Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቀድሞ ሠራዊት የተጋረጡበት ችግሮቹና የወደፊት ተስፋው

የቀድሞ ሠራዊት የተጋረጡበት ችግሮቹና የወደፊት ተስፋው

ቀን:

የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለመንግሥት ያቀረባቸው ልዩ ልዩ የመብትና የሀብት ጥያቄዎች ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጥባቸው 27 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጥያቄዎቹ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው እየተካሄደ ያለው ጉትጎታ እስካሁንም አልተቋረጠም፡፡ ለዚህም ዓይነቱ ሥራ ተጨማሪ ኃይል፣ ብርታትና ግብዓት ይሆንለታል ተብሎ የታመነበት የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሠራዊት ማኅበራት ኅብረት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ኅብረቱ ወደ ሥራ የገባው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የጠቅላላ ጉባዔ አመራሮችን ከመረጠ በኋላ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የኅብረቱን የዕለት ተዕለት ሥራ የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን የቀሩት አመራሮች ደግሞ ኅብረቱ የሚጠራውን ጠቅላላ ጉባዔ የመምራትና የማስተባበር ተግባር ያከናውናሉ፡፡

የሥራ አመራር ኮሚቴው ሰብሳቢ ኮሎኔል ጋረደው ለውጤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኅብረቱ የተመሠረተው በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ለተቋቋሙት የጦርና የፖሊስ ሠራዊቶች፣ ለአየርና ለባህር ኃይሎች ማኅበራት እንዲሁም ለቬትራን አሶሴሽን ጥሪ በማድረግ ነው፡፡ ጥሪው ከተላለለፈላቸውም መካከል 17ቱ ተወካዮቻቸውን ልከው በኅብረቱ መሥራች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የቀሩትም ኅብረቱን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማኅበራቱ በየራሳቸው እያካሄዱ ያሉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ኅብረቱ በምንም መልኩ ጣልቃ እንደማይገባባቸው ነው ኮሎኔል ጋረደው የተናገሩት፡፡

ኅብረቱ እንዲመሠረት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የቆየውና ለምሥረታውም ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተባበረው አሜሪካ የሚገኘው የቀድሞ ሠራዊት ማኅበር መሆኑን ገልጸው፣ ወደፊት ግን ኅብረቱ ለሚያከናውነው የዕለት ተዕለት ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍንበት የፋይናንስ ድጋፍ ከአባል ማኅበራት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ግለሰቦች ለማግኘት ማቀዱንም አስረድተዋል፡፡

እንደ ኮሎኔል ጋረደው አባባል ለመንግሥት የቀረቡት ጥያቄዎችም የጡረታና የሕክምና መብቶችን የማስጠበቅ፣ የተወረሱ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የማስመለስና የታገደውንም ማስለቀቅ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹንም ያቀረቡትና ለተግባራዊነቱም እስካሁን እየተንቀሳቀሱ ያሉት ማኅበራቱ ሲሆኑ፣ ኅብረቱ ከእነዚህ አባል ማኅበራት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ለእንቅስቃሴው መጠናከር ጉልህ ድርሻ ያበረክታል፡፡

የወያኔ ጦር ደብረ ብርሃን በደረሰበት ወቅት ግስጋሴውን ለመግታታና ለማክሸፍ ሲባል ከተለያዩ አካባቢዎች ለተመለመሉት ሚሊሻዎች የቀድሞ ጦር ሥልጠና በመስጠት ከፍተኛ ዕገዛ ማድረጉን ነው ያመለከቱት፡፡ አሁንም ቢሆን ለሥልጠና፣ ለማማከርና ለሌላም ግዳጅ በተጠየቀ ቁጥር ተገቢ ምላሽ ለመስጠትና ከመንግሥት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ኅብረቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮት ያጋጥመው ይሆናል ተብሎ ታስቧል? ተግዳሮቱንስ ለማክሸፍና ምን የታቀደ ነገር አለ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሎኔል ጋረደው ሲመልሱ፣ ‹‹ይህን ያህል የከፋ ተግዳሮት ይገጥመናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን እስከዛሬ ድረስ ከገጠመን ልምድ የግል ዝና፣ ጉራና ጥቅም ፈላጊዎች ሊያውኩን ይችላሉ የሚል ሥጋት ይኖራል፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ አድርገን የያዝነው አካሄድ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቀስ በቀስ እየተከታተልን እንቅስቃሴያቸውን ማክሸፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በሕጉ መሠረት የተቋቋሙት ማኅበራት የራሳቸው ነፃነትና ኦቶነመስ እንደተጠበቀ ቢሆንም ለቀረቡት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመሻት በኅብረት መጮሁ ይመረጣል፤›› ያሉት ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል አባልና የኅብረቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሌፍተናንት ዮሴፍ ሸጋው ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊው አነጋገር ከዘውዳዊው ሥርዓት ጀምሮ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተቋቋመው የቀድሞ ሠራዊት የሰላም አስከባሪ እንጂ ወያኔ እንዳለው ጨፍጫፊና የደርግ ሠራዊት አለመሆኑን ኅብረተሰቡ በሚገባ እንዲረዳው የማድረግ ሥራ የኅብረቱ ኃላፊነት ነው፡፡

ቀደም ሲል በተቋቋሙት የቀድሞ ሠራዊት ማኅበራት ውስጥ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች በአመራር ደረጃ በማገልገል ላይ መሆናቸውን ሌፍትናንት ዮሴፍ ገልጸው፣ አሁን ለተቋቋመው ኅብረት ደግሞ የበላይ ጠባቂ፣ አማካሪና የክብር አባል ሆነው እንደሚሠሩ፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመሻት ኅብረቱ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ አካላትን ቢሮ ባንኳኩ ቁጥር ከጎኑ እንደሚቆሙና አብረውትም እንደሚያንኳኩ ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የቀድሞን ሠራዊት ጡረታና የሕክምና መብቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ሀብቶቹና ንብረቶቹ እንዲመለሱለት ለዓመታት ሲታገሉ ከቆዩት ማኅበራት መካከል ግንባር ቀደም የሆነው የቀድሞ ሠራዊትና ሲቪል ሠራተኞች ማኅበር ሲሆን፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንትም ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ገዳሙ ናቸው፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ አባባል ማኅበሩ ወደ ሥራ የገባው አምስት ዝርዝር ሥራዎችን በመንደፍና ሥራዎቹንም በምዕራፍ አንድና በምዕራፍ ሁለት በማቀፍ ነው፡፡

በምዕራፍ አንድ የተካተቱት ሥራዎች የቀድሞ ሠራዊትን የጡረታና የሕክምና መብቶችን ማስከበር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የታገደውን ስድስት ሚሊዮን ብር ገንዘብ ማስመለስ፣ የቀድሞ ጦር ሠራዊት መኮንኖች ክበብን መረከብና ይህ ካልተሳካ ምትክ አዲስ ቦታ የሚያገኝበትን መንግድ ማመቻቸት፣ በክበቡ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ተገምተው የተገመተውን ገንዘብ መረከብ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በምዕራፍ ሁለት የተያዘው ሥራ ደግሞ የቀድሞ ሠራዊትን ታሪክና ገድል የሚገልጽ መጽሐፍ ማሳተም ሲሆን ይህም በጥሩ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹የቀድሞ ጦር 1927 እስከ 1983 ዓ.ም.›› በሚል ርዕስ ታትሞ ለንባብ መብቃቱን ገልጸዋል፡፡

በቀዳሚው ምዕራፍ አንድ ከተካተቱት ሥራዎች መካከል በጣም ጥቂት የሠራዊቱ አባላት የጡረታና የሕክምና መብቶችን ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከ95 በመቶ በላይ ያህሉ ግን እንደተነፈጋቸው ቀርተዋል፡፡ በተለይም ጉዳዩ የሚመለከተው አንድ መንግሥታዊ አካል ለቀድሞ ሠራዊት የጡረታ መብት ተጠይቆ፣ ሠራዊቱ ተሃድሶ ላይ በቆየበት ጊዜ ለትራንስፖርትና ልዩ ልዩ ወጪዎች መሸፈኛ ውሏል፡፡ በዚህም የተነሳ ምንም ዓይነት ገንዘብ ስለሌለ መጠየቁ አግባብ አይደለም፤›› የሚል መልስ መስጠቱን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት፡፡

ሕክምናው ለጊዜው ቢፈቀድም፣ ለብዙ ዓመታት በጤና መታወክ ሳቢያ ሲሰቃይ የቆየው የቀድሞ ሠራዊት አገልግሎቱን ለማግኘት በአንድ ጊዜ ግር ብሎ ወደ ጤና ተቋም መሄዱን፣ ተቋሙም ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት በዚህም የተነሳ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ እንዳትመጡ!!›› የሚል ማስታወቂያ እንደለጠፈ፣ በዚህም የተነሳ ጥቂቶች ተጠቃሚ ሲሆኑ አብዛኞቹ ሳይጠቀሙ እንደቀሩ ነው ያመለከቱት፡፡

ይህንን ችግር በወቅቱ የጤና ሚኒስትር በአሁኑ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) እንደቀረበላቸው ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው ጠቁመው፣ እሳቸውም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ልዩ የሕክምና አገልግሎቶችን በነፃ የሚያገኙበት መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆኑን ሥራው እንደተጠናቀቀ የቀድሞ ሠራዊት አባላት የመጀመርያው ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል መልስ እንደሰጡ፣ እስካሁን ድረስ ግን ምንም የታየና የተደረገ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የታገደው ስድስት ሚሊዮን ብር እንዲለቀቅለት ማኅበሩ ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመሥረቱንና ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን ማስረጃ በሚገባ ከመረመረ በኋላ ገንዘቡ የማኅበሩ አንጡራ ሀብት ስለሆነ ይመለስለት/ይለቀቅለት ሲል መፍረዱን፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ደግሞ በተሰጠው ፍርድ ቅር በመሰኘቱ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረቡን፣ የበላይ ፍርድ ቤቱም የመጀመርያውን ፍርድ ማፅደቁን፤ ነገር ግን ባለጊዜዎች የተላለፈውን ፍርድ በመናቅ ታግዶ እንዲቆይ ማድረጋቸውን ከጄኔራል ጌታቸው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የቀድሞ ሠራዋትና ሲቪል ሠራተኞች ማኅበር ያቀረባቸው ጥያቄዎች ሁሉ በአግባቡ መልስ እንዲሰጥባቸው ሲል ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በጽሑፍ ማሳሰቡን፣ እስካሁን ማሳሰቢያው የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱንም ነው ያመለከቱት፡፡

ሜጀር ጄኔራል ገዳሙ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት እንደ ብረት የጠነከረ ዲሲፒሊን የተላበሰ፣ ሕዝባዊ መሠረት ያለው፣ ለማንና ለምን እንደሚዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ወደፊት እንጂ ግልምጫ የማያውቅ፣ የሕዝብና የእናት አገር ፍቅር እንደ ውስጥ እግር እሳት የሚያንገበግበውና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በአራቱም አቅጣጫ የተነሱትን የጠላት ወረራዎች ‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ፣ ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ፤›› የሚለውን ዜማ እያስተጋባ ሲመክትና ሲከላከል የከረመ፣ በዚህም ዕረፍት ያጣ፣ ይህም ሆኖ ግን የአገሩ ጉዳይ እልህ ውስጥ ከቶት በጠላት ምሽግ ዘሎ እየገባ ጉሮሮ ለጉሮሮ በመተናነቅ ለቁጥር የሚታክቱ የጠላትን ምሽጎችን በማስለቀቅ፣ ስትራቴጂያዊና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቦታዎች በቁጥጥሩ ሥር በማዋል ድል በድል እንደተቀዳጀ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሠራዊቱ ይህን ሁሉ ገድል የፈጸመው በቀላሉ ወይም ሁኔታዎች አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይደለም፡፡ በላዩ ላይ የለበሰው ልብስ አልቆበታል፣ ቀለብ በጊዜው አይደርሰውም፣ በዚያ ላይ የቤተሰብ ናፍቆት ያሳስበዋል፡፡ ከቤተሰቡ የሚላክለት ደብዳቤ እሱ ዘንድ ከመድረሱ በፊት እየተከፈተ ይታይበታል፡፡ ትንሽ ወለም ያለ ነገር ከተገኘበት ሳይደርሰው እዚያው ይቀርበታል፣ ፍተሻውን ሁሉ ቢያልፍ እንኳን በጊዜው አይደርሰውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ሠራዊት በጀግንነት እየተዋጋ ከቆየ ለምንድነው ውጤት ያላመጣው?›› የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ሲሆን መልሱ ግን አጭር ነው፡፡ በወታደሩ ዘንድ ምንም ዓይነት ችግር አልታየም፡፡ በተረፈ በከፍተኛ ጄኔራሎች መኮንኖች መካከል አንድነት ማጣት፣ ለስምና ለዝና መሯሯጥና አምባገነንነት መስፈን ለስኬታማነቱ ማሸቆልቆል ሊጠቀሱ ከሚገባቸው አያሌ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ነው ሜጀር ጄኔራል ጌታቸው የገለጹት፡፡

የቀድሞው ሠራዊት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ የመከላከያ ሚኒስቴር የፍትሕ ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል መሸሻ አረዳን በስልክ አነጋግረናቸው ነበር፡፡ ጄኔራል መኮንኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዕውቀት እንደሌላቸው ነገር ግን ጥያቄያቸውን ለሚኒስቴሩ በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችሉና ሚኒስቴሩም ሕጋዊ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...