በየዓመቱ ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የገና (ልደት) በዓል ነው፡፡ የዘንድሮው በዓል የ2015ኛው ዓመቱ ነው፡፡ ቅዳሜ ታኅሣሥ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የገና በዓል በኢትዮጵያና የጁሊያን ካሌንደርን በሚከተሉ ኦርቶዶክሳውያን ተከብሮ ውሏል፡፡
የጁሊያን ቀመር የሚከተሉት ምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን እነ ሩሲያ እነ ግሪክ ገናን ሲያከብሩ ዕለቱን ዲሴምበር 25፣ 2022 ብለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታኅሣሥ 29፣ ግብፅ (ኮፕቲክ) ደግሞ ኪያክ 29 ብለው ነው ያከብሩታል፡፡ ቀኑ በግሪጎሪያን ቀመር ጃንዋሪ 7 2023 ላይ ውሏል፡፡
በ16ኛው ምዕት ዓመት ከጁሊያን ካላንደር ተከልሶ የተዘጋጀውን የግሪጎሪያን ካላንደር የተከተሉት ምዕራባውያን ደግሞ በእነርሱ ዲሴምበር 25 ባሉት ከ13 ቀናት በፊት ታኅሣሥ 16 ቀን አክብረውታል፡፡ በዓሉ አንድ ሆኖ የቀኑ ልዩነት የተፈጠረው መሬት ፀሐይን ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ በምሥራቆች 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው በማለታቸው ምዕራቦች ደግሞ 365 ቀን ከ5 ሰዓት 48 ደቂቃ 46 ሰከንድ ነው በሚል ልዩነት በመፈጠሩ ነው፡፡
ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም (የዓለም ቤዛ ዛሬ ተወለደ) እያሉ ኢትዮጵያውያኑ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን ያከበሩት በመንፈቀ ኅዳር የጀመሩትን ጾም ለ44 ቀኖች ካሳፉ በኋላ ነው፡፡
‹‹ያለም ሁሉ መድኃኒት
ተወለደ በበረት፣
እያሞቁት እንስሳት
ብርሃን ሆነ በዚያች ሌት
ሲዋዥቡ መላዕክት
ደስ አሰኙ ለኖሩት›› የሚለው ኅብረ ዝማሬ የበዓሉ መገለጫ ነው፡፡
የቅርስ ባለሥልጣን ባዘጋጀው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ሰነዱ ላይ እንደተጠቆመው፣ የልደት በዓል ከመድረሱ በፊት በሚኖሩት ሦስት እሑዶች በኢትዮጵያ ሥርዓተ አምልኮ መሠረት እሑድ እሑድ ነቢያት የክርስቶስን መወለድ በተመለከተ የተነበዩትን ትንቢት የተመለከቱ ማህሌቶች ይቆማሉ፡፡
በመጀመርያ እሑድ ‹‹ስብከት›› የተባለው ቀለም ማለትም “ወልዶ መድኅነ ንሰብክ” የጌታችንን ልደት እናውጃለን (ነቢያት ስለክርስቶስ መወለድ ሰበኩ) የሚለው በያሬዳዊ ዜማ ይዜማል (ይወርባል) ይሸበሽባል፡፡ በሁለተኛው እሑድ እነዳዊት ስለክርስቶስ በተነበዩትና “ብርሃን” የተባለው ቀለም ማለትም ‹‹ብርሃን የሆነው ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ›› የሚለው ቀለም ይዜማል፡፡ በሦስተኛው እሑድ ኖላዊ (እረኛ) የተሰኘው ቀለም ማለትም ‹‹ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃለ ለእግዚአብሔር›› የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ወደዚህ ዓለም መጣ ለእኛ እረኛ ሊሆን›› የሚለው ቃል ይዜማል፡፡
በእነዚህ ቀናት የሚደረጉ ቅዳሴዎችም እነዚህኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎች የሚመለከቱ ይሆናሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ዛሬ ስብከት ነው››፣ ‹‹ዛሬ ብርሃን ነው››፣ ‹‹ዛሬ ኖላዊ ነው›› እያሉ ሦስቱን እሑዶች የሚጠሯቸው፡፡
በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሌሊቱ ማሕሌት ተቁሞ ቅዳሴ እንዳበቃ፣ የበዓል ፍፃሜ ቢሆንም፣ በተለይ በላሊበላ ከተማ ግን በተጨማሪ በዕለቱ ጧት ላይ ቤዛ ኵሉ የተሰኘው ክብረ በዓል ከአለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ በቤተ ማርያም ካህናቱ በጋራና መሬት ላይ ሆነው ያከብሩታል፡፡
ከምዕመናን ባለፈ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ትኩረት የሚስብ ዓቢይ ትርዒት ነው፡፡ የላሊበላው ቤዛ ኵሉ አከባበር ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ማሜ ጋራ ላይ ያሉት የመላዕክት ምሳሌ፣ መሬት ላይ ያሉት ደግሞ የእረኞች ምሳሌ ሆነው ዝማሬውን በሆታና በዕልልታ ያጅቡታል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስን መወለድ መጀመርያ ያወቁ እረኞች በመሆናቸው በአገር ቤት ትውፊቱ እየተነገራቸው የሚያድጉት እረኞች በተለየ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
ታላቁ ኢትዮጵያዊ የስድስተኛው ምዕት ዓመት ቲኦሎጂያን ቅዱስ ያሬድ እንዳተተው፣ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፡፡ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሃ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች ይላል፡፡
የበዓለ ልደት ማሕሌቱ በካህናት በሚቀጥልበት ሌሊት ሊቃውንቱ ልደቱን አስመልክተው በየአጥቢያው በቅኔ ማሕሌት ዙርያ ቅኔውን ይዘርፉታል፡፡ አንዱ፣ ከሰባት አሠርታት በፊት ሊቁ አለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ በግዕዝ የተቀኙትና ወደ አማርኛ የተመለሰው ይሄ ነበር፡፡
‹‹ፍጡራን ሁሉ፣ ሐሳባቸውን በፈጣሪያቸው ይጥሉ ዘንድ በሕገ ልቡና ተነግሯል፡፡ ዛሬ ከልማዱ ሥራ ፈጣሪ አረፈ፡፡ የተረፈ የልጁን ድህነት መዋረድ በጎል (በረት) ሲያይ
የመንግሥት ዙፋን እንዳይሻ የወርቅ ልብስ እንዳይሻ አሳቡን ከድንግል ማርያም ላይ ጣለ፡፡››
የገና ጨዋታ
በላሊበላ ከተማ ማሜ ጋራ ከሚኖረው አከባበር በተጨማሪ ምእመናንም በቆይታቸውም ዕለቱ የቅዱስ ላሊበላ የተወለደበት በመሆኑ እርሱንና ሥራውን ከበሮ እየመቱ እልል እያሉና እያጨበጨቡ ያወድሱታል፡፡
ከበዓሉ ውሎና ከድግሱ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚደረገው ወጣቶች ዱላቸውን አሽለምልመው፣ አለባበሳቸውን አሳምረው፣ ቁምጣ ሱሪ (ሶራ) ለብሰው የገና ጨዋታ በቡድን ሆነው ይጫወታሉ፡፡ ይህ ጨዋታም ወንዶች ከእንጨት የተሠራች ትንሽ ድቡልቡል ኳስ በቆልማማ ዱላ እየመሩ አንዱ ቡድን በአንዱ ቡድን ድንበር አልፎ ኳሷን በማስገባት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው፡፡
‹‹ቓርሳ››
በትግራይ በዓለ ልደቱ በሃይማኖታዊ ሥርዓት ከመከበሩ ባሻገር፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሚዘወተረው የገና ጨዋታ ዓይነት ‹‹ቓርሳ›› የሚባል ጨዋታ ይከናወናል፡፡ የቅርስ ባለሥልጣን ሃቻምና ባሳተመው የትግራይ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፣ ቓርሳ በተለይ በምሥራቃዊ ትግራይ ዞን አፅቢ ወንበርታ ወረዳ አካባቢ በተሻለ ሁኔታ እየተተገበረ ያለ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታው በብዛት የሚካሄደው በገና ሰሞንና በዓቢይ ጾም ገበሬዎች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ሥራቸውን አጠናቀው ዕረፍት በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ ሠፈርን፣ ጎጥን ወይም ቀበሌን መሠረት ያደረገ ቡድን ይመሠረታል፡፡ የቡድኑ አባላት ብዛትም በሠፈሩ በጎጡ ወይም በቀበሌው በሚገኙ ለጨዋታው ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ባላቸው ወጣቶች ብዛት ይወሰናል፡፡ ጨዋታውን ከመከወን በፊት ጊዜ ከወይራ ወይም ከሌሎች ጠንከር ካሉ እንጨቶች ተጠርቦና ድቡልቡል ቅርፅ እንዲይዝ ተደር የሚዘጋጅ ነው፡፡
‹‹ጨዋታው ሁለት ዓይነት የአጨዋወት ሒደት ያለው አንደኛው ተጋጣሚዎች እስከቻሉት ርቀት ድረስ ቓርሳውን በማራቅ የሚከናወን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጎል ተዘጋጅቶ እየተቆጠረ አሸናፊው የሚለይበት ነው፡፡ ጎል የሚዘጋጀውም የአንድ ሰው ማሳ ለአንደኛው ቡድን፣ በተቃራኒ አቅጣጫ ደግሞ የሌላ ሰው ማሳ ለሁለተኛው ቡድን ሲሆን፣ ጎል ሆኖ የሚቆጠረውም ቓርሳውን ከማሳው ላይ ማሳረፍ ሲቻል ነው፡፡›› ይላል መጽሐፉ፡፡
የጨዋታውን ሒደት ጽሑፉ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡ ጨዋታውን ለማከናወን አመቺ ሜዳ ይለይና በአካባቢው ታላላቅ ሰዎች መሀል ሜዳ ላይ የሚያስጀምሩት ሲሆን፣ ቓርሳውን ተሻምተው በያዙት በትር በአየር ላይ እየለጉ ወደ ተጋጣሚ ቡድን አቅጣጫ ያርቁታል፡፡ ተቃራኒ ተጋጣሚዎችም በአፀፋው እየመለሱ ይጫወታሉ፡፡ ቓርሳውን መለጋት የሚቻለውም በአየር ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚሁ መልኩ እስኪሸናነፉ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታው ተጋጣሚን በማራቅ የሚካሄድ ከሆነ በተቃራኒ አቅጣጫ ብዙ ርቀት የተጓዘው አሸናፊ ሲሆን፣ አሸናፊው የሚረጋገጠውም ተሽናፊዎች በቃኝ ሲሉ ወይም መሽቶ ፀሐይ ብርሃን መስጠቷን ስታቆም ነው፡፡ ጎል እየቆጠሩ የሚጫወቱ ከሆነም ብዙ የተቆረጠባቸው በቃኝ ሲሉ ወይም በመምሸቱ ምክንያት ጨለማው ሊያጫውታቸው ካልቻለ ነው፡፡