣ ነገር ግን የፖለቲካ ገበያውን እንደገና ያዋቅረዋል እንጂ አያፈርሰውም፤›› ይላል። 

ተመራማሪው አሌክስ ዴዋል (ፕሮፌሰር) እንደሚለው ከሆነ፣ በሙስና ላይ ያነጣጠረ ዕርምጃ መውሰድ እንዲያውም የፖለቲካ ገበያ አለመረጋጋትን እንደሚያስከትልና ይህም ወደ ለየለት ብጥብጥ ሊያመራ ይችላል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ መብቀል የጀመረው አገሪቱ የምትከተለው የብሔር ተኮር ፖለቲካ ከነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር መቋጫ ማግኘት ወይም እንዲለዝብ ማድረግ ባለመቻሉ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የፖለቲካ ገበያ ዘር እንዲበቅል በማድረግ ረገድ ኢሕአዴግን ይከሳሉ።

የቀድሞው ኦሕዴድ በኢሕአዴግ ውስጥ የተከሰተውን የሥልጣን ሽኩቻ ለማሸነፍ የተጠቀመው መንገድ አመፃን መሆኑን የሚጠቅሱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ ይህንን የተሳሳተ መንገድ ሳይታረም የሰሜኑ ጦርነት መከሰቱና ይህንን ለማሸነፍም የሁከት መንገድን የመረጡ ኃይሎችን ከማረም ይልቅ ጦርነቱን እንዲደግፉ የማቅረብና በጦር መሣሪያ ጭምር የመደገፍ ሁኔታ መፈጠሩ የፖለቲካ ገበያውን አስፈሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተቋማዊ ሥርዓትንና መርህን ባለመከተል ከሃይማኖት ተቋማትና ሰባኪዎች ጋር ያደርጉት የነበረው ግንኙነት አሁን ላይ ቀዝቀዝ ቢልም፣ ከእሳቸው በተቃራኒ የቆሙፖለቲከኞች የእሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ ማበረታታቸውን ይጠቅሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማው ባልመደበልኝ በጀት ሊጠይቀኝ አይችልም በማለት ያደረጉት ይፋዊ ንግግር፣ በቂ ምክንያት ቢኖራቸው እንኳን ሕጋዊና ተቋማዊ የፖለቲካ መርህን የጣሰ ከመሆኑም በላይ፣ ሌሎችም በዚሁ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የሚያበረታታ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በመሆኑም የፖለቲካ ገበያ ሥርዓትን ለማጥፋት መርህ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ አስተዳደርን ዳግም መመለስና ያልተገቡ ግንኙነቶችን ማጥፋት እንዲሁም የፖለቲካ ገበያው እንዲንሰራፋ ምቹ የሆኑ የሚዲያ አጠቃቀሞችን መቅረፅ በአጠቃላይ ደግሞ ተቋማዊ ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል ይላሉ።

 

 

 

 

 
       

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -