Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ጀበርቲና ጀበርቲነት በኢትዮጵያ በሶማሊያና በኤርትራ

ክፍል ፪

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

‹‹ጀበርቲ›› የተባለው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የየመንና የሰሜን ኬንያ ሙስሊሞች የጋራ መጠሪያና ሰፊ ሙስሊም ኅብረተሰብ የያዘ ሲሆን፣ ስለቃሉ አመጣጥም የተለያዩ መገለጫዎች እንዳሉት በክፍል አንድ ጽሑፍ ላይ ገልጸናል። በዚህኛው  ሐተታችንን እንቀጥላለን፡፡

ኤድዋርድ ኡሎንዶርፍ ዋናው ርዕሰ ጉዳዩ የነጃሺ ጀበርቲዎችን የሚመለከት ቢሆንም፣ የመጀመሪያዎቹ ጀበርቲዎች ዘይላዕ ውስጥ ጀበርታ ተብሎ በሚጠራው የጀበርቲዎች መኖሪያ ቦታ ይኖሩ እንደነበር ያስረዳና እነሱም ከሒጃዝ እንደመጡ፣ ቀጥለውም ወደ ይፋት (ምሥራቅ ሸዋ) እንደመጡና መኖሪያቸውንም ጀበርታ በማለት ሰይመው እንደኖሩ ያስረዳል። ቀስበቀስም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመስፋፋት እስከ ኤርትራ፣ ትግራይ፣ ጎንደርና ጎጃም እንደደረሱ ይገልጣል።

ኡለንዶርፍ ከዚህም በተጨማሪ ጀበርቲ የሚለው ቃል የተገኘው ጀበርታ ከሚለው የዓረብኛ ቃል ሲሆን፣ ቃሉንም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙበት ነቢዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ወደ ሐበሻ የተሰደዱ የመጀመሪያዎቹ እስልምናን የተቀበሉ ተከታዮቻቸውን ተቀብለው ያስተናገዱትንና ከጠላቶቻቸው ሊደርስባቸው ይችል ከነበረው ችግር የታደጉላቸውን የንጉሥ አርማህን ውለታ ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል እንደሆነ ጠቁሞ፣ ‹‹አኺ አሕመድ ጀበርና›› ማለትም ‹‹ወንድሜ አሕመድ ነጃሺ ከፍተኛ ውለታ ዋለልኝ፣ ፍላጎቴን አሟላልኝ፣ ግዴታዬን ተወጣልኝ፣ ረዳኝ፣ አገዘኝ›› እንደማለት እንደሆነ፣ ይህም ቃል ከጊዜ በኋላ ወደ ጀበርቲነት ተቀየረ በማለት ያብራራል። ኡሎንዶርፍ እንደሚለው ቃሉን የሚጠቀሙበት አማርኛ፣ አገውኛና ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሲሆኑ፣ እነዚህም ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ከነጃሺ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስልምናን የተቀበሉ የመጀመሪያ ሙስሊሞች እንደሆኑ አጥንት ጉልጥምታቸውን ቆጥረው የሚያስረዱ እንደሆኑ የአካባቢውን ሰው ጠቅሶ ያስረዳል። በዚህም መሠረት የሰሜን ኢትዮጵያ (ኤርትራ)፣ ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘሩን ከዑስማን ኢብን ዓፋን እንደሚወርድ ይተነትናል። አፈታሪኩ እንደሚለው ዑስማን ኢብን ዓፋን የተባሉት የነቢዩ ሙሐመድ የመጀመሪያው ተከታይ (በኋላ ሦስተኛው ኸሊፋና ሩቅያ የተባለችው የነቢዩ ሙሐመድ ልጅ ባለቤት) በምድረ ሐበሻ በነበሩበት ጊዜ አንድ ልጅ ከአንዲት ሐበሻ  እንደወለዱ፣ እርሱም ከእናቱ ጋር በሐበሻ እንደቀረና የሱም ዘር ሲራባ የሰሜናዊ ሐበሻን እንደሞላ ይወሳል።

