Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት መጨመሩ ተገለጸ

በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት መጨመሩ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ ግድያና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች መጨመራቸውን፣ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ ሰባት አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት ተቋማት አስታወቁ፡፡

ተቋማቱ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ እየጨመረ የመጣው በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሰለባ በሆኑት ሴቶች ላይ ከማስከተሉም ባሻገር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወት እስከማሳጣት የሚያደርስ ነው፡፡

‹‹በተለይም ተመሳሳይ ጥቃቶች መደጋገምና አሳሳቢነት (ለምሳሌ በአሲድ የሴቶችን ገጽታ ማበላሸትና የነበራቸውን ሙሉ ጤንነት ማሳጣት) እንዲሁም አዳዲስ የጥቃት ዓይነቶች መምጣትም ሁላችንም እየታዘብነው ያለ ዕውነታ ነው፡፡ በተለይም  በሚሳዝንና በሚያሰቅቅ ሁኔታ በአብዛኛው ግድያው የሚፈጸመው በቅርብ ወዳጅ/በትዳር አጋር መሆኑ ነው፤›› ያሉት ተቋማቱ፣ ይህ ለቀጣዩ ትውልድም ስለ ትዳር ሕይወት ያለውን አዎንታዊ አመለካከት የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ የማኅበረሰብ ዋና ምሰሶ የሆነውን ቤተሰብ የሚያናጋና ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚደፈርስ የጥቃት ዓይነት ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

መግለጫውን ያወጡት ተቋማት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች፣ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት መከላከያ፣ የተሃድሶና ማቋቋሚያ ድርጅት፣ ትምራን፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከልና ሴቶች ይችላሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ሴቶች ማኅበር ያስጠናው ጥናት እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2022 ብቻ 47 የግድያ እና የግድያ ሙከራ ወንጀሎች፣ 32 የአስገድዶ መድፈር፣ 158 የድብደባ ወንጀሎች በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉልና ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ ተመዝግበዋል፡፡

ሪፖርቱ በአምስት የክልል ከተሞችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ባሉ ቢሮዎች አማካይነት የተመዘገቡ ከጥቃት ጋር የተያያዙ ሰነዶች መሆናቸውንም ይገልጻል፡፡

የሪፖርቱ ቁጥር ለማኅበሩ የቀረቡ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ቢሆንም፣ ለማኅበሩ ሪፖርት ያልተደረጉና በቀጥታ ለፖሊስ ሪፖርት ተደርገው በፖሊስና በአቃቤ ሕግ ክትትል ሥር ያሉ ብዙ ጉዳዮች እንደሚኖሩ የሚጠበቅም ነው ብለዋል፡፡

እንደ ተቋማቱ ገለጻ፣ ችግሩ የሚያሳው በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ እንዳልሆነ፣ ሌሎች ጥቃቱን ለመከላከልም ሆነ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀየስ እንዳለባቸው የሚጠቁም ነው፡፡

የሴቶች ጥቃት መጨመር ዋናው መንስዔ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ የሚገኘው አድሏዊ አመለካከት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ አመለካከት፣ በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል፣ ሱስ፣ መጠጥና አደንዛዥ ዕፆች ከተጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በተጨማሪም በአገር አቀፍ ያሉ ግጭቶች፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዲሁም የሕግ የበላይነት አለመከበር እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል፡፡

ለዚህም ከሕግ ክፍተቶች በተጨማሪ በእጅጉ የሚስተዋለው የአፈጻጸምና ያሉትን ሕጎች የመተግበር ችግር እንዲሁም በጥቃት አድራሾች ላይ አስተማሪ የሆኑ ቅጣቶች አለመወሰናቸው እንዲባባስ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

መንግሥትና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ ለመሄዱ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል ብለዋል፡፡

ማኅበራቱ በዚህ ጉዳይ ይመለከታቸዋል ላላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማትና የሃይማኖት ተቋማት የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና የሴቶችን ደኅንነት እንዲጠብቁ ለአሥር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጥሪ ከቀረበላቸው መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ተቋማት፣ የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶች፣ የሃይማኖትና የጎሳ መሪዎች ይገኙበታል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...