ጆን ስፔንሰር ትሪሚንግሃም (ከ1904-1987) የተባለው ስለአፍሪካ እስልምና በስፋት እንደጻፈ የሚነገርለት እንግሊዛዊ ‹‹እስልምና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስና ስለሱፊ ሥርዓት በመጻፍም የሚታወቅ ነው። ትሪሚንግሃም በተለይም ‹‹እስልምና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ1965 ለንባብ ባበቃው መጽሐፉ ልዩ ልዩ መረጃዎችን በመጥቀስ ስለ ጀበርቲዎች ያገኘውን መረጃ ያቀረበ ሲሆን በዚህም መጽሐፉ፣ በኢትዮጵያ ገጠሮችና ከተሞች ጀበርቲዎች መኖራቸውን ይገልጽና ከእነዚህም መካከል ከየመን የመጡ ጀበርቲዎች ይገኙባቸዋል ይላል። ከእነዚህ ተለይተው ከሚታወቁት የመናውያን በስተቀር ኢትዮጵያውያን ጀበርቲዎቹ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የተለዩ እንዳልሆኑ ይገልጻል። ትሪሚንግሃም እንደሚለው የመጀመሪያዎቹ ጀበርቲዎች የመጡት ከሒጃዝ ሲሆን እነሱም በመጀመሪያ ጀበራ (ጀበርታ) ከሚባል በይፋት ሱልጣኔት ሥር ከነበረ ግዛት ውስጥ ሰፈሩ። ጀበርታም ያኔ የዘይላዕ አካል እንደነበረች ‹‹አል-ዒልማ›› በሚል ርዕስ በ1434 ታሪክ የጻፈውን አልመቅሪዚን በዋቢነት ያቀርባል።  አልመቅሪዚ ‹‹ይፋትን፣ ዋፋትና ሉፋት›› እያለ በማፈራረቅ እንደሚጠቅስ ያስታውሳል። ሆኖም እነዚህ ስሞች አንድ መሆናቸውና አለመሆናቸውን መጪው ትውልድ መርምሮ ሊደርስበት እንደሚችል የዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ያምናል። ትሪሚንግሃም ከዚህም በተጨማሪ በ1515 ፕሪስተር ጆን የተባለ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትን ትብብር ለመፈለግ ወደ ምድረ ሐበሻ መጥተው የነበሩትን የፖርቱጋል ሚሲዮን አባል የነበሩትን ፍራንሲስኮ አልቫሬዝን በመጥቅስ የጀበርቲዎች መንደር ከውቅሮ የአንድ ቀን ጉዞ ርቀት ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ይጠቅሳል። ትሪሚንግሃም በዚህ ጽሑፉ በፉቱሑል ሐባሽ  በአንድ ቀን ርቃ ትገኛለች የሚለው የዛሬዋ ውቅሮ ከተማ ከነጋሺ በጥንት ጉዞም ቢሆን ከግማሽ ቀን የበለጠ ስለማይርቅ ምናልባት ከገረዓልታ፣ በአብርሃ ወአጽብሃ ወይም ከአጽቢ ወንበርታ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥንት የነበረው የግዛት ስም መጠሪያ ሰፊ ሊሆን ስለሚችልና በነጋሺ  ዘርያ የአንድ ቀን ጉዞ ገብ የሆኑ የውቅሮ ግዛቶችን መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም በፉቱሑል ሐበሽ ውስጥ እንደ ሐረማትና ቐርቅራ ተብለው ተለይተው የተቀመጡ ስለሆነ የፈረንጆቹን ግምታዊ ስሌት ትተን የነጃሺ ጀበርቲዎች የተጓዦቹ መነሻ የትም ይሁን የት ነጃሺ መሆኑን መሠረት በማድረግ  የወደፊት ተመራማሪዎች ጥናታቸውን መቀጠል ከነጃሺ 40 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ያላቸውን ቦታዎች ማሰስ ይችላሉ፡፡ በዚህም መሠረት፣ የተገለጸው አሕመደል ነጋሽ የተቀበሩበት ቦታ መሆኑን ስለሚያመለክት የአሁኑ ነጋሽ ነው ተብሎ ይገመታል።

 ትሪሚንግሀም ከዚህ በተጨማሪ ቻርለስ ጃኮስ ፖነቸ (Poncet, Charles Jacos, A voyage to Ethiopia 1709) የተባለው በግብፅ ይኖር የነበረና በትውልዱ ፈረንሳዊ የሆነ የሕክምና ባለሙያ የቁምጥና በሽታ የደረሰበትን የቀዳማዊ ኢያሱን ልጅ ለማከም ወደ ጎንደር በ1698፣ በ1699፣ በ1700 ወደ ኢትዮጵያ የተመላለሰውንና ከአፄ ፋሲለደስ ጋር መልካም ግንኙነት የነበረውን አውሮፓዊ በመጥቀስ ጀበርቲዎች በጎንደር እንደነበሩ መግለጹን በዋቢነት ይጠቅሳል። ፖንቸ ጀበርቲዎች እንፍራዝም እንደነበሩ ይጠቅሳል። ትሪሚንግሃም ከዚህም በተጨማሪ ኤድዋርድ ሩፔል የነበረ ጀርመናዊን  ጠቅሶ እንዳሰፈረው ጀበርቲዎች በክርስቲያኖቹ መካከል እንደሚኖሩና ልጆቻቸውን ሁሉም ማንበብና መጻፍ እንደሚያስተምሩ ገልጿል።

ኡሎንዶርፍ እንደሚለው ቃሉ ጀበርታ ከሚለው ዓረብኛ ቃል የተገኘ ከሆነና አንደኛው ትርጉሙ ከግዴታ ጋር የተያያዘ ከሆነ የቃሉ ትርጉም ገበረ፣ አግበረ፣ አገበረ፣ አስተግበረ ከሚለው የግዕዝ ቃል ጋርም የሚያያዝ ሲሆን ትርጉሙም አደረገ፣ አሠራ፣ አስገደደ፣ አስገዳጅ የሚል ትርጉም አለው። በትርግኛም ‹‹ገበረ›› የሚለው ቃል ቢሆን በጉልበትም በሕግም ተገዶ የግብርና፣ የንግድ ወይም የሌላ ሥራ ግብር እየከፈለ የሚኖር እንደማለት ነው። ኡሎንዶርፍ የትኛው ትግርኛ መዝገበ ቃላት እንደሆነ አላመለከተም እንጂ በአዲሱ የትግርኛ መዝገበ ቃላት፣ ጀበርቲ ማለት ‹‹ጎበዝ፣ ረዳት፣ አዳኝ፣ አማኝ፣ የፈጣሪ አገልጋይ ማለት እንደሆነ ጠቅሶ ነቢዩ መሐመድ (ሱዓወ) ችግር ላይ በነበሩበት ጊዜ ከጎናቸው የቆመ›› ማለት እንደሆነ ያስረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ገበርቲ›› ማለትም ግብር እየከፈሉ የሚኖሩ ወይም የሚገብሩ ስለሆነና ‹‹ገ›› ፊደል በዓረብኛ ስለሌለ ‹‹ጀ›› ተተክቶ መግባቱን ያሳየናል። ይህም ልዩ ልዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለመንግሥታቱ እየገበሩ የሚኖሩ ወደሚል ይወስዳል።  

 በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ታዋቂ ከሆኑት አውሮፓውያን አንዱ የሆነው ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ በመጽሐፉ (ETHIOPIA, ANATOMY OF TRADITIONAL POLICY) ኢትዮጵያ በነጋሺ ዘመን እስልምናን ከተቀበሉት አገሮች አንዷ እንደሆነች ቢናገርም እስልምና የተስፋፋው በደቡብ ምሥራቅ ሡልጣኔቶች በኩል እንደሆነ ጥናቱ ያስረዳል። በስፋት አልተገለጸም እንጂ ዊልያም ፒተር ኤድዋርድ ሲሞን ሩፔል (1794-1884) ጀርመናዊም እስከ ምጽዋ መጥቶ እንደነበረና በዚያ አካባቢ ይኖሩ ስለነበሩ ጀበርቲዎች ጽፏል።

ጀበርቲዎችን ከዓለም አቀፉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አኳያ የነበራቸውን ወይም ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ሲታይም በአንድ በኩል በአውሮፓና በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዓረቢያና በኢትዮጵያ ሙስሊሞች (ጀበርቲዎች) መካከል ከነበረው የኃይል ሚዛን አኳያ የሚታይ ነው። በዚህም መሠረት ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ11ኛው፣ 12ኛው፣ 13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ (ከአውሮፓ ተሐድሶ በኋላ) በተነሳው የመስቀል ጦርነት ለአውሮፓውያን እንዲወግን ሲፈለግ ጀበርቲዎች ደግሞ የዓረቡ ዓለም ደጋፊዎች ሆነው እንዲገኙ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። ለምሳሌ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በሥልጣን የነበሩት አፄ ዓምደ ጽዮን ሡልጣን ሳዕደዲንን ድል ማድረጋቸው እንደተሰማ አውሮፓውያን አጋራቸው እንዲሆኑ ፈልገዋል፡፡ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመንም ዓሚር ማሕፉዝን ድል ካደረጉት አፄ ገላዎዴዎስ ጋር ለመወዳጀት (አንዳንዶች እንደሚሉትም ዕርዳታቸውን ለመሻት) በወቅቱ ገናና የነበረችው ፖርቱጋል አምባሳደሯን ወደ ኢትዮጵያ ልካ እንደነበረና አልቫሬዝን የምናገኘውም በዚህ ዘመን እንደሆነ እንረዳለን።

በ15ኛው ክፍለ ዘመን የኖሩት አፄ ዘርአ ያዕቆብም ጀበርቲዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሙስሊሞችን ለማጥፋት ከፍተኛ ምኞት ነበራቸው። ኤድዋርድ ኡሎንዶፍ ‹‹ኢትዮጵያውያኑ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚለው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከአፄ ኢዛና (330ዎቹ የነበሩ የአክሱም ንጉሥ) ወዲህ የተገኙና ወደር ያልነበራቸው ንጉሠ ነገሥት እንደነበሩ ይገልጻቸዋል። ኡሎንዶርፍ ምናልባት ተወዳዳሪ አላቸው የሚባል ከሆነ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያወሳል። ምንም እንኳ እንደ አፄ ዓምደ ጽዮን፣ አፄ ዘርአ ያዕቆብ፣ አፄ ይሥሐቅ፣ አፄ በዕደ ማርያም፣ አፄ ዳዊት ቀዳማዊና ዳግማዊ የአዳል ሡልጣኔትንና ጀበርቲዎቹን  ለመጣል ያልተቆጠበ ጥረት ቢያደርጉም ግዛታቸው እያደር እየጠበበ፣ አቅማቸው እየቆየ እየተዳከመ መሄዱ ከቶ አልቀረም። ይልቁንም የቀይ ባህር የንግድ መስመርና የንግድ እንቅስቃሴ በአዳሎችና በጀበርቲዎች እጅ ስለነበር የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በጦርነት እንዲኖር አስገድዶታል። በመጨረሻም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢማም አሕመድ ኢብራሂም የአፄዎቹን መንግሥት ድል አድርገው ሥልጣን ይዘዋል።

በኢማም አሕመድ የድል ዘመን በርካታ የኢስማዒል ጀበርቲና የሸኽ ዒሳ ዝርያ የሆኑ ሶማሊ የጦር መሪዎችና ሸኾች በመላው ኢትዮጵያ ተሠራጭተው የነበሩ ሲሆን እነዚህም ዝርያዎች በጎንደር፣ በትግራይ፣ በኤርትራ መኖራቸው አይጠያይቅም። ከዓረቡ ዓለም ጋር ይደረግ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመስፋት እናርያን፣ ጎማንና ጅማን አካቶ ነበር። ሆኖም በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተስፋፋው የገዳ ሥርዓት የኢትዮጵያን የታሪክ መልክ ቀይሮ ስለነበረ፣ በዚህ ዘመን በርካታ የአፄዎቹ የታሪክ መረጃዎችና የሙስሊሞች ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ተቀያይረው ስለነበር ዘመነ መሳፍንት እስኪከሰት ድረስ የታሪክ ክፍተት መከተሉ አልቀረም። በዚህ የታሪክ ሒደት የምንመለከተው አንድ ከፍተኛ ቁም ነገር ሶማሌዎች፣ ሐረሪዎች፣ አርጎባዎች፣ ጉራጌዎች፣ ሥልጢዎች፣ አማራዎች፣ ትግራዮች፣ ከፍተኛ ቦታዎችን ይዘው ራሳቸውን ከኦሮሞ ጥቃት እየተከላከሉ መኖራቸውን፣ እንቅስቃሴያቸው ግን ተገድቦ መኖሩን ነው። በዚህ ረገድ ያለው ታሪካችንን በሚገባ ቢጠና የገበርቲን ትርክት መለወጥ ይቻል ይሆናል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ፣ ሶፍያ አሕመድ ‹‹የብሔር ማንነትና የፖለቲካ አናሳነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ለአንደኛ ዲግሪዋ ማሟያ ትግሪ ወርጂዎችን በሚመለከት በ1999 ባደረገችው ጥናት ስለ ጀበርቲዎችም በጥናቷ አካትታለች፡፡ እርሷም ትሪሚንግሃምን በመጥቀስ ትግሪ ወርጂዎች የዓረብኛና የጀበርቲኛ ቅልቅል የሆነ ቋንቋ እንደነበራቸውና በኋላ ግን ወደ ኦሮምኛ እንደተቀየረ ታቀርባለች።

ጀበርቲዎችና የንግድ መስመር

ስለጀበርቲዎች ስናጠና ሌላ የምርምር ዓምድ ሆኖ የምናገኘው የንግድ መስመርና ጀበርቲ ነጋዴዎችን የሚመለከተው ነው። በዚህም መሠረት አይሁዳዊው አቢር ሞርዶች (1927-2014) ስለ ዘመነ መሳፍንት፣ ኢትዮጵያንና ቀይ ባህርን በሚመለከት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያንና ክርስትናን በሚመለከት ለንባብ ባበቃቸው መጻሕፍቱ ስለኢትዮጵያውያን በስፋት የዳሰሰ ሲሆን፣ በጥናቱም ምንም እንኳን እስልምና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በነቢዩ ሙሐመድ  ዘመን ቢሆንም ቀስበቀስ የተስፋፋው ግን በደቡብ ምሥራቅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው በገቡ ነጋዴዎች እንደሆነ ያብራራል። ስለወላስማ፣ መኽዙማዊና አዳል ሡልጣኔትም ያብራራል። አቢር ሞርዶች በተጨማሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ወደ የመን በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንደሄዱ ገልጾ እነዚህም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በየመን ከ1022-1150 የዘቢድ ነጃሺ ስርወ መንግሥት አቋቁመው እንደነበረ በመጠቆም ኢትዮጵያውያን ባለጸጎች፣ ባለሥልጣናት፣ ቄሶች፣ ገበሬዎች፣ ወዘተ እንደነበሩ ያብራራል። በዚህ ዘመን በርካታ ነጋዴዎች ከየመን፣ ከዘቢድ፣ ከጅዳ፣ ክዊዝ፣ ከካይሮ፣ ከደማስቆ፣ ከባግዳድና ከፋርስ ጭምር ወደ ኢትዮጵያ መጥው ይነግዱ እንደነበር ሲታወቅ፣ ከንግዱም ጋር እስልምናን የማስፋፋት ተግባር ያከናውኑ ነበር። አቢር ሞርዶክ በዚህ ረገድ ከኡሎንዶርፍ ጋር ይስማማል።

እንደ አል-መቅሪዚ፣ አል-ዑማሪና ኢብን ባቱታና የተባሉት የዓረብ ጸሐፍት በምሥራቅ ሸዋ፣ በተለይም ጀበርታ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ጀበርቲዎች እስልምናን አስፍነው መኖራቸውንና በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወታቸውም ከሌላው ኅብረተሰብ የተሻለ እንደነበረ መግለጻቸውን አቢር ሞርዶክ ያብራራል። ሞርዶክ ከዚህም በተጨማሪ በግብፁ አልአዝሃር፣ በመዲናና በደማስቆ ከፍተኛ ተቀባይነት እንደነበራቸው የዓረብ ጸሐፍቱን ጠቅሶ ያስረዳል።

ጀበርቲዎች የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ዓረቡ ዓለም፣ በዓረቡ ዓለም የሚገኙትን ልዩ ልዩ ሸቀጦች ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ ለገበያ ያቀርቡ እንደነበር ማለትም የኤክስፖርትና የኢምፖርት ሥራው በእነሱ ይከናወን እንደነበረ ይታወቃል። የዓረቡ ዓለም ጸሐፍትም የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚፈልጓቸውን የውጭ ምርት የሚያቀርቡላቸው፣ ከአጎራባች ዓረብ አገሮች ጋር እየተገናኙ የዲፕሎማዊ ሥራ የሚሠሩላቸው ጀበርቲዎች እንደነበሩ ይመሰክሩላቸዋል። ይህም ማለት አፄዎቹ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በዲፕሎማሲ የሚያሰማሩት ሹም አልነበራቸውም ማለት ነው።

ጀበርቲዎች ራሳቸው የአገር ውስጥ ምርት ለውጭ አገር ገበያ እያቀረቡና የውጭ አገር ምርት ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ እንደኖሩ ቢታወቅም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዓረብ ነጋዴዎች ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከየመን፣ ከዓረቢያ፣ ከግብፅና ከሱዳን ሸቀጦችን ይዘው እየመጡ የአገር ውስጥ ምርቶችን (እህል፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድ፣ ከርቤ፣ ዕጣን ወዘተ) ገዝተው ይሄዱ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ልዩነቱ ከእስልምና መምጣት በኋላ ለሃይማኖታዊ ግዳጃቸው ማሟያ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ከጀበርቲዎች ያለ ችግር ማግኘታቸው ነው።  

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles